“የዋጋ ተመን ምጸት”
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የኢትዮጵያ መንግሥት “በስግብግብ ነጋዴዎች” የኑሮ ውድነት ተከስቷል በሚል ምክንያት በመላ አገሪቱ ድንገተኛ የሸቀጦች ዋጋ ተመን ይፋ ካደረገ በኋላ በተለይ የምግብ ዓይነቶች ከገበያ አንዲጠፉ አሊያም አለቅጥ እንዲወደዱ ምክንያት ሆኗል። በመላ አገሪቱ ስኳር ብርቅ ሸቀጥ ኾኗል፤ ዘይት በጥቂት አስመጭዎች እጅ ላይ በመውደቁ ከተተመነለት ዋጋ በላይ ተሽጧል። በስተኋላ ላይም መንግስት “ስግብግብ ነጋዴዎች” ኅብረተሰቡን እንዳይጎዱት ሲል ዘይትን ወደ ግምጃ ቤት አስገብቶ ለማከፋፈል ሞክሯል።
የዋጋ ተመኑ ሸማቾች እና ነጋዴዎች በዐይነ ቁራኛ እንዲተያዩ አድርጓቸዋል። ነጋዴዎች በኪሳራ ላለመሸጥ እና አንጡራ ሀብታቸውን አሙዋጠው ከገበያ ውጭ ላለመኾን በውድ የገዟቸውን ዕቃዎች ላለመሸጥ ወስነው “የለንም” እስከማለት ደርሰዋል። ከእነዚህ ሸቀጦች መካከል በብዙዎች ዘንድ እጅግ አነጋጋሪ የነበረው የስጋ ዋጋ ተመን ነው። በተለያዩ ስጋ ቤቶች ውስጥ እንደ አገልግሎት አሰጣጡ እና እንደ ስጋው የጥራት ደረጃ የዋጋ ልዩነት የሚስተዋልበት የስጋ ንግድ በመንግሥት ግብታዊ አዋጅ በአንድ ላይ ተጨፍልቆ አንድ አይነት ተመን እንዲወጣለት መደረጉ እንዲኾን መደረጉ በነጋዴዎችም ኾነ ላይ የፈጠረው ስሜት አዎንታዊ አልነበረም። መንግሥትንም በጥናት ላይ ያልተደገፈ ድንገተኛ አዋጅ አውጇል ሲሉ ብዙዎች ተችተውታል።
ይህ ትችት ውኃ የቋጠረ ትችት መኾኑን የሚያሳዩ ኹኔታዎች መከሰት ከጀመሩ ቆየት ብለዋል። አንዱ ማሳያ በአዳማ (ናዝሬት) በታዋቂው ይልማ ስጋ ቤት ውስጥ የተለጠፈው ማስታወቂያ ነው። ይልማ ስጋ ቤት ለብዙ ስጋ ወዳድ የናዝሬት ጎብኚዎች እና ነዋሪዎች ማረፊያ ነው።
ማስታወቂያው ለተከበሩት ደንበኞቹ የአንድ ኪሎ ጥሬ/ጥብስ ስጋ ዋጋ 40 ብር መኾኑን ከገለጸ በኋላ ለተጨማሪ አገልለግሎት ክፍያ 50 ብር ይጠይቃል። በተጨማሪም ደንበኞቹ አንድ ኪሎ ስጋ በ90 ብር ብቻ እንዳልኾነ እንዲረዱት የ15% ተጨማሪ እሴት ታክስ የመክፈል ግዴታው የእነርሱ መኾኑን ጭምር አስፍሯል። ምጸቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጀው የዋጋ ተመን በአገልግሎት ክፍያ፣ በአዋዜ እና ሰናፍጭ ዋጋ ምክንያት ዋጋ ቢስ መኾን መቻሉ ነው። መንግሥት የስጋ ዋጋ ተመንን ሲቆጣጠር ነጋዴው ሊቆጣጠረው በማይችለው በኩል ከፍ ያለ የዋጋ ተመን ያወጣሉ።