በመተከል ግጭት የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ ።

በመተከል ግጭት የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ከሁለት ቀናት በፊት በተፈጸመ የሰዎች ግድያ የተጠረጠሩ አምስት ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር መሀመድ ሃምደኒል እንደገለጹት ሰኔ 30 ቀን 2011ዓ.ም በወረዳው ገነተ ማርያም ቀበሌ ተፈጥሮ በነበረ ግጭት የሰዎች ሕይወት አልፏል።

በግድያው የተጠረጠሩ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን የተናገሩት ኮሚሺነሩ፥ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሁለቱ ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው ለፖሊስ በሰጡት የእምነት ቃል አረጋግጠዋል ብለዋል።

በቀሪ ሦስት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራው መቀጠሉን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት አካባቢው እየተረጋጋ በመምጣቱ ከነዋሪዎች ጋር ህዝባዊ ውይይት መጀመሩን ተናግረዋል።

በግጭቱ የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉን የተናገሩት ኮሚሽነር መሃመድ፥ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም በጤና ተቋም የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

“ፖሊስ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የሚያካሂደውን ዞኑን የማረጋጋት ሥራ ዘላቂነት እንዳይኖረው በድብቅ ትንኮሳ የሚያካሂዱ ግለሰቦች አሉ” ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ከግጭቱ በስተጀርባ ያለውን ድብቅ ሴራ ለማክሸፍ ፖሊስ በአዲስ ስልት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽነር መሀመድ እንዳሉት ሚያዚያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ምሽት በተከሰተው ግጭት የተጠረጠሩና የአሁኖችን ጨምሮ 98 ሰዎች ተይዘዋል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ በማሰባሰብ ጉዳያቸው በጊዜ ቀጠሮ እየታየ መሆኑንም ኮሚሽነር መሃመድ ጨምረው ገልጸዋል።

( ኢዜአ )