አድጎ ለአባልነት፤ ተምሮ ለግዞት
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ኻያ አምስት ዓመት ኾኖኛል። ነገር ግን ይህ ዕድሜዬ ያለፉትን የኢትዮጵያ መንግሥታት በአካል ለመታዘብ እና ለመገንዘብ ላይኾን ይችላል። ይኹን እንጂ በዘመኔ ስለደረስኩበት የወያኔ አገዛዝ እና ትዉልድን የማበላሸት ዉጥን እንዲሁም በአገራችን እየተካሄደ ስላለዉ የትዉልድ ግዞት እኔ ከቋሚ ምስክሮች አንዱ ነኝ።
ልጅ ሳለሁ የኢትዮጵያ ካርታ ከእነሙሉ ቅርጹ በአንዲት እንስት ተመስሎ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል፤ በተለይም በክፍለ ሀገር ተጓዥ አዉቶቡሶች ላይ ተለጥፎ መመልክት የተለመደ ነበር። ያ ሙሉ የነበረ የኢትዮጵያ ምስል ከአንገት በላይ ተቆርጦ፤ ካርታዋን በሥነ-ሥዕል ትምህርት ክፍለ ጊዜ እንኳ ለመሳል እስከሚያስቸግር ሰባራ እንስራ መስሎ መመልከት የዘመኔ ተማሪ ያለፈበት እውነታ ኾኗል። ከዚህ አለፍ ሲልም ለየትኛዋ ኢትዮጵያ ክብር እንደኾነ ያልታወቀውን “የዜግነት” መዝሙር መዘመር በዚያዉ በልጅነት ወቅት ያሳለፍኩት ነዉ።
ኋላም አዲስ አበባ ኮተቤ አካባቢ በሚገኘው በደጃዝማች ወንድይራድ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ኢሕአዲግ/ወያኔ አጨቃጫቂው የኾነውን አንቀጽ 39 ድንጋጌን እንድናምንበት ከክፍል ጎደኞቼ ጋር በፕሮፓጋንዳ ነዢዎች ለውይይት ተጋበዝን፤ እኔም መነሻ ምክንያቱ እና ግቡ ምን እንደኾነ ሳላዉቅ ከክፍል ጓደኞቼ ጋራ ታደምኩ። ሲያልፍም በየቀበሌዉ ለወጣቶች ተብሎ በተዘጋጀዉ የዚሁ አንቀጽ መድረክ (የምርጫ 97 ዝግጅት መኾኑ ነዉ) ተካፈልኩ። በወቅቱ መምህራኖቻችን ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸዉን ማንኛዉንም መልዕክት እንዳያስተላልፉ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዉ ጀመር። ምርጫዉም ተደረገ፤ ግር ግር ተነሳ፤ አቶ ተስፋዬ እሸቴ የተባሉ ዩኒት ሊደርን ጨምሮ ብዙ መምህራን ለእንግልትና ለእስር ተዳረጉ።
በ1998 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ“ፋካልቲ ኦፍ ቢዝነስ ኤንድ ኢኮኖሚክስ” ዲፓርትመንት ተቀላቅዬ የሥራ አመራር ትምህርት ማጥናት ጀመርኩ። በትምህርቴም ጥሩ ዉጤት አስመዘገብኩን፤ በመመረቂያ ዓመት ላይ ለዩኒቨርሲቲ መምህርነት ጥሩ ዉጤት ያለዉ ተመራቂ ተማሪ ማመልከት እንደሚችል የሚያመላክተውን ማስታወቂያ ባየሁ ጊዜ አመለከትኩ። ነገር ግን የሥራ ዕድሉ ክፍት የኾነዉ ለኢሕአዴግ አባላት ብቻ ነበር። ኋላም በዩኒቨርሲቲዉ የኢሕአዴግ ተወካይ በኾነ ተማሪ አማካኝነት የድርጅቱ አባል እንድኾን ተጠየኩ። ይህ ባይኾን ተመርቆ የሥራ ዕድል ማግኘት ከንቱ ልፋት እንደሚኾን አስረግጦ ነገረኝ። ታዲያ ከጥቂት የዩኒቨርሲቲዉ ተማሪዎች በስተቀር ብዙኀኑ በዚሁ የሥራ ማግኘት ተስፋ የኢሕአዴግ አባል ለመኾን የተገደደ ነዉ። እኔም ከእነርሱ እንደ አንዱ ኾንኩ።
ከዩኒቨርሲቲ ምረቃው ከአንድ ወር በኋላ “ከባህር ዳር የብአዴን ጽሕፈት ቤት ነዉ” የሚል የስልክ ጥሪ ደረሰኝ። በኢሕአዴግ አባልነቴ በኢትዮጵያ የገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለሥልጣን ዉስጥ የሥራ ዕድል እንዳገኘሁ እና ለሥልጠና በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ አጥር ግቢ እንድገኝ አሳወቀኝ። በተባለዉ ወቅት እና ቦታ ተገኘሁ። ሥልጠናዉም በተጀመረበት ወቅት ወደ 450 የሚኾኑ እንደኔዉ ከተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ አዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የኢሕአዴግ አባላት በቦታዉ ተገኝተው ነበር። ሥልጠናዉ ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት የኢሕአዴግን ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በሚመለክት ሲኾን የመጣዉም ሠልጣኝ በሙሉ በቡድን በቡድን ተከፋፍሎ የኢሕአዴግን ፖሊሲ በተመለከተ ዉይይት የሚያደርግበት ነው። በዉይይቱም እያንዳንዱ ሠልጣኝ ምን ብናገር ወይም ምን ስናገር ብሰማ በአወያዮቹ የግምገማ መዝገብ በጥሩ ኹኔታ እመዘገባለሁ ብሎ እንጂ ማንም የሚያምንበትን መናገር የሚችልበት መድረክ አልነበረም። ሥልጠናዉ በአስተባባሪዎቹ እንደተነገረዉ ስድስት ሚልዮን የኢትዮጵያ ብር የፈጀ ነበር። ይህም ለሁለት ወራት መኝታን ጨምሮ ሙሉ የምግብ እና የሠልጣኝ የኪስ ወጪን የሸፈነ ነዉ።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የተደረገዉ ይኸዉ ሥልጠና ለሁለት ወር ያልተቋረጠ የሠርግ ድግስ ይመስል ነበር። ቁርስ፣ ምሳ እና እራት ሙሉ የቡፌ ዝግጅት እና እንዲሁም በሻይ ሰዓት በቀን ሁለት ግዜ በተለያዩ የታሸጉ ዉኃ እና ለስላሳ መጠጦች ከብስኩቶች እና ዶናቶቸ ጋራ የሚቀርብበት ነበር። ይህን ያየ የአገራችንን ድህነት ቢጠራር አይፈረድበትም።
የሥልጠናዉ ማጠናቀቂያ ቀን ደረሰ። ላምበረት አካባቢ በቻይና መንግሥት በተሠራዉ የፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አጥር ጊቢ ዉስጥ “ድል ያለ ድግስ” ተሰናዳ። መጠጦች እነ ዉስኪን ጨምሮ በዐይነት በዐይነቱ ቀረቡ። ቀስ በቀስም ዋነኛ እና ቀንደኛ የተባሉት የኢሕአዴግ አባላት እና የተለያዩ መድረክ መሪዎች ከመሥሪያ ቤቱ እና ከዉጭ ተጋብዘዉ መጡ። ቀኑ እየመሸ ሲመጣም የተጠሩት እንግዶች ተሸኙ። ሽኙቱን ተከትሎ ሌላኛዉ ዙር የፌሽታ ድግስ በዲጄ በታጀበ ሙዚቃ ምሽቱ ተጀመረ። ቢራዉ እና ወይኑ በገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን መኪኖች እየተጫኑ ግቢውን ሞሉት። በምሽቱ የተሰበሰብነዉ አዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ሠልጣኝ አገርን ለማልማት ወይም በአገር እድገት ዉስጥ ተሳትፎ ለማድረግ ሳይኾን ለአምባገነኑ ገዥ ሥልጣን ላይ የመቆየት ሕልም አስተዋጽኦ የማድረግ የጥምቀት ሥነ- ሥርዐት ላይ ነበርን።
ወደ “ክንፈ ማሠልጠኛ ማእከል”
የሁለት ወሩ ሥልጠና እንዲህ በመሰለ ኹኔታ እንደተጠናቀቀ እኔን ጨምሮ 46 የምንኾን ሠልጣኞች ተመርጠን ለተጨማሪ ሥልጠና ታጨን። በመጀመርያ የሥልጠናዉ ይዘት እና ምንነት ለአብዛኞቻችን አልገባንም ነበር። ሥልጠናዉም ለሦስት ወራት እንደሚዘልቅ በአስተባባሪዉ በኩል ተብራራልን። ኋላ ላይ ግን ሥልጠናዉ በኢትዮጵያ የደኅንነት ቢሮ (በክንፈ ማሠልጠኛ ማእከል) እንደሚሰጥ በታወቀ ጊዜ ምን ሊያሠሩን ይኾን በማለት ፍርኀቱ እና ጥረርጣሬው ጨመረ። ኾኖም ግን ይህን ማዉራት ኀጢአት ወይም ወንጀል ይመስል ትንፍሽ የሚል አልነበረም። የእያንዳንዳችን የጣት አሻራ፤ ፎቶ ግራፍ እና የግል መረጃዎች ተወሰዱ። ሥልጠናዉ ጥብቅ ምሥጢር እንደኾነ እና ማንኛዉም የሥልጠና መረጃ በሌሎች መታወቅ እንደሌለበት በማስጠንቀቅ የመረጃ አሰባሰብ ሥልጠናዉ ተጀመረ። ተካልኝ፣ ሰለሞን፣ ገብረ እግዚአብሔር እና ፍትኀ ነገሥት እንዲሁም ባልሳሳት ገብረ ማርያም በተባሉ አምስት አስተማሪዎች ሥልጠናው ተጀመረ።
የመጀመሪያው የንድፈ ሐሳብ ትምህርተ ስለ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሲኾን በቀጣይ ስለ አጠቃላይ መሠረታዊ መረጃ አሰባሰብ ሰፋ ያለ ሥልጠና ተሰጠ። ቅድመ ተልእኮ እና ዕቅድ፣ የመረጃ ምንጮች፣ መረጃ ሠጭዎች ምልመላ፣ ስለ ስለላ እና ጸረ ስለላ በሥልጠናው ከተዳሰሱ ርእሶች የተወሰኑት ናቸው።
ከአንድ ወር የንድፈ ሐሳብ ሥልጠና በኋላ የመስክ ልምምድ ተደረገ። በዚሀ ጊዜ የባሰባቸው እና ኹኔታዉን ሊቋቋሙት ያልቻሉ ሲጠፉ እኔን የመሰሉ ጥቂት የሌላ ብሄር ተወላጆች በፍርኀት እና በጥርጣሬ፤ ጥቂት የትግራይ ተወላጅ የኾኑ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በድፍረት ሥልጠናውን ተከታተልን። እኔ እና መሰሎቼ ዛሬ ነገ ምን ተከትሎ ይመጣ ይኾን ስንልና ለመዉጣትም ምቹ ኹኔታ ስንጠባበቅ የሥልጠናው ግዜ አለቀ። የክንፈ ማሠልጠኛ ማእከል ዋና አስተዳዳሪ፤ አሠልጣኞች እና የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል አስተዳዳሪ በተገኙበት የምረቃዉ ሥነ-ሥርዐት ተካሄደ።
በቀጣዩ ሳምንትም በአፋር ክልል በሚሌ የመግቢያ በር እና በአካባቢዉ በሚካሄደዉ እንቅስቃሴ፤ በተለይም የገዥዉን የኢሕአዴግን ሥልጣን ስጋት ላይ ሊጥሉ የሚችሉ በድንበር አካባቢ የጦር መሣርያ ዝዉዉርን የተመለከተ መረጃ እንድከታተል መመደቤ ተነገረኝ።
ይህ ሲኾን አንድ የተረዳኹት ነገር ቢኖር ለነጻነቴ የመታገል አቅሙ ባይኖረኝ እና መንገዶቹ ቢጠቡም፤ በወቅቱ ላደርገዉ እችል የነበረዉ የመጀመርያ ርምጃ ቢያንስ የዚሁ የጥፋቱ ተባባሪ እና አባል ከመኾን መቆጠብ ነበር። ነገሩ በዚህ ከቀጠለ መዉጫ እንደሌለኝ ስለተገነዘብኩ፤ ምንልባትም “ምንም እንኩዋን ጉዳት ሊደርስብኝ ይችላል” የሚል ስጋት ባይለቀኝም፤ በዚሁ ከገፋሁ የበሰ ችግር እንደሚገጥመኝ በማሰብ በግል እና በቤተሰብ ምክንያት ወደ ተመደብኩበት ቦታ ሄጄ ልሠራ እንማልችል ገልጬ የሥራ መልቀቂያ እስገባሁ። በጊዜዉ የነበረዉ የሥልጠናዉ አስተባባሪ ጥሩ ሐሳብ እንዳልኾነ ነገረኝ። ከዚያ በኋላ በመረጃ ቡድኑ አስተባባሪ ተጠርቼ ወደ ተመደብኩበት ስፍራ ሄጄ የመሥራት ድርጅታዊ ሐላፊነት እና ግዴታ እንዳለብኝ ተነገረኝ።
በዉሳኔዬ ፀንቼ ሳልሄድ ቀረሁ። ከቀናቶች በኋላ በገዛ መንደሬ ከምኖርበት ቤት በሦስት ሰዎች ተደበደብኩ። ለጊዜዉም ቢኾን የመኖርያ አካባቢዬን በመቀየር ለመሰወር ብሞክርም አልቻለኩም። የማደርገዉ እንቅስቃሴ ሁሉ በክትትል ሥር እንደኾነ ተገነዘብኩ። በስተመጨረሻም በየካ ክፍለ ከተማ አቧሬ አካባቢ የሥራ ዕድል አገኘሁ። በኋላም ወረዳ 06 ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ በድጋሚ የኢሕአዴግ አባል እንድኾን በዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ አብዱል ሽኩር በተባሉ ሰዉ ተጠየኩ። ጥቂት ጊዜያቶች እንዲሰጠኝ በመጠየቅ ምላሼን ባዘገየዉም የቡድን አስተባባሪ ሊያደርጉኝ እንደፈለጉ እና በቅድሚያም የአባልነት ፎርም እንድሞላ ጠየቁኝ። በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሰንበት ቀኖችን ጨምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ከግቢዉ መዉጣት የማይፈቀድበት የአመራሮች ሥልጠና ስላለ አንሶላ፤ ብርድ ልብስ እና ሌሎችም የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ይዤ እንድገባ ተነገረኝ። በድጋሚ ድርጅቱን በመቀላቀል የጥፋት ቡድኑ አባል እንድኾን ግዳጅ መሰል ትእዛዝ እየተሰጠኝ ነበር።
አሁን ከአገሬ ተሰድጄ በውጭ አገር እገኛለሁ። ይህ ሁሉ ያጫወትኩዋችሁ ምን ያህል እነዚህ ጥቂቶቹ የወያኔ አስተዳደር የቡድን አባላት የኢትዮጵያ የተማረ የሰዉ ኀይልን በገዛ አገሩ ለአባልነት አስገድደዉት አገልግሎቱንም ያለ ፈቃዱ እንደሚሰጥ እና ለኢኮኖሚ አስተዋዖኦ ከማድረግ ይልቅ የደኅንነታቸዉ ጠባቂ ዘበኛ እንዴት እየተደረገ ለማመልከት ነዉ። እነዚሁ የኢትዮጵያ አጥፊ የቡድን አባላት በድርጅታቸዉ በተነደፈዉ ዜጎችን የፓርቲዉ ባርያ የማድረግ ዘመቻ የተማረዉን የኅብረተሰብ ክፍልም ለባርነት ከመጋለጡ በላይ ለግዞቱም በየወሩ ሠርቶ ከሚያገኘዉ ደመወዝ ላይ የአባልነት ክፍያ እንዲከፈል ያስገድዳሉ። የፕሮፓጋንዳ መንዣ ጋዜጦቹን እና መጽሔቶቹን የመግዛት ግዴታ ተጥሎበት ማየት ለተገነዘበው ገዥዉ ፓርቲ እና እነዚሁ ጥቂት አመራሮቹ ቅኝ ገዥዎች እንጂ ከኢትዮጵያ ምድር የወጡ አይመስሉም። አዲስ የደኅንነት አገልጋይ ምልምሎችን ለማፍራት ትኩረቱን ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያዞረዉ የጥቂቶቹ የወያኔ አመራር ቡድኖች ተገዥ የኾነዉ ኢሕአዴግ በእኔ ላይ ስላደረሰዉ አገልግሎትን ያለፈቃድ የመስጠት፤ በሞያዬ እና አገሬ ባስተማረችኝ የእዉቀት ደረጃ እንዳልሠራ እና በነጻነት የመደራጀት መብት ጭምር ነው የነፈገኝ። በወቅቱ የተመለመሉ ሌሎች እኔን መሰል የዩኒቨርሲቲዉ ምሩቃን በተመሳሳይ መንገድ ለመረጃ ድርጅቱ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
(በአውሮፓ የሚገኙት የጽሑፉ አቅራቢ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉት ለደኅንነታቸው ሲሉ ነው)