የትራንስፖርት ችግር በኑሯችን እንዳንለወጥ መሠናክል ሆኖብናል – የሰሜን ጎንደር መንገደኞች

‹‹42 ወንበሮች ያሉት መኪና እስከ 110 ሰዎችን ጭኖ ይጓዛል፡፡›› መንገደኞች

‹‹ከደባርቅ-ጃናሞራ እና በየዳ መስመሮች በቂ መኪና ስለሌለ የትራፊክ ቁጥጥር አናደርግም፡፡›› የሰሜን ጎንደር ዞን መንገድ እና ትራፊክ ደኅንነት

 (አብመድ) ለዓመታት የዘለቀው የትራንስፖርት ችግር በኑሯችን እንዳንለወጥ መሠናክል ሆኖብናል ሲሉ ከደባርቅ ጃናሞራ እና በየዳ የሚጓዙ መንገደኞች ነግረውናል።

የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ለዓመታት የዘለቀውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ እንደሆነ ገልጿል።

መምህር አወቀ አበባው ከደባርቅ ወደ ጃናሞራ ለመጓዝ መኪና እየፈለጉ ያገኘናቸው መንገደኛ ናቸው። መምህር አወቀ በአካባቢው ከስምንት ዓመት በላይ በተለያዩ ጊዜያት በዚሁ መስመር መመላለሳቸውን ነግረውናል፤ ‹‹አንድም ቀን ግን የተመቸ ጉዞ አድርጌ አላውቅም›› ብለዋል። ‹‹ሁልጊዜም ከዕቃ ጋር ነው ተጭነን የምንሄደው፤ መንግሥት በሰለጠነ ዘመን ይህን ታላቅ አካባቢ ለምን እንደረሳው ግራ ተጋብተናል›› ነው ያሉት። በትራንስፖርት እጦት ምክንያት ወላድ እናቶች ለሕክምና እንደማይደርሱ እና ለሕጻናትና እናቶች ሞት መንስኤ እንደሆነም ነግረውናል። ‹‹42 ወንበሮች ያሉት መኪና እስከ 110 ሰዎችን ጭኖ ይጓዛል፤ ይህም ለሕይወታችን አስጊ በመሆኑ መንግሥት ትኩረት ይስጠው›› ብለዋል።

ሌላኛው ተጓዥ ተስፋው አበራ ‹‹ጃናሞራ ወረዳ በንግድ ሥራ ተሰማርቼ እየሠራሁ ነው፤ ነገር ግን በትራንስፖርት ችግር ሥራ ለማቆም እየተገደድኩ ነው›› ሲል ምሬቱን ተናሯል። በትራንስፖርት መዘግየት እና አለመኖር ምክንያት የሥራ ተነሳሽነቱ እንደደከመ የተናገረው ተስፋው ለንግድ የሚወስደው የሸቀጥ ዕቃ በወቅቱ ስለማይደርስ ገበያው ላይም ተፅዕኖእየፈጠረበት እንደሆነም ያስረዳል።

Image may contain: one or more people, people standing and outdoor

መምህርት አማሩ አየነው ደግሞ ‹‹ከ10 በላይ መንገዱን አውቀዋለሁ፤ መንግሥት አይቶት የማያውቅ መንገድ ነው፤ በቀን አንድ መኪና ብቻ ስለሚጓዝ ትርፍም ተጭኖ የሚቀረው ሰው ቀጣዩን ቀን ለመጠበቅ ይገደዳል›› ነው ያሉት። ከዚህ ባለፈም ከታሪፍ በላይ እንደሚጠይቁ አመልክተዋል። በትራንስፖርት ችግር ዘመናዊ ግብርና፣ ንግድ እና ትምህርት በቀላሉ ማግኘት ፈተና መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ መንግሥት ከስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የሚያገኘውን በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጥቅም ቅድሚያ እንዲሰጥም ጠይቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደባርቅ ከተማን ጨምሮ በአካባቢው በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች አገልግሎት የሚሰጡ ባጃጆች ከአቅም በላይ እና ካለታሪፍ በመጫን ለኅብረተሰቡ ችግር እየሆኑ እንደሆነ የከተማዋ ነዋሪዎች ነግረውናል።

የሰሜን ጎንደር ዞን መንገድ እና ትራፊክ ደኅንነት ባለሙያ ኮማንደር ፈንታ አዲሴ ‹‹መንገዱ ላለፉት 20 ዓ መታት የዘለቀ ችግር ያለበት ነው፤ ባለፉት 20 ዓመታት ሰው ከዕቃ ጋር እየተጫነ ከታሪፍ በላይ ሲጠየቅ ቆይቷል። ከደባርቅ ጃናሞራ እና በየዳ መስመሮች በቂ መኪና ስለሌለ የትራፊክ ቁጥጥርም አናደርግም። ቁጥጥር ስናደርግ ሰልፍ እየተደረገብን ስለሆነ ለመሥራት ተቸግረናል። መንግሥት የተጀመሩ መንገዶችን አጠናቅቆ ለችግሩ መፍትሔ መስጠት ካልቻለ ችግሩ ቀጣይነት ይኖረዋል›› በማለት ችግሩ የተቋማቸው አለመሆኑን ገልጸዋል። መንግሥት ያወጣው የቅጣት መጠንም በቂ ባለመሆኑ አሽከርካሪዎች ለመቀጣት ዝግጁ ሆነው እንደሚጭኑም ገልፀዋል። በደባርቅ ከተማ የሚታየውን ያለታሪፍና ከልክ በላይ መጫን ችግር ለመፍታት ግን ጥረት እየደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

Image may contain: one or more people, people standing, crowd and outdoor

የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወገኔ አማረ በአካባቢው እየተሠሩ ያሉ መንገዶች ከመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር ርክክብ ስላልተፈጸመባቸው ለችግሩ መባባስ እንደምክንያት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ችግሩ የሚታወቅ እና ለዓመታት የቆዬ ነው›› ያሉት ኃላፊው ወደ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመግባት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተመካከሩ መሥራት እንደሚጠይቅም አስንዝበዋል። ‹‹ችግሩ በዚህ ቀን ይቀረፋል ባይባልም የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን›› ብለዋል አቶ ወገኔ አማረ።

የደባርቅ-ጃናሞራ-በየዳ የመንገድ ችግርን ለመቅረፍ የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች የመጠናቀቂያ ጊዜ ከዓመታት በፊት ቢያልፍም አሁንም በመጓተት ላይ መሆናቸውን አብመድ በተደጋጋሚ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ የደባርቅ-በለስ-መካነብርሃን-ቧኂት መንገድ መጠናቀቅ ከነበረበት ከአምስት ዓመታት በላይ ተጓትቷል፤ የበኋት-ድል ይብዛ (በየዳ) 74 ኪሎ ሜትር መንገድም መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ ከአራት ዓመታት በላይ ተጓትቷል፡፡ መንገዶቹ አሁንም በመጓተትና ጥራት ችግር የሕዝብ ቅሬታ እንደሆኑ መቀጠላቸውን አብመድ አረጋግጧል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE