«የኢትዮጵያ እግርኳስ ሜዳዎች ከስፖርታዊ መንፈስ የራቁ እየሆኑ ነዉ»የስፖርት ቤተሰቦች

DW : መቐለ ሰብዓ እንደርታ ዛሬ በ30ኛ ሳምንት የመጨረሻ የኢትዮጵያ ፕሪመርሊግ ጨዋታ ድሬዳዋ ከነማን 2 ለ 1 በማሸነፍ እንዲሁም ፋሲል ከነማ በሽረ፣ ከሽረ እንዳስላሰ ጋር ተጫውቶ ነጥብ መጣሉ ተከትሎ ነው የውድድሩ ሻምፒዮን መሆኑ ያረጋገጠው፡፡ ድሉን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸው በትግራይ ስታድዮምና በከተማዋ ጎዳናዎች እየገለፁ ይገኛሉ፡፡

መቐለ ሰብዓ እንደርታ የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪመርሊግ ሻምፒዮን የሆነው በሰላሳ ጨዋታ ባስመዘገበው 59 ነጥብ ሲሆን፣ ሲዳማ ቡና በ58፣ ፋሲል ከነማ በ57 ነጥብ ሻምፒዮኑን ተከትለው የወድድር ዓመቱ አጠናቀዋል፡፡ ከእግርኳስ ውድድሩ በዘለለ በርካታ ስፖርቱን የሚከታተሉ አካላት እንደሚሉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ሜዳዎች የብሄርና ፖለቲካ መልእክቶች የሚንፀባረቅባቸው ከስፖርታዊ መንፈስ የራቁ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

የደጋፊዎች ግጭት፣ የክለቦችና እግርኳስ ፌደረሽን ሰጣገባ፣ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል እንዲሁም ሌሎች ችግሮች ከዓመት ዓመት እየተበራከቱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስን በቅርበት የሚከታተልና ለአለማቀፍ መገናኛ ብዙሐን የሚዘግበው ጋዜጠኛ ግርማቸው ከበደ “አሁናዊው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፈተናዎች ከወቅታዊ የሀገሪቱ ችግር ጋር ይዛመዳሉ” ይላል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪመርሊግ የወቅቱ ሻምፒዮን መቐለ ሰብዓ እንደርታ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይለ በበኩላቸው ዓመቱ ለሳቸውና ክለባቸው ከባድ እንደነበረ ይገልፃሉ፡፡ ክለባቸው እግርኳሳዊና እግርኳሳዊ ባልሆኑ ሁነቶች ሲፈተን መቆየቱ የሚገልፁት አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሃይለ ውድድሩ ለማሸነፍ ከባድ ሁኔታ ማለፍ እንደሚጠበቅ ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪ የስፖርት ጋዜጠኛ ግርማቸው ከበደ የኢትዮጵያ እግርኳስ ችግሮች ለመፍታት ጥናት ላይ የተመሰረቱ እርምጃዎች መውሰድ ይገባል ባይ ነው፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US