የሱዳን ሕዝብ ለድጋሚ ሕዝባዊ አመፅ አደባባይ ወጣ

ግጭት እየናጣት ባለችው ሱዳን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚታገለው የሱዳን ንቅናቄ የህዝባዊ አመፅ ጥሪን አቅርቧል።

ጥሪው ከዛሬው ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ያወጀ ሲሆን የሲቪል መንግሥት እስከሚመሰረት ቀጣይ እንደሚሆን አስታውቋል።

ምንም እንኳን የህዝባዊ አመፁ ዝርዝር ሁኔታ ባይታወቅም “ህዝባዊ አመፅ በዓለም ላይ ያሉ ኃያላንን በሰላማዊ መንገድ ማንበርከኪያ መንገድ ነው” የሚል መግለጫ ከንቅናቄው ተሰምቷል።

በተለይም መንግሥትንና ተቃዋሚዎቹን በማሸማገል ላይ የነበሩ ሦስት ተቃዋሚዎች እስርንም ተከትሎ ነው የአመጽ ጥሪው የቀረበው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ፍጥጫ ላይ ያሉትን የሱዳን መንግሥት ወታደራዊ መሪዎችና ሕዝባዊ ተቃውሞውን የሚመሩትን ተቃዋሚዎችን ያነጋገሩ ሲሆን ይህንኑም ተከትሎ ሦስቱ ተቃዋሚዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

መሀመድ ኤስማት አርብ ዕለት የታሰሩ ሲሆን፤ የአማፂው ቡድን ኤስፐኤልኤም ኤን መሪ የሆኑት ኢስማኤል ጃላብና ቃል አቀባያቸው ሙባረክ አርዶል ቅዳሜ ዕለት በቁጥጥር ስር ውለዋል። ግለሰቦቹ እስካሁን ድረስ ያሉበት እንደማይታወቅም ተዘግቧል።

ከአልበሽር ስልጣን መውረድ በኋላ ወደ ሱዳን የተመለሱት የኤስፒኤልኤም ኤን ምክትል ኃላፊ ያሲር አርማን ረቡዕ እለት እንደታሰሩም ቡድኑ መግለጫ አውጥቷል።

መሀመድ ኤስማትናና ጃላብ አሊያንስ ፎር ፍሪደም ኤንድ ቼንጅ የተባለው የተቃዋሚዎች ጥምረት አመራር ናቸው።

“ወታደራዊው ምክር ቤት ግለሰቦቹን ማሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የጀመሩትን የማሸማገል ጥረት ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደረገ ነው በማለት” የጥምረቱ አመራር ካሊድ ኦማር ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ወታደራዊው ምክር ቤት እስሩን አስመልክቶ ምንም አይነት ምላሽ ያልሰጠ ሲሆን፤ የቢቢሲ አፍሪካ ኤዲተር ሜሪ ሃርፐር በበኩሏ ወታደራዊው ኃይል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ጥረት ችላ እንዳሉት የሚያሳይ ነው ትላለች።

ተቃውሞውን እየመሩ ያሉ ግለሰቦች ከሽግግሩ ወታደራዊው ምክር ቤት የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በደም አፋሳሹ ግጭት ምክንያት እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት አልበሽር በሃገር አቀፍ ተቃውሞ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ሃገሪቷን እየመራ ያለው የሽግግሩ ወታደራዊ ምክር ቤት ሃገሪቷን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሸጋገር ቃል ቢገባም ተቃዋሚዎች ከጦር ኃይሉ ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት በመቀመጥ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፤ በምላሹም ሰኞ የደህንነት ኃይሎች ሰልፈኞች ላይ ተኩስ መክፈታቸው ግጭቱን አቀጣጥሎታል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሺር ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ከፍተኛ ሟቾች የተመዘገበበት ነው በተባለው በዚህ ደም አፋሳሽ ግጭት አርባ ያህል አስከሬኖችም አባይ ወንዝ ውስጥ ተጥለው ተገኝተዋል ተብለዋል።

የሱዳን ጤና ጥበቃ ሚኒስትር የተገደሉት ተቃዋሚ ሰልፈኞች 61 ብቻ ናቸው ያሉ ሲሆን፤ ከተቃዋሚ ሰልፈኞች ጋር ግንኙነት ያላቸው የሐኪሞች ቡድን ግን ሟቾቹ ከመቶ በላይ 100 እንደሆኑ መግለፃቸው ይታወሳል።

ብዙዎች በፍራቻ ላይ እንደሆኑ ለቢቢሲ የገለፁ ሲሆን ብዙ ሴቶች በልዩ ኃይሉ ድብደባ እንዲሁም የግድያ ማስፈራሪያ እንደደረሳቸው ገልፀዋል። ወታደሮች እየተኮሱ እየሮጡ እንዲያልፉ የተነገራቸው፣ የቦይ ውሃ እንዲጠጡና የተሸናባቸውም ግለሰቦች እንዳሉም እየተነገረ ነው።

ሀሙስ አፍሪካ ህብረት ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር እስክትመለስ ድረስ ከየትኛውም የህብረቱ እንቅስቃሴ ያገዳት ሲሆን ፤ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሸን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት ግድያዎቹ ላይ አፋጣኝ ምርመራ እንዲጀመር አስጠንቅቀዋል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US