የሰሜን ዕዝ አዛዥ የሚናገሩት ንግግር በጣም የተሳሳተና የአማራን ህዝብ መብትም ታሳቢ ያላደረገ ነው

ሰሞኑን በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ሸዋ ዞን ለተከሰተው ግጭት ተጠያቂው ማን ነው የሚለውን በተመለከተ የተለያዩ እርስ በርስ የሚቃረኑ ሃሳቦች እየተሰነዘሩ ነው።

የአካባቢው የአስተዳደር፣ ነዋሪዎችና የአማራ ክልል የጸጥታ ኅላፊዎች የችግሩ ፈጣሪና ጥቃት ፈጻሚው ኦነግ ነው ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ኦነግ እዚያ አካባቢ ወታደር የለኝም ጥቃቱን አላደረስኩም ብሏል።

በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አዛዥ ሜ/ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ ደግሞ “በክልሉ የጸጥታ መዋቅር የሚመራው የጸጥታ ኃይል ነው በዋናነት ችግር ያደረሰው” ብለዋል።

የአማራ ክልል የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ምክትል ኅላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉ “ልዩ ኃይሉም ሆነ የጸጥታ መዋቅሩ ተልዕኮውን በሚገባ የሚያውቅና የአማራ ክልል ህዝብን ደህንነት የሚጠብቅ እንጂ መልሶ የአማራን ህዝብ የሚጎዳበት ምክንያት የለውም” ብለዋል።

አቶ ገደቤ እንዲህ አይነቱ ሃሳብ በጣም የተሳሳተና የአማራን ህዝብ መብትም ታሳቢ ያላደረገ ነው በማለት “እዚያ አካባቢ የሚንቀሳቀስ ኃይል መኖሩ ይታወቃል ማስረጃዎችም አሉን። የተፈጸመው ጥቃትም በአማራው ህዝብ ላይ እና በንጹሃን ላይ ነው። ይህን የፈጸመው ልዩ ኃይል ነው ማለት ምን ማለት ነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

እሳቸው እንደሚገምቱት ይህን የሚሉ አንድም ይህንን የፈጸመው አካል በህግ እንዳይጠየቅ ለማድረግ ወይም ደግሞ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት የሚጠብቀውን የፖሊስ አካል ህዝባዊ አመኔታ እንዳይኖረው ለማድረግ ሊሆን ይችላል።

ታዲያ በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ አዛዥ የተሰጠውን መግለጫ አንቀበለውም እያሉ ነው? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ “እኔ አልሰማሁትም ነገር ግን በዚህ መልኩ ተላልፎ ከሆነ ትክክል ነው ብዬ አላምንም። ተቀባይነትም የለውም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል አቶ ገደቤ ።

በሌላ በኩል ሜ/ጀኔራል ጌታቸው “ግጭቱ በአካባቢው በሁለቱም ወገን ባሉ የታጠቁ ኃይሎች መካከል የተፈጠረ ነው። ከሌላ አካባቢ በመጣ አካል ነው ችግሩ የተፈጸመው የሚባለው መሰረተ ቢስ ነው” ቢሉም በአማራ ክልል መንግሥት በኩል ደግሞ በተለያዩ የአስተዳደር መዋቅሮች በተደጋጋሚ ጥቃት ፈጻሚው ኦነግ ስለመሆኑ ይነገራል።

ጥቃቱ በኦነግ ለመፈፀሙ አቶ ገደቤ ሦስት ምክንያቶችን እንደ ማስረጃ ያስቀምጣሉ። “አንደኛ ቤት ለቤት እየዞረ የኦሮሞ አርሶ አደሮችን አማራ እምነታችሁን ለማስቀየርና ማንነታችሁን ሊነጥቅ እየተንቀሳቀሰ ነው በማለት ቅስቀሳ ማድረጉን የኦሮሞ አርሶ አደሮች ራሳቸው ነግረውናል፤ ሁለተኛ ከአካባቢው የጸጥታ መዋቅር አቅም በላይ የሆነ፣ የቡድን መሳሪያ የተጠቀመና የተቀናጀ ነው፤ ሦስተኛ አሰላለፉና ስምሪቱንም መመልከት ይቻላል። አማራውና ኦሮሞው ተሰባጥሮ የሚኖርበት ነው። ነገር ግን ጥቃቱ የተፈጸመው አማርኛ ተናጋሪዎች በሚኖሩበት አጣዬና ማጀቴ ነው ይህንንም ያደረገው የጸጥታ አካሉ ማረጋጋት ሲጀምር በሌላ ቦታ ሄዶ ነው” ይላሉ።

አቶ ገደቤ ይህን ይበሉ እንጂ ሜ/ጄኔራል ጌታቸው “እኛ ደርሰን አካባቢውን ካረጋጋን በኋላ በሌላ አካባቢ ሂዶ የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ጥቃት ያደርሳል” ሲሉ ክልሉን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ከወራት በፊት በምሥራቅ አማራ ወታደራዊ ስልጠና የሚሰጥ ቡድን መኖሩን የአማራ ክልል መንግሥት በተለይ ለቢቢሲ ገልጾ ነበር። ይህን መቆጣጠር ያልቻልነው በሁለት ምክንያት ነው ብለዋል ምክትል ቢሮ ኀላፊው። “አንደኛ ይህ አይነት ስልጠናው የተካሄደው በአፋር አማራና ኦሮሞ አዋሳኝና ድንበር አካባቢዎች በመሆኑ ከስልጣናችን ውጭ ነው። ሁለተኛ ጉዳዩን ራሱ ለማጥናት ጊዜ ያስፈልግ ነበር” ብለዋል።

የሰሜን እዝ አዛዡ ሜ/ጀኔራል ጌታቸው ግን “የአካባቢው ማህበረሰብ ኑሮው ከትጥቅ ጋር የተቆራኘ ነው። ከዚያ ውጭ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለ የጸጥታ አካል ካልሆነ በስተቀር ሌላ የታጠቀ አካል የለም” የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል።

ታስቦ የተቀነባበረና ጥቃት አድርሶ የመደበቅ እርምጃ ስለሆነ አስካሁን የተያዘ ጥቃት ፈጻሚው ቡድን አባል እንደሌለ የገለፁት ምክትል ቢሮ ኅላፊው የሞቱና የቆሰሉ ሰዎችን የሚመለከት መረጃም ተጠናቅሮ አላለቀም ብለዋል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE