የኢትዮጵያ መንግሥት ቦንድ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


(ሳ. ግርማ)

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች የሰሞኑ አሰልቺ ሙዚቃ “ቦንድ፣ ቦንድ፣ ቦንድ” ሆኗል:: የገንዘብ እና የንግድ አስተምሮት እምብዛም ባልጠናበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ማኅበረሰብ ውስጥ መደናገር ቢበዛ አይደንቅም:: ስለዚህም ጊዜው የመረጃ እንደመሆኑ ለራሴ ግንዛቤ ለመጨበጥ ይረዳኝ ዘንድ አስተማማኝ የሆኑ የመረጃ ምንጮችን ፈተሽኩ::ለራስ አውቆ ለሌላው አለማካፈልን ስላልወደድኩት ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ እንደሚከተለው ከትቤ እነሆ ብያለሁ:: “እውነት ግን ቦንድ ምንድነው?” ከሚለው ጥያቄ እንጀምር።

Millennium Dam

ይህን ጥያቄ ለመመለስ ከመሞከሬ በፊት እንደዚህ አይነት እንግዳ እና መጤ ቃላት በኅብረተሰባችን ውስጥ ለፖለቲካም ይሁን ለሌላ ማደናገሪያነት እንዴት እንደሚያገለግሉ ያሳይ ዘንድ እውቁ የኮሜዲ ሰው ተስፋዬ ካሳ በአንድ ወቅት ያካፈለንን ጨዋታ ለመንደርደሪያ ማስታወሱ አይከፋም። ምናልባት ቀልዱን ቃል በቃል ላላስታውስ እችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ መሠረታዊው መልዕክት ግን እንዳለ ነው::

ሰውዬው በሰፈሩ ባለሥልጣን ወይም የአንድ ፕሮጄ መሪ ብጤ ይመስለኛል:: ‘የሰፈሩን ሰው ሰብስቦ “ፈንዱ” አዲስ መንገድ ይሠራላችኋል:: “ፈንዱ” አዲስ ትምህርት ቤት እንዲኖራችሁ ያስችላችኋል:: “ፈንዱ” አዲስ ጤና ጣቢያ ያሠራላችኋል::…’ እያለ የ“ፈንዱ”ን ጥቅም ወይም አስፈላጊነት ይደሰኩራል:: ታዲያ ይሄኔ ነው አንዲት የሴት አዛውንት እጃቸውን ለጥያቄ ያነሱት:: እንዲህም ሲሉ ጠየቁ “እንደው ለምሆኑ ካልፈነዳን በቀር ይህ ሁሉ የምትለን ነገር አይሆንም ማለት ነው ወይ?” ብለው ጠየቁ ብሎ ጨዋታውን በዚህ ደመደመ:: አቤቱ የተስፋዬን ነፍስ ማር! መቼም “ቦንዱ”ም የ“ፈንዱ”ን ያህል ብዙዎችን ሳያደናግር ብዙዎቹንም ሳያሰለች አይቀርም ባይ ነኝ::

መንግሥታት የሚከተሉትን የፖለቲካ ስርዓት ሳልጠቅስ የግል እና የወል ንብረት ማፍራትን የሚፈቅዱ ሲቀጥልም እንደ ስቶክ ማርኬት እና ቦንድ ማርኬት የመሳሰሉ የገንዘብ እና የንብረት ባለቤትነትን እና መገበያየትን ከዚህ ጋር ተያይዞም ዝውውርን የሚያስችሉ የገበያ ስርዓቶችን በዘረጉ አገራት ውስጥ ቦንድ እንግዳ ነገር አይደለም:: በዘርፉ ቋንቋ የጋራ ባለቤትነት የሚገለጽበት ቃል ሴኪዩሪቲ (Security) ይባላል:: በዋናነት ሦስት አይነት የወል አንዳንዴም በግል የንብረት ባለቤትነት የሚገለጹባቸው የሴኪዩሪቲ አይነቶች አሉ:: እነርሱም ስቶክ (Stock)፣ ቦንድ(Bond)፣ እና ዴሪቬቲቭ (Derivative) ይባላሉ:: (እነዚህ ቃላት አቻ የአማርኛ ፍቺ እንዳላቸው አላውቅም:: ምናልባት በሰፋ ዝርዝር ለማየት ለፈለገ ሌሎች በቁጥር የበዙ የሴኩዩሪቲ አይነቶች ሞልተዋል:: ከነዚሁም ውስጥ treasury notes, treasury bills, debentures እያለ ይቀጥላል::)

የጽሑፌ ዋና አላማ ቦንድ እንደመሆኑ ሐሳቤን ወደ ቦንድ ልመልስ እና ጽሑፌን ልቀጥል:: ከሴክዩሪቲ አይነቶች ውስጥ ቦንድ የቋሚ ገቢ (fixed-income security) ሴክዩሪቲ አይነት ሲሆን ከሦስቱ የንብረት አይነት መደቦችም (Asset classes) ውስጥ አንዱ ነው:: ሌሎቹ ሁለቱ ደግሞ ስቶክ (Stock) እና “የገንዘብ አቻ” (Cash equivalents) ተቀማጭ ገንዘብ ወይም ገንዘብን ሊተኩ የሚችሉ እንደወርቅ አይነት የንብረት መደቦች ናቸው:: ቦንድ ማለት በግርድፉ ሲፈታ የ’አለብኝ’ ስምምነት ነው:: ይህም ማለት ቦንድ የሚሰጠው ወይም የሚሸጠው አካል ለገዢው ሰው “ይህን ያህል እዳ አለብኝ” (በእንግሊዘኛው I owe you እንደሚባለው ማለት ነው) ብሎ እንደ ማስረጃ የሚሰጠው ማስረጃ ነው:: ቦንድ ገዢዎች ማንኛውም ትርፍ ፈላጊ ኢንቨስተር ሲሆኑ፤ ቦንድ ሻጭ ደግሞ በኩባንያ ደረጃ የሕግ እውቅና የተሰጠው አካል ወይም አንድን አገር የሚያስተዳድር መንግሥት (መንግሥት ሲባል የክልል እንዲሁም የማዘጋጃ ቤት መንግስታትንም ይጨምራል) ሊሆን ይችላል:: ቦንድ ሲሸጥ ለአንድ ሁነኛ ፕሮጀክት ወይም ለተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሊሆን ይችላል:: ቦንዱን የሚሸጠው ወይም የሚሰጠው አካል ቦንዱን ሲሸጥ የሚኖረውን ወለድ (coupon/interest rate) እንዲሁም ቦንዱ የተገዛበትን ዋና የገንዘብ መጠን (Bond principal) እና የሚመለስበትን ጊዜ በግልጽ ማሳወቅ ይኖርበታል:: ይህም ጊዜ “የመብሰያ ጊዜ” (Maturity date ) ተብሎ ይታወቃል ::

ቦንድ በራሱ እንደ ቦንድ ሻጩ አይነት እና እንደሚከፈልበት ጊዜ (maturity duration) ርዝመት የተለያየ አይነት ስያሜ አለው:: ከእነዚህ ውስጥ በማዕከላዊ ባንኮች የሚሰጡ/የሚሸጡ እንደ “የግምጃ ቤት ሰነዶችን” (Treasury bills/Treasury notes) የመሳሰሉትን ማንሳት ይቻላል:: ቦንድ በደፈናው ከስቶክ ማርኬት አይነት የንብረት መደቦች ጋር ሲነጻጸር አስተማማኝ የገንዘብ ማቆያ መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል:: ይህ ማለት ግን ሁሉም ቦንዶች እኩል ዋስትና አላቸው ማለት አይደለም:: ለምሳሌ የአሜሪካን መንግስት ማዕከላዊ ባንክ የሚሸጣቸው/የሚሰጣቸው የቦንድ አይነቶች በጣም አስተማማኝ በመሆን ይታወቃሉ:: ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት የአሜሪካን መንግሥት ሁሌም ቢሆን ቋሚ ፣ ጠንካራ እና በማይነቃነቁ የዴሞክራሲ መሠረት ላይ የተተከለ ስለሆነ፣ ዛሬ ያለው መንግሥት የተበደረውን (ቦንድ ማለት ብድር መሆኑን አይዘንጉ!!) ተከታታይ መንግሥታት የመክፈል ግዴታውን ማክበራቸው ስለማያጠራጥር ነው:: ሌላው ምክንያት ደግሞ የተበዳሪዎችን ብድር የመክፈል ደረጃ የሚያወጡ ገለልተኛ የገንዘብ ተቋማት ደረጃ መዳቢዎች (Credit rating agencies) የአሜሪካ መንግሥትን ብድር በመመለስ የባለ ሶስት ኮከብ ታላቅ ደረጃ ስለሚሰጡት ነው:: ምናልባት እንኳን አሁን እየሆነ እንዳለው የአሜሪካን መንግሥት ገንዘብ ቢያጥረው መቼም ቢሆን ታክስ ከፍ በማድረግ እዳውን መክፈል እንደሚችል ስለሚታወቅ ሰዎች የአሜሪካን መንግሥት ማዕከላዊ ባንክ የሚሰጠውን/የሚሸጠውን ቦንድ በመግዛት ሃብትን ለወደፊት፣ ለክፉ ጊዜ፣ ወይም ለጡረታ እና ለልጆች ከፍተኛ ትምህርት ያኖራሉ::

እንደውም የአሜሪካን አገር ፖለቲካን ልብ ላለ ሰው የሰሞኑ የፖለቲካ ጭቅጭቅ የአገሪቷን የብድር ጣሪያ ከፍ በማድረግ እና ባለማድረግ ላይ ነው:: ክርክሩም በፖለቲካ ፍልስፍናቸው ከፕሬዚዳንቱ ወገን ባሉ እና ጣራው ከፍ መደረግ አለበት (ጣራው ከ14 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ነው) የሚሉት ወገኖች የሚያነሱት መከራከሪያም “ይህ ጣሪያ በጊዜ ከፍ ካልተደረገ የአሜሪካን የብድር ነጥብ (Credit score) ይጎዳል:: ወደፊትም ማዕከላዊ መንግሥቱ ብድር በየትኛውም መንገድ ቢፈልግ ለማግኘት ይቸግረዋል : ስለዚህም ጣራውን በጊዜ ከፍ ማድረግ አለብን” የሚል ነው፤ በሌላው ወገን ያሉት ሪፐብሊካኖች ደግሞ “የለም መንግሥት የሚያጠፋውን የገንዘብ መጠን ካልቀነሰ እና ወጪ የሚያስወጡ መርሃ ግብሮችን ካላጠፈ የብድር ጣሪያውን ከፍ አናደርግም” የሚል ነው::

የኢሕአዴግ ቦንድ

አሁን ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት ቦንድ ልመለስ። የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጣው ቦንድ የ5፣ የ7 እና የ10 ዓመት የመብሰያ ጊዜ (Maturity date) ያላቸው ሲሆኑ የወለድ መጠናቸውም እንደቅደም ተከተላቸው 4%፣ 4.5% እና 5% ነው (በ1% የወለድ መጠን ልዩነት ብቻ የ10 ዓመቱ ቦንድ ከ5 ዓመቱ ቦንድ እንዴት የተሻለ ሳቢ ኢንቨስትመንት (attractive investment) ሊሆን እንደሚችል አልገባኝም!!!):: እንደ ማንኛውም ኢንቨስትመንት ቦንድም የራሱ የሆኑ የአክሳሪነት ወይም የአትራፊነት እጣ እድል አለው:: ምናልባትም ያሉትን የአክሳሪነት አደጋዎችን እዚህ በመዘርዘር እጅግ አስፈላጊ ነው።

Millennium Dam coupon

አንዱ የቦንድ አደጋ (Bond risk) የወለድ ምጣኔ መዋዠቅ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ይሄ በጣም ሲበዛ የሚከስት እና አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ ነጻ ባልሆነ እና በህወሃት የፖለቲካ እሽክርክሪት ስር ያለ ማዕከላዊ ባንክ ባለበት ሁኔታ መሆኑ የአደጋውን (Risk level) ደረጃ ከፍ ያደረገዋል:: መንግሥት የሚሸጠው ቦንድ ዋጋ ምን ያህል ከወለድ ምጣኔ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ምንም የሰጠው መረጃ ባለመኖሩ ያለዚህ መረጃ እንዴት ሰዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለመጠየቅ እንደደፈረ የሚደንቅ ነገር ነው:: ይሄ ነገር በብዙዎች እንደተገመተው የፖለቲካ እይታን ለማንሸዋረር ወይም ገንዘብ ለማግበስበስ በአጭር ጊዜ ብዙም ሳይታሰብበት የተጀመረ ለመሆኑ አንድ ማስረጃ ሊሆን ይችላል:: ወለድ ሁለት አይነት ነው፤ ይኸውም የአገር ውስጥ የገንዘብ ወለድ ምጣኔ ሲሆን ከውጪ አገር በሌላ አገር ገንዘብ ለሚገዙ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ምጣኔም (Exchange rate) ሌላ ተጨማሪ አደጋ ወይም እድልንም ሊሰጥ እንደመቻሉ የቦንድ ግዢ ውሳኔ ስሌት ውስጥ ማስገባት ግድ ይላል::

ሌላው አስተውሎት የሚፈልግ የቦንድ ሁነኛ አደጋ ደግሞ የዋጋ ግሽበት ነው። ይህም አሁን ቦንዱ በተገዛበት ወቅት ያለው የገንዘብ ዋጋ እና ቦንዱ የመብሰያ (Maturity date) ጊዜው ደርዶ በገንዘብ ሲለወጥ ያለው የመግዛት አቅም ሲነጻጸር የሚኖረውን ልዩነት ማለት ነው:: አሁን ያለውን የዋጋ ግሽበት ላስተዋለ ሰው እና ለምሳሌ ከአምስት ዓመት በፊት 500 ብር ሊገዛ የሚችለውን ነገር እና ዛሬ ላይ 500 ብር ሊገዛ የሚችለውን በማወዳደር፣ ከዚያም ተነስቶ ከዛሬ ላይ ወደፊት አምስት ዓመት በመሄድ 500 ብር ሊገዛ የሚችለውን ነገር ወይም ሊኖረው የሚችለውን የመግዛት አቅም በማገናዘብ መረዳት ይቻላል:: አሁን ባለው መንግሥት ባመነው እና በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን ባወጣው የዋጋ ግሽበት አሃዝ የ25% የዋጋ ግሽበት አለ። በዚህ ስሌት ብቻ አንድ ቦንዱን የገዛ ሰው በቦንዱ የመብሰያ ጊዜ (maturity date) የዋጋ ግሽበትን ተከትሎ በሚፈጠር የመግዛት አቅም መውደቅ ምክንያት አብዛኛውን የገንዝቡን መጠን ሊያጣ እንደሚችል ግልጽ ነው።

ብድር ያለመክፈል (Credit/Default risk) አደጋ ሌላው የዝርዝሩ አካል ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት “የምከፈለው ብር አቅም የለኝም” ካለ የለኝም ነው:: ምን ታረገዋለህ/ታረጊዋለሽ?! ቦንድ ምንም ማስያዣ (Collateral) የሌለው የብድር አይነት ነው:: እንደ ኢትዮጵያ ሕግና ፍርድ ቤት የገዢዎች መቀለጃ በሆነበት አገር ወደ ፈጣሪ እንባን ረጭቶ ዝም ከማለት የተለየ አማራጭ ማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል። አለቀ ደቀቀ::

ሌላው እና ሊሆን የሚችለው አደጋ የሊኩዊዲቲ (Liquidity) አደጋ ሲሆን ይህም ፕሮጄው ከእነአካቴው አክሳሪ እና የማያዋጣ ሆኖ የመገኘቱ ጉዳይ ነው:: ለመሆኑ ቦንዱን የሚገዙ ዝርዝር የአዋጭነት ጥናት (Feasiblity study) አይተዋልን? ፕሮጀክቱ አዋጭ ነው ወይ? ምናልባት ሁለት ዓመት ከተሰራ በኋላ የፕሮጄ ወጪው በፍጹም ሊያዋጣ የማይችል ሆኖ ቢገኝስ? ቀጣይነቱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ቢገባስ? ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ነገር ጀምሮ ማቆም ብርቅ አይደለም:: የጣና በለስ እና የአልዌሮ ግድቦች በምሳሌነት ይወሳሉ:: ሌሎች የብድር ደረጃ ማቆልቆልን (Rating downgrades) የመሳሰሉ አደጋዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ሲጀምርም የብድር ደረጃ ስለሌለው እምብዛም አይመለከቱትም::

ከመንግሥት ቦንድ መግዛቱ ጥቅሙም ሆነ ክፋቱ ምኑ ላይ ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ልሞክር:: አንድ በፌስ ቡክ ላይ በወዳጅነት ፖለቲካ የምናወጋ ወዳጄ ቦንዱ እየተሸጠለት ያለው ግድብም ሆነ ቦንዱ እራሱ በኔ እምነት ለጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ የመጡ አዲስ ስልቶች መሆናቸውን ለማስረዳት እና ምንም እናኳን ቦንዱን የመዛግትም ሆነ ያለመግዛት የመጨረሻ ውሳኔ የግል ቢሆንም እኔ የመሰለኝን ሃሳብ ሳስረዳ ምን አለችኝ መሰላችሁ:: “ቀነኒሳ በቀለ እንኳን ቦንድ ገዝቷል።” ነገርዬው ፈገግ አደረገኝ:: እኔም ለጠቅ አድርጌ “ታዲያ ቀነኒሳ ከመቼ ጀምሮ ነው የዎል ስትሪት ባንከር የሆነው ብዬ?” ለምላሹ ሌላ ጥያቄ ሰነዘርኩ:: መቼም ነገሩ ፕሮፖጋንዳ አይደል? ቀነኒሳ ስለገዛ አንተም፣አንቺም ግዛ ነው ነገሩ:: ለነገሩ ቀነኒሳ ምናልባት አውቆትም ይሁን ሳያውቅ ዛሬ በዚህ ቢከስር ነገ ሮጥ ብሎ ብር ሊያመጣ የሚችልበት አቅምም በገንዘብ ሊሸጥ የሚችልም ስም ስላለው ለሱ ብዙም ሊያሳስበው አይችል ይሆናል:: ለእንደ እኔ አይነት ብዙኀን ለፍቶ አዳሪዎች ግን ደግመው ደጋግመው አስበው ሊያደርጉት የሚገባ ውሳኔ ነው::

እስቲ አስቡት የኢትዮጵያ መንግሥት ኤልክትሪክ እሸጣለሁ ካለ ይኸው ስምንት ዓመት አለፈው:: ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው ከእንግዲህ ወዲያ ከተራ ዜጎች ገንዘብ ሰብስቦ ግድብ ሰርቶ ከዛ በኋላ ችስታ ለሆኑ ሌሎች ጎረቤት አገሮች ኤሌክትሪክ ሸጦ ከዛ በኋላ ከነወለዱ ለእኛ በጊዜ ገንዘባችንን ሊመልስ የሚችለው? ከኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቦንድ ቢገዙ ገንዘቡን ከማጣት በላይም (አዎን ይህ ሊሆን የሚችል ነገር ነው) ገንዘብ ሰዶ እንግልት ማምጣት ይኖራል:: ቤት ሰርተው ያከራዩ ሰዎች እንደ ወንጀለኛ አሻራ አምጡ እየተባሉ ሲንገላቱ ይኸው እያየን አይደል! ከሥራ ፈቃድ ወስደው ከአሜሪካ ኢትዮጵያ ድረስ አሻራ ለመስጠት ሄደው የተንከራተቱ ሰዎችን በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ላይ እሮሮ ሲያሰሙ ማድመጤን አስታውሳለሁኝ:: በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁኝ ማለት ይህ ነው::

ነገሬን ለማጠቃለል እንደ ኢሕአዴግ የመሳሰሉ በሕዝብ ውክልና የሌላቸው መንግሥታት ዕድሜ መተንበይ አዳጋች በሆነበት በዚህ ወቅት ለታማኝነት ብዙም ዝና ከሌለው መንግሥት ጋር የገንዘብም ሆነ ሌላ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ውል መዋዋል የኢኮኖሚ አስተዋይነት (Economically prudent) አድርጌ አልወስደውም::