ከ386 ቢሊየን ብር በላይ የ2012 ፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት እንዲሆን ተወሰነ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2012 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 386 ቢሊየን 954 ሚሊየን 965 ሺህ 289 ብር እንዲሆን ውሳኔ አሳለፈ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 71ኛ መደበኛ ስብሰባው በ2012 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህ መሰረትም በ2012 በጀት ዓመት በፌደራል መንግስት ለሚከናወኑ ስራዎች አገልግሎት የሚያስፈልገውን በጀት አፅድቆ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ወቅት ላይ ስራ ላይ ማዋል አስፈላጊ መሆኑና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወሰነው ቀመር መሰረት የፌዴራል መንግስት በጀት 386 ቢሊየን 954 ሚሊየን 965 ሺህ 289 ብር እንዲሆን ተወስኗል።

ከዚህ ውስጥም ለመደበኛ ወጪዎች 109 ቢሊየን 468 ሚሊየን 582 ሺህ 456 ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች 130 ቢሊየን 710 ሚሊየን፣ 876 ሺህ 568 ብር ፣ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 140 ቢሊየን 775 ሚሊየን 506 ሺህ 265 ብር እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፅሚያ ድጋፍ 6 ቢሊየን ብር በድምሩ 386 ቢሊየን 954 ሚሊየን 965 ሺህ 289 ብር እንዲሆን ተመድቧል።

ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ተቀብሎ ይፀድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

FBC