­

እንዲህም ተኑሯል…(የአንድ መድረሻ ቢስ ስደተኛ ሕይወት…)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


(ካሳሁን ይልማ)

የአሸዋው ጉም ላንድ ክሩዘሯን እንደ ሸራ አልብሷታል።  40 ዲግሪ ሴልሺየስ የሚጠጋው ሙቀት እንደ ዕቃ ተጠቅጥቀው የተጫኑትን ተሳፋሪዎች ትንፋሽ አሳጥሯቸዋል። አንዳቸውም ከሌላ ጋራ አይነጋገሩም። በረኀውን ሰንጥቆ እንደ ምንጣፍ የተዘረጋው አስፋልት የት እንደሚያደረሳቸው በማሰላሰል አዕምሮአቸውን ያስጨነቁ ይመስላሉ። ለሰዒድ ሐጎስ ግን እንዲህ ያለ ጉዞ አዲስ አይደለም።

ወጣትነቱ ያለፈው ሲኳትን ነው። ቢሆንም የአሁኑ ለየት ይላል።  በዕድሜ ዘመኑ ከወሰናቸው ሁለት ከባድ ውሳኔዎች አንዱ ስለመሆኑ ጥርጣሬ የለውም። በለጋ እድሜው በትውልድ ቀየው ጠግቦ ሳይጫወት የአካባቢው ታላላቆቹ የፈጸሙት ጀብዱ በየጓዳው ሲነገር እርሱም ከእነርሱ አንዱ ለመሆን ጫካ ገብቷል፤ ለኤርትራ “ናጽነት።” ዛሬ ደግሞ ለራሱ ነጻነት።

ከመኪናው ፍጥነት እና ከመንገዱ ርቀት  እኩል የቀድሞውን ማሰብና ማሰላሰሉን አላቋረጠም። የወጣትነቱ ድካም ሁሉንም እንደዋዛ ርግፍ አድርጎ ጥሎ ሌላ የሕይወት ፍልሚያ ለመጋፈጥ መዘጋጀቱ በፍርሀት ቢያስውጠውም የተነሳለት ዓላማ ብርታት ሆኖታል።

ሰዒድ ተወልዶ ያደገው  ኢትዮጰያ ውስጥ ነው፤በዛሬው አፋር ክልል።  አባቱ ደግሞ  በግብርና እና አነስተኛ ንግድ ሳሆ ይኖራሉ-ኤርትራ። ወደ እነ ሰዒድ እናት ቤት የሚመጡ እንግዶች ሰለ አባቱ  መልካምነት እና የተሻለ ኑሮ ሲያወሩ ሰምቶ አባቱን ለመቀላቀለ  ልቡ ተነሳ።  “የምወዳት እናቴን ሳልሰናበት ተደብቄ ጠፋሁ “ይላል። በዚያው  ከእናቱ እንደተለየ ቀረ።

አባቱም የሚነገርላቸውን ያህል የተደላደለ ኑሮ ባይኖርቸውም  ኑሯቸው ስዒድን “ባልመጣሁ” የሚያስብል አልነበረም።  በደስታ እንባ ተቀብለው ከንግድ ጋር አስተዋወቁት። ሸቀጣ ሸቀጥ ቀረብ ብለው በሚገኙ ከተሞች ይነግድ  ጀመረ። የአባቱ ጥላ ሆነ። አባቱን በጎረምሳ አይደክሜ ጉልበቱ እያገዘ ሳለ  ኤርትራን ነጻ ለማውጣት ጫካ ገብተው ብረት ስላነሱ  የአካባቢው ወጣቶች ወሬ ይሰማል። ጓደኞቹ  አንድ አንድ እያሉ የሻቢያን ጦር ሲቀላቀሉ የእርሱም ልብ ሸፈተ። በድንገት የተገናኛቸውን አባቱን በድንገት ጥሏቸው ሄደ።

ሰዒድ  የትግል ሕይወት እንዳሰበው አልጠበቀውም። ልጅ ቢጤ  ስለነበር  ቶሎ ጥንካሬ ማግኘት አልቻለም።  ወደ አባቱ መመለስ ደግሞ በፍጹም የማይሞከር  ነበር።  “ከእናቴ ተለይቼ ወደዚያ ምድር የመጣሁበትን ቀን የረገምኩት እና የተጸጸትኩት ያኔ ነው። ይሁን እንጂ የግዴንም ቢሆን ከትግል ሕይወት ጋራ ተላመድኩ “ይላል። ”እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ የተሻለ ሕይወት የምናገኘው ከኤርትራ ነጻነት በኋላ እንደሆነ አዕምሮዬ አምኖ ተቀበለ።”

1983ዓ.ም። ጦርነቱ ሻእቢያ አስመራን፤ወያኔ አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ ተጠናቀቀ።  ኤርትራም ተገነጠለች። ሰዒድም ወላጆቹን በይበልጥ አራራቀ – እናት ኢትዮጵያ ፣ አባት ኤርትራ። ኤርትራ እንደ ሀገር ከቆመች። በኋላም አንዳንድ ተዳፍነው የቆዩ ጥያቄዎች ያቃጭሉብት ጀመር። “ራሴን መቼ ነው ከታጋይነት በላይ ከፍ አድርጌ የማየው” የሚል።

ከነጻነት በኋላ በነበሩት ሁለት እና ሶስት ዓመታት እነዚህ ስሜቶች አልነበሩትም።  “ኤርትራ እንደሀገር መንቀሳቀስ ስትጀምር  የኑሮ እና  የሥራ እድገት ፈለግሁ። ሆኖም ግን የእኔ ሐሳብ እና እውነታው ለየቅል ሆነ። ከበረኅው ሕይወቴ የሚለየው ጥይት አለመተኮሴ እና ነገ እሞት፤ ዛሬ እሞት የሚለው ስጋት መጥፋቱ ብቻ ነበር።”  ከ”ናጽነት” በኋላ ስሙ ወደ  “ይክኣሎ” (ሁሉ ይቻላዋል) ከመለወጡ በስትቀር ጠብ  ያለለት  ነገር አልነበረም።  ኢትዮጵያ  ትቷቸው የሄዱት እናቱ የት እንደሚኖሩ አያውቅም። አሁን  እናቱን ስለ ማግኘት ማሰብ ይዟል።

የሰዒድ ጥያቄዎች ሳይመለሱ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የድንበር ጦርነት ትኩስ ዜና ሆነ። የ“ይክአሎ” ( ሁሉ ይቻላዋል፣ ምን ይሳንዋል) ጦር ከዋርሳይ ( ወራሼነህ-የሳዋ ስልጣኞች) ጀርባ በተጠንቀቅ እንዲሆን ታዘዘ። እርሱም ሰንዓፌ ላይ ግዳጁን ሊወጣ ተሰለፈ። የጥይትን ድምጽ እንደዚያ በጋመ ሁኔታ ከሰማ ስምንት ዓመታትን አሳልፎ ነበር።ውትድርና ሞያው ሆኖበት እንጂ የልጅነት ወኔው አብሮት አልነበረም። “የጦርንቱ ፋይዳ  ምንም ሳይገባን ከ70 ሺህ በላይ ወታደር እልቂት ከታየበት እሳት ውስጥ ተርፌ ወጣሁ።” የጦርነቱ ቁስል ሳይድን ኢትዮጵያዊ ደም ያለባቸውን ዜጎች ከኤርትራ  ማባረር ተጀመር።

ይህን ርምጃውን ቀድማ ኢትዮጵያ ከመውሰዷ ባሻገር አፈጻጸሙ የከፋ ነበር። አምቼዎቹ የኤርትራን ምድር ሲረግጡ ደግሞ ሁኔታው ተጋግሎ በሀገሩ ናኘ። ይኽም አጸፋውን አባባሰው። ከልጅነት እስከ እውቀታቸው በኤርትራ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ እናት ወይም አባት ያለው ኤርትራዊ ሁላ ጨርቄን ማቄን ሳይል እንዲሰደድ ተፈረደበት። ሁኔታው የበቀልም ጭምር ስለነበር በስሜታዊነት የተሞላ ሆነ።

እናም የዚህ ጦርነት ጦስ ለሰዒድ ተረፈ። በጦር ሠራዊት ውስጥ ኢትዮጵያዊ ደም ያላቸው ወታደሮች በይፋም ባይሆን በሌላ ዐይን መታየት ጀምሩ። ጠንከር ባሉ ጉዳዮች ላይ ከሚደረጉ ውስጥ ስብሰባዎች ወጪ ሆኑ። የወቅቱ ሞቅታ ኤርትራ ውስጥ ለሚኖሩ ቅይጥ ኤርትራውያን ዱባ እዳ ወረደባችው። ከኢትዮጵያ ተገፍተው የመጡ አምቼዎች “ልጆቻችን”  የሚል አቀባበል ሲደረግላቸው ኤርትራ የነበሩት ቅይጥ ዜጎች ግን የበቀል በትር እንዲያርፍባቸው ተደረገ። ጎረቤት፣ ወዳጅ፣ ጓደኛ እነርሱን አሳልፎ መሰጠቱ እንደሀገር ባለውለተኛ ነጥብ ተቆጠረላቸው።

የእርምጃዎቹ አወሳሰድ የእውር ድንበር ስለሆነ ቅይጥ ዜጋ ዋስትና አጣ። የዜግነት ፓስፖርት የነበራቸው ድብልቅ ኤርትራውያን በአፋጣኝ መብታቸው ተገፍፎ ቢጫ መታወቂያ ታደላቸው። “የሁለቱ መንግስታት ጭካኔ የተሞላ እርምጃ እንደእኔ ኢትዮጵያዊ ደም ያለውን ወገን አስደነገጠ”ይላል ሰዒድ። ኢትዮጵያ የነበሩት አምቼዎች ንብረታቸው ተቀምቶ እጅ እና እግራቸውን ይዘው እንዲመጡ መደረጉ አስመራ ላይ ምላሹን እሳትን በእሳት አደረገው። “እኔም ኢትዮጵያ ስላለችው  እናቴ ናፍቆት በተደጋጋሚ እናገር ስለነበር ስጋት ገባኝ። ሳልቀደም ልቅደም ብዬ ከሠራዊቱ ገንዘብ የተወሰነ ወስጄ (ዘርፌ ላለማለት)  ከኤርትራ ኮበለልኩ።”

ከዚህ በኋላ ወደ ኤርትራ ሊመለስ አለመቻሉን፣ ከአባቱ፣ ከወንድሞቹ እና ለዓመታት አብረውት በትግል ያሳለፉትን ጓደኞቹን ባልጠበቀው መልኩ ሊለይ መሆኑን ሲረዳ አዘነ። ……ከሐሳቡ የባነነው የላንድ ክሩዘሯ ሹፌር የጉዟቸው መጨርሻ መሆኑን እየተናገረ የመኪናውን ሞተር ሲያጠፋ ነበር። በነጻነት ትግል ወቅት ወደሚያውቃት ካርቱም ደረሰ።

ጉዞ ወደ “እናት” ሀገር

ካርቱም ለሰዒድ አዲስ  አይደለችም። ከያዘው በቂ ገንዘብ አንጻር ደግሞ የማደርያና ምግብ ጉዳይ ከችግር የሚገባ አልነበረም። የእርሱ ራስ ምታት ካርቱምን እንደሁለተኛ ከተማቸው የሚመላልሱባት የአስመራ ደኅንነቶች ናችው። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሰንዓፌ ላይ ውለታ የዋለላቸው ወዳጆቹ ወደ ኢትዮጵያ አሻግረው ከእናቱ ሊያገናኙት ቃል ገብተው ሱዳን ቀጠሮ ቢያስይዙትም አዲስ አበባ አድርሰው ምን ያደርጉኝ? ይሆን ብሎ ተሳቋል። ቢሆንም ዱካቸው ከማይታየው የኢሳያስ ደኅንነቶች ለመትረፍ ሲል እና አስቀድሞ አምኖበት ከወያኔ  ሰንሰልት ውስጥ ከመግባት ውጭ አማራጭ አላገኘም። ብዙም ቀናት ካርቱም ሳይቆይ የወያኔ ሰዎች ባዘጋጁለት ስም እና ፓስፖርት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አበባ ገባ።

አዲስ አበባ ሲደርስ ከሱዳን ይዘውት የመጡት ስዎች ለሌሎች  አስረክበውት ሄዱ። ለጥቂት ቀናት በቅጡ በማያስታውሰው አንድ ግቢ ውስጥ ቆየ።  ከዚያም  እናቱ ይኖሩበታል ወደ ተባለው የአፋር ክልል ከተማ ተጉዞ ፍለጋ ጀመረ። “እርሷን የሚያውቋት የቀድሞ ጎረቤቶቿ ከብዙ ዓመት በፊት ወደ አባቷ አገር ወሎ ሄዳ መሞቷን አረዱኝ።” ሕይወቴ እንደገና ጨለመ። ግራ ገባኝ። እህትና ወንድሞቼን ወይም ሌላ ዘመዶቼን እንዳልፈልግ አድራሻቸውን የሚያውቅ አልተገኘም። “ ይላል  ሰዒድ።  “በኅዘን እንደተዋጥኩ ከሕዝብ ጋር ተቀላቅዬ እንድኖር  ወደተፈቀደልኝ ጅማ ተላኩ።  ከውትድርና ሙያ ውጪ ያለው ዕውቀት መኪና ማሽከርከር ነበር።  “ሰራ አልነበረኝም። ተስፋዬ በአጠቃላይ የጨለመ ስለነበር ሌት እና ቀን አልኮል መጋት ልማዴ ሆነ። ቡና ቤት ማንጋት እና ከሁሉ ጋራ መጋጨትን የዕለት ከዕለት ክንውኔ አደረግኳቸው። “

የመጠጥ ቤቴ ሴቶች ወዳጆቹ ኾኑ። ገንዘቡ  እየመነመነ ሲመጣ የአይሱዙ ሾፌር ሆኖ ተቀጠረ።  ዲማ፣ ቢፍቱ፣ አሊቴና፣ ሚዛን…መስራት ጀመረ። በዚህ ወቅት መረጋጋት ጀምሮ ህይወትን እንደአዲስ እየጀመረ ነው። ቡና ቤት ከተወዳጃት አንዲት ሴት ወንድ ልጅ አገኘ።

ነገር ግን የልጁን ፍቅር በቅጡ ሳያጣጥም ባላሰበውና ባልጠበቀው ሁኔታ ጅማን ለቀቀ። ወደ እስር ቤት ተወረወረ። በታጠቅ እስር ቤት ለአንድ ዓመት ሲታሰር አንድም ሰው የታሰረበትን ምክንያት የነገረው አልነበረም። ድብደባ እና እንግልትም አልደረሰበትም። ለአንድ ዓመት ያህል በእስር ከቆየ በኋላ እስሩ ላይ “ብይን” ተሰጠው። ኢትዮጵያ ከምትባል ሀገር እንዲወጣ መወሰኑ ተነገረው። ውሳኔው ለእርሱ የመለቀቅ ሳይሆን ከድጡ ወደ ማጡ ነበር። አባቱን ትቶ እናቱን ፍለጋ፣  እናቱን የማጣቱን ጠባሳ በልጁ ሊሽር ሲጥር ያንንም እንዲያጣ መሆኑ ጽልመት ውስጥ ከተተው። “በታጠቅ በሁለት ወታደሮች ታጅቤ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ወደ ሞያሌ ሄድኩ። ረጅሙን ጉዞ እጄ ታስሮ መወሰዴ ግዴታ ቢሆንም ወታደሮቹ ጥሩ ሰዎች ስለነበሩ ከካቴና ነጻ አድርገው ሞያሌ አደረሱኝ።”

“ካሪቡ”

የኢትዮጵያ ሞያሌን ድንበር እንደተሻገረ የኬንያ ሞያሌ ተረከበችው። በባዕድ ሀገር ራሱን ማግኘቱ እንግዳ ነገር ባይሆንበትም የመግባቢያ ቋንቋ ማጣቱ ዱዳ አደረገው። ዐረብኛ ሱዳን ላይ እንደረዳው በችግሩ ሰዐት የሚደርስለት ቋንቋ አጣ።ከመግባቢያ ቋንቋ በላይ ገንዘብ (ሽልንግ) ተናጋሪ በሆነበት ምድረ ኬንያ ሰዒድ አንደበት አጣ። የኬንያ ፖሊሶችም በተለመደ አቀባበላቸው “ካሪቡ” (እንኳን ደህና መጣህ) አሉት።  ወደ ናይሮቢ ለመግባት በፖሊሶች የተጠየቀውን 6 ሺህ ሽልንግ የመክፈል አቅም አልነበረውም። ሁለተኛው አማራጭ እስር ነበርና ወደዚያው ተወረወረ። ተገቢ የእስረኛ አያያዝ በሌለበት የስምንት ወራት ስቃይ አሳልፈ። በመጨረሻም ወደመጣበት ሀገር እንዲመለስ (Deport) ተፈረደበት። ነገር ግን በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማህበር እገዛ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የማይችልባቸው ምክንያቶች አሳማኝ ሆነው ወደ ናይሮቢ እንዲሄድ ተደረገ። በዋና ከተማዋ በሚገኘው ሚሊማኒ እስር ቤት ዲፖርት (Deport) የሚለው ወረቀት እስኪሰረዝ ለተጨማሪ ሶስት ወራት በእስር ቆየ። ከዚያም በተባበሩት መንግስታት የስደተኛ ጉዳይ ሁኔታውን ተቀብሎ ከስደተኛ ጎራ ቀላቀለው።

“ቻይ መንገድ “

ናይሮቢ ከተማ እንድስፋቷ መጠን ስደተኞችን በእቅፏ መያዝ የረጅም ጊዜ ልማዷ ነውና ለሰዒድ ቦታ አላጣችለትም። እርሱም ካሉት አማራጮች ውስጥ ወደአሻው መሄድ ይችል ነበር። ካኩማ ወደሚባለው የስደተኞች መጠለያ ገብቶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን መረዳትን መምራጥ ይችላል። ካልኾነም  ቻይ ሮድ ወደተሰኘው የኤርትራውያን ሰፈር ከእርሱ ቢጤ የናይሮቢ ስደተኞች ጋር መቀላቀል ወይም በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት የናይሮቢ የንግድ እምብርት ኢስሊ ሀበሻው ስደተኛ እንደሚሆነው ለመሆን መወሰን የእርሱ ፋንታ ነበር።

ስለካኩማ ወይም ዳዳብ (ብዙኀኑ ሶማሌያዊ  ስድተኛ ቢሆንም) ከሰዎች የሰማው ነገር ብዙም አላስደሰተውም።   ከዋና ከተማ ያላቸው ርቀት አና የኑሮ ሁኔታ ከባድነት የመሄድ ድፍረት አሳጡት። ኤርትራውያን በብዛት የሚኖሩበት የናይሮቢ ክፍል እንዳለ ሲሰማ  የሚረዳኝ አላጣም  ብሎ  ቻይ ሮድ በተባለው የናይሮቢ አካባቢ  ለመኖር ወሰነ።

ቻይ ሮድ በጣም ብዙ የኤርትራ ስደተኞች ተጠጋግተው ስደትን የሚገፉበት አካባቢ ነው። ነገር ግን በኤርትራ ኤምባሲ የሚተዳደረው ኤርትራ ሆቴል ለእርሱ አስጊ ኾኖ አገኘው። “ለእንደኔ ዐይነቱ በአገር ሻጭነት ለተፈረጀ አሰቃቂ ነው። “አለባበሴን በመለወጥና እንቅስቃሴዬን በመቆጠብ ራሴን ደብቄ መኖር ጀመርኩ። ሆኖም ግን ለልመና አስፋልት ዳር መቀመጥ በማይቻልበት ቦታ ያለረዳት የዕለት ከዕለት ኑሮን መወጣት የማይታሰብ ነበር። ጥቂት ቀናት ሳይቆጠሩ ረኅብ ሲያገኘኝ እስር ቤቱ ናፈቀኝ። በዚያ መጠለያ እና የምትፈልገውም ባይሆን ለጊዜው የሚያኖር ምግብ ይቅርብልሀል።” ሲል ይገልጻል። ኑሮው ከድጡ ወደ ማጡ የሚሉት አይነት እየኾነ ነው።

ጅማ መቀማመስ የጀመረውን ጫት ለችግሩ መደበቂያነት መረጠው። ቀን ጫት በሚቃምባቸው የቻይሮድ ስፍራዎች እየተዟዟረ ገረባም ቢሆን እየቃረመ ማታ እንቅልፍ በመጣበት እና ድካም በጣለው ቦታ መተኛትን ለመደ። ጎዳናዎች የእርሱ የመኝታ ክፍሎች ሆኑ። ሲጋራ ብርድልብሱ። ጫት ከረፋድ ሰዓት ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት ከአፉ አይወጣም። በየቀኑ መመርቀኑና ምርቃናው የሚያመጣው የሕይወት ክለሳ ከጭንቀት ወደ ድብርት አሸጋገሩት።

ለችግር እጅ የማይሰጠው ሰዒድ ከእድሜ መግፋቱ ጋራ የጎዳና ተዳዳሪነት ሕይወት ተሰባሪ አደረገው። ለአምስት ዓመታት በጎዳና ላይ ማሳለፉ በአዕምሮው ጤናው ላይ ችግር አደረሰበት። ቤተሰብ በተለይም የልጁ ናፍቆት ተስፋ እንዲቆርጥ፣ ትናንትን እንዲረግም፣ ዛሬን እንዲጠላ እና ነገን እንዳያልም ተጫኑት።

በሳንባ በሽታ  ተያዘ።  ከሞተ በላይ እና ከነዋሪ በታች አደረጎ አስቀመጠው። በጎዳና ሕይወት ቀርቶ በቤት ውስጥ እንክብካቤ ለመፈወስ አድካሚ ጊዜያትን የሚያስቆጥረው የሳንባ ነቀርሳ ፋታ ነሳው። ፈጽሞ ተዳከመ።  በዚህ ሁሉ መሀል የተባባሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት የእርዳታ እጁን ዘረጋለት።  “ቤት ተከራዩልኝ፣ ምግብም በየወሩ እየሄድኩ በራሽን እቀበላለሁ።”

ዛሬ ሰዒድ እድሜው ወደ ኅምሳዎቹ ቢገባም ሕይወት ያዘጋጀችለት  የማታ ማታ ስጦታ  እንዳለ ያስባል። ነገን ማለም ጀምሯል-በተስፋ።  አንድ ቀን ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ  ልጁን በአይነ ስጋ እንደሚያየው ያልማል፤ ወደ ጅማ- ኩሎ በር ተጉዞ። ምናልባት አንድ ቀን።