የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ፥ በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራውን የህወሓት ቡድን አስጠነቀቁ።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ፥ በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራውን የህወሓት ቡድን አስጠነቀቁ።

ፕሬዜዳንቱ በማስጠንቀቂያቸው ” ቡድን ” ሲሉ የጠሩት ሃይል የወረዳና የከተማ የህዝብ ምክር ቤቶች ለመረበሽ እየሄደበት ያለው ርቀትና በማድረግ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ማቆም አለበት ብለዋል።

መስከረም 14/2017 ዓ.ም በፕሬዜዳንቱ ፊርማ ተፈርሞ ለሁሉም የወረዳና የከተማ ም/ቤቶች የተፃፈው የማስጠንቀቅያ ደብዳቤ ” የህዝብ ምክር ቤቶች የትግራይ ጊዚያዊ መንግስትና የህዝቡ አካል እንጂ የህወሓት መዋቅር አለመሆናቸው አውቆ ‘ ቡድኑ ‘ የራሱ መሳሪያ ለማድረግ እያካሄደ ያለውን መሯሯጥና ውንብድና ማቆም አለበት ” ይላል።

ስለሆነም ምክር ቤቶቹ የመንግስትና የህዝብ መዋቅር መሆናቸው በማመን ‘ ቡድኑ’ ምክር ቤቶቹ በመጠቀም ያልደገፉትንና ሃሳቡ ያልተቀበሉት የመንግስት ሹመኞች ጥላሸት ለመቀባትና ከሃላፊነት ለማውረድ የሚያደርገው ጥረት መቆም አለበት ሲል አስጠንቅቋል።

ምክር ቤቶቹም ይህንን የመንግሰትና የፓለቲካ ድርጅት የሚቀላቅል ህገ-ወጥ ጣልቃ ገብነት ማውገዝ አለባቸው ብሏል።

” ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ህግና ስርዓት ለማስከበር ሲባል ወደ ህጋዊ ተጠያቂነት መሸጋገር የግድ ይሆናል ” በማለት አክለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህወሓት ከቀናት በፊት የጊዚያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ  ያወጣውን የአቋም መግለጫ የሚቃወም መግለጫ  አውጥቷል።

በዶ/ር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት መስከረም 14/2017 ዓ.ም ያወጣው  ባለ 4 ነጥብ የተቋውሞ መግለጫ ፤ ” ጊዚያዊ አስተዳደሩ ጊዚያዊ  ስራዎች ለመስራት መቋቋሙ ተዘንግቶ ከተቀመጠለት የቆይታ የጊዜ ሰሌዳ በላይ እንዲቆይና ራሱን ወደ ተሟላ የመንግስት ሃላፊነት  ለመለወጥ የሚያደርገው ጥረት ፀረ ዴሞክራሲና ኢ-ህገመንግስታዊ ነው ” ብሏል።

ምንም እንኳን ” ኢ-ህገመንግስታዊ ” ብሎ ቢገልጽም የአገር ወይም የክልሉ ህገ-መንግስት አንቀፆችን አላጣቀሰም።

የእነ ዶ/ር ደብረፅዮን ቡድን ” ጊዚያዊ አስተዳደሩ የተሰጠው ተልእኮ ወደ ጎን በመተው ህወሓት ለማፍረስ ፣ ሰራዊት ለማዘዝና የመንግስትና ህዝብ ሃብት በመጠቀም የትግራይ ህዝብ አንድነት ለመበተን እየሄደበት ያለውን የተሳሳተ መንገድ ሊያቆም ይገባል ” ሲል አሳስቧል።