ጥብቅና ለሻእቢያ – ይድረስ ለአንዳርጋቸው ፅጌ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ይድረስ ለአንዳርጋቸው ፅጌ
ጥብቅና ለሻእቢያ
ቁጥር 2 – ለቁጥር 2
ከአንበሳው ይብራ ([email protected])
አንዳርጋቸው ፅጌ ሁለተኛውን የኢሳት ቃለ መጠይቅዎንም አበጥሬ አንጠርጥሬ ሰማሁት ። ግሩም ደንቅ ነው መቼም ።
ጠያቂው 2ኛውን ክፍል የሚጀምረው በባሕር በር ጥያቄ ነው ። ይህ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው ። ጥያቄው የሚያጠነጥነው በሁለት አበይት ጉዳዮች ላይ ነው ። ጠያቂው ስለ አሰብና ስለምፅዋ ወደቦች ከተነተነ በኋላ ፤ ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ አገር መሆኗ የመለስ ዜናዊ ጥፋት ነው ወይስ የኤርትራ? የሚለው አንዱ ጥያቄ ሲሆን ይህ ጥያቄ ለዛሬው ተጨብጭ ሁኔታ የሚፈይደው የለውም ። ኽርማን ኮሀን ተናገረ የተባለውን ሰምተነው ሰምተነው ዛሬ ላይ የወሬ ቋንጣ ሆኗል ። ሁለተኛው ጥያቄ ግን ዋናና የድርጅታችሁን የግንቦት7ን አቋም በወደብ ጥያቄ ላይ እንዲያብራሩ የሚጠይቀው ነበር ። እርስዎም ከተነሱት ጥያቄዎች መርጠው ትንታኔ የሰጡበት ይህንኑ የወሬ ቋንጣውን ነበር ። እንዲህም አሉ እጠቅሳለሁ “የኤርትራ ጥፋት ነው የሚባለው በምን አይነት መለኪያ ሊመጣ ነው ? ሲሉ ራስዎ ጥያቄ ያቀርባሉ ። ወይ ጉድ እንዲሁ ነበራ ሻእቢያን ስንወነጅል የኖርነው ኤርትራን ለመገንጠል አላማው አድርጎ የተነሳ ድርጅት ለኢትዮጵያ አሰብ ያስፈልጋታል ብሎ ሊተውልን ነበር ? ከጅምሩስ ቢሆን የሻእቢያ አላማ ኢትዮጵያን የባህር በር በማሳጣት ጥገኛው በማድረግ እንደፈረንጅ ላም ሊያልባት አልነበረም ? ቀጥለውም አንዳርጋቸው እንዲህ አሉ “የምልህ የባህር በር ያስፈልገኛል ካለች… ኤርትራ ሁለቱንም ትልልቅ ወደቦች እንድትይዝ አድርጎ የቀረፀው መለስ ዜናዊ ነው ፤ መለስ ዜናዊ ብቻ ሳይሆን ወያኔ ነው ። ኤርትራ ፋታ አግኝቶ መቼ ነው ህዝቡ ደቡብ ሱዳን ላይ እንደተወሰነው ውስኔ ማለት ነው የአምስት አመት እረፍት አግኝቶ ከነፃነት መለስ በሆነ መንገድ በፌዴሬሽን ይሁን በኮንፌደረሽን ወይም በሌላ አረንጅመንት መኖር ይሻላል ያለው ። በዛ መንገድ በመሄድ ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን መቋቋም ይቻላል በሚል መንገድ ሚዛናዊ የሆነ ፍርድ መስጠት በማይቻልበት ሁኔታ በፍጥነት በተጣደፈ መንገድ ወደ ድምፀ-ውሳኔ እንዲሄድ ለማድረግ ወያኔ የሰራውን ስራ ስለማውቀው ነው” ። ምንድነው የሚያውቁት ? እባክዎ አንዳርጋቸው ስለእግዚአብሄር ይግለፁልን እስኪ ይህን እርስዎ የሚያውቁትንና እኛ የማናውቀውን ምስጢር ።
እርስዎ ከላይ የገለፁትን ለማድረግ ሻእቢያ ጊዜ አልነበረውም ነው እያሉን ያሉት ? ሻእቢያ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ከመገንጠሉ በፊት የ3አመታት ጊዜ ተሰጥቶት አልነበረም እንዴ ? ፋታ አልነበረውም ነው የሚሉን ። በዚህ ላይ ህዝቡን በአሳፋሪ ሁኒታ ከባርነትና ከነፃነት ምረጥ አልነበረም እንዴ የተባለው በሻእቢያ በእርስዎ የማሳመሪያ አጠራር በህዝባዊ ግንባር ? ምነው አንዳርጋቸው እርስዎ ኢትዮጵያ ውስጥ ከነቤተሰብዎ በስልጣን ላይ ሆነው ያዩትና እኛ ደግሞ አገር አልባ ሆነን ተሰደን በያለንበት የሰማነው ጉዳይ አይደለም እንዴ ? እኛም እንደተሰደድን አለን እርስዎም ተቀላቅለውናል ዛሬ ። ግን ግን ያኔ ከነመለስ ጋር እያሉ አሁን ለኛ የሚሰጡትን ምክር ለወያኔዎቹ ሹክ ብለዋቸው ነበር ? ወይስ ዛሬ እኛን ለማማለል ነው። ቀጥለውስ ሻእቢያ ጊዜያዊ መንግስት ውስጥ ለመግባት ጠይቆ ተከለከለ የሚሉን ። እውነት እርስዎ እንደሚስሏቸው እንዲህ የዋሆች የአብርሃም በጎች ናቸው እንዴ ሻእቢያዎች ፤ ግቡ ሲሏቸው የሚገቡ ውጡ ሲሏቸው የሚወጡ ።
ቃለ መጠይቅ አድራጊው ይቀጥልና ፤ ወያኔዎች ሻእቢያን ጊዜያዊ መንግስት ውሰጥ ባለማስገባት ምን ይጠቀማሉ? ይልዎታል ። ሲመልሱም እንዲህ አሉ ፤ “አየህ ቅድም ስለወያኔና ስለ ሻእቢያ የምናወራውን ከተመለከትክ እንደወያኔ አይነት ውሸታም አጭበርባሪ ለሌብነት ለዘረፋ የመጣ ሃይል እንሱ (እነሻእቢያ) የአንድ መንግስት አካል በሆኑበት ሁኔታ የማይፈቅዱት ነገር ነው” ሲሉን ሻእቢያ ዘራፊ አይደለም ወይም አልነበረም እያሉን ነው ያሉት ። ምነው አንዳርጋቸው በነዚያ ሻእቢያና ወያኔ ፍቅራቸው ብን ባለባቸው አመታት ከጦርነቱ በፊት ማለቴ ነው የኢትዮጵያ ሃብት በሻእቢያ ሲዘረፍ አልነበረም ? የኤሌክትሪክ ጀነሬተሮች ፤ የፋብሪካ ምሽኖች ፤ የሆስፒታል እቃዎች ወደኤርትራ ሲጋዙ አልነበርም ? ጤፍ ፤ በርበሬ ቅቤና የቁም ከብት ከአዲስ አበባ ይልቅ አስመራ ላይ ይረክስ አልነበረም ? በክፍል 1 ቃለ መጠይቅዎ ላይ እንደነገሩን ኤርትራን ከላይ እስከታች ጎብኝተዋልና እስቲ አንድ ቦታ ላይ ኤርትራ ውስጥ አንድ እግር ቡና የሚበቅልበት ስፍራ አይተው ያውቃሉን ? በዚህ አይነት ሁኔታ አይደለም እንዴ ፤ ኤርትራ ያኔ ፤ የቡናን ምርት ለውጪ ገበያ በማቅረብ ከአለም 18ኛ ደረጃ ላይ ደርሳ የነበረው ? ታዲያ ይህን ሁሉ ዘረፋ የረሳነው መስሎዎት ነው ጨዋዎች ናቸው ሊሉን የሚቃጣዎት ። እነሱም ነን ብለው ደፍረው አይናገሩም ። ምናልባት እርስዎ ጦር ሜዳ ላይ ከግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይል ሰራዊት ጋር ሆነው ወያኔዎቹን በህልም እየተዋጉ አላነበቡት ይሆናል እንጂ ፤ ባጠቃላይ የወያኔንና የሻእቢያን ማንነት “ ኤርትራ እንደ እናት ሃገር ፤ ችግሮችና ፈተናዎች ትናንትም ዛሬም” በሚል ርእስ ተስፋ ጽዮን መድሃኔ (ፕሮፌሰር) ከ ጀርመን ብረመን ዩኒቨርሲቲ January 2013 ላይ የጻፉትን ቢመለከቱ የሁለቱንም የወያኔዎቹንም ሆነ የሻእቢያዎችን አላማዎች ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው ፤ እንዲያነቡትም እመክራለሁ ምናልባት ላንቃዎን ከማላቀቅዎ በፊት የህሊና ጥያቄ ያስነስብዎ ይሆናልና ።
የኤርትራ ህዝብ ይላሉ አንዳርጋቸው “ያ ሁሉ ጦርነት ያ ሁሉ እልቂት ያ ሁሉ ሰው ለኤርትራ ነፃነት ሞቶ ኤርትራዎች ምን አማራጭ ነበራቸው ከነጻነት ሌላ ለመምረጥ ? ስለዚህ የኤርትራ ህዝብ ፋታ ስላላገኘ ነጻነት የመረጠበት ሁኔታ ነው ያለው” ብለው ሲሉንና “ሌላው ቀርቶ ምንያህል እንደተጨነቁ እኮ እኔ ከነሱ ጋር ነበርኩኝ” ሲሉና አብረዋቸው በሃሳብ ሲጨነቁንና ሲጠበቡ አስተዋልን በኢሳት መስኮት አቶ አንዳርጋቸው ። እኛ ጭንቀታቸውን ሳናውቅላቸው ቀርተን ነፃነት መረጡ እያልን ስናማቸው ፤ ለሻእቢያ ገንዘብ እያዋጡ መለገሳቸው ፤ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚያገኟቸውን መረጃዎች ሁሉ ለሻእቢያ ያቀብሉ እንደነበር እያወቅን ፤ ከመገንጠል በኋላ የኤርትራን ባንዲራ በእራፊ ጨርቅ አይነት ግንባራቸው ላይ እያሰሩ በትእቢት በከተሞቻችን ላይ ሁሉ እንዳልፏለሉና “ላለይ ላሎ” እያሉ ከበሮ እንዳልመቱብን ፤ እትዮጵያዊ ነን ያሉ ኤርትራዊ ትውልድ ያላቸውን ሰዎች በጠራራ ፀሃይ ከአገራችን ከምድራችን ካለፈቃዳችን እያፈኑ ሲወስዱብን ፤ በርእሰ-ከተማችን በአዲስ አበባ ቀድሞ የወጣቶች ኮሚሽን የነበረውንና በመስቀል አደባባይ በሚገኘው ኤንባሲ ብለው በከፈቱት ቦታ የራሳቸውን እስር ቤት ፤ መመርመሪያና ማሰቃያ ስፍራ ከፍተው ዜጎቻችንን ፍዳ ሲያሳዩ እንደነበር ዛሬም ድረስ የምናስታውሰው ሃቅ ነው ። ተጨንቀው ነበር ብለው ዛሬ እርስዎ ሊሞግቱላቸው ሲቆሙ ነፍስያዎ እንዴት ነው የምትገለባበጠው ፤ የምናውቀውን እንኳ ልታስክደን ትፈልጋለች አሳዛኝ ነፍስ ምፅፅ ። ስለ ኤርትራውያኑ ደም ያን ያህል ሲዘበዝቡ ፤ የኛ ወገኖች ለአንድነት የሞቱት ኢትዮጵያውያን ደም ግን ለእርስዎ ደመ-ከልብ ነበር ። ደመ-ከልብ ማለትን ልተርጉምልዎ በደንብ እንዲገባዎ ፤ የውሻ ደም ማለት ነው ። በኋላ ላይ ሌላ ቦታ ስለዚሁ የተናገሩት ላይ ስለምመጣበት ላሁኑ በዚሁ ልተወው ።
ከላይ ወደጠቀስኳት ሁለተኛዋ ጥያቄ ልምጣ ፤ አዎ የወደቡ ጉዳይ ፤ እንዲህ አሉ አንዳርጋቸው “ቅድም ያነሳኽው ጥያቄ አለ በወደብ ጉዳይ ላይ ፤ ከዚህ በፊትም ተናግሬአለሁ ፤ በኤርትራ በኩል የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘቱ ጉዳይ ራሱም ፕሬዚደንቱም (ኢሳኢያስ ) ሲናገር ሰምታችሁታል ያለው መንገድ ሊፈለግለት የሚገባ ጉዳይ ነው ይህንንን ወደብ በተመለክተ የተለያዩ የሁለቱን ህዝቦች መሰረታዊ ግንኙነቶች አንድ ጊዜ ብታስጀምር የወደብ ጉዳይ ትልቅ ነገር ሆኖ የማይመጣበት ሁኔታ መፍጠር እንደሚቻል እርግጠኛ ነኝ ያለሁት ። ለወደብ ተብሎ የሚደረግ ጦርነት በሁለቱ ህዝቦች መካከል ከዚህ በኋላ ነው የምልህ ያለው ከዚህ በኋላ ለምንም ተብሎ የሚደረግ ግጭት በምንም አይነት የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ ህዝብ allow ሊያደርገው የባይገባ ነው መሆን ያለበት ። ስለወደብ ዛሬ ማንሳት ወያኔ ባጠመደው ውስጥ መግባት ነው የሚመስለኝ ያለው” ሲሉ አብራሩልን ። እኔ በዚህ ላይ ጠብቄው የነበረው ድርጅታችሁ በወደብ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም ያብራራሉ ብዪ ነበር ፤ እርስዎ ግን አንድ የኤርትራ ባለስልጣን ሌላውን ህዝብ እንደሚሸነግለው አይነት ሽንገላ ነው ያስቀመጡልን ፤ ባዶ ገለባ የሆነ ንግግር ። ስለወደብም ማንሳት ወያኔነት ነው አሉን ፤ ወያኔ እንዳልባል አፋችንን ዘግተን መቀመጥ ሊኖርብን ነው ? አሁን ይህን ያበደ የሻእቢያ መንግስት ማን ሊያምነው ይችላል ከናንተ በስተቀር ?
እስቲ ዘወር ብለው ይመልከቱና ያስታውሱ ፤ ሩሲያውያን ለኢትዮጵያ ከፍተውት የነበረው የነዳጅ ማጣሪያ ዛሬ ላይ አፈር በልቶት ትቢያ ሳይሆን በፊት ፤ ወያኔዎች ወደስልጣን ከመጡ በኋላ እንኳ ለኢትዮጵያም ሆነ ለኤርትራ ነዳጅ ማጣሪያ ሆኖ አገልግሎአል ። ይህ የምናገረው ከጦርነቱ በፊት የሆነውን ነው ። በምን ምክንያት ማጣሪያው ስራ እንዳቆመ ያስታውሳሉ ? ካላስታወሱ እኔ ላስታውስዎት ። የነዳጅ ድፍድፍ ኢትዮጵያ ትገዛና አሰብ ላይ እያጣራች የሚያስፈልጋትን ትወስዳለች ። ለማጣሪያው በሚከፈለው ገንዘብ ምትክ ኤርትራ የተጣራ ነዳጅ ያለክፍያ በኢትዮጵያ ኪሳራ እንድታገኝ ይደረጋል ። ይህ የሻእቢያ እቅድ ነበር ። ሻእቢያ ይህን ያደረገው ኢትዮጵያ ሌላ አማራጭ ስለሌላት የምንላትን ትቀበላለች በሚል ስሌት የተቀመረ ነበር ። “እባብ ያየ በልጥ ይደነግጣል እንዲሉ” ፤ ታዲያ ዛሬ ላይ አንዳርጋቸው እንደሸነገሉን በወደብ ጉዳይ እንስማማ ቢባል እንኳ ፤ ከሻእቢያ ጋር የሚደረግ ስምምነት ምን ዋስትና ይኖረዋል ?
ከዛሬ 8አመት በፊት ወደነበረ አንድ ትዝታ ልውሰድዎት እኔ ያኔ ኤርትራ ነበርኩ እርስዎ ደሞ አዲስ አበባ ነበሩ ፤ ያኔ ታዲያ እርስዎ የቅንጅት የምክር ቤት አባል ነበሩ ፤ የቅንጅት ማኒፌስቶ ደግሞ አሰብ የኢትዮጵያ ነው የሚል አቋም ነበረው ፤ የሻእቢያ ባለስልጣናት ያኔ በዚህ የቅንጅት አቋም ላይ ምን ያስቡ እንደነበር እንዴት ያበሳጫቸው እንደነበር አውቃለሁ ። እንዴት አድርገው አይምሮዎን ቢያጥቡት ነው ያኔ ይዘውት የነበረውን አቋም ለውጠው ፤ የአሰብ ወደብን በተመለከት እንዲህ አድርገው የሚሸነግሉን ። በዚህ ላይ የዛሬው የግንቦት ሰባት መሪ ብርሃኑ ነጋ በዚያን ጊዜ የቅንጅት አመራር አባል የነበሩ ጊዜ የአሰብ የባህር በር የኢትዮጵያ ነው የሚለውን ሃሳብ በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች ትግራይን ጨምሮ እየተዘዋወሩ ያስተምሩ ነበር ፤ ዛሬ ምን ተገኝቶ ነው አቋማችሁ 180 ዲግሪ የዞረው ። ድርጅታችሁ ከኢትዮጵያ ህዝብ ደብቆ የተስማማበት ሁኔታም ካለ ግልፅ ያድርጉልን ።
ስለግድቡ ስለሌላ ሌላ ያሉትን እንተወውና ስለ ማህበራዊ ዋስትና የተናገሩት እጅግ ጣፍጭ ፤ ንግግር ናት
በተለይ ጠያቂው የሆነ ነገር ተሳክቶ (ጠያቂውም ይሆናል ብሎ እንዳላመነበት ያስታውቃል) ወደስልጣን ብትመጡ ወታደሮቹ ምንድነው የሚሆኑት ? ይልዎታል ። የመለሷት መልስ የአሪፍ አራዳ ልጅ መልስ ነች ። መቼም ተዋጊ ኖሯችሁ የቆሰለና የሞተ ባትቆጥሩልንም ፤ እንዲህ ነበር ያሉት ፤ ከመጥቀሴ በፊት ግን አንድ ነገር ላንሳ ሲመልሱ ያስተውልኩትን ። ከዚህ በፊት አስበውበት የማያውቁት ጥያቄ ነበር ይህ የማህበራዊ ዋስትና ጉዳይ እና እንዴት ወደ ገንዘብ ሊከረብቷት እንደፈለጉ በግልፅ ይታይ ነበር ፤ የመልስዎ አቀራረብም በግልፅ ይህንኑ ያሳያል ። እንዲህ ነበር ያሉት “እ…..እ…….እ…….እ…….እ……… አጠቃላይየ………የ……..የ………. ትግሉንና የአገሪቱን ሁኒታ ግምገማ ውስጥ የሚጨምር ጥያቄ ነው ያቀረብከው ። አዎ እምልህ እ….በእ……በ
አንዱም እ……ንዲቋቋም የምንፈልገው” አዎ ይህ አባባልዎ ጊዜ መግዣ ይባላል አስበውበት የማያውቁት ነገር ስለሆነ ። አዲስ አሳብ ያልኳት ይህች ነች ፤ይቀጥሉና “ስራም የተጀመረበት ማህበራዊ ፈንድ የሚባል ነገር ነው በዚህ አይነት መንገድ ጉዳት ለሚደርስባቸው ሰዎች ልጆች ቤተሰቦች የሚሆን ወይም ደግሞ በህይወት ተርፈው አካል ጉዳተኞች ሊሆኑ ይችላሉ ፤ እነዚህን ሊደግፍ የሚችል ካሁን ጀምሮ መዘጋጀትና እያደገ እንዲሄድ መደረግ አለበት” በምን ነው የሚዘጋጀው በገንዘብ ነው? እስኪ ይቀጥሉ ። “እኔ ደግሞ አንድ ነገር እርግጠኛ የሆንኩበትን ነገር ልናገር እችላለሁ ። ኢትዮጵያዊ አገሩን እንደሚወድ አቃለሁኝ ያለሁት ። ስፋት ባለው መንገድ በአለም ላይ ተንቀሳቅሼ ኢትዮጵያውያን አይቻለሁኝ ያለሁት። በኢትዮጵያ ውስጥ ከራሱ ጋር ከህዝቡ ጋር የታረቀ መንግስት በሚመጣበት ሰአት ላይ ወይም ደግሞ” ወይም ደግሞ ማንን ሊሉን ነው እናንተን ማለትዎ ነው ! “መሰረታዊ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ ህዝብ የሚያምነው ድርጅት በሚንቀሳቀስበት ሰአት ላይ እነዚህ አሁን ያልኩትን ማህበራዊ ፈንድ በሚሊዮን የሚቆጠር $ዶላር ምን አሉኝ $ዶላር? አሁን ገና ገባኝ ። “አውጥቶ የሚያቆም ህዝብ እንዳላት ደግሞ አውቃለሁ” ፤ አሉ አንዳርጋቸው።
አዎ እኛም ራሳችንን እናውቀዋለን ። ከዚህ በፊትም አምስት አምስት መቶ አዋጥተን ውሃ በልቶን ቀርቶአል ተአምር እናሳያችኋለን ተብሎ ቃል ከተገባልን ጊዜ አንስቶ ይሀው ስምንት 6 ወራቶች አለፉ ። በዚህ ደሞ ሌላ አሁን ለማህበራዊ ፈንድ መዋጮ ልንጠየቅ ነው ማለት ነው ። ዶላር ሊሰሩብን መንገድ ተገኘ ማለት ነው ? ከላይ የአራዳ ልጅ ሁኔታውን ወደ ገንዘብ ከረበተው ያልኩት ለዚህ ነው ።
ጠያቂው በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ነገር ቢመጣ የሚፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ዝግጁዎች ናችሁ ? በማለት ይጠይቃል ። “አይደለንም” ሲሉ እቅጯን ይናገራሉ ። እንዲህ እያደረጉ እውነቱን የነገሩን እንደሆነ ይመሰገናሉ ። ቀሪው ንግግርዎ የፅንሰ-ሃሳብ ጉዳይ ስለሆነ ሊሆንም ላይሆንም ስለሚችል አልጨነቅበትም ። መሃል ላይ ግን አንድ ነገር ይላሉ ። “የሲቪል ማህበረሰቡ በዋነኛነት ጉልበት አግኝቶ የተቃዋሚ ድርጅቶች ሲቢክ ድርጅቶች የፖለቲካ ድርጅቶች በዋናነት ለውጥ አምጪዎች የሚሆኑበትን ሁኔታ መፍጠር ከተቻለ በጋራ የቆመ መንግስት ለመፍጠርም ፤ የተረጋጋ መንግስት ለመፍጠርም ፤ ጊዜያዊ መንግስት ይሁን ዲሞክራሲያዊ መንግስት ለመፍጠርም ፡ መሳሪያ ይዞ ዲሞክራሲን አመጣለሁ ከሚለው ፤ የተሻለ ጋራንቲና ዋስትና ያለው ሲቪክ መህበረሰቡ በበላይነት የሚመራው ሲሆን ነው ። እኛ አገር ይህ ሲቪክ ማህበረሰቡ የሚመራው እንቅስቃሴ ፤ ወያኔ እንዲህ ጥጋቡ በተነፋበት ጊዜ የሚደረግ አለመሆኑ ነው እኛን ወደ አመፅም ሰላማዊ እምቢተኝነትም የወሰደን” ብለውናል ። ታዲያ እናንተ ለአመፅ ትግል ተነስተናል ስትሉ የሽግግር ምክር ቤት ነኝ የሚለው ድርጅት ደግሞ አሁን ከዚህ በላይ የገለፁትን መርህ ይዞ አይደለም እንዴ ተነሳሁ የሚለው ። እንግዲህ እናንተ በተመቻችሁ ጊዜ መርህ የመቀማት መብትም አላችሁ ማለት ነው ?
መጨረሻ ላይ የተናገሩትም ይደንቃል። “ኢትዮጵያ ውሰጥ ያሉት ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን አስመልክቶ እንዲህ ነው ያሉት። “የሚታየው ነገር ነው ወያኔን አስወግደህ በሚቀሩትስ ተቃዋሚዎች መካከል በባህል አድገዋል ወይ ? ለምንድነው አንድ አይነት አመለካከት ያሉት ባንድ ላይ የማይሰሩበት ምክንያት ምንድነው? ለምንድነው ተገነጣጥለው ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉት ? አሁን እኛ በኛ አካባቢ ያሉትን ድርጅቶች ለማድረግ እይተሞከረ ያለው ። ተባብሮ ያለመስራትን መጥፎ ባህል መቅረፍ የሚቻልበት ። እያንዳንዱ ግለሰብ ከራሱ በላይ ሃገርና ወገን የሚባል ነገር እንዳለ ፤ የራስ ስም የራስ ክብር የሚባለው ነገር በጣም በዝቅተኛ ደረጃ መታየት ያለበት የአገርና የህዝብ ክብር መቅደም እንዳለበት የሚያደርጉ ትምህርቶችን በመስጠት የባህል ተሃድሶ ላይ የተመሰረተ ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ ነው እኛጋ የምንሰራው ። ሌሎችም ድርጅቶች በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን የሚሉት በዚህ ላይ መስራት አለባቸው” ። ሲሉ መከሩ ጥሩ ምክር ነው ።
ወያኔ ዲሞክራሲ አምጥቻለሁ እያለ ዛሬ የሚደሰኩረው ያመጣ እየመሰለው ራሱን ስላሳመነና ማንነቱን ማየት ስለተሳነው ነው ። እርስዎና እርስዎን የመሳሰሉ ሰዎችም ራሳቸውን ዘወር ብለው ማየት ስለሚያቅታቸው ዛሬ ላይ ሆነው ምን አድርጌ ነበር ብለው ራሳቸውን አይጠይቁም ግብዞች ናቸው ። አገርቤት ስላሉትና ወያኔን በምኞት ሳይሆን በተግባር እየታገሉ ያሉትን ድርጅቶች እርስዎ ለመተቸት የደፈሩት በምን ልብ ነው ። እርስዎና ጓደኞችዎ በቅንጅት ጊዜ ምን ነበር ይሰሩ የነበረው ተረሳዎት እንዴ አቶ አንዳርጋቸው ? ላስታውስዎት መሰለኝ ። እነሃይሉ ሻውል ገና ከእስር ቤት ሳይወጡ እናንተ መቻቻል አቅቷችሁ ለመበታተን ስትሰሩ አልነበረም እንዴ ? ከለንደን በድብቅ ዋሺንግቶን ዲሲ ድረስ መጥተው ከአውሮፕላን ወርደው ወዲያውኑ Rock Creak ጫካ ውስጥ የሚገኘው Hebrew Congregation ውስጥ ከዋሽንግተን ህዝብ የተደበቀ ስብሰባ ከቀድሞ አምባሳደሮችና ከተመረጡ ሰዎች ጋር ስታደርጉ ፤ የመቻቻል ባህል አስተምራችሁን ነበር ? የታሰሩ ሰዎች ነበሩ ብላችሁ እንኳን ባህላችን የሆነውን ለተጎዳ የማሰብ መርህ ጥሳችሁ አልነበረም ለመበታተን ስትዶልቱ የነበረው ? የአሜሪካው ሚሊየነር ኢትዮጵያዊ ፤ ከኢትዮጵያ ለመጣሁት (የኢትዮጵያዊ ብር) ሚሊየነር እንዴት ስለ ባንክ ስርአት ሊነግረኝ ከጀለ ብላችሁ አልነበረም እንዴ ትጣሉ የነበረው ። ምን ተለውጦ ነው ዛሬ እርስዎ ስለመቻቻል የሚነግሩን ። ዝንጀሮ የራሷ ቂጥ ስለማይታያት በሌላው ዝንጀሮ ቂጥ መላጣነት ታሾፋለች አሉ ። አሁን እውን አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎችን እርስዎ ስለመተባበር ሊያስተምሯቸው ? እነሱ እኮ ሻእቢያ ጉያ ተደብቀው አይደለም እየታገሉ ያሉት ። እየተገርፉ እየታሰሩ እየተደበደቡ ነው የሚታገሉት መከራውን እየቻሉ ።
ይገርማል እርስዎም ብርሃኑ ነጋም አንድ ባህርይ ይስተዋልባችኋል ። በዙሪያችሁ የሚያጨበጭቡ እስካሉ ድረስ ይጋረድባችኋል መሰለኝ ፤ ትላንት የሰራችሁትን ረስታችሁ እናንተ ባልሄዳችሁበት መንገድ ሌላው እንዲጓዝ ለመምከር ሲቃጣችሁ እፍረት እንኳ አይሰማችሁም ።
ስለ ቃለ መጠይቁ ሁለተኛ ክፍል እዚህ ላይ ላብቃ ።
አቶ አንዳርጋቸው ወደሰሞነኛው የአሜሪካ ከተሞች ጉብኝትዎና ከራሞትዎ ላቅናና የተናገሩትን ሁሉ ላስታውስዎት ። በሲያትል ዋሽንግቶን የተገኙልዎ ደጋፊዎች ከ20 የማይበልጡ ስለነበሩ ክፍት ብሎዎ ደስተኛ ሳይሆኑ ተመልሰዋል ። በላስ ቬጋስ ያደረጉት ግን አዘጋጆቹ ይህን ውጣ ያን ግባ እያሉ ወገን ከማጉላላታቸው ሌላ እርስዎ ተደስተውብወት ነበር ። እዚያ የተናገሩትን ታዲያ ላስታውስዎ ።
ስድስት አበይት ጉዳዮች መንጋ ደጋፊዎችዎን አስደስተዋል ፤ አስተዋይ ታዳሚዎችን ደግሞ አስደምመዋል ፤ ኢትዮጵያዊነትን መርህ ያደረጉትን ደግሞ አስቀይመዋል ልበል አላውቅም ። ለሁሉም እንሂድበት፤
አንደኛው ስለኦሮሞዎቹ የተናገሩት ነው ። እንዲህ ነበር ያሉት “የኦሮሞዎቹን የውስጣቸውን ጠብ ብትመለከቱ ለመሆኑ እኛ እየተጣላን ነው ወይ ትላላችሁ ፤ ድብልቅልቃቸው የወጣ እንደ ድርጅት የሌሉ ባዶ ቀፎ ናቸው ብለዋል ። ለሁላችንም አዲስ ነገር ነግረውናል ።
ሁለተኛው ኮለኔል ታደስ ሙሉነህን አስመልክተው የተናገሩት በጣም የሚደንቅ ነው ። ታደስ ሙሉነህ የታሰረው ፡ ድሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያውቀውና ዛሬ የኤርትራ አየር ሃይል አዛዥ ከሆነ ሰው ጋር የኢሳኢያስን መንግስት ለመገልበጥ ሲያሴር ተገኝቶ ነው ብለው አረዱን ።
ሶስተኛው የአርበኞች ግንባርን በተመለከት ስማቸውን መፃፍ እንኳ የማይችሉ bunch of ጎንደሬ ባላገሮች ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል ። አርበኞቹ ባላገሮች ናቸው ። አዎ ናቸው ። ዶክተሮች ተዋግተው ነፃ ያደረጉት አንድ ሃገር በታሪክ ቢጠቅሱልኝ ደስ ይለኝ ነበር ። ጎንደር እርስዎ እንደሚሉት አይነት ቆዳውን የሚለዋውጥ አይምሰልዎ ፤ የአባቶቻችን የኔቴዎድሮስ የነፋሲል የእናቶቻችን የነጣይቱ ፤ የነአሞራው ውብ ነህ አገር እኮ ነው ። ለኢትዮጵያ አጥር ሆኖ ነፃነቱን ሲያስጠብቅ የኖረ ህዝብ ነው ። እንኳን ለሃገሩ ለርስዎ በኢሕፓ ዘመን መጠለያ ሆኖ ነፍስዎ እንድትከርምና ወደሱዳንም እንድትሻገሩ የረዳዎ ያገሬ የጎንደር ባላገር እኮ ነው ።
አራተኛውና ብዙዎችን ያስደመመው አባልዎ ፤ ለኤርትራ ችግር ተጠያቂዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው ፤ በተለይ የፊውዳሉ መንግስት ከሸዋ ሲልካቸው የነበሩ ገዢዎች የፈጠሩት ችግር ነው ። ሲሉ የተናገሩት ነው ። ይህ የሻእቢያ የድሮ ዘፈን በጋዜጠኛና የታሪክ ፀሃፊው በአምባሳደር ዘውዴ ረታ “የኤርትራ ጉዳይ” በሚለው መፅሃፍ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በተጨባጭ ማስረጃዎች ማሰሪያ ተደርጎለት የነበረ ታሪክ ነው ። ሻእቢያም ቢሆን ይህን ታሪክ ያስተባበለበት አንድም ቦታ የለም ። አቶ አንዳርጋቸው ግን ዛሬ ከአስመራ መልስ ይህን ያረጀ ያፈጀ የሻእቢያን ዘፈን በኛ በኢትዮጵያውያኑ መድረክ አቀነቀኑልን ። ይህ ታዲያ አይገርምም ? እንኳን እኛን ሻእቢያዎች ሲሰሙት ይደንቃቸዋል ብየ እገምታለሁ ። ኢትዮጵያዊው ደሞዝ እየከፈለ ኤርትራ የላከዎ ለዚህ ነበር?
አምስተኛውና ዋናው ፡ እመጣበታለሁ ያልኩት ከላይ የጠቀስኩት አባልዎን እዚህ ላይ እንደገና ልጥቀሰው ። እንዲህ ይነበባል “ደመ-ከልብ ማለትን ልተርጉምልዎ በደንብ እንዲገባዎ ፤ የውሻ ደም ማለት ነው” ። ብየዎ ነበር ። “በውጊያም ቢሆን በጀግንነት መዋጋት የሚችሉ ፡ ለሃገራቸው ቀናኢ የሆኑ ነፃነታቸውን የሚወዱ በጀግንነት ኖረው በጀግንነት የሚሞቱ ናቸው ኤርትራውያን ብለውናል ። እኛ ኢትዮጵያውያን ይህ ወኔ የለንም ማለት ነው? ለነጻነታችን ቀናኢ አይደለንም ማለት ነው ? ለኢትዮጵያ አንድነት የወደቁትስ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ፈሪዎችና ቦቅቧቁች ነበሩን ? በዚህ አባባልዎ ደማቸውን የውሻ ደም አድርገው አረከሱት ፤ ያሳዝናል ።
ስደስተኛውና የመጨረሻው ፤ ከሽእቢያ ተቀበላችሁት ስለተባለው ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ያንሱት ጉዳይም ድንቅ ነበር ። ግማሽ ሚሊዮን ዶላር አይደለም ግማሽ ሚሊዮን ኤርትራዊ ለኢትዮጵያ ይሞታል ብለህ ለአለም ንገር ተብየ ተልኬያለሁ ብለውናል ። ማን ይሆን እንዲህ ብለው እንዲነግሩን የላከዎ ! ሻእቢያ ነው ? ደሞዝዎን የሚከፍለው የዲያስፖራው ኢትዮጵያዊ ፤ እርስዎ ጥብቅና ቆመው የሚነግሩን ስለሻእቢያ ።ውድ አንባቢዎቼ ! ስለ ደሞዝተኛ እና በኮሚሽን ስለሚሰሩ ታጋዮች በቅርቡ የማቀርብላችሁ ፅሁፍ ይኖራል ።
በነገው ስብሰባችሁ ላይ ኢትዮጵያዊው ብዙ ጥያቄዎች ይኖሩታልና ፤ ተድላ አስፋው ትላንትና ባወጣው ፅሁፉ ላይ “ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ህዝቡን ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባቸውል” ሲል ከፃፈው መጣጥፍ ላይ እንዳለ የወሰድኩትን ከዚህ በታች ተመልከቱት።
This coming Sunday many people who care deeply for freedom to come to Ethiopia should be free to ask all questions. It is up to Ginbot 7 leadership to answer all, it will be a decision time for members and supporters of Ginbot 7.
For the rest of us who wish change in Ethiopia should not be shy in expressing our views.
ፅሁፌን ላጠናቅቅ ስል የደረሱኝን ሁለት አዳዲስ ዜና ላካፍላችሁ ። የኢሳትን ቋንቋ ልጠቀም ነው አሁን ። “ሰበር ዜና!” አሁን ከራሳቸው ከግንቦት 7 የውስጥ አዋቂ ምንጮች የደረሰኝ መረጃ እንደሚያመለክተው ። በነገው እሁድ በሚደረገው ስብሰባ መድረኩን የሚመሩት ሰዎችና ጥያቄ የሚጠይቁት ሰዎች ሁሉ በቅድሚያ ተዘጋጅተዋል ። ለነዶ/ር ብርሃኑ በነሱ እይታ አላስፈላጊ ጥያቄ የሚጠይቁ ሰዎች የሚኖሩ ከሆነም ወከባ ሊፈጥሩ የሚችሉ አደንቋሪዎችም ተዘጋጅተናል ሲል ይህን ስራ እንዲሰራ ከተመደቡት ውስጥ አንዱ በኩራት ገልፆልናል ።
ሌላው ፡ የሰበር ዜና ፡ ሰበር ዜና ! 4 የወያኔ ፓይለቶች የግንቦት 7ን ህዝባዊ ሃይል ተቀላቀሉ ሲል ኢሳት ያስተላለፈውን መረጃ በተመለከተ ነው ዜናችን ። ይህን ዜና ከተለያዩ የአለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ ፈልገን ለማግኘት አልተቻለም ። ከዲያስፖራው የዜና ዌብ-ሳይቶች ላይ ፈልገን ከሁለቱ ላይ ማለትም ከEthiopian review እና awramba times ላይ ብቻ ነው ልናገኛቸው የቻልነው ። የአውራምባ ታይምስ አቀራረብ ፖይለቶቹ በብቃት ማነስ ምክንያት ከሰራዊቱ ከአንድ አመት በፊት የተባረሩ ናቸው የሚል ሲሆን ፤ Ethiopian review ደግሞ durane.com የተባለ መሰረቱን አምስተርዳም ያደረገ ድረ-ገፅን የአንድ አየር ሃይልን ፎቶ አስደግፎ ዜናውን አውጥቶአል ። durane.com የተባለው ደግሞ ዜናውን አገኘሁት ያለው ከኢሳት ላይ መሆኑን ገልጿል በዚህ አይነት የዚህ ዜና ምንጭ አንድና አንድ ብቻ ሆኖ ተገኝቷል esat ብቻ ። ኢሳት ዜናውን አወጣ ዱራም ተቀበለው Ethiopian review ከዱራም ተቀበለው ምንጩ ሲፈለግ ያው ኢሳት ብቻ ሆነ ። ሆኖም Ethiopian review ላይ በፎቶ የተደገፈና ሁለት ጀቶች ከኋላው የቆሙ አንድ ፓይለት የሚገኝበት ፎቶ ብዙዎችን አደናግሯል ። ምክንያቱም ይህ ፎቶው ላይ ያለው ፓይለት ጀቶቹን እያበረሩ ኤርትራ ገቡ ከተባሉት አንዱ እንዲመስል ተደርጎ ቀርቧል ። ይህን ፎቶ Ethiopian air-force ብላችሁ ጉግል ብታደርጉ የዛሬው ኢትዮጵያ አየር ሃይል ድረ-ገፅ ላይ ታገኙታላችሁ ። ፓይለቶቹ በርረው ገቡባት የተባለላት ኢርትራ እንኳ ስለዚህ ዜና ትንፍሽ ያለችው ነገር የለም ። ይሁንና የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ አስመራ ከሚገኙት የበታች ሹማምንት መረጃ ምንጮች ያገኘው ዜና እንደሚያመለክተው የሁለቱን ሰዎች ወደአስመራ አመጣጥ ግልጽ ሆኗል ። አንደኛው በኬንያ ሁለተኛው ደግሞ በደቡብ አፍሪካ በስደተኝነት ለተወሰነ ጊዜ የኖሩና በቅርቡ ወደአስመራ የመጡ ፤ ቀደም ብሎ በአየር ሃይል ውስጥ ያገለገሉ ፓይለቶች ሲሆኑ በግንቦት ሰባት ተመልምለው በኬንያና በደቡብ አፍሪካ በኤርትራ ኤምባሲዎች አስፈላጊው የፓስፖርትና ቪዛ ጉዳዮች ሁሉ ተሟልቶላቸው የመጡ ሰዎች ናቸው ። የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ እንደታዘበው ከሆነ ፤ በቅርቡ አንዳርጋቸው ፅጌ በሰጡት ቁጥር አንድ ቃለ-መጠይቅ ላይ ምሁራንና የጦር ሰዎች የወያኔ መንግስት ከድተው ከግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይል ጋር እየተቀላቀሉ ነው ሲሉ የሰጡትን ቃል ማረጋገጫ አድርጎ ለማቅረብ ኢሳት የተጠቀመበት ፕሮፓጋንዳ መሆኑ ነው ። የቀሩትን የሁለቱን ፓይለቶች ዜና እንደደረሰን አቀርብላችኋለሁ ። ሰበሩ ዜና በዚሁ አበቃ ።