በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በምንጃር ወረዳ እና በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ከ700 በላይ አርጎባዎች ከመተሐራ ከተማ ተፈናቅለዋል ተባለ። በመተሐራ ከተማ ደርሶብናል ባሉት ማስፈራሪያ የሸሹ ሰዎች በአዋሽ ከተማ መጠለያ ይገኛሉ። በምንጃር ወረዳ እና በፈንታሌ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት ሳቢያ ሰዎች መፈናቀላቸውን ያረጋገጡት የአርጎባ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (አሕዴድ) ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኻሊድ ይሱፍ ገልጸዋል።
በመኖሪያ ቤታቸው ከተፈናቀሉ አራት ቀናት እንደተቆጠሩ የሚናገሩ የመተሐራ ከተማ ነዋሪ ቀድሞም ማስፈራሪያዎች ይደርሱባቸው እንደነበር ለDW አስረድተዋል።
አሁን በአዋሽ ከተማ በሚገኝ መጠለያ የሚገኙት እና ስማቸው እንዲገለፅ የማይሹት ተፈናቃይ እንደሚሉት “የከተማው ወጣቶች እና በቄሮ ስም ከተለያዩ ቦታዎች የተሰባሰቡ አሉ። ውጡ ውጡ፤ አደጋ ይደርስባችኋል፤ አለዚያ ከነቤታችሁ ትቃጠላላችሁ” የሚሉ ማስፈራሪያዎች ይደርሷቸው ነበር። “ስራ ቦታ ቁጭ ባልኩበት መጥተው የአካል ጉዳት አድርሰውብኛል። ጥርሴ ተሰብሯል፤ ተደብድበናል።የሕግ አካል መጥቶ የጠየቀን የለም። ምን ደረሰባችሁ ያለ የለም” የሚሉት ተፈናቃይ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ይሁኑ የጸጥታ አስከባሪዎች ይደርሱባቸው ለነበሩ ማስፈራሪያዎች ትኩረት እንዳልሰጡ ይወቅሳሉ።
“እኛ አንወጣም ብለን ተቀምጠን ነበር። ግን በአደባባይ ሰው መገደል ጀመረ። እንዴት ሰው ይቀመጣል?” የሚሉት ጎልማሳ ከአስራ ሶስት አመታት በፊት በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ግጭት አባታቸው መገደላቸውን ለDW ገልጸዋል። ተፈናቃዩ እንደሚሉት ኹኔታው እየከፋ ሲሔድ መተሐራን ጥለው ወደ አዋሽ ሸሽተዋል። ጎልማሳው “መጠለያ ውስጥ ከ700 በላይ ሰው አለ። በእርግጥ የአፋር ክልል እና እዚህ ያለው ሰው በጥሩ ኹኔታ እያስተናገደው ነው። ሌላ ግዙፍ ችግር የለም። ግን ሰዉ ወደመጣበት ለመመለስ ዘላቂ መፍትሔ ይፈልጋል” ሲሉ አክለዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት በመተሐራ ከተማ በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ግጭት የሸሹ ነዋሪ በበኩላቸው በአዋሽ የተጠለሉ አብዛኞቹ ሰዎች ወንዶች መሆናቸውን ገልጸው “አሁን ሴቶቹ በምን ኹኔታ ላይ እንዳሉ አልታወቀም” ሲሉ ተናግረዋል። ወደ አዋሽ አቅንተው ከተፈናቀሉ ሰዎች ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ናቸው የተባሉትን የመተሐራ ከንቲባ ለማግኘት ያደረግንው ጥረት አልሰመረም። የአርጎባ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (አሕዴድ) ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኻሊድ ይሱፍ እንደሚሉት በአማራ ክልል ምንጃር ወረዳ ነዋሪዎች እና በፈንታሌ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል ከዚህ ቀደምም በግጦሽ መሬት ሳቢያ ግጭቶች ነበሩ። አቶ ኻሊድ “እዚያ ከግጦሽ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ግጭት መተሐራ የሚኖሩ ሰላማዊ የአርጎባ ሕዝብ በቄሮ ስም የሚንቀሳቀሱ እንደተተናኮሏቸው” አረጋግጠናል ብለዋል። ከመተሐራ ተፈናቅለው በአዋሽ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ400 እስከ 500 እንደሚደርስ አቶ ኻሊድ ገልጸዋል። በሁለቱ ወረዳዋዎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው “ግጭት መፍትሔ አላገኘም። መከላከያ ገብቶ እንዳረጋጋ ሰምተናል” ያሉት አቶ ኻሊድ ከኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ጋር በመሆን መፍትሔ ለመፈለግ ቀጠሮ መያዙን ገልጸዋል።