ግጭት ቀስቃሽ አተካሮዎች አገር እያደሙ ነው!

ኢትዮጵያ ማባሪያ ካጣው ግጭት ውስጥ በፍጥነት የሚያወጣት መፍትሔ ማፍለቅ እንደማያዳግት ማንም በቀላሉ የሚገነዘበው እውነት ነው፡፡ ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› እንደሚባለው፣ ለብዙዎቹ ግጭቶች ምክንያት የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ለሰላም ጀርባቸውን መስጠታቸውም ይታወቃል፡፡ መንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ግጭት በመቀስቀስና በማባባስ የተጠመዱ መኖራቸው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ከመንግሥት በተቃራኒ የተሠለፉ ስብስቦች ውስጥም እንዲሁ፡፡ ለግጭት መቀስቀስ መንስዔ ከሆኑት መካከል የተወሰኑት ኢፍትሐዊነት፣ አግላይነት፣ ሥልጣንና ጥቅም አጋባሽነት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ጨፍላቂነት፣ ቂመኝነት፣ ግትርነት፣ ሴራና ጭካኔ ይጠቀሳሉ፡፡ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ለአገር የማይበጁ ክፋቶች ገለል በማለት በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ለመፍጠር ጥቂት ጥረት ቢደረግ ኢትዮጵያ የግጭት፣ የድህነትና የተስፋ መቁረጥ ምሳሌ አትሆንም ነበር፡፡ ነገር ግን ግጭት ቀስቃሾችና አባባሾች በዝተው አገርና ሕዝብ የመከራ ቀንበር ተሸካሚ ተደርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተዘፈቀችበት ድህነት ውስጥ ወጥታ በልማትና በዕድገት ጎዳና መገስገስ የምትችለው፣ ለግጭትና አላስፈላጊ ለሆኑ ድርጊቶች የሚያመቻቹ ተግባራት ሲገቱ ነው፡፡ እነዚህ የማይጠቅሙ ተግባራት ሊቆሙ የሚችሉት ከጥላቻና ከክፋት ውስጥ ለመውጣት ፈቃደኝነት ሲኖር ነው፡፡ ይህ ፈቃደኝነት አገርን ለማስቀደም የሚያስችል ሞራላዊ ከፍታ መላበስ አለበት፡፡ ማንኛውም ዓይነት የሥልጣንም ሆነ የጥቅም ጉጉት ከአገር መብለጥ እንደሌለበት የሚያስገነዝብ ሊሆን ይገባል፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በእኩልነትና በመግባባት ላይ የተመሠረተ ምኅዳር እንደሚያስፈልጋቸው መግባባት መፈጠር ይኖርበታል፡፡ ከሌብነት፣ ከኢሞራላዊ ዝቅጠት፣ ከራዕይ አልባነትና ከኢሰብዓዊነት ጋር የተቆራኙ አስተሳሰቦች መገራት ይኖርባቸዋል፡፡ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ መከበር አለበት፡፡ በዚህ ዓይነቱ ከፍታ ላይ መገኘት ሲቻል ግጭት ቀስቃሽነት ዋጋ ቢስ ይሆናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ እጅግ በጣም የመረረ የድህነት ኑሮ እየገፉ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ በተለያዩ አካባቢዎች በሚካሄዱ ግጭቶች ሳቢያ ሕይወታቸው በከንቱ እየጠፋ ነው፡፡ ሕይወታቸው የተረፈውም ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት፣ ለንብረት ውድመት፣ ለመፈናቀል፣ ለዕገታና ለዘረፋ ከመዳረጋቸው በተጨማሪ ለአስገድዶ መድፈርና ለሌሎች አሳዛኝ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ተጋልጠዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ፣ መሥራት፣ መኖር ካለመቻላቸውም በላይ ሰላማቸውና ደኅንነታቸው ተቃውሷል፡፡ እነዚህ ሁሉ መከራዎች ባሉባት አገር ውስጥ ለመስማት የሚዘገንኑ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችና ወንጀሎች እየተፈጸሙ ነው፡፡ ከእነዚህ ክስተቶች ይፋ መሆን በኋላ በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች የሚቀነቀኑ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች፣ የነገን ተስፋ እያጨለሙ ዕልቂትና ውድመት በስፋት እንዲቀጥሉ መንገዱን እየጠረጉ ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ተዋንያን ለአገር ህልውና ሲሉ መላ ይፈልጉ፡፡

በመረጃ ልውውጥ ረገድ በአደገኛ ሁኔታ ሐሰትና ማደናገር በሞላበት በዚህ ዘመን ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች ከመጠን በላይ በዝተዋል፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሐሰተኛ መረጃዎች ኃላፊነት በጎደለው መንገድ በስፋት እየተሠራጩ ሲሆን፣ በዚህ ድርጊት ውስጥ ከመንግሥታት ጀምሮ የተለያዩ ዓላማ ያላቸው በርካታ ተዋንያን በብዛት እየተሳተፉ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ስንመለስ ሐሰተኛና አደናጋሪ መረጃዎች በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ተባባሪዎቻቸው አማካይነት እንደሚሠራጩ የታወቀ ነው፡፡ የአንድን ወገን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል በስፋት የሚሠራጩ ሐሰተኛና አደናጋሪ መረጃዎች፣ ጥላቻንና መቃቃርን በማጋጋል በየቦታው በጭካኔ የተሞሉ ጥቃቶች እንዲከፈቱና ንፁኃን እንዲጎዱ በተደጋጋሚ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ ታይተው የማይታወቁ ሰብዓዊነት የጎደላቸው ጭካኔዎች፣ ግጭት ለማቀጣጠል ሁነኛ ግብዓት ሆነው እንዲያገለግሉ ግፊት ሲደረግም እየታየ ነው፡፡

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መግለጫዎች እንደሚያሳዩት፣ አብዛኞቹ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት በቀላሉ ሊገቱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎች ቢሰጡም አዳማጭ በመጥፋቱ፣ ዘግኛኝ ጭካኔዎች እየተፈጸሙ ችግሩ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ነው፡፡ የሐሰተኛና የአደናጋሪ መረጃዎች ጠንሳሾች በሴራ ፖለቲካ የተካኑ በመሆናቸው፣ በግጭቶች ወይም በጥቃቶች ሳቢያ በደረሱ የጭካኔ ግድያዎች ላይ በማተኮር ፍትሕ ከመሻት ይልቅ የፕሮፓጋንዳ አተካሮ ይፈጥራሉ፡፡ አተካሮው ሲካረር አንዱን ወገን በሌላው ላይ ለማስነሳት መልካም አጋጣሚ ስለሚፈጠርላቸው፣ የግጭት አዙሪቱ ባለበት እንዲቀጥል እሳቱን ይቆሰቁሳሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ነውረኝነት ለአገር ህልውና ሲባል ተባብሮ ማስቆም ሲገባ፣ ማዶ ለማዶ ሆኖ ጣት መቀሳሰር መፍትሔ ያመጣ ይመስል ሌሎችም በዚያው መስመር መንጎዳቸው ያስተዛዝባል፡፡ ይህ የማያዋጣ መንገድ ስለሆነ ደጋግሞ ማሰብ ግድ ነው፡፡

በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው በተለይ ለግጭት ቅስቀሳ የሚውሉ አደገኛ መልዕክቶች በማኅበራዊ የትስስር መረቦች ሲለቀቁ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብዙዎቹ የፖለቲካ ኃይሎች ከእነ ተከታዮቻቸው እጃቸው እንዳለበት ነው፡፡ ማንነታቸው በማይታወቅ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ባለቤቶች ከሚለቀቁ መልዕክቶች ጀርባ የገዥውን ፓርቲ አባላት ጨምሮ፣ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት እንዳሉበት ነጋሪ አያስፈልግም፡፡ በመንግሥት የተሰጣቸው የኃላፊነት ወንበር ላይ የተቀመጡ ግለሰቦችና ለሕዝብ እንታገላለን የሚሉ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት ሰዎች ድረስ፣ ሰላማዊው አየር ተመርዞ ግጭት የዕለት ተዕለት ሥራ እንዲሆን ማድረግ ከተለመደ ዓመታት እየነጎዱ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ሳያስቡት ከአንደበታቸው ከሚወጣው ኃይለ ቃል ጋር ተዳብሎ የሚታየው ስሜታቸው፣ ሰላም እንዳይሰፍንና መከራው እንዲቀጥል ምን ያህል ፍላጎት እንዳላቸው ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ግጭት ቅስቀሳ ያንገሸገሸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን፣ አገሩ እየደማችበት መዝለቅ እንደማይቻል ገብቶት የሰላም ያለህ እያለ እየጮኸ ነው!