የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻይና ሰራሽ አይሮፕላን ለመግዛት ንግግር መጀመራቸው ተሰማ

ኮማክ በተባለው የቻይና አውሮፕላን አምራችና የኢትዮጵያ አየር መንገድ መካከል የተደረሰው ስምምነት ምን አይነት ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ማኔጀሩ ሲመልሱ ንግግሩ ከተጀመረ ከሁለት ዓመት በላይ መሆኑን በማስታወስ ንግግሩ ገና ያላለቀና ወደፊትም የሚቀጥል ነው በማለት ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

BBC Amharic

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን መጋቢት 1/2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ኬንያ ሲበር አደጋ ካጋጠመው በኋላ ድርጅቱ አውሮፕላኖቹን ማገዱን አስታውቆ ነበር።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ለቻይናው ዜና ወኪል ዢንዋ በሰጡት መረጃ ድርጅቱ ኮማክ የተባለው የቻይና አውሮፕላን አምራች ኩባንያ የሚያመርታቸው ‘ሲ 919’ የተባሉትን አውሮፕላኖች ሁኔታ የሚከታተል ኮሚቴ አዋቅሯል።

የአውሮፕላኖቹን አስተማማኝነት ለመቆጣጠርም ኢትዮጵያ አየር መንገድ መሀንዲሶች ከኮማክ ጋር በቅርበት እየሰሩ ስለመሆኑም ዢንዋ ዘግቧል።

በቻይና የተሰራው የመጀመሪያው ‘ሲ 919’ መንገደኛ አመላላሽ አውሮፕላን በአውሮፓውያኑ 2017 ከሻንግሃይ ፑዶንግ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በመነሳት ነበር የሙከራ በረራውን ያደረገው።

የቻይናው ኩባንያ ‘ሲ 919’ ለተባሉት አውሮፕላኖች ከ300 በላይ ትዕዛዞችን የተቀበለ ሲሆን አውሮፕላኖቹን በአውሮፓውያኑ 2021 ማስረከብ እንደሚጀምር ገልጿል።

ትእዛዙን የሰጡት አየር መንገዶች ደግሞ ሁሉም ከቻይና ናቸው።

እውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፊቱን ወደ ቻይና እያዞረ ይሆን?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ማኔጀር የሆኑት አቶ አስራት በጋሻው ቻይና ለኢትዮጵያም ሆነ በአጠቃላይ ለአፍሪካ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና ሌሎች ዘርፎች ላይ ትብብር እያደረገች እንደመሆኑ አየር መንገዱም በአቪዬሽን ዘርፍ ከቻይና ድርጅቶች ጋር ሲሰራ እንደቆየ ያስታውሳሉ።

አያይዘውም አየር መንገዱ ወደ አምስት የቻይና መዳረሻዎች እንደሚበር በመጥቀስ ከቻይና ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረጉ ከዚህ በፊትም የነበረ፣ ወደፊትም የሚቀጥልና የሁለቱ ሃገራት ግንኙት ላይ የተመሰረተ ነው ይላሉ።

”የቻይና ምርት የሆኑ አውሮፕላኖችን ኢትዮጵያ አየር መንገድ ሊገዛ ነው የሚባለው ዜና ግን በታሳቢነት ደረጃ ያለ ነገር እንጂ ያለቀለትና ያበቃለት ጉዳይ አይደለም” ብለዋል አቶ አስራት።

አክለውም ድርጅታቸው ቦይንግ ማክስ አውሮፕላኖችን በመተው ፊቱን ወደ ቻይና አዙሯል የሚለው መረጃ የተሳሳተና ያልተረጋገጠ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ደጋግመው መግለጻቸውን አስታውሰዋል።

በቻይና እና በኢትዮጵያ መካከል የሚደረገው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ እንደሚቀጥል ግን ይናገራሉ አቶ አስራት።

ኮማክ በተባለው የቻይና አውሮፕላን አምራችና የኢትዮጵያ አየር መንገድ መካከል የተደረሰው ስምምነት ምን አይነት ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ማኔጀሩ ሲመልሱ ንግግሩ ከተጀመረ ከሁለት ዓመት በላይ መሆኑን በማስታወስ ንግግሩ ገና ያላለቀና ወደፊትም የሚቀጥል ነው በማለት ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ቻይና ቦይንግና ኤርባስን የመገዳደር አቅም አላት?

ቻይና ላለፉት አስር ዓመታት በቅርቡ የዓለምን የኤቪዬሽን ኢንዱስትሪ ለመቆጣጠር በማሰብ የራሷ የሆኑና ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ስታመርትና ስትሞክር ቆይታለች።

በምጽሃረ ቃል ኮማክ በመባል የሚታወቀው የቻይና አውሮፕላን አምራች ኩባንያ የሚያመርታቸው አውሮፕላኖች ብዙ ትችቶች እየተሰነዘሩበት ቢሆንም የሃገር ውስጥ አየር መንገዶች ግን ምርቶቹን ከመጠቀም ያገዳቸው የለም።

እንደ ዘርፉ ባለሙያዎች ትንበያ ከሆነ ግን በቅርብ ጊዜያት ቻይና ሰራሽ አውሮፕላኖች የቦይንግና ኤርባስን ምርቶች ገበያ መሻማት መጀመራቸው አይቀርም።

በኤቪዬሽን ዘርፉ የማማከር ስራ የሚሰሩት ሹኮር ዮሱፍ እንደሚሉት የቻይናን ገበያ ሰብሮ የመግባት አቅም እንደ ቀላል መመለከት አይቻልም።

”የአቪዬሽን ዘርፉ በቅርቡ በአውሮፓና አሜሪካ አምራቾች ብቻ መዘወሩ ቀርቶ፣ ተጨማሪ ሶስተኛ አካል መግባቱ አይቀርም። ከቻይና የተሻለ አቅምና ቴክኖሎጂ ያለው ሃገር ማሰብ ደግሞ ዘበት ነው” ብለዋል።

በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድና ሌሎች ከቦይንግና ኤርባስ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ከዚህ በኋላ በምን አይነት መልኩ ያስቀጥላሉ የሚለው ጥያቄ ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ማኔጀር የሆኑት አቶ አስራት በጋሻው ግን አየር መንገዱና ቦይንግ ያላቸው ግንኙነት የቆየና ከ70 ዓመታት ያላነሰ እንደሆነ ይናገራሉ።

”የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ ምርት የሆኑ ወደ 80 አካባቢ አውሮፕላኖች አሉት። አውሮፕላኖቹንም አሁንም እየተጠቀመባቸው ነው”ብለዋል።

አክለውም አየር መንገዱም ከቦይንግ ጋር ያለው ግንኙነት ሰላማዊና ልክ እንደበፊቱ በንግድ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ አቶ አስራት ገልጸዋል።

በዓለም ላይ ያሉት 737 ማክስ አውሮፕላኖች 370 ሲሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድም አራቱን እየተጠቀመ ነበር። በመጋቢት ወር ይሄው አውሮፕላን ባጋጠመው አደጋ መከስከሱን ተከትሎ አየር መንገዱ አራቱንም አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ በማድረግ አስቀምጧቸዋል።

”አውሮፕላኖቹ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግቢ ውስጥ ደህንነታቸው ተጠብቆና ዓለማቀፍ ደረጃዎችን በጠበቀ መልኩ እንደቆሙ ነው የሚገኙት። አየር መንገዱም ወደፊት የሚሰጠውን የመጨረሻ ውሳኔ ተከትሎ ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል።” ይላሉ አቶ አስራት።

የቻይናው ኮማክ ኩባንያ የሚያመርታቸው አውሮፕላኖች የሃገሪቱን የደህንነትና ተያያዥ መስፈርቶች በማሟላታቸው በቻይና፣ አፍሪካ፣ ደቡብ አሜሪካና አንዳንድ የኢስያ ሃገራት መብረር የሚያስችል ፈቃድ አግኝተዋል።

ነገር ግን አውሮፕላኖቹ የዓለማቀፉን ገበያ ለመስበርና ተወዳዳሪ ለመሆን አሁንም የአሜሪካና አውሮፓ ሃገራት የበረራ ፈቃድ ያስፈልጋቸዋል።

ለነዚህ አውሮፕላኖች ከሃገራቱ ፈቃድ ማግኘት ደግሞ ቻይናን የሚጠብቃት ትልቁ ፈተና ነው።