ማስታገሻ መርፌ ውጋው – ይድረስ ለአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ከአንበሳው ይብራ
ይድረስ ለአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ
ጤና ይስጥልን አቶ አንዳርጋቸው እንደምን አሉ ፤ በኢሳት መስኮት እንዳየሁዎ ጤናዎ በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል ብየ እገምታለሁ ። እንደባህላችን ከብቶቹስ እንዴት ናቸው እንዳልልዎ ኤርትራ ከብት ለማርባት እንዳልሄዱ አውቃለሁና ምንም እንዲሉኝ አልጠብቅም ። ልጆቹስ እንዳልል መንታዎቹ ልጆችዎ በsingle mother ለንደን በእንክብካቤ እያደጉ መሆኑን ስለሰማሁ በጥያቄ አላስቸግርዎትም። ትግሉ ብል ይሻላል እንዴት ነው እየሰመረ ነው ? በረሃውን እየለመዱት ነው? በቃ የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ህይል በየጦር ሜዳው ወያኔን እያርበደበደው ነው አይደል ? እንግዲህ አራት አመት ሞላዎ እኮ! ዘመኑ እንዴት ይሮጣል ጃል። በረሃ ከመግባትዎ በፊት ያኔ አምስት አምስት መቶ ዶላር አዋጡ በ6ወራት ወስጥ አዲስ አበባ እንገባለን ብሎ ድርጅትዎ ሲያውጅ እንዴት ደስ ብሎኝ ነበር መሰለዎ በቃ ገና አሁን መጡ ከህመማችን የሚገላግሉን ብየ ፈንድቄ ነበር። እኔም የድርሻየን ከ500 ዶላር የዘለቀ ለግሻለሁ ። የ6ወራቱን ተልእኮ ውጤቱን ባታሳዩንም አልተከፋሁም ተስፈኛ ነኝና ፤ ቀጥሎ በርሃ ገቡ ማለትን ስሠማ ደግሞ እንደገና አሁንም ከህመማችን መፈወሻው ቀን ደረሰ ብየ ፈንድቄ ነበር። ለምን መሰልዎ እኒም ገባ ወጣ እያልኩ እርስዎ ያሉበትን ስፍራ አውቀዋለሁና ለዚህ ነው ተስፋ ማደርጌ ።
በኢሳት የሰጡትን ሙሉ ቃለ መጠይቅ ከሰማሁ በኋላ ደግሞ ፤ እንደገና መርፌ ሊወጉን ነው እንዴ የመጡት ብየ መጠርጠር የጀመርኩ ። እየደነቀኝ ደጋግሜ ሰምቼዎታለሁ የሰጡትን ቃለ መጠይቅ ። ከዚህ ፅሁፍ ላይ በቀይ ቀለም የተፃፉት አረፍተ ነገሮች በሙሉ ራስዎ በቀጥታ ከሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ቃል በቃል የተወሰዱ ናቸው ። ስለመለስ ሞት የተናገሩትን እና ከዚያም ብኋላ ያሏቸውን ነገሮች ልለፋቸውና “ 19ኛው ደቂቃ ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች ጠመንጃ ለማንሳት ወደ ኤርትራ እየገቡ ያሉትን ባይኔ ነው የማያቸው ያለው። 10ሺህ የሚደርሱ እስከ ጥርሱ ድረስ የታጠቀ ጦር ያለው ድምሕት የሚባለው ድርጅት የትግራይ ተቃዋሚ ድርጅት ነው ። ከነዚህ ወጣቶች ጋራ እነጋገራለሁ ፤ ህይወት ምን እንደሚመስል ሲናገሩ …” ምናምን ብለው መቀባጠር ይጀምራሉ የድምህት ተዋጊዎች ለሰራዊቱ ወታደርነት እንዴት ከአገራቸው እንደሚሰበሰቡ ያልተናገሩት ነገር እንዳለ ሳልጠቁም ማልፍ አልፈልግም ። እርስዎ ለማለት እንደፈለጉትም ወጣቶቹን ሲያነጋግሯቸው በትግራይ የሚደርሰውን ጭቆና አጫውተውኛል ለማለት ነው ፡ በመጀመሪያ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የአፍ ልጉምት በድምሕት ስለአለ እንኳን ግልፅ ሆነው ሊያወሩዎ ይቅርና እንደርስዎ አይነቱን ሰው በሙሉ አይናቸው እንዲያዩ አይፈቀድላቸውም ። በነገራችን ላይ ይህ ልጉምት በኤርትራ የሚገኙ የድርጅት አባላት ላይ በሙሉ የሚታይ ነው ። አንዳንዶቹን እርስዎ እንዲያነጋግሯቸው ቢፈቀድ እንኳ እውነት እንደማይንግሩዎ አውቃለሁ ። ምክንያቱም በግዳጅ ፤ ለእርሻ ስራ እንደባሪያ እየተፈነገሉ ስለሚመጡ ፤ ተፈንግለው መምጣታቸውን እንዲናገሩ ደሞ ሻእቢያ አይፈቅድም ። አቶ አንዳርጋቸው ታዲያ ይህን ወይ እያውቁም አለያም ደብቀውናል ። በአስር ሺህ የሚቆጠር ሰራዊት ድምህት አለው ካሉ ደግሞ ትግራይ ውስጥ ጭቆናው ስር ሰዶ ወጣቱ ውስጥ ሰርፆ ገብቷል ብለው እንዳያስቁኝ ።
“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ይሏታል ጅግራ” የሚለውን ተረት ያውቁታል ብየ እገምታለሁ ። ሾልኮ በወጣባቸው የምስጢራዊ ስብሰባ ድምፃቸው ፤ ዶ/ር ብርሃኑ እንደተናገሩት ድምህትን ከሻእቢያ ጋር ተደራድረው ጦራቸው የማደርግ ምኞት ስላላቸው ፤ ከአሁኑ አቶ አንዳርጋቸው ድርጅቱን ጠንካራ ሃይል አድርጎና አስመስሎ በመቅረፅ ለሚቀጥለው አመት “የማስታገሻ መርፌ ውጋው” ፕላን እያዘጋጁን ይመስለኛል ። ድምህት ካሉት ድርጅቶች ጋር ሁሉ ሲወዳደር በተሻለ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን እኔም አሌ አልልም ፤ ግን እርስዎ እንዳሉት አስር ሽህ ጦር የለውም ። እንኳን አይቼው ይቅርና ባላየውም አላምንዎትም ነበር ። 10 ሽህ ጦር እኮ ሁለት ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ማቋቋም የሚያስችል የስው ሃይል ነው ። አስር ሺህ ጦር እኮ ፤ በመደበኛ የመንግስት ሰራዊት ላይ ቢያንስ ከተለያየ አቅጣጫ ጦር በመክፈት ማስጨነቅ የሚችል ኅይል ነው ። እኛ ግን ኮሽ ሲል እንኳ አንሰማም በድምህት በኩል። ከድምህት ማሰልጠኛ ጣቢያ በጥቂት ኪ/ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ተሰነይ ክተማ እንኳ ያላት የህዝብ ብዛት 3800 ነው። የድሮ የተፈሪ መኮንን ተማሪ ነበሩ ማለትን ስለሰማሁ የቁጥር ችግር እንደማይኖርብዎት ተስፋ አለኝ እንዲያው ላጩኸው ካላሉ በስተቀር። በማህበራዊ ሁኔታስ አስር ሺህ ሰው አንድ ቦታ ያለስራ ተከማችቶ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስተውለዋል ? አቶ አንዳርጋቸው ከዚያም ስለ ትግራይ ይተነትኑልን ያዙ ፤ ጥሩ ትንተና ነው እንዳፍዎ ያድርገው፤ እኔ እንኳ ትግራይ ውስጥ ገብቼ ስለማልውቀው መዘባረቅ አልፈልግም። ጠያቂው ግን 21 ኛው ደቂቃ ላይ የርስዎን የአስመራ እንቅስቃሴና አስመራ ምንድነው የሚያደርጉት ብሎ ሲጠይቅዎ እንዲህ ነበር ያሉት እጠቅሳለሁ እንደገና “ እኔ በዋናነት አስመራ አይደለም ያለሁት ነው ያሉን የተለያዩ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ባሉበትና በተደራጁባቸው ቦታዎች በስፋት በኤርትራ ውስጥ እየተንቀሳቀስኩኝ ከነዚህ ሃይሎች ጋራ የሚደረግ ውይይትም መተባበርም የሚቻልበትን ሁኔታዎችም ብለው ሲናገሩ የሌለ ነገር ስለተናገሩ ፤ የአካል እንቅስቃሴዎ ሲከዳዎት ይታይ ነበር በመስኮቱ ። በዚህ ላይ ውጪ ያለው ኢትዮጵያዊ የእርስዎን የአስመራ ኑሮ ባያውቅም ፤ አስመራ የሚያውቁኝ ሰዎች እንኳ ይታዘቡኛል ብለው ቢያስቡ ይበጅ ነበር አስመራ አይደለሁም ያለሁት ብለው ሲናገሩ “ከዚያም አልፎ ይሄ በአመፅ ሃይል ካልሆነ በስተቀር በሌላ መንገድ የወያኔ ስርአት አይወገድም ብለው የሚያምኑት ሃይሎች አመፅ ምን ለማምጣት በዛ አገር ላይ ፤ አመጽ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ ፤ አመፅ ህዝብ የመረጠውን የምንመኘውን ዲሞክራሲያዊ መንግስት ለመፍጠሪያ መሳሪያነት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል እያንዳንዱን ተራ ታጋይ እስከ አመራሩ ድረስ በጋራ ስልጠናም ትምህርትም የሚሰጥበት ሁኔታ ላይ እየሰራሁ ነው ያለሁት እኔ” ሲሉ ነገሩን ። ዲሞክራሲን እየተመኙዋት ነው እንዴ አስመራ ቁጭ ያሉት እኔ እኮ እየታገሉላት መስሎኝ ? አራት አመታት ሙሉ አስመራ ተቀምጠው በምኞት ላይ እየሰሩ ነው ገና ። ይገርማል ? ከመረብ በታች ያለው ሃገር ሁሉ የግንቦት ሰባት ጦር በአንዳርጋቸው እየተመራ መጣ ተብሎ ተነግሮት ፤ በፍርሃት የሚርደውም እየተንቀጠቀጠ፤ በደስታ የሚፈነድቀውም የሙገሳ ግጥሙንና መሰንቆውን እያዘጋጀ እየጠበቀዎት ነው ብየ ሳስብ ገና በጋራ ስልጠና የሚሰጥበት ጉዳይ ላይ እየሰራሁ ነው ያለሁት እያሉ ያሳፍሩናል እንዴ ! አንድ ሌላ ያልነገሩን ነገር ጊዜዎን ካላጣበበብዎት በቀር በአራት አመታት ውስጥ ገና እየተዘጋጀሁ ነኝ አይሉንም ።
ጠያቂውም ይቀጥልና የከዚህ በፊት መግለጫችሁንና አለቃዎ ብርሃኑ ነጋ የሰጡትን ቃለ- መጠይቅ ጠቅሶ ግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይልና ግንቦት ሰባት ንቅናቄ የሚባል ሁለት ሃይል እንዳለ ይጠይቅዎታል ፤ እንደገባኝ ከአመፀኞቹ ጋር ምንም ግንኙነት የለንም ፤ ግን እንደግፋለን ሲሉ ብርሃኑ ነጋ የተናገሩትን ለመጥቀስ አስቦ መሰለኝ፤ ታዲያ እርስዎ ምን ያደርጋሉ ሲል ያፋጥትዎታል ፤ ተፍልጎም ሆነ ሳይፈለግ ጥያቄው ድንቅ ነበር ። ሲመልሱ እንዲህ ነበር ያሉት “ናቸው አይደሉም ለጋዜጠኞች የምንተወው ፡ ጥንቆላ ነው የሚሆነው” ጠያቂው እንደገና “እርስዎ ታዲያ ምን ያደርጋሉ?” ኦ አሁን እንደተናገርኩት ነው ከግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይልም ጋር ቢሆን ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ትምህርትና ስለጠና የሚሰጠውን… የሚደረገውን… የማደርገውን ስራ እዚያም አካባቢ ነው ሲሉ ይንተባተባሉ ስሜት አይሰጥም ንግግርዎ ደህና አድርጎ ላዳመጠዎ ። ቀጥለውም ድምህቶችም ጋር እንደማደርገው ከሌሎች ድርጅቶችም ጋር እንደማደርገው በጣም ሰፊ የሆነ የፖለቲካ ትምህርትና ስልጠና ግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይልም ጋ እሰጣለሁኝ አሁን ። ሲሉ ራስዎን በኤርትራ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ድርጅቶች ሁሉ የፖለቲካ ምጡቅ ተመራማሪና አስተማሪ አድርገው ሊያሳዩን ይጥራሉ። ደግሞስ በምን ሁኔታ ቢቀመር ነው የግንቦት ሰባት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በኤርትራ የሚንቀሳቀሱት ተቃዋሚዎች ሁሉ የፖለቲካ አስተማሪ ሊሆን የሚችለው ? እንዴት ቢገምቱን ነው እባክዎ ?
በነገራችን ላይ “ለጋዜጠኞች የምንተወው ጥንቆላ ነው” የምትለዋ አባባልዎ አስደንቃኛለች፤ ለወሬ ማሳመሪያም ይሁን ወይም መልሱ ቸግሮዎ አላውቅም የተናገሯት፤ ሆኖም` እርስዎን የመሰለ የፖለቲካ አስተማሪ ፤ የመለስ የቀድሞ ጓደኛና የሃገር ተቆርቋሪ እንዴት ጋዜጠኝነትና ጥንቆላ አብሮ እንደማይሄድ ሳይጠረጥሩ ቀሩ ? ጋዜጠኝነትን ስንማር የጥንቆላውን ክፍል ሳልማር በመቅረቴ ይኽው እንድቆጭ አደረጉኝ እኮ ።
ጠያቂው አያርፍም “የት ነው ይህን ትምህርት የሚሰጡት አስመራ ነው”? ሲል ይጠይቅዎታል ። አይደለም በረሃ ውስጥ ነው ያሉት ሲሉ ይመልሳሉ ። የጠየቀዎት እኮ ታጋዮቹ የት እንዳሉ አልነበረም የት ትምህርቱን እንደሚሰጡ ነበር ?
በርሃ ውስጥ መሳሪያ የያዙ ሃይሎች አሁን እየታገሉ ነው? ሲል ይቀጥላል ጠያቂው፤ መልስዎ ምን ይመስል ነበር እንየው እስኪ፤ “በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ትግል አለ ፤ ከፍተኛውን ስልጠና የኤርትራ መንግስት በሚያደርገው እርዳታ የመመልመል የማሰልጠን የማደራጀቱ ስራ በኤርትራ ውስጥ ይካሄዳል ያለው”፤ ሲሉ ይመልሳሉ ። ጥያቄው ግን መሳሪያ የያዙ ሃይሎች አሁን እየታገሉ ነው ወይ የሚል ነበር ስለ ኤርትራ መንግስት እርዳታ አልነበረም ። የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይል መሳሪያ አንስቶ አዎ እየታገለ ነው ሲሉ ለምን አልነገሩንም ጦር የለውም እንዴ ? በዚህስ ላይ አርበኞች ግንባር ድምሕትና እና ኦነግስ ቀደም ብለው ትግል የጀመሩ አይደሉም ? እርስዎ ከላይ እንደተናገሩት አመጽ ለምን አመጽ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ የሚለውን ትምህርት ለዛ ሁሉ መንጋ ታጋይ እስከ አመራሩ ድረስ ፤ ትምህርት የሚሰጡ ሰው አይደሉ እንዴ፤ ምነው እነ አርበኞች ግንባር ከአስር አመታት በላይ መሳሪያ አንስተው እየታገሉ መሆኑን ሳይነግሩዎ ቀሩ ወይስ እርስዎ የሚኖሩት አስመራ ከወዳጅዎ ጋር ስለሆነ አሳፍሮዎ ነው ። መቸም ሄደው አይጠይቁም ሻእቢያም አይናገርም ብለው ከሆነ እኔ ሄጀ የመጣሁትና አስመራንም “ጉልችንም” ማሰልጠኛ ጣቢያውን “ሃሬናንም” ጭመር ከሰው በፊት ሄጄ ተመላልሼም አውቀዋለሁና አያስቡ እነግርልዎታለሁ ፤ እንዲያውም አንዱ ጉዞየ ከውንድምዎ ብዙነህ ፅጌ ጋር ነበር፤ በበርኔጣና በመንፅር ራሱን ሲሸፋፍን ያነሳሁት የቪዲዮ ፊልም በጄ ላይ ይገኛል ፤ ይገርማል እርስዎም በመነጸርና ባርኒጣ መሸፋፈን ይወዳሉ በኋላ ላይ እመጣበታለሁ ፤ ከላይ የጠቀስኳቸው የማሰልጠኛ ጣቢያው አካባቢ ስፍራዎችም ምስጢርነት ከስምንት አመት በፊት አክትሞለታል ሚስጥር አውጣ ብለው እንዳያሙኝ ።
የተማሩ ሰዎች ወደበርሃ አለመግባትና በእርስዎ ጊዜ፤ ገና ዛሬ እንደተጀመረና ምሁራን ገና መግባት እየጀመሩ ነው ሊሉን ይቃጣዎታል ። መሬት ላይ ሳይወርዱ ፤ አፈር ሳይበሉ ፤ አፈር ላይ ሳይተኙ ነጻነት ይመጣል ብሎ መጠበቅ አይቻልም ብለውናል። እስማማለሁ።
ምን ሆነ መሰለዎት እኔና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ፤ ወንድምዎን ብዙነህን ጨምሮ ወደማሰልጠኛው ጣቢያ ስንጓዝ “ሃይኮታ” የምትባል ትንሽ የገጠር ከተማ ላይ ምሳ ለመብላት ወርደን ነበር ። ከተማዋን ያውቋታል ብየ እገምታለሁ ፤ ወደ ማሰልጠኛ ጣቢያ ሲሄዱ ከተሰነይ ቀደም ብላ ያለችው ትንስ ከተማ ናት። ከመኪና ወርደን አለች የተባለችው ሆቴል ትሁን ሻይ ቤትነቷ የማይታወቅ ቤት ገባንና እርጎ በበርበሬ ከማባያው ዳቦ ጋር ቀረበልን ፤ ወንድምዎ እርጎውን ለመብላት ሲጠየፍና ሆዴን ያመኛል ያልተመረመረ pasteurized ያልሆነ የወተት ዘር አልመገብም ሲል ትዝ ይለኛል።
እናልዎ የአርበኞችንም ሆነ የድምሕቶችን ምግብ አብሬ ስለበላሁ አውቀዋለሁ ። የማሽላ ቂጣና የምስር እንቅጥቃጭ ወጥ፤ በርበሬም ሆነ ማጣፈጫ የሌለው እንደሆነ ቀምሻለሁ ። እርጎ የሚጠየፈው ወንድምዎ ተዋጊዎችን ለማሰልጠን ወደማሰልጠኛ ጣቢያ ገብቶ ነበር ማለትን ስሰማ፤ በርግጥ ምግቦቹን ከለንደን አስጭኖ ገብቶ መሆን እንዳለበት ሳልገምት አልቀረሁም። ይህ ታዲያ እርስዎ እንዳሉት አፈር መብላት አይደለም ። እርስዎም ቢሆኑ አስመራ ቤት ተከራይተው መጀመሪያ ላይ ከወዳጅዎ ጋዜጠኛ ተስፋየ ገብረአብ ጋር አስመራን ሲያካልሉ እንደነበር በአይናችን በብረቱ እናየው የነበር ሃቅ ነው። እንዲያውም ተስፋየ “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” በሚል ርእስ ያሳተመውን መፅሃፍ መቅድም ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እንዲፅፉለት ያግባቡት ያኔ ነው ይባላል።
አቶ አንዳርጋቸው ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በወያኔ ታስረው የነበረ ጊዜ ከለንደን አዲስ አበባ ድረስ መጥታ እስር ቤት እየተመላለሰች የጠየቀችዎትንና በኋላም ለንደን ላይ መንታ ወላዳልዎ ልጆች ያስታቀፈችዎን ወይዘሮ ትተው ፤ ታክሲ እየነዱchild support ከመክፈል ሸሽተው አስመራ እንደገቡ ከማን ጋር እንደተዳበሉና የት ውለው እንደሚያድሩ ፤ በድፍን አስመራ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሁሉ የሚያውቀውና ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው ። እንዲህ ሆኖ እያለ ፤ አፈር ካልበሉ አፈር ላይ ካልተኙ ፤ እያሉማ አይመፃደቁብንም።
አንድ ነገር እቅጩን ልንገርዎ፤ እኔ እርስዎን አውቅዎታለሁ፤ እርስዎ ግን በመልክ አያውቁኝም አስመራ ራስዎን ለመደበቅ መነፀርና ኮፍያ ደፍተው ስለሚወጡ በየቀኑ እታዘብዎ ነበር ። ትዝብቴ የክፋት ሳይሆን የአግራሞት ትዝብት ነበር ። ምን መሰለዎ ኮፍያውም ሆነ መነፀሩ እርስዎነትዎን መደበቅ አይችልም ነበር፤ ጎፈሬው ቅንድብዎ ቀድሞ ስለሚወጣ ፤ የማይደበቅ ፊት ይዘው ለመደበቅ ሲጥሩ አንዳንዴ ያስቁኝም ነበር ። ታዲያልዎ የምንገናኘው ሁሉም የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች እርስዎም፤ ኦነጎችም ፤ የአርበኞች እንግዶችም ጠዋት ጠዋት ለቁርስ የምንገናኝባት ከኒያላ ሆቴል ፊት ልትፊት ገባ ብላ በምትገኘው መንገድ ላይ ያለችው ከአስመራ ምርጥ ቁርስ ቤቶች በአንዷ ፤ ያስታውሷት የለ ? አዎ “ቤት ቁርሲ ምፅዋ” ወይም “ምፅዋ ቁርስ ቤት” ተብላ የምትጠራው ጋ ነበር። በየጠዋቱ አገኝዎ ነበር ታዲያ እዛች ቤት እኔ አፈር ሲበላባት አይቼም ሰምቼም አላውቅም ። የቁርስ ቤቷ የታወቁት የቁርስ አይነቶች ፤ በአስመራ ቋንቋ “አይኒ ብእራይ” “ቅጫ ፍትፍት” “ፍሪታታ” እና “ፉል ብጠስሚ ወይም ብዘይቲ” ናቸው ። እዚያ ታዲያ እኔ እስከማውቀው፤ እርስዎ የሚወዱት ቁርስ ፉል ብጠስሚ ነበር፤ ከጎኑ እስፕሬሶ ቡናና በረጅም ብርጭቆ እንደ ኤርትራ ባንዲራ የትዥጎረጎረውን ጭማቂ አስቁመው ሲያምጉ ነው እንጂ አስተውል የነበረው፤ አፈር አቅርቡልኝ ሲሉ ሰምቼ አላውቅም ። ደግሞስ ለንደን ከሚያገኙት የታክሲ ገቢ በላይ ደሞዝ ተቆርጦልዎ child support እና ታክስ መክፈል የማይገደዱበት አስመራ ውስጥ እንደልብዎ መኖርን የመሰለ ነገር የት ይገኛል። እያንዳንዱን መቶ ዶላር በአምስት ሺህ ናቅፋ እየዘረዘሩ መንበሽበሽ ነው ምናለ ፤ ደሞዝ የሚከፍልዎን ወገን ይጭነቀው እንጂ እኔማ ምን አገባኝ ! እርስዎ በጨዋነትና በአይነ-አፋርነት ያለፉትን ሁሉ እኔ እነግርልዎታለሁ አያስቡ።
አንድ የከነከነኝ ነገር አለ ? ምን መሰለዎ ይቺ ኤርትራ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሁሉ የፖለቲካ ስልጠና እየሰጠሁ ነኝ ያሉዋት ጉዳይ ገርማኛለች ። እንዴት መሰለዎ የኔ ጥያቄ ፤ እንዲህ ትምህርት እየሰጧቸውና እየለፉላቸው ነው የአርበኞቹ ግንባር “የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ባለቤት የሌላቸው ታማኝ ሎሌዎች ጉሮኖ ሊሆን አይገባም፡፡” ሲል በርድጅትዎ ግንቦት7 ላይ መግለጫ የሚያወጣው ። የፖለቲካ አሰልጣኛቸውን ድርጅት ሰው ፤ እንዲህ ከፍ ዝቅ የሚያደርጉ ፡ ምን ውለታ ቢሶች ቢሆኑ ነው ጃል ።የአርበኛውን ሙሉ መግለጫ ካላነበቡት በ http://www.ginbot7d.org ወይም www.ethiopatriotc.com ያገኙታል ። በምንስ መለኪያ ነው እርስዎ የአርበኞች ግንባርን ፖለቲካ የሚያተሰምሩት አርበኞችን እንደማያስተምሩም በሚገባ አውቃለሁና ?እንዲያው በምን መለኪያ ነው እርስዎ ኦነግን ፖለቲካ የሚያስተምሩት ? እንዴትስ ነው ኦብነግን ፖለቲካ የሚያስተምሩት ፍፁም የማይቻል ነገር ነው ፤ ምክንያቱን በሎጂክ ላብራራ ፤ እነዚህ የጠቀስኳቸው ድርጅቶች ሁሉ ይዘው የተነሱት አላማ እርስዎ ቢያንስ በፕሮግራም ደረጃ ይዠዋለሁ ከሚሉት መርህ ጋር ይጣረሳልና ምንም ሊያስተምሯቸው የሚችሉት ነገር የለም ።
እዚህ ላይ አንድ ነገር አቶ አንዳርጋቸው አደራ አደራ እልዎታለሁ ! አለቃዎን ብርሃኑ ነጋን ይምከሯቸው ። እንዲያው ከመሬት እየተነሱ ድርጅቱን ሁሉ ባይዘልፉት መልካም ነው በተለይ አርበኞች ግንባርን ። ለሁሉም በር ከፋች ነውና ፤ በር ከፋች ብቻ ሳይሆን የአርበኞቹን አባላት አገር ሳይሻገሩ ሸዋ መዝለቅ አይቻልምና ቢታሰብበትም መልካም ነው ፡ አርበኞቹም የዋዛ እንዳይመስሉዎ በአንድ ክልሽ ሽህ መትረየስ መመከት የሚያስችል ብቃት ያላቸው ጀግኖች አሉበትና እየተስተዋለ ። ገና አንድ ጥይት ያልተኮሰና መኖርና አለመኖሩ የማይታወቅ ህዝባዊ ሃይል የሚባል ነገር ፤ እርሾው እንኳ አራት አመት የፈጀና ገና ምንነቱ ያልታወቀ ሽል ይሁን ፅንስ ፤ ከመጠንሰሳችሁ ፤ ደም ፈሶበት አጥንት ተከስክሶበት የህይወት መስዋእትነት ተከፍሎበት እዚህ የደረሰን የአርበኞች ግንባር ጊዜውን ጠብቆ ይከስማል እያሉ ያላዩትንና የማያውቁትን ሲናገሩ ትንሽ እንኳ አልሰቀጠጣቸውምና ይምከሯቸው ። እንዲያውም ከሰሙኝ ጥፋቱ የርስዎ ነው እላለሁ አቶ አንዳርጋቸው ፤ ይህን ሲናገሩ ስብሰባው ላይ አጠገባቸው ሳይሆኑ አይቀሩም ብየ እገምታለሁ እና ምነው ዘለው አፋቸውን ቢይዙላቸው ኖሮ! ሌላው የእርስዎ ጥፋት ደግሞ ፤ መቼም ዶ/ሩ እንኳን በረሃውን አስመራንም አያውቋትም ፤ ለድርጅቱ የአስመራ አምባሳደር የዶ/ር ብርሃኑ ደግሞ ሪሞት ኮንትሮል ነዎትና ተገቢውን መረጃ ቢሰጧቸው ኖሮ ከስህተት ይታደጓቸው ነበር ። ብርሃኑ ይህን ብቻ አይደለም ያሉት ፤ በዛ በጦሰኛው የሚስጥር ቅጂ ላይ እንደሰማነው ፤ ሌላም ምኞት አላቸው ። ግንቦት ሰባት የፖለቲካ ሃይል ሆኖ ድምሕትን “ድሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይን” በወታደራዊ ሀይልነት የራሳቸው ጦር የማድረግ ምኞትም አላቸው ። እሳቸው ፖለቲካ ሰርተው ድምሕትን ፈረስ አድርገው እየጋለቡ ምኒሊክ ቤተ-መንግስት ሊገቡ ይመኛሉ ። ቢሆንልንማ በማን እድላችን እኔም ደስ ባለኝ ፤ ግን ብርሀኑ ነጋ የተመኙት ፈረስ ባለቤት አለው እየገራ እዚህ ያደረሰው ። አቶ አንዳርጋቸው አሁንም ጥፋቱ የእርስዎ ነው ፤ ለምን ቢሉ የፈረሱን ባለቤት መርጃዎች ለአለቃዎ መስጠት ወይም መንገር ነበረብዎ እንዳይሳሳቱ ! ተመልሼ እመጣበታለሁ ላሁኑ ፤ እንቀጥል …
ሌላው አባባልዎ እንዲህ ይላል አንዳርጋቸው ፡ በወታደራዊም ሆነ በፖለቲካው መንገድ መምራት የሚችለው የህብረተሰብ ክፍል የተለያየ ምክንያት እየሰጠ 22 አመት ሙሉ የርሱንም የህዝቡንም ባርነት ባራዘመበት ሁኔታ ነው የሚገኘው ብያለሁ ። ውጪአገር ተቀምጦ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ሆኖ የወያኔን መሰረታዊ ባህርይ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ የመረረ ትግል ለማድረግ ቆርጠው ሳይነሱ መሬት ላይ ሳይወርዱ አፈር ሳይበሉ አፈር ላይ ሳይተኙ ነፃነት በቀላሉ ሊገኝ አይችልም ። አዎ እውነት ተናግረዋል እዚህ ላይ ! ግን የ22አመታቱን የጥፋታችንን ወቀሳ ሲያወርዱብን ራስዎ የት እንደነብሩ አስተውለው ይሆን ? አንገት የተፈጠረው አዙሮ ለማየት ነው ሲባል አልሰሙም ? ወይስ 22አመታት ከናንተ ጋር ሆኜ ስመክራችሁ ስነግራችሁ አልሰማችሁም እያሉን ነው ። እኛ የምናውቀውና ከራስዎ አንደበትም የሰማነው ከትምህርት ቤት ጓደኛዎ መለስ ዜናዊ ጋር የኮለኔል መንግስቱ ኃይለ ፡ ማርያምን ኮፍያ ፍለጋ ቤተ መንግስት ገብተው የነበሩ መሆንዎን አይደለም እንዴ ? ፈጥረው አወሩብኝ እንዳይሉ ደግሞ ፤ በየቤታችን የሚገኘው የራስዎ መፅሃፍ ነው የነገረን ። ያኔ ታዲያ የኢትዮጵያን ህዝብ ለባርነትና ስቃይ አሳልፈው ሰጡትና ወያኔን አጠናክረው ወጡ ወይስ ለህዝባችን ችግሮቹን ሁሉ ቀርፈውለት ወደለንደን ተሰደዱ ። ሌላው እባክዎ በሞቴ አቶ አንዳርጋቸው ይቺን የላይኛዋን አባባልዎን ለዶክተር ብርሃኑም ይንገሯቸው ፤ አዎ መሬት ላይ ሳይተኙ መሬት ላይ ሳይወርዱ አፈር ሳይበሉ ስልጣን አይገኝም ይበሉልኝ ፤ የአምቡላንስ ሳይረን ብቻ በሚጮህበት ዋሽንግተን ዲሲ በአጃቢ መሄድም ለችግራችን መፍትሄ አይሆንምም ይበሉልኝ ።
የተማረው ሃይል ከአውሮፓም ከአሜሪካም ከአገር ውስጥም በበቂ ሁኔታ እየመጣልን ነው ብለዋል ። እዚች ላይ ጠያቂው Advocacy journalism” ስልት በመጠቀም ጥያቄውን ሲያመቻችልዎ ትግል ውስጥ እየገቡ ነው ? ሲል ያሟሙቅልዎታል ። አቤት ጥያቄው እንዴት እንደተመችዎ!.. ተረተሩልን ልበል ወይስ ቀደዱልን ነው የሚባለው በአራዳ ቋንቋ ። ይቀጥልና ጠያቂው እንዲህ ይላል ፦ ምንም ሃይል ኤርትራ ውስጥ ቢገባ ሻእቢያ የሚጠቀምባቸው ለማስፈራሪያ ነው እንጂ ምንም ፈቅ የሚል ስራ ሲሰሩ አይታይም የሚለውን የብዙዎች ስጋት ያነሳል ። ልክ ነው ለአመታት ኤርትራ በተመላለስኩባቸው ጊዜ ሁሉ የብዙው የውጪ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ ጥያቄና ስጋት ይኸው ነው ። እዚህ ላይ ነው ቀደም አድርጌ የገለፅኩት የፈረሱ ባለቤት ጉዳይ የሚመጣው ፤ ሻእቢያ ድ.ም.ሕ.ትን እየገራ ያዘጋጀበትን ምክንያት እኔ ልግለፅልዎ ። ድንገት የወያኔ መንግስት ባልተጠበቀ ሁኔታ ሸርተት ቢያደርገውና ቢወድቅ ሻእቢያ ከትግርኛ ተናጋሪው ድምሕት ጋር ትግርኛ ተናጋሪ ወታደሮቹን በማስገባት መጪውን የኢትዮጵያ እድል መወሰን የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ይመቸው ዘንድ ነው ። ለዚህም ነው ሻእቢያ የትግራይ ተወላጆች የሆኑትን የአርበኞች ግንባር ተዋጊዎች ከግንባሩ በግድ እያስወጣ ወደ ድምሕት እንዲገቡ ያስገደዳቸው ፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው ከትግራይ ተወላጆች ከአርበኞች ግንባር አንለይም ብለው አሻፈረኝ ብለው የቀሩ ። ስለዚህም ነው ድምሕት ከማንም እርዳታ ሳይኖረው በወታደራዊ ፤ በቴክኒካዊና ፤ በአደረጃጀት ደረጃ ከሌሎች ተሽሎ እንዲገኝ አድርጎ ሻእቢያ ያዘጋጀው ። ስለዚህ ድርጅቱ የሻእቢያ ፈረስ ነው ። ቀደም አድርጌ ዶ/ር ብርሃኑን ይምከሯቸው የሰው ፈረስ እንዳይመኙ ያልኩትም ለዚህ ነው ፤ የግሪክ ፔጋስ ፈረስና ድምህት አንድ ናቸውና ። ሻእቢያ ምኞታቸውን አይከለክላቸውም እንዲሳካላቸው ግን በፍፁም አይፈቅድም ።
ለዚህ ማስረጃ የሚሆነኝን በምሳሌ አስደግፌ ላስረዳ ፤ እንዲህ ሆነልዎ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ የሻእቢያን ድጋፍ ፍለጋ ከገቡት ሰዎች አንዱ ነፍሱን ይማረውና ኢንጅነር ቅጣው እጅጉ ነበር ። ኢንጅነር ቅጣው ኢብአግ ብሎ ለሰየመው ድርጅቱ የፖለቲካ ፕሮግራሙን አዘጋጅቶና አሳትሞ ነበር ኤርትራ የገባው ፤ ታዲያ ኢንጂነሩ ቀይ ባህርን ለማየት ምፅዋ ይወርዳል ፡ እዚያ ሲደርስ “ጉርጉሱም” ከቤተ መንግስቱ አጠገብ የሚገኘው የባህሩ መዋኛ ቦታ ላይ ለነበሩት ኤርትራውያን ሁሉ የፖለቲካ ፕሮግራሙን ማደል ይጀምራል ። ፕሮግራሙን ማደሉ ችግር አልነበረውም ፡ የፕሮግራሙ ሽፋን ገፅ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ካርታ ግን ኤርትራን የጨመረ ነበር ። የሻእቢያ ሰዎች ኤርትራ አሁን ነፃ አገር ናትና ይህን ካርታ ማደል አትችልም አላሉትም ፤ ምኞቱን ግን አልከለከሉትም ፡ ሆኖም በአይነ ቁራኛ ይከታተሉት ነበር ፤ በኋላ ላይ ከተወሰኑ አመታት በኋላ እኛ አስመራ ስንደርስ ደግሞ ፤ ይህንኑ ሁኔታ ማሾፊያ አድርገው ሲቀልዱበት ሰምቻለሁ ፤ ሌላ ሌላም ምሳሌዎች ማቅረብ ይቻላል ሻእቢያ ምኞት አይከለክልም ፤ ወደሌላው አባባልዎ ልሻገር አቶ አንዳርጋቸው ።
ጠያቂው እንዲህ ሲል ይቀጥላል ፤ ተቃዋሚዎች አስመራ መግባታቸው አዲስ ነገር አይደለም በተለይ ከወያኔ ኤርትራ ጦርነት 1990 ጀምሮ በኤርትራ ይንቀሳቀሳሉ ሆኖም ግን የትም ፈቅ አላሉም የትም መራመድ አልቻሉም ያ ያልሆነው በተቃዋሚዎቹ ድክመት ሳይሆን የኤርትራ መንግስት ስለማይፈቅድ ነው ፤ ዝም ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መንግስት ለማስፈራሪያ ብቻ ነው የሚጠቀምባቸው እንጂ ሻእቢያ ቢደግፋቸው ኖሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ይቻል ነበር ብለው የሚከራከሩ ሰዎች አሉ ፤በማለት ይጠይቅዎታል ። መቸም ከጥያቄዎቹ ሁሉ ድንቅ ጥያቄ ብየ የሰየምኳት ይህች ጥያቄ ናት ።
ወደመልስዎ እንምጣ እንዲህ ይላሉ ፤ “እኔ ኤርትራ ውስጥ ከአራት አመት በላይ ነው ፤ ከፕሬዚደንቱ አንስቶ እስከ ተራ ገበሬ ድረስ አስመራ ብቻ ሳይሆን በመላው ኤርትራ እየተንቀሳቀስኩ የኤርትራ ህዝብንም ሆነ መንግስትንም ፍላጎት ያየሁት ያለው በደንብ ነው የማውቀው ። እዚያ ቦታ ላይ የተፈጠረው ትልቁ ችግር ያለው የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ድክመት ነው ። ነገ ጠዋት እኛ ስራ መስራት ቢያቅተን ችግሩ እዛ ቦታ ላይ የተሰባሰብነው እኛ መሆናችንን ነው የማውቀው ኤርትራ መንግስት አይደለም ። ኤርትራ መንግስት መስዋእትነት እየከፈለ መስዋእትነት እየከፈለም በአለም አቀፍ ደረጃም gang up እየተደረገበት የተለያዩ ማእቀቦችም እየተደረገበት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች በእግራቸው ቆመው አገራቸው ውስጥ ያለውን አስከፊ የሆነ ስርአት እንዲያስወግዱ የቻለውን ሁሉ ያለው ፤ እያደረገም ነው ያለው። ነገር ግን ይህንን ድጋፍ ቅድም ባልኩት ችግሮች የተነሳ በሚገባ መጠቀም የሚችል የሰው ሃይል መመደብ ሳይችል ቀርቶ የነሱን ድጋፍ የነሱን ድካም ከንቱ ያደረገው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ራሱ ነው ። በነሱ በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ችግር የሌለበት ነው ። ሲሉ ጭፍን ያለ ውንጀላ በተቃዋሚው ላይ ካርከፈከፉብን በኋላ ስለሻእቢያ ቅድስና ደግሞ ምስክርነት ይሰጡናል ። እውነት እውነት እልዎታለሁ ራሳቸው ሻእቢያዎች የመደቡት የፖለቲካ ካድሬ እርስዎ ከዚህ በላይ የተናገሩትን እንዲናገር ግንባሩ ላይ ሽጉጥ ተደግኖ ቢገደድ እንኳ ደፍሮ አይናገረውም አሳፋሪ ስለሆነ ።
ለመሆኑ ስለነጌታቸው ሞት ያውቃሉ ፤ ስለ ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ ደብዛ መጥፋት ያውቃሉ ፤ አስመራ እንዳይገቡና በየትናንሹ ከተማ በቁም እስር ላይ እንዲቆዩ ስለተደረጉት ተቃዋሚዎች ያውቃሉ ፤ ከዘጠና ሰባቱ ምርጫ በኋላ ፤ ከኢትዮጵያ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ነቅለው የመጡት የዩኒበርሲቲ ተማሪዎች ዛሬ የት እንደደረሱ ያውቃሉ ፤ ሌላው ቢቀር በራስዎ ላይ በ2010 የመጀመሪያዎቹ ወራት የደረሰብዎን አይዘነጉትም ። እነዚያ ከማሰልጠኛ ጣቢያ እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው የመጡት የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይል እርሾ ይባሉ ከነበሩት ሁለት ሰዎች ፤ በእርስዎ ላይ ቂም እንደቋጠሩ እየታወቀ አስመራ መኖሪያ ቪላዎ ድረስ በሻእቢያ ትራንስፖርት ተሰጥቷቸው ነበር የመጡት ። በምግብና በኑሮ እየተጎዱ መሆኑን ሲገልፁልዎ እነሱን ማነጋገር ባለመፈልግዎና በመተበትዎ ፤ ሻእቢያ በሰጠዎ ቪላ ቤት ውስጥ ቀኑን ሙሉ እስረኛ አድርገው በጥፊ በመጠፍጠፍ ፤ ከአፈር ደባልቀው አሳርዎትን ካሳዩዎት በኋላ ኮፕዩተርዎን ሰብረው ኪስዎ ያገኙትን በኤርፖርት ሲገቡ (declare) ይፋ ያልተደረገ ዶላር ለሻእቢያ አስረክበው ፤ እርስዎም “እንዳ-ኮርያ” የሚገኘው “ሰምበል” ሆስፒታል አገግመው እንደወጡ የሁላችንም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ። ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ ይፈልጋሉ ስለሻእቢያ ተቃዋሚዎችን የማጋጨት ስራ ። ተቃዋሚዎች እንዳይተባበሩ የማደርግ ሴራ ። ኦነግ ውስጥ ስላለው የማጋጨት ስራም ቢሆን ሳይሰሙት የቀረ አይመስለኝም ። ምሳሌ ፤ ጀነራል ከማል ገልቹ ከአስመራ የማይነቃነቅ የቁም እስረኛ መሆኑንና ፤ አቶ ዳውድ ኢብሳ ደግሞ በፈለገው ጊዜ ወደ አውሮፓና ሌሎች አገሮች እንደልቡ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ምነው ዘለሉት ? ኤርትራ ለሚገኝ ተቃዋሚዎች የተመደቡት የኤርትራ ወታደራዊ ሌይዞን ኦፊሰሮች ተግባርስ ምንድነው ? ሊገልፁልን ይችላሉ ? አቶ አንዳርጋቸው ከዚህ ቀደም ከእርስዎ ጋር የሰሩ ሰዎች አንዳርጋቸው ዋሾ ነው እያሉ ሲናገሩ እሰማ ነበር ፤ ግን ይህን ያህል … ይህን ያህል ይቀጥፋሉ ብየ አስቤ አላውቅም ነበር ።
በነገራችን ላይ እንዲህ እያንዳንዷን የሚናገሯትን ነገር በጥንቃቄ አድምጬዎ አላውቅም ነበር ፤ ይገርማል ! ከፍተኛ የሆነ የአማርኛ ቋንቋ ችግር ይስተዋልብዎታል ። አንዳንዴ ቃላቶች ይምታታብዎታል ፤ አንዳንዴ ደግሞ አረፍተ ነገሮችዎ ስሜት የማይሰጡ ሆነው አገኛቸዋለሁ ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በአማርኛ ሃሳብዎን ሳይጨርሱ ወደሌላ ሃሳብ ይዘላሉ ። ይህ በሁለት ምክንያቶች እንደሚከሰት የጋዜጠኝነት ጥንቆላ ሳይሆን ትምህርቱ ያስረዳል ። አንደኛ ፤ ሰውየው በሚናገርበት ቋንቋ የሰዋሰው ችግርና የቃላት ጥርቅም ሲጎለው ሁለተኛው ደግሞ ሲዋሽ ነው ። የአማርኛ ቋንቋ ነገር ከተነሳ ስለ አለቃዎ ዶ/ር ብርሃኑም ይማስታውሰው አለኝና ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ ። አሁን ወደ ቃለ መጠይቅዎ እንዝለቅ ፤ ሻእቢያ ለኢትዮጵያ ሲል መስዋእትነት እየከፈለም ነው ሊሉ ይቃጣወታል ። እውነት እንዳው ሰው ያምነኛል ብለው አስበው ነው እንዲህ የሚሉን ። ሻእቢያ በምን ምክንያት ማእቀብ እንደተደረገበት አለም እያወቀው ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በሚያደርገው እርዳታ ሲሉን ትንሽ እንኳ አያሳፍርዎትም ? ወያኔስ ለኤርትራ ተቃዋሚዎች በግልፅ ይረዳ የለም እንዴ ምነው ማእቀብ አልተደረገበት? ሻእቢያ የመንግስታትን የተከበሩ ዲፕሎማቶች ጋጠ-ወጥ በሆነ መንገድ መዝለፍና ማዋረድስ ባህርይው አይደለምን ? ያስታውሱ ከሆነ ሻእቢያ ለምእራባውያኑ በምስራቅ አፍሪቃና በአካባቢው የጦር ሃይል ሆኖ ለማገልገል ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት ነበረው። ወታደሮቹንም ባስፈላጊው ቦታ ሁሉ በመላክ ምእራባውያኑን ለማገልገል ዝግጁነቱን ያሳየ ሃይል ነበር በጊዜው ፤ የነቢል ክሊንተንን ሞገስ ሁሉ አግኝቶ ነበር ። ትዝ ይልዎታል ከ1998ቱ እ.ኤ.አ በወያኔና በሻእቢያ መካከል ጦርነቱ ከመደረጉ በፊት በአሜሪካ መንግስት ይገፋ የነበረው shuttle diplomacy ሁሉ በኢትዮጵያ ኪሳራ ኤርትራን የመጥቀም አዝማሚያ ነበረው ። ይህ ሁሉ ሆኖ ሻእቢያ በራሱ ጥጋብና እብሪት እንዲሁም ባህርይ ምክንያት እንጂ ማእቀብ የተደረገበት ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሲል መስቀሉን ተሸክሞልን እንዳልሆነ አስረግጬ ልነግርዎ እወዳለሁ ። በአለማችን በየትኛው መለኪያ ነው አንድ መንግስት ራሱን ለሌላ አገር ጥቅም ሲል አሳልፎ የሚሰጠው ፤ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም ፤ ኤርትራ ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ስትል ማእቀብ ተጣለባት እያሉ ከሆነ የፖለቲካ ትምህርት ለተቃዋሚዎች ኤርትራ ውስጥ የሚሰጡት ፤ እንኳን የፖለቲካ መሪዎቹ ፤ተራ ተዋጊዎቹም አይቀብሉዎትምና ጊዜዎን አያጥፉ ፤ ወይም ዜግነቴን ቀይሬአለሁ ይበሉንና እንረፈው፤ ግልግልም ነው ።
ኢሳትን ወደኤርትራ ይጋብዛሉ አቶ አንዳርጋቸው ። ከተቃዋሚዎች ኤርትራ በመግባት የመጀመሪያዎቹ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የሆንኩት የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ወደ ኤርትራ የገባሁት በኤርትራ መንግስት ፈቃድ እንጂ እንደርስዎ ባለ የተቃዋሚ ፖለቲካ መምህር ተብየ ተጋብዤ አይደለም ፤ ተብየ ያልኩበት ምክንያት አለኝ በተረጋገጠ ማስረጃ የርስዎን የፖለቲካ መምህር አለመሆን ስለማውቅ ነው ።
ጠያቂዎን ኤርትራ ድረስ መጥቶ ዶኩመንታሪ ፊልም እንዲሰራ እንደ ኤርትትራ ሙሉ ባለስልጣን ይጋብዛሉ ፤ እንዴት ነው ነገሩ ምናልባት የኤርትራ ቪዛ መቺነት ስላጣን ተሰጥቶዎ ከሆነ በግልጽ ያስቀምጡልን ።
ቀጠል ያደርጉና እንዲህ ይላሉ አቶ አንዳርጋቸው ፡ “በኤርትራ ህዝብ ወስጥ በኤርትራ መንግስት ወስጥ ያለው አመለካከት ኢትዮጵያ ኤርትራን ኤርትራ ኢትዮጵያን በጠላትነት ፈርጀው አንዱ አንዱን ኪሳራ ውስጥ ለመጨመር በሚሄድበት መንገድ በዚያ አካባቢ ሰላምም መረጋጋትም እድገትም የሚባል ነገር አይኖርም የሚል እምነት ነው”። የማን እምነት እንደሆን አልገለፁትም እኮ ፤ አቶ አንዳርጋቸው ፤ ቀደም አድርጌ በተነተንኩት የቋንቋ ችግርዎ ምክንያት ይሆን ? እንዲህ የሚሆኑት ወይስ ስለሚዋሹን ። ይቀጥሉና “”ከኛ ጋር በምናደርገው ውይይት” ይላሉ የኢሳቱ እንግዳ “ከኛ ጋርም በምናደርገው ውይይት ወያኔን ለማዳከም በሚል ስሌት እዚህ ቦታ ላይ የምትመጡ ከሆነ ወይም ደግሞ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎችን የሚፈልጋቸው ወያኔን እንዲያዳክሙለት ነው በሚል እምነት ከሆነ የምታዩን ፤ ተሰብስባችሁ ወደ ፈለጋችሁበት መሄድ ትችላላችሁ ። ከኤርትራ ፕሬዚደንት ጋር በማደርገው ውይይት ነ……የ….. አሉ ። ምነው እዚህ ላይ አፍዎ ተያያዘሳ አቶ አንዳርጋቸው ፤ አንድ ያልሆነች ነገር ካፍዎ ሳይታሰብ ውልቅ አለች መሰለኝ ። የኤርትራው ፕሬዝደንትማ ይህን አይልም ! እኔ ብዙዎቹን የሚሏቸውን ሰዎች ሁሉ ከፕሬዝደንቱ በስተቀር ማለት ይቻላል ፤ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ የሚያገባቸውን ባለስልጣናት አነጋግሬአለሁ እንዲህ እርስዎ እንደሚቀቧቸው አይነት ቀለም አላየሁባቸውም ። ምናልባት እኔ ያልታየኝ ነገር ይኖር ይሆናል በማለት ቀድሞ ኤርትራን የጎበኙትን የማውቃቸውን ሁሉ ብጠይቅ እነሱም እንዳላዩባቸው እጄን እየመቱ ምለውልኛል ። ከኔ በኋላ ደብረ-ቢዘን ገዳም ተሰብስበው ገብተው ሱባኤ አድርገው ይሆን ? እመ-ብርሃን የአንድየ እናት ታርቃቸው ይሆናላ ። እንደርስዎ አይነቱን ሰዎች አይተው ኤርትራውያን ሲተርቱ እንዲህ ይላሉ “አዴካ ከም ዝላአከትካ ዘይኮነስ እዳጋ ከምዝፀንኽካ” ይቺ በኤርትራ ቆይታየ ከተማርኳቸው ተረቶች አንዷ ነች ። እንደምን ትተረጎማለች መሰለዎት ፤ “እናቱ ገበያ የላከችው ልጅ የተላከበትን ሳይሆን ገበያ ላይ ያጋጠመውን ገዝቶ መጣ” እንደማለት ነው ።
ኤርትራና ኢትዮጵያ በአንድ ሺህ አንድ ክር የተሳሰሩ ናቸው ያሉት አባባል ደግሞ በጣም በጣም እንደተመቸኝ ሳልገልፅልዎ አላልፍም ።
አዎ ኤርትራ ወስጥ እርስዎ እንዳሉት ዘርን ያማከለ ፖለቲካ የሻእቢያ መርህ እንዳልሆነ እኔም የምመሰክረው ነገር ነው ። እርስዎ አልነበሩም እንጂ የኤርትራ ቴሌቪዥን እያዘጋጀ ያቀርብ የነበረው አንድ ፕሮግራም ነበረው ስለ ኤርትራ ሲያቀርብ “ሕዝቢ ሃደ ልቢ” ይለው ነበር ለአንድነታቸው መሰረቱ የአንድ ልብ ልጆች መሆናቸውን መግለጫ ፕሮግራም ነበር ፤ ስለኢትዮጵያ የሚሰራውን ተመሳሳይ ፕሮግራም ደግሞ “የአንድ ባንዲራ ልጆች” ብሎ ሰይሞት ነበር ይህም በልባችን አንድነት የሌለንና ባንዲራችን ብቻ አንድ ያደረገን የብሄር ብሄረሰብ ጥርቅምነታችንን የሚገልጽ ፕሮግራም ነበር የቀረውን እንግዲህ ራስዎ ይፍቱት ።
ሻእቢያ ቀድሞ የነበረውን የቦታና የአስተዳደር ታሪካዊ አጠራር ሁሉ እየለወጠ ህዝቡን ወደአንድነት ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረት እመሰክራለሁ ። ይሁንና እኒም እንደርስዎ ሻእቢያ ትግል ላይ እያለ የዘር ፖለቲካ ለኢትዩጵያ እንደማይጠቅም ለወያኔ ይመክር እንደነበር ከባለስልጣናቱ ሰምቻለሁ ግን የተከራከሩበትና በውሳኔ ያሳለፉት አቋም እንደነበረ በግልፅ የሚያሳይ ፤ አንድም የሰነድ ማስረጃ አላሳዩኝም አልቀረቡልኝም ። በአንፃሩ መለስ ስለኤርትራ መገንጠል ያወጣቸው ማኒፌስቶዎች በሰነድ አሉ ። ዛሬ ላይ ቆመን ደሞ እንዲህ ብለን ነበር ቢባል ምን ዋጋ አለው ?
ኢትዮጵያውያን ፕሬዚደንት ኢሳኢያስን ግልፅ ቃለ-መጠይቅ አድርገውለት እንደነበር እርስዎም እኛም የምናስታውሰው ነው ፤ ታዲያ ራሱ ኢሳኢያስ እንኳ ፤ እንደርስዎ ሲቃ እየትናነቀው ስለ ኤርትራ የሰጡትን የጥብቅና ትንታኔ ፤ አላስቀመጠውም፤ ለኤርትራ ደግሞ ከሱ በላይ ነኝ እንዳይሉኝና እንዳያስቁኝ ። በኤርትራ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የፖለቲካ አስተማሪው ሆይ ! ለርስዎ ማስተማር አይሁንብኝና ፤ በዘመናዊው ህሳቤ አንድ መንግስት ትልቅነቱ የሚመዘነው የሚያስተዳድረውን ህዝብ ህይወት ለመለወጥ በሚሰራው ስራ ነው እንጂ እርስዎ እንደሚሉት የጣሊያን ኤምባሲን አንደኛ ፀሃፊ ከምፅዋ አስሮ አምጥቶ በኤርፖርት በኩል ስላባረረው ወይም የአሜሪካንን አምባሳደር በስድብ ስላዋረደውም አይደለም እንዲያውም ይህ ተስፋ የመቁረጥ ምልክት ነው።
የኤርትራን ህዝብ አኗኗርም አልነገሩንም ። ለመሆኑ የአስመራ ዳቦ ቤቶች ወረፋ የሚያዘው በስንት ሰአት ነው ? ለሊት ላይ ወጣ ብለው አይተውታል ? ምስኪን የሆኑ ሴቶች ከጠዋቱ አንድ ሰአት ለሚከፈት ዳቦ ቤት በዋዜማው ከምሽቱ አምስት ሰአት ጀምሮ አይደለም እንዴ ወረፋው የሚይዙት ። ደሞ ለምን ከዳቦ እንደጀመርኩም ልግለጽልዎ ። ለሰው ልጅ የመጀመሪያው ጥያቄ ዳቦ ነውና ፤ ዳቦ የቸገረው ህዝብ የአገሩ መንግስት ኮራ አልኮራ ጉዳዩ አይደለም ። ይህ ጎደለ ብሎ ለጠየቀ ኤርትራዊ ፤ የመንግስቱ መሪ እኮ “የጎረቤት አገር ቅልውጥ የለመዱ” ብሎ የራሱን ህዝብ የሚዘልፍበት ሁኔታ ነው ያለው ፤ ይህን አልሰሙ ይሆን ? አቶ አንዳርጋቸው ። በኢትዮጵያ ትግራይ “ሽመልባ” ውስጥ የፈሰሱትን ፤ በሱዳን “ሸገራብ” እና በሊቢያ “ሚስራታ” በግብፅ ሲናይ በረሃ በደቡብ ሱዳን “ጁባ” በዩጋንዳ ከካምፓላ ውጪ ያለው የስደተኛ ካንፖች ሁሉ በኤርትራ ወጣቶች እንደተሞሉ ያዩታል ። በአለም አቀፍ ሚዲያም የምንመለከተው ላስቲክ እየቀለጠ ሰውነታቸው የሚቃጠሉ ዜጎች እግራቸው በእግር ብረት የታሰሩና በግብፅ በሲናይ በረሃ በችጋርና በረሃብ አገራቸውን እየለቀቁ እንዲሰደዱ ያደረገን ሃገር መንግስት ነው በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው መንግስት ብለው የሚያሞካሹት ። ሴት ኤርትራውያንን ብቻ አይደለም ወጣት ወንዶች በየምሽቱ ከሱዳን የስደተኛ ካምፕ በሱዳን የጦር መኮንኖች እየተገደዱ እየተወሰዱ የሚፈፀምባቸውን የወሲብ ጥቃት እንዲደርስባቸው ያደረገና እነዚህ ወጣት ዜጎች በፈጣሪ የተቸራቸውን ህይወት አሰልቺ በሆነ ወታደራዊ አገልግሎት እንዲገፉና ፤ ለአገልግሎት የገቡበትን እንጂ የሚወጡበትን ዘመን በማያውቁበት ሁኔታ እንደባሪያ መገዛታቸው ነው መንግስታቸውን ታላቅ መንግስት የሚያደርገው? እነዚህ ወጣቶች ተስፋቸው ተሟጦ ተቸግረው ከሃገር በመውጣታቸው ፤ “ድርብ ጥርስ” ድሮም ዋጋ የለውም የሚል ቅፅል ስም የሚሰጣቸውን መንግስት ነው ኩሩ መንግስት የሚሉት ።
ስለ ሙስናው ደግሞ ሌላ ሌላውን እርስዎ ያተቱትን ትቼ አንድ ነገር ልንገርዎ ከነዚሁ ወጣቶች ጋር የተያያዘ ።መጠኑ ከሃገሪቱ ገቢ ጋር ይለያይ ይሆናል እንጂ ሙስናውማ እዚያም አለ ። ኤርትራ ውስጥ እንደሃገሩ ሁኔታ የሃብታም ልጆችና የድሃ ልጆች አሉ ። የሃብታም ልጆች ለወታደራዊ አገልግሎት ቢመደቡም ሁል ጊዜ አስመራ ናቸው ። ለምን መሰለዎ የሃብታሙ ልጅ ለወታደራዊ አገልግሎት ሃላፊው ቤተሰብ ፤ አስመራ ውስጥ ቀለብ እስከ ሰፈረ ድረስ “መንቀሳቀሲ” ወይም የመንቀሳቀሻ ወረቀት እየተፃፈለት ፤ ያለ አገልግሎት ከቤተሰቦቹ ጋር በሰላም ይኖራል ። በወራት አንዴ ብቻ ለአገልግሎት የተመደበበት ቦታ ደረስ ብሎ መመለስም በቂው ነው ። የኤርትራ ድሃ ልጅ ግን በእድሜ ዘመኑ መቼ እንደሚወጣ የማይታውቀው ገሃነብ ውስጥ ሲለበለብ ይኖራል ። ልቀጥል ወይስ ይበቃዎታል ፤ ኮራፕሽንማ የለም አይበሉን ፤ ይህን ጉዳይ ደግሞ እንደአስፈላጊነቱ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ ።
“የኤርትራ salvation የኤርትራ እንደሃገር የተጠናከረ ክብር ያለው የሚያድግ ሃገር ሆኖ ለመውጣት ኢትዮጵያ ወሳኝ ናት ብለው ያምናሉ በዚህ ደረጃ ነው ያለው” ። ይሉናል ቃለ መጠይቅዎ ላይ አቶ አንዳርጋቸው” እየነገሩን ያሉት ሌላ ፕላኔት ላይ ስላለች ኤርትራ መሪዎች ነው ወይስ ይቺ እኛ የምናውቃትን ኤርትራ መሪዎችን ነው ? ራሴን ማመን እስኪያቅተኝ ድረስ ነው የተጠራጠርኩት ። የማያልቅ ተንኮል የኤርትራ መንግስት እየጠነሰሰ ይላሉ በመቀጠል አቶ አንዳርጋቸው የሚቀጥልበት ሁኔታ ቢፈጠር ፤ የፈለከውን ያህል ጥረት ማድረግ ትችላለህ ፤ እንኳን አንድ ሃገር አይደለም አንድ የፖለቲካ ድርጅት ቆርጦ ከተነሳ ለአንድ መንግስት እንዴት ራስ ምታት እንደሚሆን እናውቀዋለን ። ሲሉ አቶ አንዳርጋቸው ሻእቢያ ምንም ተንኮል አይጠነሥሥም ለማለት ሲዳዳቸው አስትውያለሁ ? እንኳን በኢትዮጵያ ላይ አይደለም በርድጅት ሰዎች መሃከል እየገባ የሚጠነሠው ሴራ እርስዎን እስከመደብደብ እንዳደረሰዎ ከላይ ገልጫለሁ ። ሌላው ገጠመኜን ልንገርዎ ፤ የመጀመሪያው የኤርትራ ጉዞየ አቢይ አላማ ወያኔ ጋር እየተፋለመ ያሉውን የአርበኞች ግንባር አይቶ መምጣት ነበር ። እዚያ ስንደርስ አርበኞቹ ጋር ከመገናኘታችን በፊት የኤርትራ ወታደራዊ ሌይዞን መጥቶ እዚህ ከአርበኞቹ ጋር የደቡብ ህዝቦች እና የቤኒሻንጉል ነፃ አውጪ ድርጅት አባላትም ስለሚገኙ ፤ ንግግሮቻችሁ ላይ ጥቀሷቸው ብሎ ማሳሰቢያ ቢጤ ሰጥን ፤ ሰአቱ ደርሶ ንግግር ስናደርግ እኔ ስለማላውቃቸውና በተልእኮየ ስላልተካተቱ ድርጅቶች ባልናገርም ሌሎቹ እንግዶች ስማቸውን በቃሉ መያዝ ቢያቅታቸው በፅሁፍ እየያዙ ፤ ጠቅሰው ተናግረዋል ። በኋላ ላይ እንደተረዳሁት እነዚህ ድርጅቶች ምንም አባላት የሌላቸውና ለወደፊት ማምታቻ ሆነው የተቀረፁ ድርጅቶች ናቸው። የድርጅቱ መሪዎች ተብለው የተመደቡት ሰዎች ደግሞ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ላይ የተማረኩ ወታደሮች የነበሩና የድርጅት መሪዎች ሆናችኋል ተብለው ሳይፈልጉ የተገደዱ ሰዎች ናቸው ። ይህ ታዲያ ሴራ አይደለም ? አቶ አንዳርጋቸው እርስዎ ከሚሉት በእጅጉ ይጣረሳል ።
በዚህ አንደኛው ክፍል ቃለ መጠይቅ ላይ ስለፕሬዚደንት ኢሳኢያስ ሲናገሩ የጥንት ጓደኛዎ መለስ ስለኢሲያስ ያለውን ባእድ አምልኮ መሰል ሁኒታ ይገልፁና መለስን ካውገዙ በኋላ ወዲያው ሰከንዶች ሳይወስድብዎ እርስዎም እዚያው አይነት አምልኮ ወስጥ ገብተው ፤ ኢሳኢያስ በተራ መኪና ራሱ እየነዳ ፍሬቻ ቆሞ ሲያሳይ አየሁ ከተራ ሰዎች ጋር ተቃቅፎ ሲሄድ አይቸዋለሁ በጣም ትሁት ሰው ነው ሲሉ ይደመጣሉ ፡ ኢሳኢያስ ባይሆንስ ሌላ ሾፌር ላይ ከኋላ የቆሙ መኪናዎች ምን ማድረግ ነበረባቸው ። አንድ የሩሲያ ተረት አለ እንዲህ ይላል “ትንሹ አፕል ከትልቁ አፕል ጋር አብሮ ይወድቃል” አርስዎም መለስ ወደቁ ያሉበት ስፍራ ላይ አብረው ነው የወደቁት ። አንገት የተፈጠረው ………አሉ ። ሌላም አለ እርስ በርሱ የሚጣረስ አባባል ቃለመጠይቅዎ ላይ ስለመለስ ወንድሞችና እህቶች ጠላና ሳንድዊች ሻጭነት ጠያቂው ሲጠይቅዎ ፤ መለስ ማንነቱን ስትመለከት ግለኛ የሆነ ሰው ነው ለሌሎች ሰዎችም ጊዜ የሚኖረው ሰው አይደለም ፤ ይላሉ ፤ ኢሳኢያስ ግን እንደ አቡነ-አረጋዊ ቅዱስ ፤ ልጆቹን ከሁሉ እኩል የሚያይ ነው ለማለት ይቃጣዎታልና የሁለቱም አምባገነኖች ባህርይ አንድነቱን ቢያስረዱን ይሻል ነበር ለማለት ፈልጌ ነው ።
በቴሌቪዥን መስኮት ሳይዎ እጅጉን አምሮብዎታል ሊፈርጥ የደረሰ ኮሽም መስለዋል ፤ ያማረብኝ እስቱዲዮ ከመግባቴ በፊት ሜካፕ አድርገውልኝ ነው እንደማይሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ ። ታዲያልዎ አፈር ላይ የወረደ አፈር የበላ ሰው እንዲህ ካማረበት ወደኤርትራ በረሃ መውረድ ለሁላችንም ሳይጠቅም አይቀርም ብየ ለአንባቢዎቼ እንድመክር እየዳዳኝ ነው ። ግን እጠረጥራለሁ ኤርትራ እየተኖረ እንዲህ አበባ መምሰል የሚቻለው ፡ ለቁርስ “ምፅዋ ቁርስ ቤት” ለምሳ “ብሉ ናይል ሬስቶራንት” ለራት ደሞ “ካዛ ኢታልያኖ” ሬስቶራንት ውስጥ የሚያዘወትር ብቻ መሆን ይኖርበታል ። የማሽላ ቂጣ እየበሉ የሚታገሉትንማ እናውቃቸዋለን ፊታቸው ምን እንደሚመስል ።
በአጠቃላይ ይህን ክፍል አንድ የቃለ-መጠይቅዎን ፤ ስመዝነው የአሻእቢያ ታላቅነት የገዘፈበት ኢሳኢያስ አፈወርቂ የተሞገሱበት ፤ የድርጅትዎ ግንቦት ሰባት ስራዎች በአጠቃላይ ምንም ያልተወሱበት ፤ ራስዎ እየሰራሁት ነው ስለሚሉት ነገር ያወሩት ሁሉ ውሃ ያልቋጠረበት አመታዊ “የማስታገሻ መርፌ ውጋው” ሆኖ አግኝቼዋለሁ ። ምን ማለቴ መሰለዎ ማስታገሻ መርፌ ውጋው ስል ፤ ሰዎች ይታመማሉ ፤ ሲታመሙ ደግሞ መድሃኒት ይሻሉ ፤ በፀሎት ለሚያምን በፀሎትና በፀበል ድህነቱን ያገኛል ። ከዚህ ሌላ ደግሞ ወደ ዶክተር የሚሄድ የሚሰጠው መድሃኒት ይኖራል ። መድሃኒቶች ሁሉ ለበሽተኛው መፍትሄ ይሆናሉ ማለት ግን አይደለም ፤ እስከሚቀጥለው የህመም ስሜት ድረስ ግን ያስታግሳሉ። በሽተኛው አሁንም ሲታመም እንደገና መድሃኒት ይታዘዝለታል፤ የህመሙ ምክንያትም በዶክትሩ ይብራራለታል ። የህመም ስሜቱ እንደገና ያገረሸብህ ምናልባት ከሌሎች ሁኔታዎች ጋር በሽታህ ተወሳስቦ ይሆናልና ፤ መርፌ ልውጋህ ይልዋል ዶክተሩ ፤ በሽተኛውም መቀመጫውን ገልቦ መርፌ ይወጋል ፤ መቼም ጤናውንና አገሩን ያለ የማይሆነው የለም አይደል የሚባለው ። የኛም ነገር እንደዚሁ እንዳይሆን ሰግቼ ነው ። እንዴት መሰለዎ በየአመቱ እርስዎ በኢሳት መስኮት ብቅ እያሉ የማስታገሻ መርፌ እየውጉን እየሄዱ መሆኑን በማስተዋሌ ነው ። በሁለተኛው ዙር ቃለ-መጠይቅዎ ላይ እንገናኝ ሰላም ያገናኘን ። ሰላም ይሁኑልኝ !
ጥያቄ ስላቀረበልዎ ጋዜጠኛ ትዝብት ፡
1) ታማኝ በየነ ከዚህ በፊት ኢሳኢያስ ፤ የበየነ ጴጥሮስን ወንድም እንዲለቀው መጠየቁንና ፤ ምላሽ አለማግኘቱን 2) ከካናዳ ወደ አስመራ ተጉዘው የነበሩት ካህን ፤ የኤርትራ ባለስልጣናትን አነጋግሬ ኢትዮጵያዊ እስረኞችን በሙሉ እንፈታለን ብለው ቃል ገብተውልኛል ያሉት ፤ ጉዳይ እንደተነጠለጠለ መቅረቱን 3) የነኮለኔል ታደሰን ደብዛ መጥፋት ሳያካትታቸው መቅረቱ ፤ በተለይ ከፕሬዝደንቱ ጋር ቅርብ ግንኙነት አለኝ ያለውን ሰው አግኝቶ ፡ ለፕሬዝደንቱ ይህን አንስተህባቸው ነበር ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢነት ነበረው ፤ ምንም ይሁን ምን በኤርትራ ስቃይ ላይ የሚገኙት ሁሉ ኢትዮጵያውያን ናቸውና። በተለይ በወያኔ አፈና ደርሶብኝ መጣሁ የሚል ፤ ይህን አለማንሳቱ ፤ መለስና ወያኔ ኢቲቪን በቅንብር ከሚጠቀሙበት ጋር ስለተመሳሰለብኝ “ኢሳት የህዝብ አይንና ጆሮ ነው” ከሚለው ጋር እንዳይጣረስ ስጋቴን መግለፅ እወዳለሁ ።
Email: [email protected]