ለተፈናቃዮች ከግንቦት 30 ቀን 2011ዓ.ም በኋላ በመጠለያ ውስጥ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደማይደረግ ተገለጸ፡፡

ለተፈናቃዮች ከግንቦት 30 ቀን 2011ዓ.ም በኋላ በመጠለያ ውስጥ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደማይደረግ ተገለጸ፡፡ ሁሉም አካባቢ ሠላም ስለሆነ ተፈናቃዮች ወደ ነበሩበት ቀዬ መመለስ እንደሚችሉና ድጋፍ የሚደረገውም መጀመሪያ በነበሩበት ቀበሌ ብቻ እንደሆነ አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል፡፡ (አብመድ)

በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ተከስቶ በነበረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራው ውጤታማነትና ወደ ፊት መደረግ በሚገባው ድጋፍ ዙሪያ በጎንደር ከተማ ምክክር ተደርጓል። በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል የተመራው የምክክር መድረኩ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አማረ ክንዴን ጨምሮ የክልል ከፍተኛ መሪዎች፣ ከሁለቱም ዞኖች የተውጣጡ የዞን እና የወረዳ መሪዎች ተሳትፈውበታል።

ምክከሩ በሚያዚያ 30 ሁሉም የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ውጤታማ ያልሆነበትን ምክንያት በመመርመር ላይ አተኩሯል፡፡ ከወራት በፊት የክልል፣ የዞን እና የወረዳ መሪዎች በተገኙበት እና በደረሱት መግባባት ሚያዚያ 30 ሁሉም ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር።

ነገር ግን ሚያዚያ 30 አልፎም ወደ ቤታቸው የገቡ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተጠበቀውን ያክል አይደሉም። ለዚህ ደግሞ ሕዝብን ከሕዝብ የማመካከር እና ወደ ሠላም ለማምጣት የተሠራው ሥራ ደካማ መሆን፣ ከተጎዱ ቀበሌዎች ውጭ ያልተጎዱ ጎረቤት ቀበሌዎች በጉልበት እና በቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ የተሠራው የሕዝብ ንቅናቄ ማነስ፣ የሚፈለገውን ያክል አናፂ አለመገኘት፣ ያልተፈናቀሉ ዜጎች እንደተፈናቀሉ ሆነው መቅረብ በዋና ዋና ችግርነት ተነስተዋል፡፡ በተለይ ያልተፈናቀሉ ዜጎች ተፈናቃይ መስለው መቅረብ ለሠላሙ፣ ለድጋፍ እና ለቤት ግንባታው አደጋ መሆን፣ ያልተቃጠሉ ቤቶች አንደተቃጠሉ አድርጎ መቁጠር እና ሌሎች ምክንያቶች ሚያዚያ 30 ሁሉም ወደቤቱ እንዲገባ የታቀደውን ሥራ ማጓተታቸው ተገምግሟል፡፡

በምክክሩ በተለይም በምዕራብ ጎንደር ዞን እየተሠራ ያለው ሥራ ደካማ መሆንና ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ከተሳታፊዎች ተመላክቷል። በየቀበሌው የተፈናቀሉ ዜጎችን ቁጥር በትክክለኛው መንገድ አጣርቶ አለማቅረብ ለሥራው መጓተት እንቅፋት መሆኑም ተነስቷል፡፡ የሁለቱ ዞኖች እና የወረዳ አመራሮች በቅንጅት አለመሥራትም በችግርነት ተመላክቷል፡፡

የአማራና ቅማንት ሕዝብ ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የተሠራው እርቀ ሠላም መዘግየትም ሌላኛው ችግር እንደነበር ተገምግሟል። ሠላም እንዲደፈርስ እና ነውጡ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውና በተፈናቃዮች ላይ እየነገዱ መሆኑም ተነስቶ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት ተመላክቷል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞችን ወደነበሩበት መመለሱ መልካም ቢሆንም እርስ በርሰ እያገናኙ በማመካከር ረገድ ክፍተት እንዳለ ተነግሯል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ለማቅረብ የተፈናቀሉ ዜጎችን እና የሚታረሰውን መሬት እንዲያጠና ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር፤ ነገር ግን የተሰጠው መረጃው የተሳሳተ መሆን ለድጋፍ አስቸጋሪ መሆኑ ተመላክቷል።

በምክክሩ የተገኙት የአብክመ የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር ‹‹የክልሉ መሪዎች የክልሉን ሠላም ከመጠበቅና የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀደመ ሕይወታቸው ከመመለስ በላይ ኃላፊነት የለባቸውም›› ብለዋል። ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ መሪዎች በቅንጅት በመሥራት ለሚቀርቡ ችግሮች እና ሥራዎች ቀልጣፋ ውሳኔ መስጠት እንደሚገባም አቶ አገኘሁ አሳስበዋል።

ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በሚሠራው ሥራ የመረጃ ክፈተት እንዳለ ያመለከቱት አቶ አገኘሁ ያለሙሉ መረጃ የተሟላ ሥራ መሥራት እንደማይቻልም ጠቁመዋል። በተለይ ሰሊጥ አምራች የሆኑ አካባቢዎችን ለማሳረስ ትራክተር ካላቸው ባለሀብቶች ጋር መገናኘት እና መከራየት እንደሚገባ አሳስበዋል። የወረዳ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በአካባቢው የተፈናቀለው ዜጋ ወደ ነበረበት ሳይመለስ ሌላ ሥራ መሥራት አይገባውም ነው ያሉት አቶ አገኘሁ።

የምዕራብ ጎንደር ዞን የእርሻ ጊዜ ሳያልፍ በተገቢው መንገድ መሥራት ካልተቻለ ለሥራ የሚሄደው ሁሉ ‹‹ተፈናቃይ ነኝ›› ቢል ችግር እንደሚሆንበትም አስታውቀዋል። የምዕራብ ጎንደር ዞን የእርሻ ወቅት ጥቂት ጊዜ ስለሚሰጥና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የእርሻ ወቅት ስደረሰ ማፋጠን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የጤና ጥበቃ ቢሮ የተፈናቀሉ ዜጎች ከመጠለያ እያሉም ሆነ ወደ ቤታቸው ከሄዱ በኋላም የጤና እክል እንዳይገጥማቸው የቅድመ ጥንቃቄ ሥራውን እንዲያጠናክርም አሳስበዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአብክመ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል ደግሞ ‹‹አሁን ያለንበት ደረጃ ከነበርንበት የተሻለ ነው። ‹ወደ ቀዬያችን አንመለስም› የሚል አመለካከት ነበር ይህ ተስተካክሏል። በርካታ ቤቶችም ተሠርተዋል›› ነው ያሉት። ችግር የሚፈታውም የሚመጣውም በመሪዎች መሆኑን ያመለከቱት አቶ መላኩ ‹‹መሪዎች በትጋትና በጥራት በሠሩባቸው አካባቢዎች አስደሳች ሥራ ተሠርቷል። ሕዝቡ አንድ ሆኖ ሳለ መሪዎች አንድ ባለመሆናቸው ሕዝቡን ለማለያየት የሚሠራ ሥራ አለ›› ነው ያሉት፡፡ መሪዎችን አቀናጅቶ በመሥራት በኩል ችግሮች እንዳሉና ማስተካከል እንደሚገባም አሳስበዋል።

የተፈናቃዮች የተረጅነት ዝንባሌ እንዳይጎለብት የአካባቢው ታሪክ የመስጠት፣ የመደገፍ፣ የማብላት እና የማጠጣት መሆኑን በማስረዳት ወደ ቀደመ ሕይወታቸው መመለስ እንደሚገባ አስገንዝዋል። ‹‹ተፈናቃይን በመጠለያ ካምፕ የምንደግፈው እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ነው፤ ከግንቦት 30 ቀን 2011ዓ.ም በኋላ በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ምንም ዓይነት ድጋፍ አናደርግም። ሁሉም አካበባቢ ሠላም ነው፤ የተፈናቀለው ሁሉ ወደ ነበረበት ቀዬ መመለስ ይችላል። ድጋፍ የምናደርገው መጀመሪያ በነበረበት ቀበሌ ብቻ ነው›› ብለዋል አቶ መላኩ በውይይቱ። ጊዜያዊ መጠለያ መሥራት እንኳ ካስፈለገ በየቀበሌዎቹ መሆን እንደሚገባው አስታውቀዋል።

‹‹የመንግሥት ሠራተኛው ከግንቦት 1 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ ወደ ነበረበት ሥራ ተመለስ ተብሏል፤ የሄደው ሄዷል ያልሄደው መሄድ አለበት›› ብለዋል። ወደየቀበሌው መመለስ ዕርዳታ ማቋረጥ አለመሆኑን ያስታወሱት አቶ መላኩ ‹‹ዜጎች ወደ ነበሩበት አካባቢ ሲመለሱ ምንም ዓይነት ችግር እንዳይገጥማቸው የዞን እና የወረዳ መሪዎች በቆራጥነት መሥራት አለባቸው›› ብለዋል።

የሀብት ማሰባሰቡ ሥራ ዝቅተኛ እንደሆነ ያስረዱት አቶ መላኩ አጠናክሮ በመሥራት የአቅመ ደካማ ቤቶችን መሥራት እንደሚገባ፤ ለባለሀብቱ የብደር አቅርቦት ማመቻቸት፣ በሁለቱ ዞኖች የሚደረገውን ድጋፍ ፍትሐዊ ማድረግ እንደሚጠይቅም አብራርተዋል፡፡

በምክክር መድረኩ እስካሁን ድረስ ከ41 ሺህ በላይ ዜጎች ወደቀያቸው መመለሳቸው ተመላክቷል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ -ከጎንደር