“የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመት የነዋሪው ውክልና የለውም” የሚለው አስተሳሰብ ህጋዊ መሠረት የለውም – አዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት

ከአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

የተከበራችሁ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች !!

Image may contain: text

አገራችን ኢትዮጵያ 76 ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚኖሩባት ታላቅ አገር ነች፡፡ የህዝባችን አብሮ የመኖር እሴት የሰው ልጆች መደበኛ ማህበራዊ ግንኙነት ተሻግሮ በደም ዝምድና ተጋምዶ በባህል ተሳስሮ ላይለያይ ተቆራኝቷል፡፡ ይህ ህብረት የብሄር ማንነት እና የእምነት ልዩነት ሳይለያየው ለሺ ዓመታት፣ ሺ ችግሮችን ተጋፍጦ ይሄው ዛሬም ድረስ በጋራ ዘልቋል፡፡

የዚህ አኩሪ ታሪክ ጉዞ አልጋ ባልጋ ያልነበረ ከመሆኑ ባሻገር፣ ህዝባችን የሚያነሳቸው የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄዎች በተለያዩ ጊዜያት የነበሩትን መንግሥታት በመታገል ለመብቱ የተከራከረበት ወቅትም በርካታ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የተነሱት የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሰብዓዊ መብትና ሌሎች መሠረታዊ ጥያቄዎች ምክንያት በአገሪቱ ለውጥ አንዲመጣ አድርጓል፡፡

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያውንን እና ሌላውን ዓለም ያስደመሙ በርካታ የለውጥ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከተማችንም ዘመን ተሻጋሪና ተጨባጭ ውጤቶች እየተከናወኑና ቀደም ሲል ህዝባችን ያነሳቸው የነበሩ የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የእኩልነት፣ የልማትና መሰል አጀንዳዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በመሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ የሚመራው የከተማችን አስተዳደር ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ መርሆዎችን ተከትሎ የአዲስ አበባ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማካሄድ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸው የከተማው ነዋሪ የሚመሰክረው ሃቅ ነው፡፡

በሌላ በኩል የከተማችን ነዋሪዎች ህገመንግሥቱ በሰጣቸው ሥልጣን መሠረት በከተማው ህዝብ ተሳትፎ ወኪሎችን በመምረጥ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፣ እየተከናወኑም ይገኛሉ፡፡ ይህ ሲባል ህዝቡ ከአስፈፃሚው አካል ጐን ሆኖ ባያግዝና ባይሳተፍ ኖሮ አሁን የተገኘውን ውጤት ማስመዝገብ አይቻልም ነበር፡፡

ስለሆነም የከተማችን ነዋሪዎች በሁሉም የሥራ መስኮች ያልተቋረጠ ድጋፍ ያደረገና እያደረገ ያለ ሲሆን በተለይም የአዲስ አበባ ሰላም ተጠብቆ እንዲቀጥል በማድረግ ለሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ትልቅ ትልቅ ተምሳሌት ሆኖ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ህዝቡ ላበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋናና ዕውቅና ሊቸረው ይገባል፡፡

ይሁንና አሁንም በከተማችን የሚስተዋሉና በልዩ ትኩረት ሊፈቱ የሚገባቸው ችግሮች እንዳሉ በመገንዘብ ችግሮችን ለመፍታት የከተማው አስተዳደር ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሆነ እና ምከር ቤቶችም የክትት ልድጋፍና ቁጥጥር ሥራችን አጠናክረን የተጠያቂነት አሠራር በጥብቅ ዲስፒሊን እየተመራ ተግባራዊ አየተደረገ ይገኛል፡፡

ከምክርቤቱ የምርጫ ዘመንጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መካሄድ የነበረበትን የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ እንዲራዘም በወሰነው መሠረት እና እንዲሁም ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የከተማውን አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995ን ለማሻሻል ባወጣው አዋጅ ቁጥር 1094/2010 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፡- የምርጫ ጊዜ እንዲራዘም የወሰነ እና“ ምርጫ ተደርጐ በምርጫው መሠረት አዲስ አ ስተዳደር እስኪደራጅ ድረስ በሥራላይ ያለው ምክር ቤቱ እና አጠቃላይ የከተማው የአስተዳደሩ በነበረበት ሁኔታ ይቀጥላል” በሚል በደነገገውና በወሰነው ውሳኔ
መሠረት ህጋዋ እውቅና አግኝቶ የቀጠለ አስተዳደር እንደሆነ ሊታወቅ የሚገባው ሲሆን በዚሁ አዋጅ ቁጥር 1094/2010 አንቀጽ 3 ስር “ምክትል ከንቲባው ከምክር ቤት አባላት ውስጥ ወይም ከምክር ቤት አባላት ውጭ የሚሾም ሆኖ የሥራ ዘመኑ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ይሆናል”ተብሎ በግልጽ በተደነገገው መሠረት የከተማው ምክር ቤት ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመት በወቅቱ በተገኙት ምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል፡፡

ስለሆነም “የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመት የነዋሪው ውክልና የለውም” ህጋዊ አይደለም በሚል የሚነሱ የተሳሳቱ አስተሰሰቦች ምንም ዓይነት ህጋዊ መሠረት የሌላቸው እና በስሜት ብቻ የሚንጸባረቁ እንዲሁም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1094/2010 የሚፃረር እና ህገወጥ እንደሆነ ሁሉም የከተማችን ነዋሪ ሊረዳው ይገባል፡፡

ይሁንና አስተዳደሩ በከተማችን ነዋሪ ተሳትፎ ጭምር በአገር ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ሌት ተቀን ደፋ ቀና በሚልበትና በዕቅድ ተይዘው እየተተገበሩ ያሉ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማሳካት እየተረባረበ እና ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ባለበት በዚህ ወቅት አንዳንድ ወገኖች በህግ የተቋቋመውን የአስተዳደሩን ተግባራት በማደናቀፍ የህዝብ ያልሆኑ ጥያቄዎችን የህዝብ በማስመሰል ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል፡፡

ስለሆነም በአገራችን ብሎም በከተማችን የመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ በቅርቡ በከተማችን ሰላምን ለማደፍረስ እየታዩ ያሉ ኢ-ህገመንግሥታዊ እንቅስቃሴዎችን በትኩረት በመከታተልና ህገወጥ እንቅስቃሴ አድራጊዎችን በሰላማዊ መንገድ በመታገል የከተማችን ነዋሪዎች እንደወትሮው ሁሉ የከተማችንን ሰላም በማስከበር የተጀመረውን ልማት በማስቀጠል የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ከከተማው አስተዳደር ጐን እንደሚቆም ያለንን ጽኑ እምነት እየገለጽን፡-

1ኛ. ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የሚያራግቡ፣ በህጋዊ መንገድ በተመረጠው አስተዳደር ላይ አመጽ የሚያነሳሱ ማናቸውም ድርጊቶች ለማንም የማይጠቅም ህገወጥ ድርጊት እና ፀረ-ህገመንግሥትም ስለሆነ ባስቸኳይ እንዲቆም፣
2ኛ. አሁን ያለው የከተማው አስተዳደር ህጋዊ መሠረት ያለው እና በም/ቤቱ ፀድቆ የተሾሙ በመሆኑ መላው የከተማው ነዋሪዎች ከከተማው አስተዳደር ጐን በመቆም በከተማችን ነዋሪዎች ድምፅ ውክልና የተሰጠውን ም/ቤት ሥልጣን ወደጐን በመተው እየተነሱ ያሉ የማደናገሪያ አስተሳሰቦችን አምርሮ እንዲታገል፣

3ኛ. በከተማችን ውስጥ የላቀ ልማት ለማስመዝገብ፣ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለማድረግ የሁሉም ወገኖች የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ በመሆኑ ለውጡን ባስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል የከተማችን ነዋሪዎች ሁሉን አቀፍ ትብብር እንዲያደርጉ እና ከከተማው አስተዳደር ጐን እንዲቆሙ ጥሪ እያቀረብን፣ የብሄርብሄረሰቦችና ህዝቦች የቃልኪዳን ሠነድ እና የህጐች ሁሉ የበላይ የሆነውን ህገመንግሥት የማክበር፣ የማስከበርና የመጠበቅ ኃላፊነታችሁን በመወጣት ህዝቡን በማደናገር የከተማችንን ሰላም ለማደፍረስ ሌት ተቀን የሚጥሩ ኃይሎችን በመታገል ከከተማ አስተዳደሩና ከምክርቤቱ ጐን በመሆን የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ

4ኛ. የአዲስ አበባ ጉዳይን በተመለከተ ከተማችን የሁሉም ብሄርብሄረሰቦችና ህዝቦች በፍቅር፣ በመተሳሰብና በመቻቻል በአብሮነት ለሰላም ልማትና ዴሞክራሲ ዘብ የቆመ ህዝብ የሚኖርባት የሁላችንም ከተማ የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መኖሪያ መሆንዎ ታውቆ ከከተማው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች የህጐች ሁሉ የበላይ በሆነው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ህገመንግሥት ምላሽ የሚያገኝ ስለሆነ ፍጸም የግጭት መንስኤ መሆን አይገባውም፣

5ኛ. የከተማው አስተዳደር እንደሌላው ጊዜ ሁሉ የከተማውን ሰላምና ፀጥታ ከማስከበር ባሻገር እያከናወነ ያላቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ፕሮግራሞችን አጠናክሮ እንዲቀጥል እያሳሰብን፣ እንደወትሮው ሁሉ የከተማችን ነዋሪዎችም ህግና ሥርዓት እንዲከበርከ አስተዳደሩ፣ ከህግ እና የፀጥታ አስከባሪ አካላት ጐን በመሆን ለሰላም ዘብ በመቆም የተለመደው ትብብሩን እንዲቀጥል እንጠይቃለን፡፡
እናመሰግናለን!!!

መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም.

አዲስአበባ