ተኝተሽ ተገኘሽ መተማመን ጠፋ – ለተስፋየ ገ/አብ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ስለ ተስፋየ ገ/አብና ተያያዥ ጉዳዮች፣

“ተማምለን ነበር እንዳናንቀላፋ
ተኝተሽ ተገኘሽ መተማመን ጠፋ”

ከጥንቱ ከጠዋቱ ከታዋቂው ድምፃዊ አሰፋ አባተ ዘፈን የወሰድኳት ስንኝ ናት።

አንቺም ላትከጂኝ እኔም ላልከድሽ ተባብለው መሃላ የገቡ ፍቅረኛሞች መካከል በተፈጠረ መካካድ ምክንያት ፤ መሃላውን የጠበቀው ፍቅረኛ የገጠማት የብሶት ስንኝ ትመስላለች ከአሰፋ አባተ ዘፈን ያገኘኋት የላይኛዋ ግጥም።

እኛ ኢትዮጵያውያን እንኳን ተወልዶባት ፤ አድጎባት ፤ ማእረግ አይቶባት ይቅርና ለሃገራችን ለኢትዮጵያ ቅንጣት ታክል ፍቅርና ክብር ላሳያት የማንኛውም ሃገር ዜጋ ልዩ ፍቅርና እንክብካቤ እናደርጋለን። አገራችን ዜጋዋ ብለን በቆጠርነው ሰው ክህደት ሲፈፀምባት ይህ የመጀመሪያው አይደለም ። ከቅኝ ገዢ ወራሪዎች ጋር ህዝባችን ሲፋለም በኢጣሊያ ሊሬ ተደልሎ ሃገሩን የከዳውን ሁሉ የባንዳ ቤት ታሪክ ይቁጠረው ። ይህን የተስፋየ ገ/አብ ክህደት ልዩ የሚያደርገው ፤ እንዲህ በራሳችን ቋንቋ በስነ- ጽሁፍ አድጎና ተመንድጎ ፣ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ትንሽ ትንሽ ስፍራ የሰጠነው ግለሰብ ፤ ከዚህ በፊት የፈፀመውን አንዱን ህዝባችንን ከሌላው ህዝባችን የማጋጨት ተግባር ይቅር ብለን ፤ እንደገና ፍቅርና ሙቀት ብንሰጠው ዳግም ከታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር ከጀርባችን ሳንጃ ሲሰካብን ስላገኘነው ነው ።

ወድ አንባቢዎቼ ! ይህን በተስፋየ ቤት ማንም አይደርስብኝም በማለት ሸሸጎት የነበረውን ሚስጥር ለውድ ሃገሩ ለኢትዮጵያ ሲል ፈልፍሎ ላወጣልን ወንድማችን አለማየሁ መሰለ ታላቅ ክብር እንዳለኝ ማሳወቅ እፈልጋለሁ ። ተስፋየ ገ/አብ በኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ ውስጥ ቅዱስም ይሁን እርኩስ ቦታ ሊኖረው እንደሚችል አልጠራጠርም ። አለማየሁ ለወደፊቱ ትውልድ ተስፋየ ገ/አብ ከሃዲ ነው ውይስ አይደለም በሚለው አተካሮ ጊዜውን እንዳይጨርስ በቂ ማስረጃ እንደተውክለት ልገልፅልህም እወዳለሁ ። የኢትዮጵያ አምላክ አንተንም ቤተሰብህንም ይጠብቅ ።

-2-
ውድ “ኢትዮጵያውያን ተስፋየ ካለው የኤርትራ ዜግነቱ ጋር ፤ በዚያ በጦርነቱ ወቅት ከፈፀመው ድርጊት ተነስተን አሁን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ጋር ካላት ግንኙነት ጋር አጋጭታችሁ ለወያኔ- ኢሕአደግ መሳሪያ እንዳንሆን እንጠንቀቅ ። የሞተ ነገር እያነሳን ኤርትራ መቼ ይታመናል ? በማለት ። በዚያ የሚንቀሳቀሱትን የኢትዮጵያ ጀግኖችን አካሄድ ለማደብዘዝ ። በፖለቲካ ዘለአለማዊ ወዳጅነት የለም ።”

ዳኛ ወልደ ሚካኤል ፤ በዚያ በቀውጢ ወቅት በህዝባችን ላይ ለደረሰው መከራ ለእውነትና ለፍትህ ብለው የወሰዱትን አቋም ከሚያደንቁ ሰዎች አንዱ ነኝ ። የተስፋየን ማንነትም ሆነ የፅሁፍ ስራውን ካለፉት መፃህፍቱ እየቆነጠሩና እየተነተኑ ስላቀረቡልን አመሰግንዎታለሁ ። ከላይ በድምቀት ያሰፈርኩት ስለ ተስፋየ ገብረአብ እርስዎ ራስዎ ከፃፉት ፅሁፍ የመጨረሻው ገፅ ላይ የወሰድኩት ነው ። አባባልዎ ወዴት እንደሚሄድ ግልፅ ነው ። እስኪ የላይኛውን አባባልዎን በራስዎ ሎጂክና ቃላት እንዲህ አድርጌ ልግለፀው ።

“ውድ ኢትዮጵያውያን ሻእቢያ ካለው የኤርትራ ብሄረተኝነት ጋር ፤ በዚያ በግንጠላው ወቅት ከፈፀመው ድርጊት ተነስተን አሁን ተስፋየ ከኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ጋር ካለው ግንኙነት ጋር አጋጭታችሁ ለወያኔ-ኢሕአደግ መስሪያ እንዳንሆን እንጠንቀቅ ። የሞተ ነገር እያነሳን ተስፋየ መቼ ይታመናል ? በማለት ። በፖለቲካ ዘላለማዊ ወዳጅነት
የለም” ።

ከላይ የተሰመረባቸው ውይም በቀይ ቀለም የተፃፉትን ብቻ ነው ከመሰረታዊው ፅሁፍዎ ላይ ቃላቶቹን የቀየርኩት ። ይህን አይተው ምን ስሜት እንደሰጠዎ ባላውቅም ፤ ይህን አባባልዎን እኔ የለዋወጥኳቸውን ቃላቶች ተክተው ነገ የተስፋየ ወዳጆች እንደሚጠቀሙበት ልገልፅልዎ እወዳለሁ ። ምን ለማለት ፈልጌ መሰለዎ ፤ ተስፋየ ገብረ-አብ በኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ፤ በእርስዎ አባባል ኤርትራ ውስጥ ያሉት “የኢትዮጵያ ጀግኖች” ደም ስር ውስጥ የገባና እንደ ኦክስጂን ያለ እሱ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ያደረገ ሰው ነው ።

ታሪኩ እንዲህ ይጀምራል ። ተስፋየ ገብረ-አብ ማንነቱን ሰፋ አድርጎ ባይገልፀውም እንዲህ ሲል የራሱን አመጣጥ ይገልፀዋል “የጋዜጠኛው ማሳታውሻ” በተሰኘው መፅሃፉ ላይ ። ገፅ41 እጠቅሳለሁ
-3-
“አባቴ ያው ኤርትራ ሳለ ገበሬ ነበር ። ኢላበርኢድ ላይ ፍራፍሬ ሲጭን
ውሎ ከመኪናዋ ጋር ወደአዲስ አበባ መጣ ። ከዚያ ወዲያ አልተመለሰም ።
ደብረዘይት ላይ ለአርመኖች ዘበኛ ሆኖ መስራት ጀመረ። አሁንም ዘበኛ ነው
። እናቴም ያው ኤርትራ መንደፈራ አካባቢ የአባቴ ሚስት ነበረች ፡ ወደ
ደብረ ዘይት ተከትላው መጣችና እኔና ወንድሞቼ ተወለድን” ።

የተስፋየ አባት አቶ ገ/አብ ኢላበርኢድ ላይ ሸክም ስራ ሲሰሩ ባለቤታቸውን የተስፋየን እናት ከዚያው ከኤርትራ መንደፈራ ወደ አጠገባቸው ማስመጣት አቅም ያልነበራቸው ሰው ነበሩ ። ይህን አቅም እንኳ ያገኙት ወደ ኢትዮጵያ ደብረ ዘይት መጥተው ለግሪኮቹ ዘበኝነት ከተቀጠሩ በኋላ ነው እንደመፅሃፉ ። ከዚህ ተነስቶ ነው ተስፋየ በኢትዮጵያ ተወልዶ፤ በኢትዮጵያ አንጡራ ሃብት ተምሮ ፤ እትዮጵያ ውስጥ እስከ ትልቅ ማእረግ የደረሰው ። ዳኛ ወልደሚካኤል እንደ ጻፉልን እና ከመፃህፍቶቹ እየጠቀሱ ማንነቱን እንዳሳዩን ደግሞ ፤ ተስፋየ ገ/አብ ንፁህ ኢርትራዊ መሆኑን እና ለኤርትራ የስለላ ድርጅት እንደሚሰራ ነው ። እርስዎ የገለፁትና በብዙ ያመሰገኑት ኢትዮጵያዊ አለማየሁ መሰለ የፈፀመው ተግባር የሚያስመሰግነው ነው ። ዛሬ ላይ የተስፋየ ገብረ-አብን ማንነት ፍንትው ስላደረገልን ።
ዛሬ የኔ ትኩረት ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ የፃፉትን መሰረት በማድርግ አሁንም እንዴት በሻእቢያ እየተሸወድን እንደሆን ለማሳየት ነው ። ከላይ መግቢያየ ላይ ከዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ የተዋስኩትን ፅሁፍ ከራሴ አተረጓጎም ጋር ሳቀርብ የሃሳባችን መንደርደሪያ ይሆን ዘንድ ነው ። ተሳፋየ ገ/አብ በመፅሃፍቶቹ ላይ እንደመመሪያ የያዘው ኦሮሞውንና አማራውን የማያልቅ ጦርነት ውስጥ የመክትት ፤ የማጋደል የማጨፋጨፍና የበቀል ተልእኮ የተስፋየ የራሱ ፈጠራና ቅዠት እንዳልሆነ ፤ ውድ አንባቢዎቼ ፤ ሁላችንም የምንረዳው ነው ብየ እገምታለሁ ። በፅሁፉ ላይ በማስረጃ እንደታየውና እንዳነበብነው ተልእኮው የሻእቢያ ነው ። የእባብን እንቁላል ወስደህ የእርግብ ጎጆ ውስጥ ከእርግብ እንቁላሎች ጋር ብታኖረውና እርግቧ ታቅፋው ቢፈለፈል እባብ እንጂ እርግብ አይወጣውም ።
በላይኛው ምሳሌ ለመግለፅ የፈለኩት ፡ ተስፋየ እኛ መሃል ገብቶ የኛን ቋንቋ እየተናገር ፤ የኛን ህመም የታመመ መስሎ አብሮን እያቃሰተ ፤ መሃላችንን እየማለ ፤ ብሶታችንን እየቆሰቆሰ ፤ ፀሎታችንን ቀምቶ ሻእቢያን በቤተ-መቅደሳችን ሊቀ-ካህን አድርጎ የሊቀ ካህኑ አገልጋይ ዲያቆናት የኛው ሰዎች ሲሆኑ አያሳዝንም ? ለዚህ ሃሳብ ማስረገጫ
-4-
የሚሆነን ራሱ ተስፋየ ገብረ-አብ “በደራሲው ማስታወሻ” ላይ “ኢህዴን የተባለውን የታምራት ላይኔ ድርጅትን ተከትሎ ገደል የገባ የወሎ አርሶ አደር የተቀኘው” ደወል ጋዜጣ ግንቦት1985 እንዳተመው ፤“ቅኔ አንዳርጋቸው ፅጌ” በማለት ገፅ 123 ላይ

“ተማምለን ነበር-በጋራ ልናርስ
ቃል ኪዳን ነበረን-በጋራ ልናፍስ
ማተብ የሌለው ሰው- ሆዱን የሚወድ
ዘሬን ሸጦ በልቶ – አደረገኝ ጉድ”
ሲል ስንኝ አስፍሯል ፤ ውድ አንባቢዎቼ ራሳችሁ አመሳስልሉት ።

ተስፋየ ገብረ-አብ የጋዜጠኛው ማስታወሻን ከፃፈ በኋላ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እኔም የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ራሴ አድናቆታችንን ቸረነዋል ፤ በድንቅ የስነ- ፅሁፍ ችሎታውና አንዳንድ የማናውቃቸውን የዛሬዎቹን የኢትዮጵያ ገዢዎች የግል ባህርያት በጣፈጠ ቃላት እየከሸነ እጉርሶናል ። ባለስልጣናቱን ድክመታቸውን እየፈለፈለ ገመናቸውን እስከ ውስጥ ሱሪያቸው ድረስ አውልቆ አሳይቶናል ። ይህም ሁኔታ ስለተስፋየ ገ/አብ ማየት የሚገባንን ሃቅ እንዳናይ ጋርዶብን ነበር ። እንዲያውም አንዴ ትዝ ይለኛል የethiomedia አዘጋጅ አብርሃ በላይ “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” የሚለውን የተስፋየን መፅሃፍ ሲትች ፤ ስለ ሻእቢያ ተስፋየ ያለውን ጠቅሶ ነበር ። የተስፋየ ፅሁፍ እንዲህ ይነበባል
“ ሻእቢያ ብዙ ጊዜ የማጥቃት ውጊያ እይመርጥም። በከባድ መሳሪያ ግን
የበላይነት አላቸው ። ተኩሰው የምሳ ሰሃንህ ላይ ቁጭ ያደርጉልሃል ።”
ማለቱን አስታውሶ ፤ የሻእቢያን sophistication (ረቂቅነት) እየገለፅክልን ነው ወይ ሲል መተቸቱን አስታውሳለሁ ። ሆኖም ግን ማናችንም የአብርሃን ማንቂያ ደወል አልሰማንም ነበር ። እንዲያውም ብዙዎቻችን የቆዪ ቂም ቢኖራቸው ነው በሚል የሞኝ ሰበብ ፤ የባሰ ተሸፋፍነን ተኛንና የዚህን ሰው ማንነት ማስተዋል ሳንችል ቀረን ።

በኋላ ላይ ግን ተሰደን ኤርትራ እንደገባን ተስፋየ ገብረ-አብን በአስመራ ከተለያዩ ወይዛዝርት ጋር በኮምፔሽታቶ መንገድ ላይ ስናገኘውና ከወይዛዝርቶቹ ሌላ ፤ ከወንድ አንድ ሰው ጋር ብቻ ሲያዘወትር ስናየው ትንሽ ሳይደንቀን አልቀረንም ነበር ። ያኔም ነው የአብርሃ
-5-
በላይ ደወል እንደገና የደወለብን ። ከወንዶች አብሮት የሚውለውና አብሮት የሚያመሸው አንዳርጋቸው ፅጌ ነበር ።
ይህንንም ራሱ ተስፋየ ገብረ-አብ እንዲህ ይገልፀዋል ። “የደራሲው ማስታወሻ” ገፅ 123 ።

“ህዳር ወር 2001 ማብቂያ ግድም አንዳርጋቸው ፅጌን አስመራ ላይ
አግኝቼው ነበር ።
ምን ማግኘት ብቻ ? ሁለታችንም በየፊናችን ስንባዝን ውለን ማምሻውን
መገናኘቱን እንደ ልምድ ያዝነው………………….”
የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ እኔና ስደተኛ ጓደኞቼ አስመራ ተቀምጠን እናይ የነበረው ደግሞ ማምሻው ላይ መገናኘት ብቻ ሳይሆን በደባልነትም አብረው ይኖሩ የነበረ መሆኑን ነው ። አንዳርጋቸው ሌላ ወይዘሮ ቤት ደባልነት እስኪገባ ድረስ ። ተስፋየ በዚሁ ምእራፍ ላይ እርስ በርሱ የሚጣረስ ነገር ስለ አንዳርጋቸው ይነግረናል ገፅ124 ላይ ። እንዲህ ያላል፦
“አንዳርጋቸውን በቅርብ ለማወቅ እድል በማግኘቴ በውነቱ እጅግ በጣም ደስ
ብሎኛል…………… ልክ እንደኔው የስነፅሁፍና የስነግጥም ወሬዎችን አንስቶ
ማውራት የማይሰለቸው ሆኖ አገኘሁት። በአጭር ጊዜ ቆይታችን
እንደታዘብኩት አንዳርጋቸው ቅኔዎችን ቢቋጥርና ትረካዎችን ቢጫጭር የበለጠ
ሊረካ የሚችል ሰው ሆኖ አገኝሁት” ።
ካለ በኋላ እዚያው ገፅ ላይ ወረድ ብሎ ደግሞ
“ከስነ ፅሁፍ ጋር የተያያዙ ወሬዎችን ሊያወጋኝ የሚችል ሰው እጥረት ነበረብኝና
ስራውን የሚጨርስበትን ሰአት እየጠበቅሁ አሳድደው ገባሁ። በእርግጥ
እንደተመኘሁት ረጃጅም ስነጥበብ ወጎችን መጫወት የሚችል አልነበረም ።”
ይላል ተስፋየ ።
አንዳርጋቸውን የስነፅሁፍ የስነግጥም ወሬዎችን ማውራት የማይሰለቸው ሆኖ አገኘሁት ካለ በኋላ መለስ አድርጎ የረጅም ስነ ጥበብ ወጎችን መጫወት የሚችል አልነበረም ይለናል ተስፋየ ገ/አብ ። በአንድ ገፅ ላይ እንዲህ ለምን ተምታታበት ስንል ፤ ክአንዳርጋቸው ጋር ላለው ግንኙነት የተስፋየ ገ/አብ ተልእኮ ስነ ጽሁፍ አልነበረም ፤ ስለ ስነፅሁፍ የሚያወራ ሰው ደግሞ በአንድ ገጽ ላይ እንዲህ አይምታታበትም ።
-6-
እነዚህን የመሃል አገር ሰዎች ከመሃከላቸው ተወልደህ አብረኻቸው አድገህ ፤ አብረሃቸው ሰርተህ አንጀት ጉበታቸውን ስለምታውቀው አንዳርጋቸውን ሰልለው የሚል ተልእኮ ተሰጥቶት ካልሆነ በስተቀር ። በሬ ከአራጁ ይውላል እንዲሉ ይኸው ዛሬ የተስፋየ ማንነት ፍንትው ሲል የሻእቢያም ተልእኮ አብሮ ፍንትው አለ ፤ የእነ አንዳርጋቸው ውሎስ በሬ ካራጁ ይውላል ከሚለው ይሆን ? ውድ ወገኖቼ እንዴት ልንመለከተው ነው ?
ወዶ-ገብ ሰላዮች ታውቃላችሁ ። ወዶ-ገብ ሰላይነት በአገራችን በኢትዮጵያ በተለይ ከቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዘመን በኋላ በጣም ተስፋፍቶ የታየ ክስተት ነው ። ሻእቢያና ወያኔ ከደርግ ጋር በሚዋጉበት ወቅት ደግሞ በስፋት የተስተዋለ ባህርይ ነበር ። ወዶ-ገብ ሰላይ የገንዘብ ክፍያ አይጠይቅም ፤ በተለያዩ ምክንያቶች የሚያገኘውን መረጃ ሁሉ ያለክፍያ ለሌላ ወገን ያስተላልፋል ። በኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ ኤርትራውያን በአብዛኛው በዚህ አይነት ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ ናቸው ። ተስፋየ ገ/አብም ከነዚህ የተለየ የሚሆንበት ሁኔታ አልነበረም ። ተስፋየ ግን ይህን ይሰራ የነበረው እየተከፈለው ነበር ። ከራሱ የእጅ ፅሁፍ ላይ እንመልከተው ፤እንዲህ ይነበባል፦
“ኤውሮፓ ላይ ሥራ የምሰራ ከሆነ፣ በእግረመንገዴም የጽሑፍ ሥራ
እየሰራሁ የተሳካ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አምኜ እንደነበር
አይዘነጋም።…………… በናንተም በኩል ቀደም ሲል
ይደረግልኝ የነበረው ወርሃዊ ክፍያ የተቋረጠውም በዚሁ ምክንያት ሊሆን
እንደሚችል ገምቻለሁ። . . . . . . ሻዕቢያና ኤርትራ ላይ ጥርጣሬ ካላቸው
ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ደባል ቤት ተከራይቼ ይህን ሥራ ልሰራ ግን አልችልም።”

አንባቢዪ ያስታውሱ እንደሆነ ባለፈው አንድ ፅሁፌ ላይ አንዳርጋቸው ፅጌ “የደራሲው ማስታወሻ” የሚለውን መፅሃፍ መቅድም ብርሃኑ ነጋ እንዲፅፍለት ተስፋየን አግባባው ብየ ነበር ። የተስፋየን “የደራሲው ማስታወሻ” መፅሃፍ መቅድም ብርሃኑ ነጋ የፃፈው ፤ መፅሃፉን ሳያነብ በአንዳርጋቸው ውትወታ ነበር። ለተስፋየ የቅርብ ወዳጅ የሆነ ኤርትራዊ ፤ አሁን የግንቦት 7 የአመራር አባል ለሆነ ሰው ይህን ሚስጥር ይነግረዋል ። ይህ ሰው ደግሞ ከሁለት አመት በፊት ፤ ይህ ጉዳይ ትክክል አልነበረም በማለት ለኔ ለዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ቨርጂኒያ ዳማ ሬስቶራንት ምሳ ጋብዞኝ አጫውቶኛል ። እኔም ለምን ብርሃኑን ራሱን ስለዚህ ጉዳይ አትጠይቀውም አልኩት ። ብርሃኑን አታውቀውም ። ይህን ብጠይቀው አንተ በዚህ ጉዳይ
-7-
አያገባህም ነው የሚለኝ ሲል ነገረኝ ፤ ወሬያችንም በዚሁ ተዘጋ ።

ለአንዳርጋቸው ፅጌ ደግሞ በተስፋየ ገብረ-አብ “የደራሲው ማስታወሻ” ላይ ለዚህ ውለታው ውብ የሆነች የሩሲያን ወርቃማውን የስነ ፅሁፍ ዘመን በምታስታውስ አይነት ስልት የተቀመረችና በውስጧ ግን የአስመራ ከተማን ውበት የምትገልጽ አይነት ፅሁፍ ተችሮታል ፤ እንዲህ ይነበባል ከገፅ 125- እስከ126 የአንዳርጋቸውን ቃል ጠቅሶ ፦
“……….. አማራነት ምንድነው? የሚለውን ጥናት ኤርትራዊው በረከት
ስማኦን እንዲያጠናው ታዘዘ ። ………..ሃላፊነቱን የሰጡት እነ ተወልደ
እነ ተፈራ ዋልዋ ፤ እነአለምሰገድ ራሳቸው አማሮች አልነበሩም ።
………ይህን ስናወጋ መሃል ከተማ ላይ አዲስ ከተመረቀው የአለክሳንደር
ፑሽኪን ሃውልት ዙሪያ ከእምነበረዱ መቀመጫ ላይ ተቀምጠን ነበር ።
ፑሽኪን በቀኝ እጁ የላባ ብእር በግራ እጁ ግጥም የፃፈበትን ደብተር
ዘርግቷል ። ………………እና ምሽቱን ሃውልቱ አጠገብ ተቀምጠን
አንዳርጋቸው ስለአማራ ምንነት ጥናት ጉዳይ እያወጋኝ
ነበር……………..አንዳርጋቸው ሲያወጋኝ እያዳመጥኩ ነው።አይኔ ግን
የፑሽኪን ሃውልት ላይ ተተክሏል ።”

በነገራችን ላይ አስመራ ከተማ ከዚህ ሃውልት ሌላ ምንም ሃውልት የሚባል ነገር የሌላት ከተማ ናት ። የሩሲያዊው አለክሳንደር ሰርጌየቪች ፑሽኪን ሃውልት በምስራቅ አፍሪካዊቱ አዲስ ሃገረ- ኤርትራ ፤ በሩሲያ መንግስት ችሮታ ከተተከለላትና ፤ ተስፋየ ገ/አብና አንዳርጋቸው ፅጌ ያደረጉትን የአማሮች ምንነት ጥናት ተያያዥነት ለማየት ያደረግኩት ጥረት ባስበው ባሰላስለው አልመጣልህ አለኝ ። የስነፅሁፍ ምሁርም ሆነ ተራ አንባቢ እንደሚረዳው የአንድ ቦታ ውበቱም ሆነ ምንነቱ የሚገለፀው አድራጊዎቹ በዚያ ሰአት ባላቸው ወግና ስሜት ላይ ተመርኩዞ እንጂ እንዲያው ያገኙትን እያመጡ እየለጠፉ አይደለም ። ለተስፋየ ዋናዋ መልእክት ግን አንድ እና አንድ ብቻ ነበረች ፤ የአስመራን ውበት (ድንቄም ውበት) ባንዳርጋቸው አስታክኮ ማሳወቅ ። “በቆማጣ ቤት አንድ ጣት ብርቅ ነው” እንዲሉ ማለት ነው ።
ተስፋየ ገ/አብ በራሱ የእጅ ፅሁፍ ላይ እንዳረጋገጠው በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ

-8-
የሚኖረውን የአማራውንም ሆነ የኦሮሞውን ልሂቅና ፖለቲከኛ ሁሉ (የትግራዮቹን አይደፍራቸውም፤ እነሱም አይስጠጉትም) በደራሲነቱ እየተጠጋ ሲፈትሻቸው ኖሯል ፤ “የደራሲው ማስታወሻን” ጠቅሼ ከላይ እንደገለፅኩት ማለትም ከነአንዳርጋቸው ጋር የሚያደርጋቸው ውሎዎቹና በእነ ብርሃኑ ነጋ የመፅሃፉን መቅድም ማስፃፍ ሁሉ ፤ የስለላ ስራዎቹ አካላት ነበሩ ። በራሱ የእጅ ጽሁፍ በዳኛ ው/ሚካኢል መረጃ ላይ እንዲህ ያስነብበናል ፤-
“ላለፉት 10 (16 ካለ በኋላ ነው ሰርዞ ወደ ሃሰቱ የገባው) አመታት
ለሻቢያ መረጃና ጥቆማ በመስጠት ሰርቻለሁ። ከሰጠሁት ጥቆማ በላይ
ግን እነዚያን ጥቆማዎች ለመስጠት በተደረገ እንቅስቃሴም ሁለት
መፃሕፍት (የጋዜጠኛው ማስታወሻ እና የደራሲው ማስታወሻ ለመጻፍ
ችያለሁ። እነዚህ ሁለት መጽሐፍት ያስገኙት ፖለቲካዊ ፋይዳ በጣም
ከፍተኛ መሆኑን ለመገንዘብ በአንድ ባለሙያ ማስጠናት ብቻ በቂ ነው።”

የተስፋየ የዚያን ጊዜው ማለትም የ2002ቱ እቅድ ምን ነበር ? የዛሬን አያርገውና ያን ሰሞን ግንቦት 7 በስድስት ወራት ውስጥ ተአምር አሳያችኋለው ያለበት ጊዜ ነበር ። በውጪ ያለው ህዝብም ተስፋ አድርጎ እነ ብርሃኑ ነጋን በገፍ መከተል የጀመረበት ጊዜ ነበር ። ብርሃኑ ነጋን መቅድም ማስፃፍና ከዚያ ደግሞ በተዋቡ ቃላት አንዳርጋቸውን ማሞካሸት ለተስፋየ መፅሃፍ ሽያጭ የማስታወቂያ ስራዎች ነበሩ ። ያን ሁሉ የግንቦት 7 ጀሌ ማግባቢያም ነበር ። እንዳሰበውም መፅሃፉ ተሸጦለታል ። እኔም ራሴ የተስፋየን መፅሃፍ ከገዙት ሰዎች አንዱ ነኝ ። ተስፋዪ ገ/አብ እንደግለሰብ ይህን ሁሉ ጨዋታ እኛ ኢትይጵያውያኑ ላይ ከተጫወተ ሻእቢያማ ምን እያደረገን እንደሆነ መገመት ቀላል ነው ።
ተስፋየ ገ/አብ በራሱ የጅ ፅሁፍና በራሱ ማስረጃ የሻእቢያ ሰላይነቱ የተረጋገጠበት ጊዜ ነው አሁን ። ስለላ የረቀቀ ጥበብ ነው ። ዋናው የስለላ ጥበብ ደግሞ ተሰላዩ ሰው ወይም ማህበረሰብ ፍላጎት ጋር ራስን አመሳስሎ ለረጅም ጊዜ የግለሰቡን ወይም የማህበረሰቡን ሚስጥሮች እንደወዳጅ መጋራት ነው ። ተስፋየ ኢትዮጵያውያንን ባነጋገረ ቁጥር የሚሰራው ለሻእቢያ እንደ ነበር ከላይ በራሱ ፅሁፍ አረጋግጦልናል ። ለሻእቢያ የነበረውንና ያለውን ፍቅር ደግሞ በራሱ የእጅ ፅሁፍ በዚህ መልኩ ነበር የገለፀው ፦

-9-
“ለመጀመሪያ ጊዜ ከሻቢያ ጋር በመገናኘት ኤርትራ ለተባለች ሃገሬ ቀጥተኛ
አገልግሎት ለመስጠት የወስንኩት የ29 ዓመት ጎረምሳ ሳለሁ ነበር። አሁን 41
ዓመቴ ነው። ኤርትራዊነት ይሰማኝ የነበረው ግን ገና ሕጻን ሳለሁ ጀምሮ
ነበር። የሻቢያ ታጋይ ብሆን ምኞቴ ነበር። በታሪክ አጋጣሚ አልሆነም።
ዘግይቼም ቢሆን ሃገሬን ማገልገል በመቻሌ ግን እኮራበታለሁ። በአንድ ነገር
እርግጠኛ ነኝ። እኔ ከኤርትራ ፕሬዚዳንት እኩል ኤርትራን አፈቅራታለሁ።
ይህ የእምነቴ መድረሻ ነው።በኤርትራና በኤርትራዊነት ጉዳይ ላይ ፅኑና
እልኸኛ ነኝ።”
ውድ አንባቢየ እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ እንዲሉልኝ እፈልጋለሁ ። እንደ ተስፋይ አገላለፅ ፤ የኤርትራ ፍቅር መለኪያ ጣራው ፤ ኢሳኢያስ አፈወርቂ ለኤርትራ ያለው ፍቅር ነው ማለት ነው ? አዲስ እውቀት ነው ለኔ ። ምን ያስታውሰኛል መሰላችሁ። በክርስትና ሃይማኖት አንድ ጥቅስ አለ ። “ሌላውን እንደራስህ አድርገህ ውደድ” የሚል ። አንድ የሰው ልጅ ፍጡር ሌላውን እንደራሱ መውደዱ የፍቅር ሁሉ መለኪያ ጣራ ነው ። እንደ ተስፋየ ገ/አብ ከሆነ ኤርትራዊ ሁሉ ኤርትራን ልክ እንደ ኢሳኢያስ አፈወርቂ መውደድ ይኖርበታል ማለት ይሆናል ። ታዲያ በቅርቡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንደዚያ አድርገው ስለኤርትራ በኢሳት መስኮት ሲሰብኩን ልክ እንድ ኢሳኢያስ አፈወርቂና እንደተስፋየ ገ/አብ ከኤርትራ ጋር ፍቅር እያናወዛቸው መሆኑን ልረዳ ችያለሁ ። አሁንም ከተስፋየ ገ/አብ “የደራሲው ማስታወሻ” መፅሃፍ ስንኝ ልዋስ ነው እነሆ ገፅ 316፤-

………..የስንቱን አይነ ልቡና አታለልክ?
አስተዋይነቱን አጭበረበርክ?
በቋዋንቋ ግርዶሽ እየተጠለልክ ፣
ተጠበብኩ ስትል ጠበብክ ፣
አውቅሁ ስትል ደነቆርክ ፣
(ግጥም ደበበ ሰይፉ)
ተስፋየ ገ/አብ እውነተኛው ልቡ የት እንዳለና እኛን ኢትዮጵያውያንን ሲሸውደን በሚቀጥለው የራሱ ፅሁፍ መረዳት ይቻላል ። ከዳኛ ወልደ ሚካኤል መርጃ ላይ በራሱ የእጅ ፅሁፍ ተስፋየ ገ/አብ የወደፊት ህይወቱን በተመለከተ እንዲህ ይላል እጠቅሳለሁ ፤
-10-
“ከስደተኛው ማስታውሻ ቀጥሎ የምፅፈው መፅሃፍ “የቀይ ወጎች” የሚል
ሳይሆን አይቀርም ይህንንም የምፅፍላችሁ እዚያው ደባርዋ ሆኜ ነው።
ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ምክንያት ወደ ኤርትራ ብቅ
ካላችሁ ድባርዋ በየት በኩል ነው? ብላችሁ ጠይቁ ። እዚያው ከአያቶቼ
እርሻ አጠገብ ከዋርካ ዛፎች ስር ተቀምጨ ስሞነጫጭር ታገኙኛላችሁ”

ይህ ፅሁፉ ተስፋየን የወደፊት የእርጅና ኑሮውን ምኞት ይገልጻል ። ወድ አንባቢ ድባርዋ የሚባለው ቦታ ኤርትራ ውስጥ በሰራዪ አውራጃ ከመንደፈራ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ አገር ነው ።

ለኛ ለኢትዮጵያኑ ደሞ እንዲህ ሲል ፅፎልናል “በደራሲው ማስታወሻ” የመጨረሻ ገፅ ላይ” ገፅ 410 ፤

“ ወደ ትውልድ ሃገሬ ተመልሼ በቢሻፍቱ ሃይቅ ዳርቻ ወይም በዝቋላ
ተራራማዎቹ ቀበሌዎች አካባቢ የራሴን ጎጆ እቀልሳለሁ ። በጎችና
ዶሮዎችን አረባለሁ። የቀዩን ዛፍ ፍሬም አፈላልጌ በግቢየ ውስጥ
እተክለዋለሁ። በግቢየ ብቻ አይደለም። በድፍን የረርና ከረዩ አውራጃ
ከተሞች በየመንገዱ ዳር ዳር ቀዩ ዛፍ ይተከላል ። እኔም ስለ ቀዩ ዛፍ
ለህፃናት የሚሆን ተረት እፅፋለሁ ።”………………

አስተውላችኋል ፤ ደባርዋ ውስጥ “የቀይ ወጎች” የሚል መጽሃፍ ነው ተስፋየ መፃፍ የሚፈልገው ። ቢሻፍቱ ደሞ የቀዩን ዛፍ ፍሬ አፈላልጎ ይትክላል ። ምን ማለት ይሆን ? ቀይ የሚለው ቃል ሁሌ ከደም ጋር ስለሚያያዝ የደም ዘመን እንዲመጣ ያለውን ምኞት እየነገረን ይሆን ? ወይስ እንደሚከተለው የተነተነውን ሊፈፅምብን ምኞትና ተሳፋ አድርጎ ይሆን? ገፅ319 ላይ

“ኢትዮጵያዊነትም ሆነ ኤርትራዊነት በአንድ ወቅት አልነበሩም ። ሰዎች
ግን ከዛሬው የማንነታቸው መጠርያ በፊትም በነበሩበት ነበሩ። በአንድ
አጋጣሚ አንድ ማንነት ሊፈጠር ይችላል። ሊከስምም ይችላል ።

-11-
…………….ኤርትራ ማለት ትርጉሙ ቀይ ማለት ነው ። ኢትዮጵያ
ማለት ደግሞ ጠይም ማለት ነው።” ይላል ።

“የቀይ ወጎች” ማለት በላይኛው ትርጉም መሰረት የኤርትራ ወጎች ማለት ይሆን ? የቀዩን ዛፍ ፍሬስ በመላዋ የረርና ከረዩ አውራጃ ከተሞች በየመንገዶቹ ዳርዳሮች ይተከላሉ ማለትስ ቀዮቹ (ኤርትራውያን) በሃገሩ ሁሉ ይሰፍሩበታል ማለት ነውን ? እስኪ ራሱ ተስፋየ ለመፅሃፉ “ለደራሲው ማስታወሻ” ወዝ ያደረጋቸውን የደበበ ግጥሞች እኔ ለራሱ አባባሎች ወዝ ላደርጋቸው አሁንም ገፅ 316 ፦
………ከህይወትህ ወዲያ ላያልፍ – የጥናትህ መደቡ፣
ከህዝብ ጉያ ላይርቅ – የምርምርህ ክበቡ፣
ምን ብትረቅ ምን ብትርቅ – እምትደርስበት ግቡ፣
ወይ የመነሻህ እርካቡ……………
(ግጥም ደበበ ሰይፉ)

አንድ ሌላ የማስታውሰው ነገር ነበረኝ ከተስፋየ ገ/አብ ጋር የደራሲው ማስታወሻ ላይ ። እኔ ያኔ አስመራ ውስጥ ስደተኛ ነበርኩ ። አቶ መልኬ መንግስቴ ከአውሮፓ መጥተው ስለነበረ በመጡ ቁጥር እንገናኝ ነበር ። ከተገናኘንበት ቡና ቤት ሻይ ከጋበዙን በኋላ ከተስፋየ ገ/አብ ጋር ቀጠሮ አለኝ ብለው እየተጣደፉ “እዚሁ ጠብቁኝ ፡ አፍታም አልቆይ ብለውን ሄዱ” ። በስደተኝነታችን ምክንያት ቤሳ ቤስቲን የሌለን ሰዎች በመሆናችን ሻይ እየጠጣን መጠበቅ ግዴታችን ነበር ። ከሁለት ሰአታት በላይ ቆይተው መጡ ።

በጉጉት ምን ተነጋገራችሁ ምንስ ጠየቀዎ ሲሉ ሁለቱ ጓደኞቼ በየፊናቸው ጥያቄ አቀረቡ ። አቶ መልኬ ከነበርነው ሶስት ሰዎች መካከል ወደኔ ዘወር ብለው ምነው ዝም አልክ አንተስ ወሬውን ማወቅ አትፈልግም ? ብለው ጠየቁኝና ከኔ መልስ ሳይጠብቁ ጨዋታቸውን ቀጠሉ ። መልኬ በጊዜው በእውነት ለተስፋየ የነገሩትን ሁሉ በመፅሃፉ ያወጣልኛል የሚል እምነት ኖሯቸው በደስታ ሰክረው ነበር ። የህይወት ታሪካቸውን ፤ ከወያኔ ጋር አለኝ የሚሉትን የትግል ተሞክሯቸውን ፤ ከኤርትራ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሁሉ ዘርዝረው እንደነገሩት አጫወቱን ። ቆይቼ መፅሃፉን ገዝቼ ሳነብ ስለ መልኬ መንግስቴ የተፃፈው “የደራሲው ማስታወሻ” ገፅ 322 ላይ ፦
-12-

“አዲስ 40 በሚል የጫካ ስም ከሚታወቁት አቶ መልኬ መንግስቴ ጋር
አስመራ ላይ ስንጫወት “እኔን የሚያሳስበኝ ቀሪዋን ኢትዮጵያን ለማዳን
እንችል ይሆን ? የሚለው ነው አሉኝ” ።

በማለት ከሳቸው አባባል የፃፈው ይህን ብቻ ሆኖ አገኘሁት ። ከተስፋየ ገ/አብ ጋር ተገናኝተው ሲመለሱ አቶ መልኬ የነበራቸውን የደስታ ስክር ሳስታውሰውና ሁሉን ዘርግፈው እንደነገሩት ስገምት በዚያ ጊዜ የተስፋየ ገ/አብ ተልእኮ ምን ነበር ? ብየ እስከዛሬዋ የዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ ፅሁፍ ድረስ መልስ ሳላገኝ ቆይቼ ነበር ።
አዲሱ የስደተኛው ማስታወሻ የተሰኘውና ለህትመት የቀረበው የተስፋየ ገ/አብ መፅሃፍ በዋሽንግቶን ዲሲ አስታሚዎች ይታተማል ። በ”ላይፍ” መፅሄት ላይ እንደተስፋየ ቃለ-መጠይቅ “ነጻነት አሳታሚ” ድርጅት ነው የሚያሳትመው ። አሳታሚዎቹ ከኢትዮጵያዊነትና ከገንዘብ ትርፍ የሚመርጡበት ጊዜ መጥቷል ብየ እገምታለሁ ። ለአሜሪካ ገበያ አሳታሚው “ነፃነት አሳታሚ” ይሁኑ እንጂ ፤ መፅሃፉ ለአውሮፓና ለአረብ አገሮች ገበያ የሚታተመውና የሚከፋፈለው በቀጥታ በሻእቢያ ከአስመራ ነው ። “የማለዳ ወግ……በጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋየ ገ/አብ ላይ ለቀረበው ክስ ማስረጃ አንድ እውነታ” በማለት ነቢዩ ሲራክ ያደረሰንን ግኝት ያጤኗል ። “ነጻነት አሳታሚ” ድርጅት ለዚህ እየተፈፀመ ላለው የሻእቢያ ሚስጥራዊ ስራ ሽፋን ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው ።
ተስፋየ በተጋለጠበት የእጅ ፅሁፉ ላይ እንደጠቀሰው የአዲሱ መፅሃፍ ፖለቲካዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ። የሻእቢያ ፖለቲካ ፋይዳ ማለት ነው ። ለዚህም ሽፋን እየሰጠን ያለነው ራሳችን ሆነን ተገኝተናል ። ሻእቢያ በደርግ ጊዜ ከተደረገው ጦርነት ጋር ኢትዮጵያውያንን የመሰለልና ወደፈለገው አቅጣጫ የማስተካከል ልምድ አዳብሯል ። ለዚህ ጥሩ ማስረጃ የሚሆነን የበአሉ ግርማ “ኦሮማይ” መፅሃፍን መጥቀሱ በቂ ይሆናል ። ይህ ፅሁፌ ተስፋየ ገ/አብን ማእከል ያደረገ ቢሆንም ተያያዥ ጉዳዮችም ላይ ያተኩራል ። የፖለቲካ ድርጅቶቻችን ፤ ሚዲያዎቻችን ፤ ዌብ ሳይቶቻችንና የፓልቶክ ሩሞቻችንም ይጨምራል ። ስንቶቹ ዌብ ሳይቶች የተስፋየን በራሱ እጅ ፅሁፍ የተገኘ ማስረጃ አወጡት ። ስንቶቹስ አፈኑት ።
ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረች አገር ናት፤ የሚለውን

-13-
የኢሳኢያስ ስላቅ ሻእቢያ እየከፈላቸው ያሉ ሚዲያዎች ባያወጡት አይደንቀኝም ። ብርሃኑ ነጋ እንደነገረን ከተገኘው $500,000 ሺህ ዶላር ውስጥ 200,000 ሺህ ተከፍሏቸዋል ። በየስድስት ወሩም ግማሽ ሚሊዮኑ በመጣ ቁጥር ተገቢው ክፍያ ስለሚደረግላቸው ስለሻእቢያ ትንፍሽ አይሉም ። በነሱ አስተያየት አንድ ድርጅት እንዴት የእንጀራ ገመዱን ይበጥሳል ፤ ለዚያውም አዙሮ ለማያይ ህዝብ ። የፈለከውን ለምትግትው ህዝብ ብለህ ፤ ከደሞዝ ከፋዮችህ ጋር እንዴት ትጣላለህ ። (ውድ አንባቢዎቼ አበበ ገላው በዚያ ሁሉ የአለማችን መሪዎች መሃል ላሳየው ቆራጥነትና ድፍረት ያለኝ ክብር እንደተጠበቀ ሆኖ) ያ ከወራት በፊት አበበ ገላው ላይ ዛቻ አደረገ የተባለው የትግራይ ወጣት ግኡሽ አበራ ላይ ልክ እንደ ተስፋየ ገ/አብ ፤ በራሱ እጅ ፅሁፍ ማስረጃ ተገኝቶበት ቢሆን ኖሮ በኢሳት ምን አይነት አኬልዳማ ይሰራበት እንደነበር ሳሳበው ይዘገንነኛል ። ለሻእቢያና ለሻእቢያ ውላጆች ግን ልዩ እንክብካቤ !
በሩሲያ ውስጥ17ኛው ምእተ አመት ላይ በንግስት የካተሪና ዘመን አንድ የሜልየን ፑጋቾቭ የሚባል ተራ ገበሬ ከፍተኛ የሆነ የገበሬዎች አመፅ በመላዋ ሩሲያ ያቀጣጥላል ። የሩሲያ ከተሞች ተወረሩ ፤ተዘረፉ ፤ ከዚያም ተቃጠሉ ። የገበሬዎቹ አመፅ እንደሰደድ እሳት ተስፋፋ ። ይህንን ብሶት የፈጠረው ፤ ጭቆና ነበር ! መገፋት ነበር ! የፍትህ እጦት ነበር! ። ታዲያ ይህን የገበሬዎች አመፅ የመራው ፑጋቾቭ የገበሬው ብሶት የወለደውን አመፅ በአግባቡ ከግብ ለመድረስ ሳይችል ቀረ ። ከተወሰኑ አመታት ትግል በኋላ የገበሬዎቹም አመፅ በኮዛክ ወታደሮች ተደመሰሰ ። የገበሬዎቹ አመፅ ግቡን ሳይመታ የቀረው መሪው ፑጋቾቭና የቅርብ አጋሮቹ ራሳቸው ፤ ገዥዎቻቸው እንደነበሩት የሩሲያ መኳንንት ለመሆን ጥረት ማድረግ ስለጀመሩና ወደ መኳንትነት እየተቀየሩ በመምጣታቸው ነበር ።

እኛስ ጋ ምን እየተደረገ ነው ? ለገዢው ፓርቲ ሚዲያ ማገልገል ባለመፈለጋችን ከማእከላዊ እስከ ቃሊቲ እስር ቤቶች መከራ አየን ፤ ታፈንን ፤ ተገረፍን ፤ ስለ እውነት በተናገርን ስቃያችን በዛ ይሉ የነበሩ የሚዲያ ሰዎችና አጋሮቻቸው የዌብ ሳይት ባለቤቶች ፤ የሚሰራውን ስህተት አውጥተው ለህዝብ ለመናገር ባለመፈለጋቸው ፤ ለድርጅታቸው ያልቆመ የመሰላቸውን ፅሁፍ በማፈናቸው ፤ ከአሳሪዎቻቸው ከወያኔዎችስ በምን ተለዩ ?
የሩሲያው የገበሬ አመፅ መሪዎች ወደ መኳንንትንት ለመቀየር እንደጣሩት ሁሉ ፤ የኛም የሚዲያ ሰዎች እንደ ወያኔው ስርአት ወደአፋኝነት ተቀይረዋል ። እነዚህ ደግሞ ወያኔን አፋኝ ነው ለማለት ምን አይነት የሞራል ብቃት ይኖራቸዋል ?
-14
ዛሬ የህዝባችንን ህመም ጭቆናና መገፋት ወስደው ፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ቁንጮ የሆነው የሻእቢያው መሪ ጋር ተባብረው ፡ አገራችንን ኢትዮጵያን ከ2ኛው የአለም ጦርነት በኋላ በሃያላን አገሮች የተፈጠርች አገር ናት ብሎ ሲሳለቅባት አይናቸውም አያይም ጆሯቸውም አይሰማም ( ወይ አይንና ጆሮ? ) ፤
በነ ብርሃኑ ነጋ በኩል ለሚደርሳቸው ክፍያ ሲሉ ሻእቢያ ኢትዮጵያን እንደፈለገ ጭቃ ቢለውሳት የሻእቢያ ውላጆች እነተስፋየ ገ/አብ የእግር መጥረጊያ ቢያደርጓት ደንታ የላቸውም ። አንድ ነገር ግን እንዲረዱ እፈልጋለሁ ። ለዛሬ የፖለቲካ ጥቅማችን ስንል ነው ሻእቢያን በዝምታና በትእግስት የምናልፈው የሚል ደካማ ምክንያትም ሆነ ሰበብ በታሪክ ተጠያቂ ከመሆን እንደማያድን ሊረዱት ይገባል ። የኢትዮጵያ ክብርና ጥቅም በምንም የፖለቲካ መለኪያ አይሰፈርም ። የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ሚዲያ ፤ ዌብ ሳይት ወይም ፓልቶክ ሩም በኢትዮጵያ ክብርና ጥቅም ላይ የመደራደርም ሆነ ክብርና ጥቅሟን የመሸራረፍ መበት የለውም ። የአገራችንን የኢትዮጵያን ክብሯና ጥቅሟ ላይ የሚደራደር ወይ ክብርና ጥቅሟን የሚሸራረፍ ሁሉ ፤ የግል ታሪኩ ፤ የዘመነ-ባንዳነት ጉልህ ታሪክ ሆኖም ይቀመጥለታል ። ስለዚህም ባንዳነትንና ለሻእቢያ ጎንበስ ቀና ማለትን ፤ ተስፋየ ገ/አብ የደረጀ በላይነህን ቅኔ ጠቅሶ ከፃፈበት “ከደራሲው ማስታወሻ” ገፅ 95 ልዋስና እንዲህ መልእክቴን ላጠቃልል ፦

አንገቱን ሽቅብ አርዝሞ – የዘመን ቁመት ተራራ ፣
በሰው ባዶነት መዝገብ ላይ – “ከንቱ ነህ” ብሎ ሲያጓራ ፣
የሰው የተስፋ ካብ ፈርሶ – የውስጥ ሃውልት ሲሰበር ፣
“መኖር!” የሚሉት ቋንቋ – ለካስ ከፊል ገፅታው ይህ ነበር!?

ቸር ይግጠመን !
ከአምበሳው ይብራ።
[email protected]