የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን አደጋ ከኢንዶኔዥያው ላየን አይሮፕላን አደጋ ጋር ተመሳሳይ ነው ተባለ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን አደጋ ከኢንዶኔዥያው ላየን አይሮፕላን አደጋ ጋር ተመሳሳይ ነው ተባለ

The black box data of Ethiopian Airlines indicated Clear similarities between Lion Air Crash and Ehtiopian Airlines Crash

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የተገኘው የበረራ መረጃ አደጋው ባለፈው ጥቅምት ወር በኢንዶኔዢያ ባሕር ላይ ከተከሰከሰው አውሮፕላን ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው እንደሚያመለክት የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስትር ገለጹ።

አደጋው የገጠማቸው ሁለቱ አውሮፕላኖች ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት የተባሉ ሲሆኑ በደረሰባቸው አሰቃቂ አደጋ በውስጣቸው የነበሩ የሁሉም ተጓዦች ህይወት አልፏል።

ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አደጋ የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ይዟቸው የነበሩት 157 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

የአውሮፕላኑ የበረራ መመዝገቢያ ሳጥኖች ወደፈረንሳይ ባለፈው ሳምንት ተወስደው የነበረ ሲሆን፤ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ የበረራ መረጃው ከአውሮፕላኑ የመረጃ ማስቀመጫ ክፍል ላይ በአግባቡ እንደተሰበሰበ ተናግረዋል።

ከአውሮፕላኑ የተገኘውና አደጋው ስለደረሰበት አውሮፕላን ለሚደረገው ምርመራ ጠቃሚ መረጃ ይሆናል የተባለው የበረራ መረጃ ምርመራውን ለሚያከናውነው ቡድን መሰጠቱም ተገልጿል።

ከተሰበሰበው መረጃም “በኢትዮጵያ እየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ ከወራት በፊት በኢንዶኔዢያው ተመሳሳይ አውሮፕላን ላይ ከደረሰው አደጋ ጋር ግልፅ መመሳሰል ታይቷል” ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የበረራ መመዝገቢያ መረጃ እንደሚያመለክቱት በሁለቱም የአውሮፕላን አደጋዎች ላይ ድንገተኛ የከፍታ መለዋወጥ እንደታየ፤ ይህም አውሮፕላኖቹ ያልተጠበቀ ከፍና ዝቅ የማለት ተመሳሳይ አጋጣሚዎች እንደተስተዋለባቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የምርመራ ባለሙያዎች በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደሃገራቸው እንደሚመለሱና ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመው፤ “የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራው ውጤት በ30 ቀናት ውስጥ ይፋ ይሆናል” ብለዋል ሚኒስትሯ።

የቦይንግ ኩባንያ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዴኒስ ሙሊንበርግ እንደተናገሩት ድርጅታቸው በአውሮፕላን አደጋው ዙሪያ በሚደረጉ ምርመራዎች ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።