ብልፅግና የማይችለውን አድርጋችሁ አሳዩ!

ብልፅግና የማይችለውን አድርጋችሁ አሳዩ!
የፋኖ አመራሮች በዋነኛነት ማተኮር የሚገባቸው ብልፅግና ማድረግ የማይችለውን አድርጎ ማሳየት ነው። በፖለቲካ ድጋፍ የሚባለው ዘላለሙን አይኖርም። በጦርነትና ስቃይ ውስጥ ያለ ህዝብ ቀርቶ በተረጋጋ ሁኔታ ያለ ህዝብ ድጋፉን ይቀንሳል። ወይ ይተወዋል። ሲብስ ወደተቃርኖ ይገባል። እየተደረገ ያለው ጦርነት ነው። የካድሬም ሆነ የሚሊሻ ዘመድ ያለው ሞልቷል። ከዚህ አልፎ በፋኖዎች መካከል ጎራ ተለይቶ ጭቅጭቅ ሰንብቷል። በዚህ ምክንያት የድጋፍ መቀዝቀዝ ብቻ ሳይሆን መቃወምም ጭምር ሊመጣ ይችላል። ሆን ተብለውም ይሁን ሳይታወቁ የሚፈፀሙ ስህተቶችን ጨምሮ በርካታ ምክንያቶች ለትችትም ለተቃውሞም ይዳርጋሉ። ፋኖ ጠንካራ ድጋፍ ከፈለገ ብልፅግና ማድረግ የማይችለውን ለህዝብ ማድረግ ነው። “የአማራ ህዝብ” እያሉ መግለጫ ማውጣት በቂ ድጋፍ አስይዞ አያስቀጥልም። ወታደራዊ ድልም ሆነ ሌላው የህዝብን ተስፋ የማይመልስባቸው ጉዳዮች ሊገጥሙ ይችላሉ። ቤተሰቡን ከመታገት ያልታደገ አባውራ፣ ህፃኗ የተገደለችባት እናት ወዘተ ወታደራዊ ድል መጣ አልመጣ ግዷ የማይሆንበት ደረጃ ልንደርስ እንችላለን። ከዚህ ሁሉ መዳን የሚቻለው፦
1) ፋኖ ብልፅግና ማስጠበቅ የማይችለውን ሰላም ማስጠበቅ ሲችል ነው። ለአብነት ያህል ፋኖ ለገጠሩም ሆነ ለከተማው ማህበረሰብ አዋጅ ማወጅ ይችላል። አነስ ባለ መንገድ የተከለከሉ ጉዳዮችን ያስቀመጠ ህግ አሰራጭቶ በሚችለው መዋቅር ማስፈፀም አቅም አለው። የአማራ ህዝብ ለህግ ቀናኢ ነው። ተግባር ታክሎበት ካየ ደግሞ በሳምንት ውስጥ በገበያ ቦታ፣ በኃይማኖት ተቋም ወዘተ የትም መዳረስ የሚችል ጉዳይ ነው። በዚህና በሌሎች መንገዶች ህግ ማስገበር ከቻለ ህዝብ ከዚህ የተሻለ የሚጠብቀው ነገር የለም። ብልፅግና ሰላም ማስከበር አይችልም። ይህን ፋኖ አድርጎ ካሳየ የትም ድረስ የሚከተለው ህዝብ ያገኛል። በሂደቱ ተግባር አንድነትን ይፈጥራል። አላማን ያጠናክራል። አመራርና አባላትን በተግባር ፈትኖ ያሳልፍበታል። ለትልቁ አስተዳደር ይማርበታል። በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ዘንድም ቀዳሚን ስፍራ ይይዝበታል። የያዙትን አካባቢ ሰላም የመፍጠርን ያህል ተፈላጊ የሚያደርግ ነገር የለም።
2) ማህበራዊ እሴቶቻችን ተነካክተዋል። በዚህ የፋኖ አደረጃጀቶችም ገብተውበታል። በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀሙ መሰል ክስተቶች ላይ እርማት አድርጎ ማሳየት ያስፈልጋል። አገር ወደ መፍረሱ እየሄደ ነው። በፈረሰ አገር ፋኖም ሆነ ህዝብ የፈለገውን አላማ መፈፀም አይችልም። አገር የሚፈርሰው ደግሞ ተራራና ገደሉ አይደለም። አሁን እንደምናየው በህዝብ ዘንድ የማይታወቁ ወንጀሎች እየበዙ፣ አረመኔነት እየገነነ ነው የሚሄደው። ለዚህ መድሃኒቱ የማህበረሰብን ህገ ልቦና፣ ግብረ ገብነት የሚያስጠብቁ እርምጃዎችን መደገፍ ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎች ፋኖ ቅሬታ ያደረበትም፣ ያሳደረባቸውም የሀይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎች ጋር እንደገና ግንኙነቱን ማጠናከር አለበት። መታወቅ ያለበት ከዚህ ቀደም አገዛዙ በፋኖዎች ላይ እስር ሲፈፅም “ልጆቻችን ናቸው” ብለው የሄዱት ሽማግሌዎች ናቸው። አሁን ችግር ኖረ አልኖረ ያስፈልጋሉ። እነሱ እንደ ግለሰብ ሳይሆኑ በማህበረሰብ ዘንድ የሚወከሉበት፣ የሚከበሩበት ማንነት ለትግሉ ብቻ ሳይሆን እንደ ህዝብ እንድንቀጥል ያስፈልጋል። ፋኖ የተቀየሙ ካሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይቅርታ ጠይቋቸው፣ አሊያም አግባብቶ ወዘተ የአገር ሽማግሌዎችንና የኃይማኖት አባቶችን ይዞ አሁን እየታየ ያለውን ውድቀት ለመፍታት መሞከር አለበት። አይደለም ፋኖ እናትና አባቶቹን፤ በፀረ አማራ ትርክት የጀመሩት ኢህአዴግና ብልፅግና የኃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎችን የሚጎናበሱት እምነትና ባህላቸውን ወደውላቸው አይደለም። ለራሳቸው ፖለቲካ ሲሉ ነው። ግን መፍትሄ ማምጣት አይችሉም። አላማቸው ፀረ አማራ ስለሆነ። የአማራን ጉዳይ የያዘ ፋኖ ግን እሴቱን ተጠቅሞ ትርምስ እንዳይፈጠር ማድረግ አለበት።
3) ብልፅግና የአማራን ጥያቄዎች ለፖለቲካ ፍጆታ እንጅ ከምሩ አይሰራባቸውም። ፋኖ የአማራ ጥያቄዎች ጉዳይ አስምሮ፣ ቁጥር አስቀምጦ መሄድ አለበት። ቀይ መስመሮችን ከነካ ከአላማው መጋጨት፣ በአላማ ጥያቄ መነሳት ይመጣል። በዚህ ጉዳይ ላይ በብስለት ማሰብ፣ የአማራን ጥቅምና ደህንነት፣ የኃይል አሰላለፉን አበጥሮ ማየት ግዴታ ነው።
4) ገዥዎቹ ልዩነት አይታገሱም። ፋኖ ልዩነት የሚፈጥሩ አሊያም አሁን ችግር ያመጣሉ የሚላቸውን ጉዳዮች በይደር ለመፍታት መጣር አለበት። ከጥቃቅን ጉዳዮች ይልቅ ዋና ጉዳይ ላይ ማተኮርና ከእነ ልዩነታቸው ( ልዩነቶቹ ከመሰረታዊ አላማ ጋር የማይጋጩ፣ ቢያድሩ ትግል የማያበላሹ ከሆኑ) አንድነት መፍጠር የሚቻልመትን አካሄድ መልመድ ያስፈልጋል። ለምሳሌ መነሻና መዳረሻ የሚለው ክርክር ከጥቅሙ በላይ ጉዳቱ ብሷል። የአማራ ጥያቄዎች ተዘርዝረው እነሱን ማስጠበቅ ላይ ማተኮር ሲቻል ጭራሽ ርዕዮት ዓለም ጭምር ተብሎ ክርክር መደረጉ ለክፍፍል ዳርጓል። ከዚህ የተሻሉ መመዘኛዎችን መምረጥ አንዳንዶቹን በይደርና ክርክር የሚፈቱ ማድረግ የተሻለ ይመስላል።
5) የጎጥ ፖለቲካ የኢህአዴግን አሁን የብልፅግና አቅመ ቢስ ካድሬ ለሹመትና ለሌብነት ሲጠቀምበት የቆየ አካሄድ ነው። ፋኖ ደጋፊዎቹን እንደ አላማው ማድረግ አለበት። ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሌላ ዞን ተወላጅን በወንዝና ተራራ ከልሎ የሚሰድብን ፋኖ አላማዬን አትመስልም ማለት አለበት። ካልሆነ ብልፅግና በየዞሩ ከሚያደራጀው የፌስቡክ ሰራዊት ተመሳሳይ ደጋፊ ይዞ ለአማራነት መቆም አይቻልም። ከብልፅግና መለየት ያስፈልጋል።
6) የትግሉ መሰረት ህዝብና ህዝብ ነው። በዚህ ጦርነት ምክንያት ህዝብ በየፊናው ተሰማርቶ የቻለውን ማድረግ ሲችል ፋኖ ደንበኛ ምሽጉን አጠናከረ ማለት ነው። ፋኖ ለደጀኑ ህዝብ ደህንነትና የኢኮኖሚ ዋስትና መጨነቅ፣ መጠንቀቅ፣ መስራት አለበት። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እንግሊዞች ህዝባቸው እንዳይጎዳ ድልድያቸው ስር ሳይቀር የጓሮ አትክልት አስተክለዋል። ብልፅግና ህዝብን በማደኸየት ነው ጦርነት ማሸነፍ የሚፈልገው። ፋኖ ነው ጦርነቱን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ እንዲኖር ህዝብን ማበረታታት፣ በሞራል ማገዝ፣ የሚችለውን እንቅፋት ማንሳት የሚችለው። ለዚህም ሲባል ዝርዝር ጉዳይ ወጥቶለት መሰራት አለበት። ፋኖን የተቀላቀሉ አሊያም የትም ሆነው የሚያግዙ ባለሙያዎች አሉ። መታወቅ ያለበት ብልፅግና አንድም የግብርና ባለሙያ የማይልክበት ገጠር ድረስ አሁን ፋኖዎች በርካታ የተማረ አባል ይዘው ይንቀሳቀሳሉ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ህዝብ የእለት ጉርሱን ማምረት ካልቻለ ግን ብልፅግና ተሳካለት ማለት ነው። በጥይት ያልገደለውን በርሃብ ይገድላል። ነገ የትግሉ ደጋፊም ለተራበ ድጋፍ ማሰባሰብ ውስጥ ይገባል። እንደታቀደው የብልፅግና አካሄድ በቀጣይ የተወሰኑ አመታት ድርቅ ከተከሰተ የሚፈጠረውን ለማሰብ ይከብዳል።
7) በቅርቡ ብልፅግና ተገድዶ “ተደራደሩኝ” ማለቱ የማይቀር ነው። በይፋ። ያኔ ችግር ውስጥ ያለው ህዝብም ሆነ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ጫና ማድረጉ አይቀርም። ብልፅግና የማይችለው፣ አላማ ማስፈፀሚያ የሚሆን ድርድር ውስጥ ለመግባት የሚታይ አስተዳደር ማዋቀር አስፈላጊ ነው። ከተማ ገብቶ ፖሊስ ጣቢያና ሌሎች መሳሪያ ያለባቸውን ቦታዎች በርብሮ መውጣት የትግሉን ዋና አላማ አያሳካም። ጣሊያን እንኳን ከሌላ አገር መጥቶ ድልድይ መስራት የጀመረው የያዙትን ማስተዳደር የፖለቲካ ብልጫ ስለሆነ ነው። በቅርብ አማራን የወ*ረ*ሩ ኃይሎች ፖሊስና አስተዳደር የሚመስል ነገር አስቀምጠው ነው ወደፊት ይሄዱ የነበረው። ይህ ካልሆነ ውሃ መውቀጥ ነው። አባላቱ እየተሰው፣ ህዝብ እየሞተ የተያዘ ከተማን በየቀኑ መልቀቅ፣ በአመት ውስጥ አንድ ከተማ አስር ጊዜ መያዝና መልቀቅ ኪሳራ ካልሆነ አላማውም፣ ልምምዱም ግራ አጋቢ ነው። የህዝብ አስተዳደር ተቋቁሞ “ይህማ ያስተዳድረናል” የሚል መዋቅር ካልተዘረጋ ቀጣይ ወታደር ወጥቶ ፋኖ ሲወጣ የሚቀጠቀጥ ህዝብ በእውነትም ሆነ በሀሰት ረጋሚህ፣ በአንተ ላይ መስካሪ፣ “የሚገቡት ሊያስመቱን ነው” እያለ አማራሪህና ለጠላት ተገዥ ነው የሚሆነው።
መፍትሔው ብልፅግና የማያስባቸውን የብልህ፣ የአማራን እሴት የተላበሱ፣ ከዜሮ ጀምረው የሚያድጉ አስተዳደሮችን እና የትግል አካሄዶችን መሞከር ነው።
ድፈሩ፣ አታካች የሚመስለውን አስተዳደር ሞክሩት። በዚህ መንገድ ብልፅግና ያልቻላቸውን ችሎ ማሳየት ካልተቻለ ህዝብን በጦርነት ሰልችቶ ” ምን አደረጉልን?” ብሎ ይጠይቃል። እያለ እያለ ከብልፅግና ጋር ማወዳደር ከጀመረ ለትግሉ ሞት ነው።