የደምቢ ዶሎ ከንቲባ በጥይት ተመትተው ቆሰሉ

BBC Amharic

ወለጋ ውስጥ በምትገኘው የደምቢዶሎ ከተማ ከንቲባ በጥይት ተመትተው መቁሰላቸውን አንድ የቄለም ወለጋ ዞን አስተዳደር ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።በተኩሱ ቢቆስሉም ህይወታቸው ተርፏል።

Image result for dembi dolo

የከተማው ከንቲባ አቶ ታደለ ገመቹ በጥይት ተመትተው የቆሰሉት ባለፈው አርብ እንደሆነ እኚሁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለስልጣን ተናግረዋል።ባለስልጣኑ እንዳሉት በከንቲባው ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት አባ ቶርቤ ተብሎ የሚጠራው ቡድን አባላት ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠረጠር ተናግረዋል።

ይህ አባ ቶርቤ ተብሎ የሚታወቀው ቡድን ጫካ ውስጥ ከቀሩት የቀድሞው የኦነግ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ ይታመናል።ከንቲባው ላይ የተተኮሰባቸው ከቢሯቸው ወጥተው መኪናቸው ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ነበር። “ከንቲባው ከሥራ በሚወጡበት ሰዓት ነበር በር ላይ ጥቃቱን ያደረሱባቸው” ሲሉ የአካባቢው ባለስልጣን አረጋግጠዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከንቲባውን በሁለት ጥይት እንደመቷቸውና አንደኛው ጥይት እጃቸውን ሌላኛው ደግሞ በጎን በኩል ኩላሊታቸው አካባቢ እንደመታቸውም ለማወቅ ተችሏል።ከንቲባው አቶ ታደለ ቀደም ሲል ከነበሩበት ቦታ ተዘዋውረው አሁን ወዳሉበት ኃላፊነት የመጡት በቅርብ ጊዜ ነው።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት እኚህ የአካባቢው ባለስልጣን እንዳሉት አቶ ታደለ ለተጨማሪ ህክምና ወደ አዲስ አበባ ተወስደዋል።እስከትላንት ድረስ በከንቲባው ላይ ጥቃት አድርሰዋል ከተባሉት ሰዎች መካከል የተያዘ ሰው እንደሌለም ታውቋል።

እንዲህ አይነቱ ጥቃት ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ በአካባቢው ባለስልጣናት ላይ ሲፈጸም ይህ የአሁኑ ሁለተኛው ነው።ከአንድ ወር በፊት የሰዮ ወረዳ የኦዲፒ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ነጌሶ አቡ ከአዲስ አበባ ወደ ደምቢ ዶሎ በጉዞ ላይ እያሉ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ ጫካ ውስጥ ተገድለው መገኘታቸው ይታወሳል።

ቀደም ሲል በተፈጸመው የአቶ ነጌሶ ግድያ በኦነግ ታጣቂዎች የተፈጸመ እንደሆነ የአካባቢው የመንግሥት ባለስልጣናት አረጋግጠዋል።አርብ እለት በከንቲባው ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት በአካባቢው ያለው የታጠቀ ቡድን ምን ያለው ነገር የለም።