በድብቅ ወደናይሮቢ ሊገቡ ነበር ያላቸውን 22 ኢትዮጵያዊያንን መያዙን ፖሊስ ገለጸ

የኬንያ ፖሊስ በሕገ ወጥ መንገድ በድብቅ ወደናይሮቢ ሊገቡ ነበር ያላቸውን 22 ኢትዮጵያዊያንን መያዙን ገለጸ።

በኬንያ የወንጀል መከላከል ልዩ ፖሊስ አባላት የተያዙት ኢትዮጵያዊያን በሁለት መኪኖች ተሳፍረው ሲጓዙ ነበር ተብሏል።

ትናንት ከሰዓት በኋላ በፖሊስ ከተያዙት ኢትዮጵያዊያን ጋር በተያያዘ ሁለት ሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ገልጿል።

የታሰሩት ኢትዮጵያዊያን ለፖሊስ እንደተናገሩት፤ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በኬንያ በኩል ከዛም ታንዛኒያን በማቋረጥ ደቡብ አፍሪካ ለመድረስ አቅደው ነበር።

ከተያዙት ስደተኞች መካከል 17ቱ ሴቶች ሲሆኑ፤ ሲያጓጉዟቸው የነበሩት ግለሰቦች ደግሞ ኬንያዊያን ናቸው።

ኢትዮጵያዊያኑ በኬንያ በኩል ለማቋረጥ እንዲችሉ ለሚረዷቸው አዘዋዋሪዎች ምን ያህል ገንዘብ እንደከፈሉ የታወቀ ነገር የለም።

የወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር የሆኑት ጆርጅ ኪኖቲ እንደተናገሩት፤ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ማዘዋዋር በመጠኑ ከፍ እያለ በመሆኑ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

የኬንያ ባለስልጣናት እንደሚሉት፤ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያዊያን በኬንያ በኩል ለማቋረጥ ሲሞክሩ ተይዘው ወደመጡበት እንዲመለሱ የተደረጉ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ሥራ ፍለጋ እና ወደሌላ ሀገር መሻገርን ግብ አድርገው ወደ ሃገሪቱ ይገባሉ።

ስደተኞቹ ከድንበር ከተማዋ ሞያሌ አንስቶ እስከ ናይሮቢ ድረስ በሚጓዙበት ጊዜ ከሃያ በላይ የፖሊስ ኬላዎችን አልፈው መሆኑ የደህንነት ባለስልጣናትን ጥያቄ ፈጥሮባቸዋል።

አንዳንድ ባለስልጣናት እንደሚሉት፤ ይህ አይነቱ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚፈጸመው በአዘዋዋሪዎቹና በጸጥታ ሰራተኞች መካከል በሚደረግ መመሳጠር ነው።

ትናንት ከተያዙት ስደተኞች ጋር በተያያዘ የፖሊስና የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት እንዳሉት፤ የተያዙት ሰዎች እንግሊዝኛም ሆነ ስዋሂሊ ስለማይናገሩ ለመግባባት አልቻሉም።

የኬንያ ባለስልጣናት በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ወጣቶች በተለያዩ መንገዶች ወደግዛታቸው እንደሚገቡ አመልክተው፤ በቅርቡም 8 የኤርትራ ዜጎች ኬንያ በመግባት ወደ እስያ ለመሻገር ሲሞክሩ መያዛቸውን ገልጸዋል።