በሱዳን ከወታደራዊ ይልቅ ህዝባዊ መንግስት ይመስረት በሚል ህዝባዊ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው፡፡

በሱዳን ህዝባዊ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው
በሱዳን የተካሄደው የመንግስት ለውጥ የሀገሪቱን መሪ ከስልጣን ቢያስወግድም ከወታደራዊ ይልቅ ህዝባዊ መንግስት ይመስረት በሚል ህዝባዊ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው፡፡

ህዝባዊ ተቃውሞው የቀጠለው በአሁኑ ሰዓት አገሪቱን እየመራ ያለው ወታደራዊ መንግስት ያወጣውን ሰዓት እላፊ ወደ ጎን በመተው እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ሰልፈኞቹ ካርቱም በሚገኘው የአገሪቱ ጦር ሰራዊት ዋና መስሪያ ቤት አቅራቢያ ቀኑን ሙሉ በመቀመጥ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ የተቃውሞው አስተባባሪዎች ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በሱዳን የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተከትሎም የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአገሪቱ ሁሉም አካላት ከግጭት እራሳቸውን እንዲያቅቡና መረጋጋት እንዲፈጥሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በተለይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት እንዳሉት መፈንቅለ መንግስት ሱዳን ላጋጠማት ፈተናና ለህዝቡ ፍላጎት ተገቢ ምላሽ አይደለም፡፡

በሱዳን የተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስትም ህብረቱ በቶጎ ሎሜ በአውሮፓውያኑ 2000 ያፀደቀውንና ኢ-ህገመንግስታዊ ለውጦችን የሚቃወመውን ስምምነት የሚጥስ ነው ብለዋል፡፡

የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታን በቅርበት እየተከታተሉ ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጽሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ የአገሪቱ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው ሁሉን አቀፍ በሆነ የሽግግር ሂደት ነው ብለዋል፡፡

ይህንንም ለመደገፍ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሱዳን ህዝብ ጎን ለመቆም ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ምንጭ፦ አልጀዚራ እና ኦልአፍሪካ