አዲስ አበባን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠዉን የሚሸራርፍ አቋም በውስጣችን ማንም የለውም – ዶ/ር አምባቸው መኮንን

BBC Amharic

የኦሮሞ እና የአማራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መድረክ ትናንት ሚያዝያ 13 ቀን 2011 ዓ. ም. በአምቦ ከተማ ተካሂዷል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የአማራ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር አምባቸው መኮንን በአምቦ ከተማ

በሕዝብ ለሕዝብ መድረኩ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር አምባቸው መኮንን እና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የክልሎቹ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።

በውይይቱ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሰሆን ከመድረኩ ተሳታፊዎችም ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል። ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ ተሳፋዬ ዳባ የተባሉ የአምቦ ከተማ ነዋሪ ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር አምባቸው መኮንን አራት ጥያቄዎች አቅርበው ነበር።

የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ሰሞኑን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄር አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ የተከሰተው ግጭት የሚመለከት ሲሆን አቶ ተስፋዬ እንዲህ ብለዋል።

ጥያቄ 1

“እርስዎ በሚያስተዳድሩበት ክልል ውስጥ የሚገኙ ኦሮሞዎች በጠራራ ጸሃይ በታጣቂዎች እንደተገደሉ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሰምተናል። እርስዎ እና የክልሉ መንግሥት ሰዎችን የሚገድሉ ሰዎች ላይ የወሰዳችሁት እርምጃ ምን እንደሆነ እና አሁን ጉዳዩ የደረሰበትን ሊገልጹልን ይችላሉ?”

ዶ/ር አምባቸው ንግግራቸው የጀመሩት በኦሮምኛ ”እንዴት ናችሁ? የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝብ ወንድማማች ናቸው። ችግር የለም። እኛ አንድ ነን” በማለት ነበር።

ርዕሰ መስተዳድሩ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄር አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ በደረሰው ችግር የሰው ሕይወት በመጥፋቱ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዝን በመግለጽ ለጥያቄው እንዲህ ምላሽ ሰጥተዋል።

”የሰው ሕይወት ጠፍቷል። ይህም በጣም አሳዝኖናል። የተጎዳው በጠቅላላ የእኛው አካል ነው። በዚህም ውስጣችን ተነክቷል። ይህንን እንዴት አድርገን እንፍታው በሚለው ላይ እየተሠራ ነው። አሁን በአከባቢው ሰላም እና መረጋጋት ተፈጥሯል። ይህ አይነቱ ተግባር በድጋሚ እንዳይፈጸም እንደምንሠራ ቃል ልገባላችሁ እወዳለው።”

የኦሮሞ እና የአማራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተሳታፊዎች
 የኦሮሞ እና የአማራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተሳታፊዎች

ጥያቄ 2

ሁለተኛው የአቶ ተስፋዬ ጥያቄ ሕገ መንግሥቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አለው የሚለውን ጉዳይ ይመለከታል። “የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ስላለው የልዩ ጥቅም ፍላጎት የእርሶ እና የክልሉ አቋም ምንድነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ዶ/ር አምባቸው ለዚህ ጥያቄ ምላሸ መስጠት የጀመሩት ”የአዲስ አበባ አጀንዳ ባልተገባ መንገድ ወደ ሳማይ ተጓጓለ። በየጊዜው አጀንዳ የሚቀርጹልን ኃይሎች ወደፊትም ሊኖሩ እንደሚችሉ አትጠራጠሩ” በማለት ነበር።

”አዲስ አበባን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠዉን የሚሸራርፍ አቋም በውስጣችን ማንም የለውም . . . የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፤ ይህ መብቱ እንዲከበርለት እኛም እንታገላለን። ከዛ ውጪ ያሉት ጽንፈኛ ሃሳቦች ተቀባይነት የላቸውም” ብለዋል።

ጥያቄ 3

ሦስተኛው የአቶ ተስፋዬ ጥያቄ፦

“አፋን ኦሮሞ ከአማርኛ እኩል የፌደራል የሥራ ቋንቋ በመሆኑ ላይ ያለዎት አቋም ምንድነው?”

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ምላሽ፦

”በክልላችን መገናኛ ብዙሃን ላይ ኦሮምኛ የስርጭት ሰዓት አለው። በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርም የመማሪያ ቋንቋ ነው። ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንሠራለን። በአማራ ክልል ሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎች በትምህርት ቤቶች ለመስጠት እቅድ አለን።”

ጥያቄ 4

ከአምቦ ከተማ ነዋሪው የቀረበው አራተኛው እና የመጨረሻው ጥያቄ፦

“የአምቦ ከተማ ነዋሪ ላለፉት በርካታ ዓመታት ትግል ላይ ነው የቆየው። በዚህም ምክንያት የከተማዋ መሰረተ ልማታዊ ፍላጎቶች አልተሟሉም። እርስዎ እና የአማራ ክልል ባለሃብቶች በዚህ ረገድ ከተማዋን እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ?”

ዶ/ር አምባቸውም፤ የአማራ ክልል ባለሃብቶች ከተማዋን ለማሳደግ መጥተው እንዲሠሩ መልዕክት አስተላልፍላችኋለው ብለዋል።