ተፈናቃይ ተማሪዎች በሚቀጥለው ዓመት ተዘጋጅተው እንዲፈተኑ ይደረጋሉተባለ

“ያልተመዘገቡና ዓመቱን ሙሉ የትምህርት ገበታ ላይ ያልነበሩ ተፈናቃይ ተማሪዎች በሚቀጥለው ዓመት ተዘጋጅተው እንዲፈተኑ ይደረጋሉ።” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2011ዓ.ም (አብመድ) በአፈታተን ሂደት ባለፈው ጊዜ የታዩ ስህተቶች እንዳይደገሙ ልዩ ጥንቃቄ እንደሚደረግ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የሀገር አቀፍ ፈተና ሰኔ 03/2011ዓ.ም እንደሚጀምር መርሀ ግብሩ ያሳያል ፡፡ ዝግጅቱ አሰራሩን ተከትሎ እየተከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናግረዋል፡፡ የመማር ማስተማሩ ሂደት ተማሪዎችን በሚያዘጋጅ መልኩ በማተኮር እየተካሄደ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡ ባለፈው ጊዜ የታዩ አንዳንድ ስህተቶች እንዳይደገሙ ልዩ ጥንቃቄ እንደሚደረግም አመላክተዋል፡፡

በአማራ ክልል ከወረዳና ከዞን እየተሸጋገሩ የ8ኛ፣ 10ኛና 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የሚፈትኑ 30 ሺህ የሚጠጉ መምህራን ተለይተዋል፡፡ አፈታተኑ ሠላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን ከ12 ሺህ በላይ የፀጥታ አካላት እንቅስቃሴ በማድረግ በየፈተና ጣቢያዎች ደኅንነትና ሠላም በማስከበር እንደሚሳተፉም ታውቋል፡፡

ከፈተና ኩረጃ ጋር በተያያዘ መኮረጅ ለሀገርና ለተፈታኞች ጠንቅ መሆኑን በማስገንዘብ እየተሠራ እንደሆነ ቢሮ ኃላፊው አስገንዝበዋል፡፡ “ኩረጃ መልካም ትውልድ ለመገንባት አጥፊ ነው፡፡ ይህን በሽታ መከላከል የሁሉም ተግባር መሆን ያለበት ነው” ሲሉ ነው ዶክተር ይልቃል ያሳሰቡት፡፡ “የእኔ ትምህርት ቤት ታዋቂ እንዲሆን፣ የእኔ ልጅ እንዲያልፍ” በሚል ፍላጎት መኮረጅን የሚያበረታታ ወላጅና የትምህርት አመራር ለሀገርም ሆነ ለአካባቢ እንደማይጠቅምም አስገንዝበዋል፡፡ በትምህርት ስኬታማ ለመሆን ከመኮረጅ ይልቅ ማጥናት፣ ልዩ ትኩረት መስጠትና መጠየቅ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባለፈው ዓመትም “ፈተናው ወጥቷል” እየተባለ ሲናፈስ የነበረው ወሬ ስህተት እንደነበረ ያስታወሱት ዶክተር ይልቃል ማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙና በአውታሩ ሥራቸውን የሚያከናውኑ ግለሰቦችም ሆኑ አካላት ከመጥፎ ተግባር በመቆጠብ ኃላፊነት እንዲሰማቸው ጥሪ አቅርበዋል። መረጃዎች ሲለቀቁም ከተገቢ ወይም ተጠያቂነትና ኃላፊነት ካለባቸው የመገናኛ ብዙኃን ሁኔታውን አንዲያረጋግጡ አሳስበዋል፡፡ በዚህ አግባብ ተማሪዎችን መረጋጋት እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡

ከተፈናቃዮች ጋር በተያያዘም በተለይ በአማራ ክልል ምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር በርካታ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የ8ኛ ክፍል የማያስፈትኑ ትምህርት ቤቶች እንዳሉም አስታውቀዋል፡፡ “በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር 47 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች አያስፈትኑም፡፡ አንዳንዶች ግን በወላጆቻቸውና በተለያዩ ድጋፎች የሚማሩ ስላሉ ፈተናውን ይወስዳሉ፡፡ ያልተመዘገቡና ዓመቱን ሙሉ የትምህርት ገበታ ላይ ያልነበሩ ተማሪዎች በሂደት በሚቀጥለው ዓመት ተዘጋጅተው እንዲፈተኑ ይደረጋሉ” ሲሉም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡