ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዛሬ አሥመራ ውስጥ ከሱዳን ወታደራዊ መሪ ጀኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር በኹለትዮሽ ግንኙነቶችና በሱዳኑ ጦርነት ዙሪያ ተወያይተዋል።
ኢሳያስ፣ የሱዳኑ ጦርነት በሱዳናዊያንና በወዳጅ ጉረቤት አገራት ጥረት ብቻ ሊፈታ እንደሚገባ አቋማቸውን ለቡርሃን እንደገለጡላቸው የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል ገልጸዋል።
ቡርሃን የደኅንነት ሚንስትራቸውን ሌትናንት ጀኔራል አሕመድ ሞፋዳልን ጭምር አስከትለው በአሥመራ ባደረጉት ቆይታ፣ ከኢሳያስ ጋር በቀጠናዊና ጅዖፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጭምር ተወያይተዋል ተብሏል።
ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ከሱዳኑ አቻቸውን ዓሊ የሱፍ ሻሪፍ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በኹለትዮሽ ግንኙነቶች፣ በሕዳሴው ግድብ ውዝግብ እና በሱዳኑ ጦርነት ዙሪያ ያተኮረ እንደነበርና ሁለቱ አገራት የጋራ በሚሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክራቸውን ለመቀጠል እንደተስማሙ ተገልጧል።
ዓሊ፣ የሕዳሴ ግድብ ውዝግብ በድርድር ካልተፈታ፣ ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችልና ጦርነት ከተቀሰቀሰም ሱዳን ከግብጽ ጋር እንደምትወግን በቅርቡ ላንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ መናገራቸው ተዘግቦ ነበር።
ይህንኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩን አስተያየት ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ ቅራታዋን ለመግለጽ የሱዳኑን አምባሳደር ጠርታ እንደነበር ባለፈው ሳምንት የሱዳን ዜና ምንጮች መዘገባቸው አይዘነጋም።