ያልተገራው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብትና የዋጋ ግሽበት አሳሳቢነት፡፡

  • ያልተገራው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብትና የዋጋ ግሽበት አሳሳቢነት፡፡
  • መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ‹ስፖንሰር› የማድረግ ዝንባሌ እየተስተዋለበት ነው፡፡

(አብመድ)

የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ጉዞ እንዳልተገራ ፈረስ ሕዝብ እያንገራገጨ ለበሽታ እየዳረገ ይመስላል፡፡ የኑሮ ውድነት በየዕለቱ እየጨመረ ሰዎች ነገን ከማለም ዛሬን ለመኖር እየተፍጨረጨሩ፣ የዋጋ ግሽበት እያንገላታቸው ነው፡፡

የዋጋ ግሽበት በአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ላይ የሚከሰት ተከታታይነት ያለው የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ወይም የገንዘብ የመግዛት አቅም መውረድ ማለት ነው፡፡ የዋጋ ግሽበት በዋናነት በፍላጎት ወይም በዋጋ መጨመር ሊከሰት እንደሚችል የምጣኔ ሐብት ንድፈ ሐሳቦች ያስረዳሉ፡፡ በኢትዮጵያ አሁን እየታዬ ያለው አሳሳቢ የዋጋ ግሽበት ግን ምክንያቱ በሁለቱም ንድፈ ሐሳቦች የሚመራ አይመስልም፡፡

‹ፍላጎት መር የዋጋ ግሽበት› በወለድ መጠን መቀነስ፣ ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ገበያው ሲገባ ወይም የደመወዝ ጭማሪ ሲደረግ የሚከሰት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የባንኮች የማበደሪያ የወለድ መጠን ላለፉት ዓመታት አልቀነሰም፤ እንዲያውም ከጥቂት ዓመታት በፊት የተወሰነ ጭማሪ ተደርጎበታል እንጅ በቅርቡ ያልተነካካ ጉዳይ ነው፡፡ ወለድ ቢቀንስ ብዙዎች እየተበደሩ ገንዘብ ወደገበያ ስለሚያስገቡ የዋጋ ግሽበት ሊያስከትል ይችላልና፡፡ ተጨማሪ ገንዘብ ታትሞ ወደ ገበያ መግባቱንም ብሔራዊ ባንክ አላስታወቀም፤ እንዲሁ በዝምታ አስርጎ እንደሆነም የሚያውቀው ባንኩ ስለሚሆን የዋጋ ግሽበት የማስከተል ዕድሉ መጠነኛ ነው የሚሆነው፡፡ ‹‹ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ገበያው አልገባም›› ሲባል ግን በጓዳ ገበያ እንደሚዘዋወሩ ውስጥ ለውስጥ የሚወራላቸውን ጨምረን አለመሆኑን ግን ልብ በሉልን፡፡

የሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ አልተደረገም፡፡ መንግሥት ለሠራተኞች ከዓመታት በፊት ቃል የገባው ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ እንኳ ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ እንዲያውም የመንግሥት ሠራተኞች ‹‹ኑሮን መቋቋም አቃተን›› እያሉ ቅሬታ እያቀረቡ ባለበት ሁኔታ ነው የዋጋ ግሽበቱ እያደገ ያለው፡፡ የደመወዝ ጭማሪ ቢኖር እንኳ የዋጋ ግሽበቱ ሊሆን የሚችለው በተመረጡ ሸቀጦች ሆኖ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ቅናሽ ነው ሊያስከትል የሚችለው፡፡
ለአብነት የሥጋ ዋጋ ጨምሮ የሽሮ ዋጋ ሊቀንስ ይችል ነበር፡፡
ሁለተኛው ንድፈ ሐሳብ በዋጋ ምክንያት የሚከሰት የዋጋ ግሽበት እንደሚኖር የሚተነትን ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች የገንዘብ የመግዛት አቅም መውረድና የታክስ መጨመር ናቸው፡፡ የብር የመግዛት አቅም በቅርቡ እንዲወርድም ሆነ እንዲያድግ አልተደረገም፤ ከዓመታት በፊት ‹‹የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ያበረታታል፤ የሀገር ውስጥ ምርትን ያሳድጋል›› ተብሎ ዶላር ከ18 ወደ 27 ብር ከፍ እንዲል ከተደረገ በኋላ የተወሰደ የምንዛሬ ማስተካከያ የለም፡፡ ስለዚህ በምጣኔ ሐብት ንድፈ ሐሳብ መሠረት ‹‹ፍላጎት መር የሆነ የዋጋ ግሽበት ኢትዮጵያ ላይ ተከሰተ›› ለማለት ያስችላል ብሎ ለመናገር ያስቸግራል፡፡

ከታክስ ጋር በተያያዘም የተደረገ የሕግ ማሻሻያ በኢትዮጵያ የለም፡፡ ዘንድሮም ከዓመታት በፊት በወጣው የታክስ ሕግና ቀመር ነው መንግሥት ገቢ እየሰበሰበ የሚገኘው፡፡ የሕግ ማሻሻያ ተደርጎ የታክስ መጠን ቢጨምር ነጋዴው ሸቀጥና አገልግሎቱ ላይ ተመጣጣኝ ጭማሪ በማድረግ የትርፍ ጣሪያውን ስለሚያስተካክል ግሽበት ይጠበቃል፤ ግን የሕግም የታክስ ቀመርም ለውጥ የለም፡፡

ስለዚህ የውጭ ምንዛሬም ሆነ የታክስ ሕግ ለውጥም ሳይኖር የዋጋ ግሽበት እንዴት ሊኖር ቻለ?

ተጠባቂ ሁኔታዎችም ለዋጋ ግሽበት አስተዋጽኦ እንዳላቸው የምጣኔ ሐብት ንድፈ ሐሳቦች ያስረዳሉ፡፡ ተጠባቂ ሁኔታዎች ሲባል የውጭ ምንዛሬ ለውጥ እንደሚኖር ከተገመተ፣ የታክስ ሕግ እንደሚለወጥ ከታወቀ፣ የሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንደሚኖር ከተተነበየ፣ ድርቅ ወይም ሌላ የተፈጥሮ አደጋ እንደሚኖር ፍንጮች ከታዩ … የዋጋ ግሽበት ሊከሰት ይችላል፡፡ እነዚህም ግን የሉም፡፡

ከኅብረተሰቡና ከመንግሥት አካላት ለዋጋ ግሽበቱ ማሻቀብ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደ ምክንያት ሲቀርቡ በተደጋጋሚ ይሰማል፤ ግን አይደለም ማለት ቢያስቸግርም ነው ብሎ ማደማደምም ይከብዳል፡፡ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየተስተዋለ ያለው ማስቲካ ወይም የውበት መጠበቂያ (ኮስሞቲክስ) ላይ አይደለም፡፡ የሽንኩርት ዋጋ ለኪሎ ግራም ከ10 ብር ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 25 ብር የገባው እንዴት በዶላር እጥረት ሊሆን ይችላል? ጤፍ በኩንታል ከ400 እስከ 600 ብር የጨመረው በውጭ ምንዛሪ እጥረት መሆኑን እንዴት ማመን ይቻላል?

ምናልባትም የምርት እጥረት ኖሮ እና ፍላጎት አድጎ የሚመስላቸው ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ከገበያው ላይ የፍጆታ ምግብ ምርቶችም ሆኑ የሸቀጦች እጥረት አይስተዋልም፡፡ የሚታየው በየዕለቱ የዋጋ መጨመር ብቻ ነው፡፡ የዚህ መሠረታዊ ክፍተቱ የገበያ ሥርዓቱ በሕግ የማይመራ፣ ግለሰቦች ተመካክረው ዋጋ የሚተምኑበት በመሆኑ ይመስላል፡፡

የሀገሪቱን የገቢና ወጭ ንግድ ጥቂት ከበርቴዎች የተቆጣጠሩት በመሆኑ እነዚህ ነጋዴዎች ተስማምተው የገቢና ወጭ ሸቀጦችን ዋጋ ለመተመን የሚቸገሩ አይደሉም፡፡ እነሱ ተመካክረው የወጭና ገቢ ሸቀጦችን ዋጋ ከወሰኑ የእነሱን እጅ ጠብቀው የሚቸረችሩ ነጋዴዎች ደግሞ በኅብረተሰቡ ላይ የመወሰን አቅማቸው ይጎለብታል፡፡ ለዚያም ነው ጠዋት 10 ብር የገዛነው ሳሙና ከሰዓት በኋላ 20 ብር ሆኖ የሚጠብቀን፡፡

‹‹ነፃ ገበያ›› በሚል ሰበብ ‹ነፃ ዘረፋ› የሚመስል ሕዝብን በኑሮ የማማረር ሥራ የተጀመረ መስሏል፡፡ ነጋዴው ምክንያታዊ የዋጋ ማስተካከያ ከማድረግ ይልቅ ሰበብ ባገኘ ቁጥር ከሚጠበቅበት በብዙ እጥፍ ዋጋ እየጨመረ በመሄዱ ሕዝቡ ለምሬት እየተጋለጠ ነው፡፡

በመንግሥትም በኩል የኑሮ ውድነትን ‹ስፖንሰር› የማድረግ ዝንባሌ እየተስተዋለ ነው፡፡ በቅርቡ የተደረገውን ሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ ማስተካከያ እንደ አብነት መውሰድ ይቻላል፡፡ በሀገሪቱ ያለውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከመንግሥት ሰፊ ኢንቨስትመንት እንደሚጠበቅ ሀቅ ነው፤ ነገር ግን ከፍተኛ ገንዘብ ለማግኘት አማራጩ የታሪፍ ጭማሪ ማድረግ መሆን አልነበረበትም፡፡ በኃይል አቅርቦት ላይ የተደረገው የታሪፍ ጭማሪ ዝቅተኛ ነዋሪውን እንደማይነካ መንግሥት እርግጠኛ ነበር፤ በሚገባ ቢጠናና ቢተነተን ግን ዝቅተኛ ነዋሪው ኤሌክትሪክን የሚጠቀመው መንግሥት እንደገመተው ለመብራት ብቻ አለመሆኑን ይረዳ ነበር፡፡

ሀብታምም ሆነ ድሀ እኩል ወፍጮ ቤት ይገናኛሉ፤ ልዩነቱ አንዱ ነጭ ጤፍ ሌላኛው ዳጉሳ ወይም በቆሎ እና ማሽላ ማስፈጨታቸው ነው፡፡ የተሻለ ኑሮ ያለው ሆቴል ላይ ዝቅተኛ ነዋሪው ከቤቱ ፓስታ ይመገባሉ፤ የፓስታ ፋብሪካው ግን በሀብታም ስም ተመዝግቦ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ጭማሪ ተደርጎበታል፡፡ ዝቅተኛ ነዋሪው በዚህ መልኩ በኤሌክትሪክ ታሪፍ ጭማሪው እየተገረፈ ነው፡፡ እንዘርዝረው ከተባለ አዲሱ የኤሌክትሪክ ታሪፍ በመኖሪያ ቤት ኪራይ ላይም ከፍተኛ ጭማሪ አስከትሏል፡፡ ለዚህ ነው መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን ስፖንሰር አድርጓል የሚያስብለው፡፡

አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ ምጣኔ ሀብታዊ መሠረት የሌለው ግን በመንግሥት ደካማ የገበያ ቅኝት የተፈጠረ የሚመስል ነው፡፡ መንግሥት ኑሮ እንዲያረጋጉ ሲያበረታታቸው የነበሩ የኅብረት ሥራ ማኅበራትም ኅልውናቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ዜጎችን ከምሬት ያልታደጉ ሆነዋል፡፡ በትራንስፖርት ዘርፉ የ10 ሳንቲም ጭማሪ በሸቀጥ ላይ 10 ብር እያስጨመረ የዜጎችን ሕይወት እያመሰቃቀለ የሚገኘው በቁጥጥር ደካማ መሆን እንጅ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ወይም በፍላጎት ማደግ አይደለም፡፡

 


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE