የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከ42 ወራት በኋላ በሕግ ተመዘገበ

[addtoany]

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሐን ምክር ቤትን ለመመሥረት ጥረት ከተጀመረ አስር ዓመት ተቆጥሯል።

Image result for የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትከአምስት ወራት በፊት የምሥረታ ጉባዔውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስብሰባ ማዕከል ያደረገው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሕጋዊ ዕውቅና አገኘ፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ፣ ምክር ቤቱ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1513/2011 አንቀጽ 57(1) መሠረት አገር በቀል ድርጅት ሆኖ በሠርተፊኬት ቁጥር 4214 የተመዘገበ መሆኑን ገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ ላለፉት 42 ወራት ሕጋዊ የዕውቅና ጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኝ፣ እንዲሁም የውስጥ አደረጃጀቱን መሠረት የማስያዝ ሥራዎች ሲያከናውን መቆየቱን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡ መገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞች ሕዝብን በተገቢው መንገድ እንዲያገለግሉና የጋዜጠኝነት ሙያ እንዲያድግ ምክር ቤቱ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበት የገለጸው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፣ ጋዜጠኞች ሕግን አክብረው እንዲሠሩ በአቅም ግንባታ ከማገዝ ባሻገር መንግሥት ሕግን በማክበር ሰበብ በሆነ ባልሆነው እጁን ከፕሬሱ ላይ እንዲያነሳ እንደሚታገል ጠቁሟል፡፡

ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ምክር ቤቱን የመመሥረት ሐሳብ በተለያዩ ወገኖች ሲነሳና ሲወድቅ ቆይቶ፣ ከብዙ ድካም በኋላ ጥር 8 ቀን 2005 ዓ.ም. በ19 መሥራች አባላት መመሥረቱ ይታወሳል፡፡ የምክር ቤቱ መሥራች አባላት የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን፣ የአሳታሚዎችና የጋዜጠኞች ማኅበራት ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት የአባላቱ ቁጥር 29 ደርሷል፡፡

ምክር ቤቱ የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ደረጃና ሥነ ምግባርን ለማበረታታትና ለማሳደግ የሚያግዙ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን የሚያከናውን ሲሆን፣ ይህንን የሥነ ምግባር ደንብ በመጣስ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ለሚቀርቡ ማናቸውም ዓይነት ቅሬታዎች ፍትሐዊና ነፃ የሆነ የቅሬታ መፍቻ ወይም የግልግል ዘዴ እንዲኖር ለማድረግ አልሟል፡፡

ምክር ቤቱ አራት ዋነኛ መዋቅሮች ሲኖሩት፣ ከላይ ሁሉንም መደበኛ አባላት የያዘ ጠቅላላ ጉባዔ አለው፡፡ ከጠቅላላ ጉባዔው ሥርም አምስት አባላት ያሉት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ኦዲተርና የዳኝነት/የግልግል አካል ይዟል፡፡ በዳኝነት/በግልግል አካሉ ውስጥ የምክር ቤቱ ዕንባ ጠባቂና የሥነ ምግባር ፓነል አሉ፡፡ የሥነ ምግባር ፓነሉ ኃላፊነትም የምክር ቤቱ አባላት በሆኑ የመገናኛ ብዙኃን  ተቋማት ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎች የሚመረመሩበት፣ ክርክር የሚካሄድበት፣ ይግባኝ የሚመራበትና ውሳኔ የሚሰጥበት ሥርዓትን አስመልክቶ ደንብ ማውጣትን ያካትታል፡፡ በደንቡ መሠረትም ቅሬታዎችን መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ የምክር ቤቱ ዕንባ ጠባቂ በበኩሉ በሥነ ሥርዓት ደንቡ መሠረት የሚቀርቡለትን ቅሬታዎች በገለልተኝነት መፍትሔ ወይም ውሳኔ ይሰጣል፡፡ የምክር ቤቱ የፓነል አባላት ቁጥር 15 ሲሆን፣ የአባላቱ ስብጥርም ከሃይማኖት ተቋማት ምክር ቤት፣ ከትምህርት ተቋማት፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከመገናኛ ብዙኃን ኩባንያዎች ጨምሮ ከሌሎች የባለድርሻ አካላት የሚዋቀር ይሆናል፡፡

Reporter Amharic