አቢሲኒያ ባንክ አልተዘረፍኩም አለ።

በትላንትናው እለት ከሰአት በኋላ 22 አካባቢ የሚገኘው የአቢሲኒያ ባንክ ተዘረፈ የሚል መረጃ በማህራዊ ትስስር ገጾች ላይ ሲሰራጭ ቢቆይም ባንኩ መረጃው ሃሰት ነው ብሏል፡፡

የአቢሲኒያ ባንክ ማርኬቲግ ኮሚኒኬሽን ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አስቻለው ታምሩ ለአሐዱ እንደገለጹት አውራሪስ ሆቴል አካባቢ አንዲት ሴት በፌስታል ብር ይዛ ስትንቀሳቀስ እሷን ለመዘረፍ 3 በሞተር ሳይክል ያሉ ወጣቶች መሞከራቸውንና ሴትየዋን በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ተረባርበው እንዳዳኗት ገልጸዋል፡፡

ይሁንና የዘረፋ ሙከራው ከአቢሲኒያ ባንክ ጋር የሚገናኝበት ምንም አይነት አግባብ የለውም ነው ያሉት፡፡

አቶ አስቻለው ጨምረው እንዳሉትም ህብረተሰቡ የገንዘብ እንቅስቃሴና ዝውውርን በባንክ ብቻ የማድረግ ባህሉን በማዳበር ራሱን ከመሰል ችግር ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በማህራዊ ትስስር ገጾች ላይ አቢሲኒያ ባንክ እንደተዘረፈ አድርገው የሀሰት መረጃ የሚያሰረጩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀው ዘረፋው የተቃጣባት ሴትም በፌስታል ይዛው ነበር የተባለው ብር ከየትኛው ባንክ ወጪ እንዳደረገች ወይም እንደተቀበለች የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡