የሺናሻ ማኅበረሰብ ታሪካዊ ቦታ ዳሐን ዋሻ ለኢንቨስትመንት መሰጠቱ ተቃውሞ ቀሰቀሰ

ዳሐን ዋሻ አካባቢ “የሺናሻ ማኅበረሰብ ከአስራ አንድ ትውልድ በላይ እዚያው ኖሮ እዚያው ሞቶ እዚያው የተቀበረበት የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው የሺናሻ ማንነት የሚገለፅበት ቦታ ነው”

Related image

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቡለን ወረዳ ታሪካዊ ቦታ ለኢንቨስትመንት በመሰጠቱ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ። በቡለን ወረዳ የሚገኘው ዳሐን ዋሻ በማዕድን ፍለጋ ለተሰማራው ቢ አይካ የተባለ ኩባንያ ተሰጥቶ ነበር። በአካባቢው ታሪካዊ አልባሳት እና የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች እንደሚገኙበት የሚናገሩ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ቦታው ታሪካዊ በመሆኑ እና “የቅድመ-አያቶቻችን መቃብር ስለሚገኝበት” ውሳኔው ትክክል አይደለም ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

“በሺናሻ ባሕል እርቀ-ሰላም የሚፈጸምበት ቦታ” የሚሉት ነዋሪው “መሰጠቱ ተገቢ አይደለም። ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አልተደረገም” ሲሉ ይወቅሳሉ።

ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ለግል ኩባንያ የተሰጠው ዳሐን ዋሻ አካባቢ “የሺናሻ ማኅበረሰብ ከአስራ አንድ ትውልድ በላይ እዚያው ኖሮ እዚያው ሞቶ እዚያው የተቀበረበት የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው የሺናሻ ማንነት የሚገለፅበት ቦታ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። “ወጣቱ ይቃወማል፤ ያገር ሽማግሌዎቹም ይቃወማሉ” የሚሉት የቡለን ወረዳ ነዋሪ “የእኛን ታሪክ ወደ ጎን በመተው የኢንቨስትመንት ሥራውን ማስቀጠል አንችልም” ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማዕድን ሐብት ልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ይሱፍ አልበሽር ቦታው ታሪካዊ ስለመሆኑ መረጃ እንዳልነበር ተናግረዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ እና ያገር ሽማግሌዎች ያቀረቡትን ቅሬታ መቀበላቸውን ያረጋገጡት ኃላፊው “ባለሐብቱ ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጠው ዝግጅት ላይ ነን” ሲሉ ተናግረዋል።