መፈናቀሉ የቀጣይ ዓመት ኑሯቸውንም አደጋ ላይ እንደሚጥለው ከቤኔሻንጉል የተፈናቀሉ ወገኖች ተናገሩ

‹‹የሁለቱ ክልል መንግስታት በጋራ ካልሰሩ በሚቀጥለዉ ዓመት ግብርናም፤ ምርትም፤ ኑሮም አይኖርም፡፡›› ከሰሞኑ በተከሰተው ግጭት ከቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖች

መፈናቀሉ የቀጣይ ዓመት ኑሯቸውንም አደጋ ላይ እንደሚጥለው በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግልገል በለሰ ከተማ የእርቀ ሰላም ተሳታፊዎች ተናገሩ፡፡

ከሰሞኑ በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ በግልገል በለሰ ከተማ እርቅ እየተካሄደ ነው፡፡
በእርቅ ስነ ስርዓቱ ላይ አስተያዬታቸውን የሰጡት የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉት ግጭት የቀሰቀሱ እና ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ ወንጀለኞች የማይያዙት ከአመራሮች ድጋፍ ስለሚደረግላቸው ነው፡፡

ሕዝቡ ስጋት ላይ ሆኖ እየተፈናቀለ አመራሩ ከማሰቆም ይልቅ በዝምታ የተመለከተዉ ማፈናቀሉን ስለሚፈልገዉ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡ በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ልዩነት እና አድሎ እየተፈጸመ መሆኑንም በውይይታቸው አንስተዋል፡፡
በነጻነት ቀስት እየተሰራ መሆኑ እና ቀስት ይዞ መንቀሳቀስ መፈቀዱም ተገቢ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት፡፡ ከቀበሌ እስከ ክልል ያሉ አመራሮች ስራቸውን በትክክል በመስራት ግጭቶችን ቀድመው ማስቀረት እንዳለባቸውም ጠይቀዋል፡፡

‹‹አሁን ሰው ተፈናቀለ፤ በሚቀጥለዉ ዓመት ደግሞ ዛሬ እርሻ ስላላረስን ረሃብ ይመጣል፤ በዚህ ደግሞ ሁሉም ተጎጂ ነው›› በማለትም የወቅቱን መፈናቀል እና ግጭት አሳሳቢነት አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ጉሙዝና አማራ አልተጣሉም፤ የሁለቱ ክልል መንግስታት በጋራ ካልስሩ በሚቀጥለዉ ዓመት ግብርናም፤ ምርትም፤ ኑሮም አይኖርም›› ብለዋል ተወያዮቹ፡፡

‹‹አይዟችሁ የሚሉ፣ ቀስት የሚያቀብሉ አመራሮች አሉ፤ በቁጥጥር ስር ይዋሉ›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ በግጭቱ ከሁለቱም ሕዝቦች ሕይዎታቸውን ማጣታቸውን የተናገሩት ነዋሪዎቹ እርቀ ሰላሙ ለይስሙላ መሆን እንደሌለበትም አንስተዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ አየነዉ በላይ አሁንም ሰላሙ እንዳልተረጋገጠ እና ገና የሚቀሩ ተግባራት እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ እንዲደራጅ የሚፈለገው እየደረሰበት ያለውን ግፍ ለመከላከል እንጂ ለማጥቃት እንዳልሆነ መገንዘብ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡ መደራጀቱ ለማንም ስጋት እንደማይሆንም ነው ያስረዱት፡፡ ሁሉም በሚኖርበት አካባቢ ሰላምና ደኅንነቱ ተጠብቆ መኖር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ከዚህ ውጭ የሚፈጸሙ ተግባራት የተወገዙ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የውይይቱ ዋና ዓላማም ተፈናቃዮች ደኅንነታቸዉ ተጠብቆ የእርሻ ጊዜው ሳያልፍ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ መሆኑን አቶ አየነው ተናግረዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ በየአካባቢው ያለው ግድያ እና የጸጥታ ስጋት መቀረፍ እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት፡፡

የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ በበኩላቸው ግጭቱ ‹‹አስፈሪ ነዉ፤ አጥፊዎቹን ለህግ እናቀርባለን፤ ማንቡክ ላይ ተደራጅተዉ ዜጎች ላይ ግድያ የፈጸሙ እና የተሰወሩ ቡድኖች አሉ፤ እነሱንም በቁጥጥር ስር አውለን ለህግ እናቀርባለን›› ብለዋል፡፡

በቂም በቀል መገዳደል መቆም እንዳለበት እና ሁሉም ግጭቱን ለማስቆም መስራት እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት፡፡ ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለንብረት ውድመት እንዲሁም ለመፈናቀል ምክንያት የሆነው ስውር ደባ ከፖለቲካ አመራሮች ውጪ በገለልተኛ ባለሙያዎች እየተጠና መሆኑም ተመላክቷል፡፡