የኢሳያስ አፈወርቂ ድመቶች


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ቀጥሎ የምነግራችሁ ታሪክ ፤ እኔ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ በኤርትራ በቆየሁበት ወራት የተፈፀመ ነው ። ጊዜው 2010 ፈብሯሪ ወር ነው ። የአልጀዚራዋ ጋዜጠኛ ጄን ዳቶን አስመራ ከገባች ገና ሶስት ቀኗ ነው ። እነዛን ሶስት ቀናት ፡ ጋዜጠኛዋን ለማግባባት ብዙ ስራ ተሰርቷል ። እሷን ለማማለልና ወዳጃዊ የሆነ ጥያቄ ለፕሬዚደንቱ እንድታቀርብ ፤ ተገቢውን ስራ እንዲሰራ በጊዜው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አሁን ግን ስደተኛው አቶ አሊ አብዶ ተመድቧል ። አቶ አሊ አብዶ ከኤርትራ ባለሰልጣናት ውስጥ ወጣትና ዘመናዊ አስተሳሰብ ያለው ነው ተብሎ የሚገመት ሰው ነበር ። ከወጣት ማህበራቱ የፖለቲካ እርከን ወደ ሚኒስትርነት ደረጃ የወጣ ሰው ነው ። ወጣትነቱ ፤ ቁመናውንና መልኩም የሰጠ በመሆኑና በማራኪ ፈገግታው ጄን ዳቶንን ያማልላታል ተብሎም ተገምቶ ነበር ።

ሻእቢያ በሽፍትነቱ ዘመን ከእርዳታ አቅራቢ ድርጅት ሰራተኞች እስከ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጠኞች ድረስ ሴት ሴቶቹን በማማለል የሚፈልገውን ግብ ሲመታባቸው ቆይቷል ። ለምሳሌ ያህል ፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዷ ፤ የአውስትራሊያ እርዳታ ድርጅት ነርስ የነበረችው ነች ። ይህች ነርስ እ.አ. አ በ1973 ዓ . ም ለድርቅ እርዳታ ወደ ኢትዮጵያ ገብታ የነበረችና ከፖርት ሱዳን በሻእቢያ ተወካይ አማላይነት ተመልምላ በአውሮፓና በአሜሪካ ጋዜጦች አስተያየቷን ደጋግማ እንድትፅፍ ተደርጋ ነበር ። ጊዜው የደርግ ዘመን ስለነበር በፀረ ደርግ ፅሁፏና በአንፃሩ የሻእቢያን ተጋድሎ እያጎላች በመፃፍ ለአንዳንድ የምዕራብ ጋዜጦች የአፍሪቃ ቀንድ ሪፖርተር እስከመሆን ደርሳ ነበር ፤ ከሻእቢያ ጋር እስክትቆራረጥ ድረስ ። በመጨረሻም አንዴ ራሱ ኢሳያስ አፈወርቂ በግል አንድ ጉዳይ እንድትፈፅም ፖርት ሱዳን ውስጥ ሆኖ ጥያቄ ያቀርብላታል ፤ ወደ ህሊናዋ የተመለሰችው የዛሬዋ መሊካ የቀድሞዋ ቫሊሪይ ብራውኒንግ ለኢሳያስ የሚፈልገውን እንደማትፈፅምለት እቅጩን ትነግረዋለች ። “ድሮውንም ቢሆን የፈጠርንሽ እኛው ነን ፤ አንቺ ካለኛ ምንም አይደለሽም” ብሎ ያባርራታል ። ይህች ሴት ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አፋር አግብታ መሊካ የሚል ስም ወጥቶላት በአፋር ክልል የበጎ አድራጎት ስራ እየሰራች የእርጅና ጊዜዋን በመግፋት ላይ ትገኛለች ።

ወደ ጄን ዳተን ልመለስ ። ቀደም ሲል እንዳነሳሁት ሁሉ ፤ ከተቻለ በዚህ ስሌት ካልተቻለ በጓደኝነት ደረጃ የአልጀዚራዋን ጄን ዳተንን አግባብቶ ጥያቄዋን ረገብ እንድታደርግ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ አሊ አብዶ ታዟል ። ጄን ዳተን አስቀድማ ኤርትራ ከመግባቷ በፊት ዶሃ ኳታር ከሚገኘው የኤርትራ እምባሲ ፤ ከፕሬዚደንቱ ጋር ፕሮግራም ይያዝላት ዘንድ ጠይቃ ነበር ወደአስመራ የተጓዘችው ። አሥመራ ከደረስች በኋላ ግን ፕሬዚደንቱ አስቸኳይ ስራ አጋጥሞአቸዋል በሚል ሰበብ የተያዘላት ፕሮግራም ተላለፈና ከተማችንን እናስጎብኝሽ በሚል ማግባቢያ የጥያቄ አቅጣጫዋን ለመረዳት በአሊ አብዶ በኩል አስፈላጊው ሁሉ ተፈተሸ ።ይህች የነጠረች ባለሙያ ጋዜጠኛ ፤ የተያዘላት ፕሮግራም መተላለፍ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሙያዊ ልምዷ ፤ በሚገባ ነግሯታል ። ሻእቢያ በዚህ ሲዘጋጅ ጄንም የራሷን ዝግጅት እያደረገች እንደሆነ የገመተ ግን አልነበረም ። ከሁለት ቀናት የአስመራ ቆይታ በኋላ ፤ ፕሬዚደንቱ ለስራ ወደምጽዋ ወርደዋልና ወደዚያ መሄድ ትፈልግ እንደሆነ ተነገራት ።

ከአሥመራ እስከ ምፅዋ ያለው ቁልቁለታማ መልክዓ ምድር ፤ በየኪሎ ሜትሩ ርቀት የሚለዋወጥ ድንቅ ትዕይንት ነው ። ቁልቁለቱን ወርዶ ከነፋሲት በታች እስከምፅዋ ድረስ የሚለበልብ ሙቀት አለ ። አየሩ ይሙቅ እንጂ ጃንዋሪና ፌብሯሪ ላይ ምፅዋ ውብ የሆነ ለብ ያለ አየር ያላት ከተማ ናት ። ዛሬ አንድ ቅንጣት ቱሪስት ለምልክት እንኳ ዝር የማይልባት ከተማ ብትሆንም ፤ ከዲሴምበር ጀምሮ እስከ ፌብሩአሪ ለጎብኚዎች ምቹ ናት ።

ተልዕኮዋን ሳትጨምርም ሳትቀንስም ፤ ለመወጣት ጄን ዳተን ምፅዋ ወረደች ። ኢሳያስንም እንድታገኘው ተደረገ ። የአለም አቀፍና የአገር ወስጥ መረጃዎችን ሰብስባ የመጣችው የአልጀዚራዋ ጋዜጠኛ ጄን ዳተን ፤ የኤርትራ ኮብላይ ስፖርተኞችን ጉዳይ ጨምራ አምባገነኑን ኢሳያስን በምፅዋ ጉርጉሱም ቤተ መንግስት ፤ ፍልሚያ ገጠመችው ። “ፍልሚያ ገጠመችው” የሚለውን ቃል የተጠቀምኩበት ዋናው ምክንያት ፤ ቃለ-መጠይቁ የቦክስ ሪንግ ላይ የተገኛኙ ባላንጣዎች ፍልሚያ አይነት ይመስል ስለነበር ነው ። አንድ የገረመኝን ጥያቄዋንና ኢሳኢያስ የሰጣትን መልስ ላስታውሳችሁ ። “አገርህ ውስጥ ችግር ከሌለ እንዴት የኤርትራ እስፖርተኞች ቡድን ስፖርተኛች እንዳሉ በየሄዱበት አገር ጥገኝነት ይጠይቃሉ?” ትለዋለች ። “እኔ አሁን የምትይውን ሰምቼ አላውቅም” ብሎ አይኔን ግምባር ያድርገው ሲል ይሸመጥጣል ። እኔ ይህን ስሰማ በአለም አቀፉ የአልጀዚራ ሪንግ ላይ ጄን ዳተን ኢሳያስን ስትዘርረው ስእሉ ታየኝ ። እረ እንዲያውም እሷ የአልጀዚራ ነብር ፤ እሱ ደግሞ የጥቢ ሳር የጠገበች የኤርትራ ፍየል ነው የመሰሉኝ ። ራሴም ሳስበው ሳቄ መጣብኝ ። በምጽዋው ጉርጉሱም ቤተ- መንግስት ጊቢ ውስጥ ስታሯሩጠው ። ወይ እመት ነብሪትና አይተ ፍየል ?

ወድ አንባቢዬ ፤ ይህን የአልጃዚራ ቃለ ምልልስ ስትመለከቱ ፤ ኢሳያስ ስለተናደደ “ኡኽ….ኽ….ኡኽ….ኽ……ኡኽ….” እያለ ደጋግሞ ሲተነፍስ ትሰሙታላችሁ ፤ ታዩታላችሁ ። ጭንቅላቱ ላይ እሳት ሲነድና ሲቃጠል ይሰማችኋል ። የት ቦታ ያራግፈው ይሆን ? ነው የምትሉት ። ጄን ዳተን ሙያዊ የጋዜጠኝነት ስራዋን ካጠናቀቀች በኋላ ወዲያውኑ ነው ቤተ-መንግስቱን ለቃ የወጣችው ። አሊ አብዶ ፤ ጄን ዳተንን ለማግባባት የተሰጠውን ስራ በሚገባ ስላልተወጣና ይሆናሉ ብሎ ለኢሳኢያስ አፈወርቂ ያቀረባቸው ግምታዊ ጥያቄዎችም አንዳቸውም በአልጀዚራዋ ጋዜጠኛ ስላልቀረቡ ፤ ኢሳያስ ፤ አሊ አብዶን ቤተ መንግስቱ ውስጥ በቦክስ ሲቀጠቅጠው የጋዜጠኛዋ እግሯ ከግቢው ገና አልወጣም ነበር ። ገላጋይ አይደፍር ተው አይባል ነገር ሰዎች አይናቸው እያየ ኢሳያስ እስኪደክመው ድረስ አሊ አብዶን ደበደበው ። ኢሳያስ እኮ በቅርቡ ያሉትን ሰዎች ይቅርና ፤ በአጋጣሚ የተጣሉት የመሰሉትን ሌሎች ተራ ዜጎችን እመንገድ ላይ መደብደብ የመጀመሪያው አይደለም ። ፕሬዚደንት ሆኖ በአስመራ ቡና ቤቶች እየዞረ ከረምቡላ ሲጫወት በተጋጣሚው ከተሸነፈ ፤ ተጋጣሚውን እያባረረ እንደሚደበድብ ድፍን አስመራ የሚያውቀው ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው ።

ዛሬ አመተ-ምህረቱን በትክክል ባላስታውሰውም በ2003 ወይም በ2004 እ .አ.ዓ. ም አካባቢ ነው ። አንድ ወጣት ቡና ቤት ውስጥ ሊዝናና ሲገባ ኢሳያስን ያየዋል። ፕሬዚደንቱን ወጣቱ በማየቱ ይደሰትና ልጋብዝህ ብሎ ይጠይቀዋል ። ኢሳያስም አንዳችም ምላሽ ለወጣቱ ሳይሰጠው ጀምሮት የነበረውን ኮሮምቦላ ጨዋታ ይቀጥላል ። በኋላም ኮሮምቦላ ጨዋታውን ይጨርስና ወጣቱ የተቀመጠበት ጠረጴዛ ላይ ሄዶ ከውጣቱ ፊትልትፊት ይቀመጣል ። ወጣቱም በደስታ ተፍለቀለቀ ። “ግብዣየን በመቀበልህ አመስግናለሁ” ብሎ የሚጠጣውን እንዲያዝዝ ይጠይቃል ወጣቱ ። ኢሳያስም የሚጠጣውን ካዘዘ በኋላ ምን አዲስ ነገር አለ ብሎ ወጣቱን ይጠይቀዋል ። ወጣቱም ፕሬዚደንቱ ሃሳቡን ስለጠየቀው በመደሰት ፤ “ኢሳያስ ከማንኛውም ተራ ሰው ጋር ተራ ሆኖ ነው የሚነጋገረው” የሚለውን የሻእቢያ ካድሬዎች ተረት ሲሰማ የኖረ በመሆኑ “ምን መሰለህ “ ብሎ ሃሳቡን መግለፅ ይጀምራል ። እነዚህ እነዚህ ጉዳዮች መሻሻል ቢችሉ ብሎ ገና ሃስቡን ሲጀምር ፤ ጆሮ ግንዱ ላይ ከፍተኛ ያልጠበቀው ህመም ተሰምቶት የቡና ቤቱ ወለል ላይ ይዘረራል ። ኢሳያስ ቡና ቤቱን ለቆ እስኪወጣ ድረስ ማን ወንድ ከወደቀበት ያንሳው ። ይህንንም ድፍን አሥመራ እስከ ዛሬ ያስታውሰዋል ።

ውድ አንባቢዬ ሆይ ! ሰሞኑን ኢሳት የሚባለው የግንቦት ሰባት ልሳን ያቀረበውን የኢሳኢያስ ቃለ-መጠይቅ ካልተመለከታችሁ አስቀድማችሁ “Talk to al Jazeera President Isaias Afewerki 2010” የሚለውን ፤ ዩ ቱዩብ ላይ ጉግል አድርጋችሁ እንድትመለከቱ እጋብዛለሁ ። ቀድማችሁ ቃለ-ምልልሱን አዳምጣችሁ ከሆነም ፤ ይህንኑ ቃለ መጠይቅ ለንፅፅር ይሆናችሁ ዘንድ መመልከቱ ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል ።

ማሳለጫ !

የአዲስ አበባው ቀለበት መንገድ ከተሰራ ወዲህ ከዋናው ቀለበት መንገድ ወደ ከተማው መንገዶች መግቢያዎች ሁሉ ማሳለጫ የሚል ስም ወጥቶላቸዋል አሉ ፤ ይቅርታ እኔ አይቻቼው ስለማላውቅ ነው “አሉ” ያልኩት፤ ማሳለጫ መባላቸውን ግን ሰምቻለሁ ።

ኢሳያስና ኢሳት ለቃለ መጠይቅ ቀጠሮ ከያዙ በኋላ ፤ ከዚህ ከዋሽንግቶን በሲሳይ አጌና አሳላጭነት ፤ ለፋሲል የኔአለምና ለመሳይ መኮንን ቃለ-መጥይቅ ተደርጎላቸው ነበር ። የመጠይቁ መንደርደርያ ላይ ከአድማጭችና ከተመልካቾች የቀረቡ ጥያቄዎችን ለፕሬዚደንቱ ሊያቀርቡ ተዘጋጅተዋል በማለት ይጀምራል ፤ አስተዋዋቂው ። “ከአድማጮችና ከተመልካቾች የቀረቡ የተለያዩ ጥያቄዎችን” የምትለዋን አባባል ኋላ ላይ እመለስበታለሁ ። ከዚያ እስከዛሬ ከምናውቀው እውነታ ያልወጣ ምንም አዲስ ነገር የሌለበት ፕሬዚደንቱ ግድብ እያሰሩ ነው ከአስመራ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ………. ግድብ እያሰሩ ነው ፤ ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱ መኮንኖችም ሊያነጋግሯቸው ተራ እየጠበቁ ነበር ……. የሚል ዝባዝንኬ ነገር ሰማሁ ። ይገርማል ።

የመስኖ ግድብ ኢሳያስ እይስገነቡ ነበር አላችሁን ? ግድብ እኮ ግድብ ? ግድብ ማለት የሚሄደውን ውሃ ገደበ ፤ አቆመ ፤ ከጉዞው አስተጓጎለ ማለት ነው ሌላ አማርኛ ቋንቋችን የማያውቀው ትርጉም እስካልተሰጠው ድረስ ።

ድሮ ድሮ በንጉሱ ጊዜ ለፓርላማ አባልነት በሚደረግ ውድድር ላይ ተወዳዳሪዎች በሚመረጡበት አካባቢ እየሄዱ ህዝቡን እየሰበሰቡ የምርጫ ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር ። አንድ ተወዳዳሪ ከሳቸው የምርጫ ቀጠና ውጪ የሆኑ ተወዳዳሪዎችን የቅስቀሳ ሂደት በየቦታው እየሄዱ ያዳምጡ ነበር ። ይህም ለራሳቸው ቅስቀሳ እንዲያመቻቸው ዝግጅት ለማድረግ እንዲረዳቸው የዘየዱት መንገድ ነበር ። ታዲያ አንድ ቀን እኚህ ሰው ተራቸው ይደርስና ለመራጮቻቸው ንግግር ማድረግ ይጀምራሉ ። በንግግራቸው መሃል ለአካባቢያችን ድልድይ አሰራለሁ የሚል ቃል ይገባሉ ። ከተቀስቃሾቹ መሃል ፤ አንዱ እጁን ያወጣና ጌታው እኛ በአካባቢያችን ወንዝ የለ እንዴት ነው ድልድይ የሚያሰሩልን ? ይላቸዋል ። ሰውየው ፈጣጣ ቢጤ ነበሩና ምን ችግር አለ ወንዙንም አብረን እናሰራዋለን ሲሉ መለሱ ይባላል ። እና ኤርትራ የትኛው ወንዟ ላይ ነው ግድብ እየገደበች ያለችው ? ኤርትራ እኮ ወንዝ የሚባል ነገር የላትም ።
ባርካና ሰቲት የሚባሉ ጎርፍ ይሁኑ ወይ ሌላ ምንነታቸው የማይታወቅ ፤ ክረምት ላይ ተራራማው ምድር ላይ ዝናብ ሲዘንብ ጎርፉን ጠራርገው አምጥተው ጅረት የሚመስሉ ፤ ዝናቡ ካለፈ ደግሞ በሰአታት ውስጥ እልም ብለው የሚጠፉ ወሃ እንኳ አቁረው ማቆየት የማይችሉ ቦታዎች ናቸው ። እነዚህ ላይ እያስገነቡ ነው እንዳልል ፤ ከአሥመራ ርቀታቸው ከሰላሳ ኪ.ሜ ፡ በላይ ነውና በዜናው ከተጠቀሰው ስም የለሽ ወንዝ ጋር አይገናኙም ። እሳቶች የክረምቱን ውሃ ለማቆር የሚሆን የውሃ ኩሬ እያስገነቡ ነው ብትሉኝ አምናችኋለሁ ። እኔም ራሴ እንዲህ አይነቶቹ ኩሬዎች እየተገነቡ ውሃ ሲቆርባቸው ኤርትራ ውስጥ አይቻለኋ ! እናንተ ግን ከባዶ ነገር ላይ የሌለ ነገር ፈጥራችሁ በሚገባ ሳስላችሁ በተመረጡና በተቀረፁ ቃላት ፤ እንዴት የሌለውን እንዳለ አድርጋችሁ እይታችን ላይ ብዥታ ትስሉብንላችሁ !! ወይስ እንደንጉሱ ዘመን የፓርላማ ተመራጭ ሰው እናንተም ወንዙን ልታሰሩላቸው አስባችሁ ይሆን ? እናንተ ኩሬውን ግድብ ያለችሁ ሰዎች ፤ የወያኔ ጋዜጠኞች ብትሆኑ ኖሮና የአባይ ግድብ አስመልክቶ ሪፖርት ስሩ ብትባሉ ፤ አለም አይቶት የማያውቅ ፤ የሰው ልጅ ጥበብ ሁሉ ያልደረሰበት የአለም ድንቅ ስራ ብላችሁ ታስተዋውቁን እንደነበር ጠረጠርኩ ።

በዚሁ ማሳለጫ ላይ ያስተዋልኩት ሌላ ነገር ሲሳይ አጌና ቤተ- መንግስት ሄዳችሁ ምን ምግብ ተጋበዛችሁ ሲል የሰነዘረላችሁ ጥያቄ ነው ። “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” ሲሳይ አጌና በደርግ ጊዜ ወታደራዊ የፖለቲካ ካድሬና መቶ አለቃ ነበረ ፤ ኤርትራንም ያውቃታል ። ቤተ-መንግስቱንም ያውቀዋል ። ለፖለቲካ ምክክርና ስራ በጊዜው ኤርትራን ያስተዳድር የነበረው ወታደራዊ ሹም ፤ ወታደራዊ ፖለቲካ ካድሬዎችን ለስብሰባ የሚጠራው በዚሁ ቤተ- መንግስት ነበር ። በዚያን ጊዜ ከአዲስ አበባ እየተጫነ ይቀርብ የነበረው ምግብ ትዝታ ሲሳይ ዛሬም ድረስ ውል ያለው ይመስላል። እናም ይህንን ስለቤተ- መንግስቱ ግብዣ ጥያቄ ቀዳሚ ያደረገው ያለምክንያት አይደለምን እያልን እንማህ ሲሳይ ። ቅ….ቅ……..ቅ….ቅ ሰው መቼም አስቀድሞ የሚጠይቀው የሚያውቀውን ነውና ።

መሳይ ይፈልገው አይፈልገው አላውቅም ፤ ፋሲል የኔ አለም ፤ የመሳይ መኮንን እንቁላል ፍርፍር ቁርስን መግለፅም ተገቢ አልነበረም እላለሁ ። ምንድነው የሚባለው “ጫጩት ፊት ፈንግል አይወራም” ። በረሃብ የሚንገላታ ህዝብ ፊት እንቁላል ፍርፍር አዘዝኩ ይባላል ? በኢትዮጵያ ረሃብ ዘመን ወሎ ወይ ትግራይ ሄጄ እንቁላል ፍርፍር አዝዤ በላሁ ይባል ነበር እንዴ ? የኤርትራ ህዝብ ረሃብ ላይ ያለ ህዝብ ነው ። የቀለድክበት ነው የሚመስለው ። ኢሳያስ አፈወርቂ አንድ ቃለመጥይቅ ላይ በአገሩ ጋዜጠኞች የምግብ መወደድን አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው መልስ ፤ ይህን የሚያስወሩ የጎረቤት ሃገር ቅልውጥ የለመዱ ናቸው ሲል ከኢትዮጵያ የተባረሩ አምቼዎቹን ዘልፏል ። ቅ….ቅ…….ቅ… ከዚህ ቃለ መጠይቅ በኋላ እኔ እዚያው እያለሁ በአስመራ ጤፍ አስራ ሁለት ሽህ ናቅፋ ገባ ። ዛሬስ ጤፍ ስንት ገብቶ ይሆን ? ገንዘብ ያላቸው ሰዎች እንኳ ማሽላ ብቻ እንዲበሉ ተገደው ፤ በሄድክበት ቦታ ሁሉ የቀይ ማሽላ እንጀራ ነበር የሚቀርበው ። ይህን እኛ እዚያ የነበርነው እናውቀዋለን ።

ኤርትሬዎች ደግሞ ባይናገሩህም ይታዘቡሃል ። የኤርትራ ሰዎች እኮ ሰርግ እንኳ ሲጠሩ ሆዳም እንዳይባሉ ቤታቸው ያፈራቸውን በልተው የሚሄዱ ሰዎች ናቸው ። እነሱ ከመሃል አገር የመጣ ሰው ሆዱን ወዳድ አድርገው ነው የሚያዩት ። መነሳት በይገባውም ፤ ካስፈለገ እንኳን ቁርስ አዘን ነበር ቢባል በቂ ነበር ፤ ለነገሩ የእንቁላል ፍርፍሩን ነገር ያነሳው ፋሲል የኔ አለም ነው ። ለምን እንዳነሳው እራሱ ይወቀው ። ፕሬዚደንቱንም ለማግኘት የሄዳችሁበትም ቦታ የሚበላ እንዳልነበረ ነግራችሁናል ። ይገርማል !!!!

የተከበሩ አንባቢዬ እንዲረዱልኝ የምፈልገው ለምን እንቁላል ፍርፍር ታዘዘ የሚል የደረቅ ጣቢያ ጥያቄ አለመያዜን ነው ። በእንግድነት የምትሄድበትን ቦታ አስቀድሞ መረዳትና ኢሜጁንም መጠበቅ የሚባል ነገር አለ ። ለዚህም ነው ይህን ነገር ያነሳሁት ፤ ያለ ምክንያት እንዳይደለ ላሰምርበት የምፈልገው ። ሰለሞን ተካልኝ አስመራ የመጣ ጊዜ ቁርስ የሚያዘው እንቁላል ፍርፍር ነበር አሉ ። የአስመራ እንቁላሎች ደግሞ የእርግብ ናቸው ወይ እስከሚባል ድረስ ትናንሾች ናቸው ። በማነሳቸው የተነሳ ሰለሞን አንድ ፍርፍር አልነበረም የሚያዝዘው ። ሶስትና አራት ሰሐን ነበር አንዴ ለቁርሱ የሚያስቀርበው ። አሥመራ ብዙዎቻችን እንደምናስበው ትልቅ ከተማ አይደለችም ። አንድ ነገር ከተወራ በሰአታት ውስጥ ሁሉም ሰዎች የሚያውቁት ጉዳይ ነው የሚሆነው ። በዚህ ምክንያት የአሥመራ ሰዎች ለሰለሞን ተካልኝ “እግር ያለው ጆንያ” የሚል ቅፅል ስም አውጥተወለት እንደነበር እዚያ የነበርን ሰዎች የምናስታውሰው ነው ።

መሳይም ክብደቱ ቀላል አይደለም ፤ በዚሁ ጉዞው ከአርበኞቹ ጋር የተነሳው ፎቶ እንደሚያሳየን በቀጫጭኖቹ ሰዎች መሃል ከእጥፍ በላይ ይገዝፋል ። ወደ ወታደሮቹ ከመሄድ በፊት እዚህ ዋሽንግቶን Rock Creak Park ለአንድ አስራ አምስት ቀናት ሰውነትን ሸንቀጥ ማድረግ ይገባ ነበር ። ወይ መካሪ ማጣት !……..

እናንት የኢሳት ጋዜጠኞች ሆይ ! ወደአስመራ የተጓዛችሁበት ተለዕኳችሁ ምንም እንኳ ኢሳያስ ባይሆንም ፤ ሲሳይ አጌና ስለቤተ- መንግስት ግብዣ ቢጠይቃችሁም ፤ የኢሳያስ ጤንነትና የቤተ-ሰብ አያያዙ እንዲህ ከልባችሁ አሳስቦአችሁ ከጠየቃችሁ ፤ አስመራን እና ህዝቧን በተመለከት የሙሉ ሌሊቱን የዳቦ ሰልፍ ፤ ሰዎች ለምኖ ለመብላት እንኳ የተከለከሉ መሆኑን ፤ ከረባት አድርገው ተደብቀው ስለሚለምኑት ሰዎች ፤ ከተማ ውስጥ በየጊዜው ስለሚደረገው አሰሳ ፤ በየቡና ቤቶቹ ስለሚገኙት እራት ብቻ ከገዛህላቸው አብረውህ ለማደር ፈቃደኛ ከሆኑ ድብቅ ሴተኛ አዳሪዎች ፤ በየመንደሩ ድብቅ ጴንጤ ቤተክርስቲያኖች ስለመስፋፋታቸው እና ምክንያቶቻቸው ፤ ኮምፔሽታቶ በአጠቃላይ አስመራ ወጣት መንገድ ላይ ማየት የናፈቃት ስለመሆኗ ፤ ስለ ሃገሩ ህዝብ ኑሮና ስለገበያው እንደምትዘግቡልን ተስፋ አድርጌ ነበር ። ሙሉ ዘገባም ታቀርቡልናላችሁ ብዬ ጠብቄ ነበር ። ግን አልሆነም….

ኢትዮጵያውያን ላይ ስለደረሰውና አሁንም እየተደረገ ስላለው ሁኔታስ ለምን ዝም አላችሁ ? ኢትዮጵያውያን አመሻሽ ላይ ከስድስት ፒኤም (6 pm) በኋላ ከተማ ውስጥ ሲዘዋወሩ ቢገኙ እንደሚታሰሩና ፤ የኤርትራ ነፃነት ቀን ከመድረሱ አንድ ወር በፊት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከየቤቱ እንዳይወጣ የሚደረግ መሆኑን ፤ የነኮለኔል ታደሰ ሙሉነህን ደብዛ መጥፋት የነኮለኔል አበበ ገረሱን መታሰር ፤ ጀነራል ከማል ገልቹ ከሚኖርበት ቤት በተወሰኑ ሜትሮች ርቀት ብቻ እንዲዘዋወር መደረጉ ፤ ሙዚቃ የሰዎች ልጆች እውነተኛ የውስጥ ስሜት መገለጫ ሆኖ ሳለ የአማርኛ ዘፈን በማንኛውም ንግድ ቤቶች መከልከሉ ፤ ሲያዘፍን የተገኘም ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት እንደሚደርስበት ፤ ሁሉ ታውቃላችሁ ። ምነው ታዲያ ለኢሳኢያስ ከነዚህ ሁሉ አንዷንም ሳታነሱ ቀራችሁ ?

ከጥያቄዎቻችሁ ውስጥ የገረመኝን ሳልነግራችሁ ማለፍ ደግሞ አልቻልኩም ። የኤርትራ ባለስልጣናት በከተማይቱ መንገዶች ስትዘዋወሩ አጀብ የላችሁም ። ወይም መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች አይከተሏችሁም አያጅቧችሁም ፤ይህን የናንተ መገለጫ እንዲሆን ፈልጋችሁ ነው ማለት ነው ? ስትሉ ያቀረባችሁት ጥያቄ ግሩም ነው ።

ኢሳኢያስም ሆነ የኤርትራ ባለስልጣናት መገለጫቸው ያ እንዳልሆነ ያውቁታል ። ያ መገለጫ ብላችሁ ያቀረባችሁት ጥያቄ የናንተ ፍላጎት ነው ። ዛሬ የኤርትራ መገለጫ ወይም አለም ኤርትራን የሚያውቃት በረሃብ ፤ በስደት ፤ በባህር ላይ ሞት ፤ በወጣት ብቻ አይደለም በህፃናት ፍልሰት ፤ ( የአዋቂዎቹን ሳልጠቅስ በሱዳን ሸገራብን በኢትዮጵያ እንዳ-አባጉና የህፃናት ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ለዚህ ማሳያ ናቸው) መሆኑን መመልከት በቂ ነው ። መረዳት ከቻላችሁ ፤ እናንተ እንዳላችሁት ሳይሆን ሌላውን የኤርትራ መገለጫ ልንገራችሁ ።

ኤርትራ ወንድ ማፍራት ካቆመች ቆየች ። አገሪቱ ውስጥ ያለው ወንድ ሁሉ ቀበቶውን በሻእቢያና በችጋር ስለተቀማ ሱሪውን በሁለት እጁ ይዞ ነው የሚዘዋወረው ። የሻእቢያ ወታደራዊ ሃላፊዎች ትልልቆቹም ሆኑ ትንንሾቹ በያሉበት ቦታ ታላላቅ መሳፍንቶች ናቸው ። በህግ ሳይሆን እነሱ በግል በፈቀዱት መጠን ማንኛውንም ሰው ባሻቸው መንገድ የመቅጣት መብት አላቸው ።

ሲፈልጋቸው በገመድ አስረው ገርፈው ፀሃይ ላይ ያለ ምግብና ያለ ውሃ ሲያንቃቁህ ይውላሉ ። ሄሊኮፕተር በሚል የሚታወቀውን እጅና እግርን የኋሊት አገናኝተው አስርው ገርፈው በቆሰለው ሰውነትህ ላይ በስኳር የተበጠበጠ ውሃ ይደፉብህና ፀሃይ ላይ የዝንብ መጫወቻ ያደርጉሃል ። የደረሰባቸው ሰዎች ሲነግሩን ፤ ውሃው ከላያቸው ላይ ትንኖ ፤ ስኳሩን ለመብላት የሚሰበሰቡ ዝንቦች በሰውነታቸው ላይ የሚያደርሱት ስቃይ ይህ ነው ተብሎ አይገለፅም ። የሚፈልጉትን ካልፈፀምክ በቤተስብህ ላይ ሁሉ በቀል ሊያደርሱ እንደሚችሉ ይዝቱብሃል ።ስትገረፍና ስትሰቃይ ህይወትህ ቢያልፍ እንኳ የሚጠይቃቸው የለም ። ዛሬ አንድ ኤርትራዊ ሳይከፋውና ሳይመረው ቀርቶ ሳይሆን ሻእቢያና ኢሳኢያስን በመቃወም በጠቅላላው ቤተሰቡና በራሱ ላይ ከሚደርስ መከራ ይልቅ ልጆቹን በበርሃ ወደ ስደት ልኮ ከራሻይዳ አረቦች ግርፋትና ኩላሊት ንግድ እግዚአብሄር ይጠብቅልኝ እያለ መፀለይ ይቀለዋል ፤ ይህ ነው ሌላው የነሱ መገለጫ ።

የሻእቢያን የሰቆቃና የቶርቸር አሰቃቂ ህይወት ገፅታ ይበልጥ ለማወቅ የፈለገ ሰው ሰንበት ካሉ መፃህፍት መካከል የግደይ ብህርይሹምን “አሞራ” በሚል ርእስ ታትሞ የነበረ አስገራሚ የግል ገጠመኝ ታሪክ መፅሃፍ ማንበብ ይጠቅማል ።

በነገራችን ላይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ ፤ አንዳርጋቸው ፅጌ የዛሬ ሁለት አመት አካባቢ በሲሳይ አጌና ቃለ ምልልስ ሲደረግለት እሳኢያስ አፈወርቂ በከተማይቱ በአስመራ ያለ አጃቢ መኪና እየነዳ ሲሄድ ይታያል ፤ ብሎ ሲነግረን ይህ ሰው ሄድኩበት ብሎት የነበረው ተልእኮ ሌላ ፤ ዛሬ የሚነግረን ደግሞ ሌላ ብለን ታዝበን ነበር ።

ስለዚህ እንደአንዳርጋቸው ሁሉ የኢሳኢያስን ሰብእና ለመገንባት ያደረጋችሁት ማሳለጫ የትም የሚያደርስ አይደለም ። “ስንተዋወቅ አንተናነቅ” አይደል የሃገሬ ሰው የሚለው ። ለነገሩ አመታዊ በጀታችሁ ከግብፅና ከኳታር በሚገኝ እርዳታ በግብፅ በኩል አልፎ በሻእቢያ አማካይነት ስለሚደርሳችሁ ከዚህ ሌላ ምንም መሆን አትችሉም ። አመታዊ በጀታችሁም ከየት እንደሚመጣ ዶ/ር ብርሃኑ ቀደም አድርጎ ስለነገረን ማየትና ማስተዋል አይሳነንም ።

እውነቴን ነው የምላችሁ ፤ እንደናንተ የነቃ አራዳ የለም ። ዛሬ ትግል ቢዝነስና የኖሮ መደጎሚያ በሆነበት ዘመን ማን የእንጀራ ገመዱን ይበጥሳል ? ስለዚህ ለኢሳያስ አፈወርቂ ድመት መሆን ይሻላል ።

ድመት አሳዳሪዋ ሲመጣ በእግሮቹ መሃል እየተሽሎከለከች ላስላሳ ሰውነቷን ወደእግሮቹ አስጠግታ ከጭንቅላቷ ጀምራ ቀስ እያለች በወገቧ በኩል ታደርግና ጭራዋ ሳይቀር ግትር አድርጋ ጌታዋን ትታከከዋለች ፤ ይህም የታማኝነት መገለጫዋ ነው ( መገለጫ ማለቴ የናንተን ቋንቋ ልጠቀም ብየ ነው) ። እናንተም የመጀመሪያው ክፍል አንድ የኢሳያስ አፈወርቂ ቃለ መጠይቃችሁ ላይ ከረባት ያደርጉ ሁለት ድመቶች ሆናችሁ ነው የታያችሁኝ ፤ እስቲ ተመልሳችሁ ራሳችሁን እንደገና ተመልከቱት ፤ እጮኛ እንደመጣላት ልጃገረድ ያ ሁሉ መሽኮርመምና መሞዳሞድ ምን አመጣው ። ቀደም ብዬ ከኢሳያስ ጋር አድርጋው በነበረው ቃለ መጠይቅ ላይ የአልጀዚራዋን ጄን ዳተንን ፤ ነብር ናት ብያ ገልጫት ነበርና ፤ እናንተን ስመለከት ደግሞ ድመት ሆናችሁብኝ ።

መዝጊያ ክፍል አንድ !

“ከአድማጮችና ከተመልካቾች የቀረቡ የተለያዩ ጥያቄዎችን” ለኢሳኢያስ አዘጋጅተናል የምትለዋን ብሎም ፤ አሉ የሚባሉትን ተዋጊዎች መሬት ላይ ሄዶ ለማየትና አንዳርጋቸው ፅጌ መሬት ላይ ወርዶ በረሃ ገብቶ አፈር ለብሶ ትግል ለማድረግ የሚፈልግ የለም ብሎ ነበርና የግንቦት ሰባት አመራሮች ወደ በረሃው ስለመውረዳቸው ፤ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ተዋሃደ ተዋሃደ የተባለው

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለፍትህና ዲሞክራሲ መሪ ብርሃኑ ነጋ ኤርትራን የነካ ውዮለት በማለት የሰጣቸውን አስተያየቶችና የግንቦት ሰባት ልሳን የሆነው ኢሳት ፤ 52 ፉል ታይምና ፓርት ታይም ሰራተኞች በጀት እንዲሁም ከኢሳኢያስ ጋር ያደረጋችሁት ቃለ-ምልልስ ፊልም ፤ ፕሮዳክሽንና ትርጉም አሰራርንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ በክፍል ሁለት ትችቴ ላይ እመለስበታለሁ ፤የሰሞን ሰው ይበለን ።

February 27, 2015.
Top