ሞባይል በኢትዮጵያ 20 ዓመት ሞላው

BBC Amharic

ኢትዮ ቴሌኮም የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሃያ ዓመታት ተቆጥረዋል። በወቅቱ አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉት የመንግሥት ባለሥልጣናትና በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ጥቂት ባለሃብቶች ነበሩ።

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮ-ቴሌኮም የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች 39.5 ሚሊየን የደረሱ ሲሆን የመጀመሪያዎቹ ደንበኞች አገልግሎቱን ለማግኘት የቤት ካርታ፣ ምሥክሮችና የማስያዣ ገንዘብ ማቅረብ ነበረባቸው።

ተንቀሳቃሽ ስልክ

ዛሬ ላይ ግን ከተማሪ እስከ ሠራተኛው፤ ከደሃ እስከ ሃብታሙ ሁሉም የተንቀሳቃሽ ስልኮች ተጠቃሚ ሆኗል። ነገር ግን የዛሬ 20 ዓመት አካባቢ የመጀመሪያዎቹን ሲም ካርዶች የወሰዱ ደንበኞች አሁን አሁን እንደዚህ ሁሉም ነገር በቀላሉ መገኘቱ እንደሚያስገርማቸው ይናገራሉ።

አቶ ፀጋዬ አስፋው የዛሬ 20 ዓመት አካባቢ ኢትዮ-ቴሌኮም ደንበኞች ተመዝግበው ሲም ካርድና ተንቀሳቃሽ ስልክ እንዲወስዱ ማስታወቂያ ሲያስነግር ያስታውሳሉ።

በወቅቱ ለእርሳቸው ቅርብ የነበረው ቦሌ ለንደን ካፌ አካባቢ የሚገኘው ቅርንጫፍ ሄደው እንደተመዘገቡም ነግረውናል።

”በመጀመሪያ ለመመዝገብ በጣም ብዙ ወረፋ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ማንነትን የሚገልፅ መታወቂያ፣ የቤት ካርታና ምሥክሮችን ይዞ መገኘት ግዴታ ነበር። ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስታውሰው በጣም የሚያስቅ ሁኔታ ነበር ግን ሌላ ምንም አማራጭ ስላልነበረ አድርጌዋለሁ” ይላሉ።

እንደ አጋጣሚ ሆኖ በመሥሪያ ቤታቸው በኩል የተመዘገቡት አቶ ፀጋዬ እንደ ሌላው ሰው በጣም ብዙ ወረፋ አልጠበቁም ነበር። ”ምናልባትም ከአንድ ሰዓት በላይ አልቆየሁም “ይላሉ።

በወቅቱ አገልግሎት ሰጪው ኢትዮ-ቴሌኮም ከሚያቀርበው ተንቀሳቃሽ ስልክ ውጪ መጠቀም አይቻልም ነበር። አንድ ግለሰብ የእራሱን ስልክ ይዞ መንቀሳቀስ የማይፈቀድ ሲሆን ቴሌ ከሲም ካርድ ጋር አብሮ የሚሰጠውን ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም ግዴታ ነበር።

”በሚያስገርም ሁኔታ ሁላችንም ተጠቃሚዎች በመላው ሃገሪቱ ተመሳሳይ ተንቀሳቃሽ ስልክ ነበር የምንጠቀመው” ይላሉ።

ሌላኛዋ ተጠቃሚ ምስራቅ አሰግድ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ተንቀሳቃሽ ስልክ የያዘችው የመጀመሪያዎቹ ማለትም 091120… ብለው የሚጀምሩት ስልኮች አልቀው ሁለተኛው ዙር 091121… ላይ እንደሆነ ትናገራለች።

”የማልረሳው ነገር ቢኖር የመጀመሪያውን ዙር ተመዝግበው ስልክ ያወጡ ሰዎች በጣም ሃብታምና የኑሮ ደረጃቸው ከፍ ያሉ ሰዎች እንደሆኑ ይታሰብ ነበር” በማለት ታስታውሳለች።

በወቅቱ ተንቀሳቃሽ ስልኩ ምን ያደርጋል፤ አላስፈላጊና ትርፍ ነገር ነው ብለው ከሚከራረኩት መካከል እንደነበረች የምትናገረው ምስራቅ “አሁን ላይ ሆኜ ስመለከተው ግን ከእስትንፋስ ባልተናነሰ መልኩ ከኑሯችን ጋር መቆራኘቱ ያስገርመኛል” ትላለች።

ተንቀሳቃሽ ስልክ

ከኢትዮ-ቴሌኮም ሲም ካርድ አብሮ የተሰጣት ስልክ ‘ኖኪያ’ ሲሆን በጣም ትልቅ እንደነበርና “እንደውም ካውያ ነበር የሚያክለው። ሌላ ስልክ መግዛትና መጠቀም አይቻልም ነበር” በማለት ስለነበረው ሁኔታ ታስረዳለች።

በኢትዮ-ቴሌኮም ይሰጡ የነበሩት ስልኮች ልክ የቤት ስልክ እጀታን የሚያክሉና ይዞ ለመንቀሳቀስ እጅግ አስቸጋሪ እንደነበሩ አቶ ፀጋዬም ያስታውሳሉ።

”ኪስ ውስጥ ይዞ መንቀሳቀስ ከባድ ስለነበረ ምናልባት መኪና ያላቸው ሰዎች መኪናቸው ውስጥ ያስቀምጡት ነበር። ተንቀሳቃሽ ስልክ ብሎ ለመጥራት ይከብድ ነበር፤ ምክንያቱም ይዞ መንቀሳቀስ የማይታሰብ ነው” ይላሉ።

የወቅቱ አገልግሎት

የዛሬ 20 ዓመት የነበሩ ደንበኞች ስልኩን ይጠቀሙት የነበረው ለድምፅ መልዕክት ብቻ ሲሆን በወቅቱ የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት የተጀመረው ትንሽ ቆይቶ ነው ።

”መንገድ ላይም ተንቀሳቃሽ ስልኩን ይዤ ከሰዎች ጋር እያወራሁ ስራመድ በአካባቢዬ ያሉ ሰዎች ትኩር ብሎ የመመልከትና ከማን ጋር ነው የምታወራው እያሉ ይጠቋቆሙ ነበር” የምትለው ምስራቅ ስልክ ከመደውል ውጪ ሌላ አገልግሎት የማይታሰብ እንደነበር ትናገራለች።።

”ሌላው ቀርቶ የድምፅ አገልግሎቱን እራሱ ብዙ አልጠቀምም ነበር። ያኔ ትንሽ ፍርሃት ነበር፤ እንደ አሁኑ እንደልብ እዚም እዚያም መደወል ያስቸግር ነበር። ወጪውም አይቻልም” ትላለች።

”አሁን ግን ሁሉም ሰው ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዞ ከመጠቀሙ በተጨማሪ እንደልቡ ሲደውልና ሌሎች ነገሮች ሲጠቀም ስመለከት ይሄ ነገር በነፃ ነው እንዴ እላለው” ትላለች ምስራቅ።

አቶ ፀጋዬም በምስራቅ ሃሳብ ይስማማሉ።

“በአካባቢዬ የነበሩ ሰዎች በቃ ወይ ጉድ፤ እንዲህም ይቻላል? እያሉ በጣም ይገረሙ ነበር። በወቅቱም የመሻሻልና የሥልጣኔ ምልክት ተደርጎም ይወሰድ ነበር” ሲሉ በሰዓቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።

በጊዜው ስልክ ይዞ እየተነጋገሩ መንቀሳቀስ የተለመደ አልነበረም። አቶ ፀጋዬ በግላቸው ያጋጠማቸው ነገር ባይኖርም ሰዎች ሲያወሩ ከሰሙት ግን ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው መንገድ ላይ እያወሩ ይሄዱ የነበሩ ሰዎች እንደ ብርቅ ይታዩ እንደነበርና እንደውም አንዳንዶቹ አብደዋል መባላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

”አሁን ያለው የስልክ አግልግሎትና የድሮውን ሳወዳድረው ልክ የቀንና የጨለማ ዓይነት ስሜት ነው የሚሰማኝ። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው እንዴት አድርጌ ሥራ እሠራና እንቀሳቀስ እንደነበረ አይገባኝም። አሁን ያለው አገልግሎት በጣም ፈጣንና የማያስቸግር ነው፤ የዝያኔ ግን እንዴት እንጠቀመው እንደነበር አይገባኝም” ይላሉ።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE