ማንን እንመን? ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን በማን እጅ ነች?
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ማንን እንመን? ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን በማን እጅ ነች?
ሳምሶን መኮንን
ከዳላስ
December 14, 2014
ለሥጋችንና ለነፍሳችን በምሳሌነት የሚጠቅም ስራ ሰርተው ሊያሳዩን ይችላሉ ተብለው የመጨረሻውን የስልጣን ልጓም የጨበጡትን መንፈሳውያንንና ሥጋውያን መሪዎች በዚህ ሰሞን የተናገሩትን ሰማን። የተጻፈውንም አነበብን። መዘርዘር ባያሻም፤ ህዝባዊውን ጥያቄ የሚመለከታቸውና ሀላፊነት ያለባቸው በተለይም ቤተ ክርስቲያናችን ያስተማረቻቸው ሰዎች ለሚሰጡን መልስ መሰረት እንዲሆን ከሞላ ጎደል መጥቀስ የሚያስፈልግ ነው። ጥያቄያችን በተወጋገዙት ሰዎች መካከል የተካሄደውን የሚመለከት ብቻ ባለመሆኑ፤ “የገላጋይ ደም የለውም” የሚለውን የባህል ንግግራችን በመርሳት አስታራቂዎችም ራሳቸውን ለመደበቅ በሽምግልና ላይ መታየት የነበረበትን ሞራል ጥለውታልና እነሱንም ይመለከታል።
፩ኛ በቤተ ክርስቲያናችን መካክል የተነሳው ይህ ውዝግብ በመንግስትና በተቃዋሚዎች መካከል ከተነሳው ውዝግብ እጅግ ውስብስብ ከታሪክ ከአገርና ከማህበራዊ ጉዳይ ባሻገር በጣም አስቸጋሪ የሆኑ እንደ ነገረ መለኮትና የቀኖናን የጣስ የመሳሰሉትን ነገሮች ያዘለ ነው። ይህን የተወሳሰበ ነገር ለመፍታት ምን ልምድ፤ ችሎታ፤ እውቀትና ብቃት አላቸው ? ማነው መልምሎ ያመጣቸው? ሰው ሁሉ ከተበከለበት ከግላዊ ጥቅም ከዝምድናና ከፖለቲካው ምን ያህል የራቁ ናቸው?
፪ኛ ተመርጠውና ወክለው ከመጡ፤ አቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ “ፓትርያርክ መርቆርዮስ ላገራቸው አፈር እንዲበቁ ነው እንጅ ከቀደመው ውሳኔ የተለየ የሚደረግ ነገር ለምን አሉ?
፫ኛ ከበጎ ህሊናና ከገርነት ተነስተው እውነቱን መስክረው ሊሆን የሚገባውን ጠቁመው ያቀረቡትን የኢ.ህ.ዴ.ግ. ፕሬዝደንት ሀሳብ መደገፍ ሲገባቸው፤ ኢሀደግ ተቃውሟል፤ ምን አገባቸው ብለው ለምን ፕሬዝዳንቱን ገሰጿቸው?
፬ኛ የሀገሪቱ ፕሬዝደንትስ በበጎ ፈቃደኞችና በራሳቸው ንጹህና ገር መንፈስ በመነሳሳት የተሰማቸውን በግላቸው መጻፋቸው ትክክል ሆኖ ሳለ፤ ለምን ከመንግስት ጋራ በማገናኘት ቃላቸውን አጠፉት? እንዳንድ አንጋፋ የሀገረ ሽማግሌና ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን አማኝ በግሌ የምመኘው ይህ ነው ማለት ለምን አልቻሉም? ዲሞክራሲ ከተባለ የራሳቸውን ነጻነት ለመጠቀም ምን አገዳቸው? ያሁኑ ጠቅላይ ምኒስቴር ወልደማርያም ብላ ያስጠመቀቻቸው የክብርትና የዋሂቱ ወላጅ እናታቸው እምነት፤ ስንት ቅዱሳን አወገኖቻችን ያለፉበትንንና አሁንም እሳቸው እመርሀለሁ የሚሉት ከ፵፩ ሚሊዮን በላይ ያቀፈው እምነት እንደሚወክል ያውቃሉ። በቤተ ክርስቲያናችን ሲወገዝ በኖረው በሰባልዮስ እምነታቸው በመለካት አበላልጠው ይህ ሁሉ ህዝብ እንዳልዳነና በክርስቶስም ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው አድርገው፤ እናቴ አልዳናችምና እየጸለይኩላት ነው ሲሉ አልፈሩም። አላፈሩም፤ የሃይማኖት እኩልነት እያሉ የምሰብኩትን አላከበሩም። የጠቅላይ ምኒስትሩ እንቅስቃሴ ይህ ሆኖ ሳለ፤ ፕሬዝዳንታችን በማያሳፍረው በታሪካዊው እምነታቸው ቀጥ ብለው ለመቆም ለምን አቃታቸው?
፭ኛ አቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ አቋማቸው ይህ ከነበረ፡ ለምን ልዑካኑ እንዲመጡ ተስማሙ? የፓትርያርክ መርቆርዮስን አካል ለአገራቸው አፈር እንዲሰጡ ለመለመን ነበር?
፮ኛ ስደተኛው ሲኖዶስ አባላት ነን የሚሉት፤ ካወገዙት ሲኖዶድስ ሰብሳቢ የተነገረውንና ከፕሬዝደንቱ የተነገረውን እየሰሙ ምን መነሻ ይዘው ነው ውይይት የጀመሩት?
፯ኛ ግዝቱንስ እንዴት ፈተውት ነው አብረን ቀድሰን አብረንም እስከ መካከል ሄደናል ያሉት? ከአሜሪካ ራዲዮ እንደተነገረው ወፈ ገዝት ናችሁ ለተባለው ጥያቄስ መልሳቸው ምንድነው? የቪ.ኦ.ኤ. ጋዜጠኛ አቶ አዲሱ እውነቱን ስላወጣ ይመሰገናል። በሞራል አንጻር ጋዜጠኛ አቶ አዲሱ የሚከሰስበት፣የሚወቀስበት አንዳች ዘይቤ የለም። ስለቤተክርስቲያኗ የሰዎችን ድምጽ ለህዝቡ አቀረበ። የራሱን ማብራሪያ አልሰጠም። የራሳቸውን የአቡነ ናትናኤልንና የፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊውርጊስን የወኪላችውን ድምጽ ነው ያቀረብው። “ልናስታርቅ ነበር ነገሩን አበላሸብን” ተብሎ በሰንካላን እኩይ መንፈስ ሊተች አይገባውም።ብራቮ አዲሱ! አይ ካላችሁም ሜዳውም ይኽው ነው ውጡና እንስማችሁ። ግን በምን ሞራል…….።
፰ኛ እንደገና አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክነቸውን ተገፈው አባ ዘሊባኖስ በመባል ክህነታቸውን የተቀበለ የተባረከ እንዳይኖር ቃል በተላለፈው ውግዘትም ተካተዋል። እንዲሁም ሌሎችም ሊቃነ ጳጳሳትም አብረው ተወግዘዋል። ይህንን እንዴት ዘለውት ነው? ውግዘቱ ሳይነሳ እንዴትስ አብረው ኪዳን አደረሱ?
ዶክተረ መርዓዊ ተበጀም እድል አያምልጠን በሚል ርእስ ጽፈው ለመላ ኢትዮጵያውያን ባቀረቡት “በአቡነ መርቆ ርዮስ ላይስህተት ካለ እንደ አቡነ መልከ ጼዴቅ በሲኖዶስ ይታይ” በማለታቸው በአቡነ መልከ ጼዴቅ ላይ የተወሰደ ውሳኔ እንዳለ በግልጽ አሳይተዋል። ከዚህ ሁሉ የተደራረበ የውግዘት ሸክም እንዴት ተላቀው ነው? ምንም እንዳልተደረገ አስመስለው ለማለፍ ለምን ሞከሩ? ፓትርያርኩም አባ ዘሊባኖስ ተብለዋል” በነሱ መባረክም አብሮ መሳተፍም የተወገዘ ነው ተብሏል? ይህን ሁሉ እንዴ ተሻግረው ነው የአዲስ አበባውም ሆነ የውጭው ሲኖዶሶች “አብረን በልተናል፤ አብረን ጸልየናል፤ አብረን ውለናል፤ ከግማሽ ጉዞም በላይ ተጉዘናል።” ለማለት የበቁት?
ይህ ከዚህ በላይ የተገለጸው አነጋጋሪና አጠያያቂ ሂደት በቅርቡ ከንሳስ ላይ ተፈጸመ ተብሎ በሰፊው በጽሁፍ እየቀረበ በመላ ዓለም ሲነበብ የነበረውን ታሪክ ዘወር ብለን በማጤን እንድንመለከተው አድርጎናል። በከንሳስ ላይ በተፈጸመው ታሪክ ተዋናይ የነበሩት አሁንም በሁለቱ ሲኖዶሶች ለተከሰተው ችግር ፈች ሆነው ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ያሉት ዶክተር አማረ ተጠያቂነቱ ስለሚመከታቸው ደራርበው የተሸከሙት ዶክተርነታቸው ከቤተ ክርስቲያናችንም ሊቃውንት በላይ እንደሆኑ የሚጠቁመው “ሊቀ ማእምራን” የሚለው ማእረጋቸው ከተማሩት ከቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና አንጻር ለዚህ መልስ በመስጠት ሊያስተምሩን የተደራረበው ማእራጋቸው ያስገድዳቸዋል።
ከዚህ ቀደም አቡነ ማትያስ ከንሳስ ላይ ሄደው ብዙ አስተማሪ የሆኑ ትምህቶችን የጻፉትን ቀሲስ አስተርአየን ለተወሰነ ጊዜ አግጃለሁ በማለታቸው። ቀሲስም አቡነ ማትያስ የሚከተሉትና ያገዱበት ምክንያት ከኦርቶዶክስ ትምርህትና ቀኖና ውጭ እንደሆነና እንደማይቀበሉት ለህዝቡ “የምነግራችሁ የኦርቶዶድክስ ተዋህዶ እምነትና ትምህርት ሳይሆን ቢገኝ ልገረፍ” በማለት መስክረው ጥለው ወደ ቤታቸው እንደሄዱና፤ ምስክርነታቸውን አምነው የተቀበሉት ምእመናን ባደረጉት ጽናት ባካባቢው ካሉት ኦሬንታልና ምስራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት ትብብርና ድጋፍ ቆሙ። ቀሲስ የምእመናን ድጋፍ ካለኝ፤ ካልተሳሳትኩ፤ መላው ኦርቶዶክስም ከደገፈኝ ለምን የራሴን ቤተ ክርስቲያን አልከፍትም ሳይሉ፤ እገዳውን በማክበር በቤተ ክርስቲያናችን ህግ መሰረት የታገድኩበት ምክንያት ተጣርቶ በስህተቴ ንስሀ ገብቼ ወይም አጋጁ አቡነ ማትያስ በስህተታቸው ተቀጥተው እስካልተገለጸ ድረስ ቤተ ክርስቲያን ሊከፍቱ ይቅርና ኪዳን አላደርስም በማለት፤ ዲሲ ላይ ጉባዔ እንዲካሄድ አስደረጉ።
ጉባዔውም “ቀሲስ አልተሳሳቱም። የተሳሳቱት እርሰዎ ነዎት። ስለዚህ በመካከላችን ይገኙና ነገሩን እንፍታው” በማለት በአቡነ ገብርኤል መሪነት ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህን መጋቤ አዕላፍ መክብብን ወደ አቡነ ማትያስ እንደላከና የተከፋፈለው የከንሳስ ህዝብም አንድነቱ እንዳይሻክር ይደረግ” ቢሏቸው አቡነ ማትያስ ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆኑ የሚያሳየው ቃለ ጉባኤ በድረ ገጾች ቀርቦ በሰፊው ተነቧል።
እንኳን ትክክለኛውን ይዘህ በመቆም የደረሰብህን እገዳ ተወውና ከእገዳ አልፎ ሁላችንስ የተወገዘን አይደለም እንዴ ዝም ብለህ ሂደህ ቀድስ እያሉ እነ አቡነ ገብርኤል ቀሲስን ቢገፏቸውም፤ ኪዳን እንዲያነቡ ቢጠየቁም በኔ ላይ የተሰነዘረው እገዳ ተመርምሮ ተጣሮ ልክ መሆኔን ወይም መሳሳቴ ተገልጾልኝ የምቀበለውን ንስሀ ሳልጨርስ ኪዳን አላነብም። የኔ ጥያቄየ እዚህ ድረስም የመጣሁት ሂድና ዝም ብለህ ቀድስ እንድትሉኝ አይደለም። በባህላችን ካህን አይደለም፤ እምነት የሌለው ሰው እንኳ አንድ ኢትዮጵያዊ በፈጠረህ የምታደርገውን አቁም ሲባል ማቆም አለበት ይህም ባህል በህዝባችን መንፈስ ስለተቀረጸ ያን ላለመስበርና በኔና በአቡነ ማትያስ ንግግር ህዝብ ስለተከፈለ ለማጥራት ነውና። ስህተቱ ካልተጣራ ወደ ከንሳስ አልመለስም። በማለታቸው ታይቶ ሁሉ ነገር ተመርምሮ እንዲጣራ ካስደረጉ በኋል የካህናቱ ጉባኤ ያቡነ ማትያስን ስህተት እንዲታረም ለበላይ ገለጸ። በአቡነ ጳውሎስ ለሚመራው የላኩትን ቃላ ጉባኤ ይመለከታቸዋል በማለት በውጭ ላለው ሲኖዶሱም ልከዋል። የከንሳስ ኪዳነ ምህረት የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ይስሀቅ ቀሲስ ትክክል መሆናቸው ገልጸው የከንሳስ ኪዳነ ምህረት ምእመናን እንደነበራችሁ ቀጥሉ” የሚል መልእክት ቢጽፉም “ማርያምን ክደዋል” እያሉ የማህበረ ቅዱ ሳን አባላት አልተቀበሉትም።
የሰንበት ተማሪዎች መከፋፈሉን ስለፈለጉ፤ ከካህናቱ ጉባዔና ካቡነ ይስሀቅ እውቀትና ስልጣንም ርቀው በመሄድ ቀሲስን ማርያምን ክደዋልና አንቀበልም ብለው በማመጻቸው ቀሲስና የተዋህዶ ምዕመናን ከአምስት አመታት በላይ የደከሙበትን ህንጻና የሰበሰሰቡትን ገንዘብ መካፈል ይገባናል ሳይሉ በሰላም አስረክበው ወጡ። ቤተ ክርስቲያንን ወደ ዓለማዊ ዳኛ መውሰድ ክልክል ነው በማለት ያላንዳች ቅሬታ በስህተት ለከሰሷቸው ሰዎች አስረክበው” መድኃኔዓለም በሚል ስም ቤተ ክርስቲያን ጀመሩ። ከዚያም በኋላ እነኝሁ ሰዎች የመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን እንዲዘጋ በከተማው የሚያሰራጩትን አሉባልታ እንዲያቆሙ የገሰጻቸው አካል ባለመኖሩና ስለዘመቱባቸው፤ በመካከላችን ተገኝታችሁ አርሙን የሚል ጥያቄ ተመሳሳይ እምነት ወዳላቸው ወደ እነ ፓትርያርክ ሽኖዳ አቀረቡ። ፓትርያርክ ሽኖዳና የቀሩትም ተመሳሳይ እምነት ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት በአካል በመገኘትና በጽሁፍ መሰከሩላቸው።
ከዚያ በኋላ ቀሲስ የተማሩትን ቤተ ክርስቲያን ያስታጠቀቻቸውን ያላንዳች መወላወል በጽሁፍ ማሰራጨት ቀጥለው የከበቧቸውን አሉባልተኞች አፍ መዝጋት ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያናችንን የነገረ መለኮት መሰረታዊ ትምህርት እያነጻጸሩ ጥርት ባለመንገድ አከታትለው በማቅረብ ሁሉን አስተማሩት። እነሆ ዛሬ ለምሳሌነት ለመጠቀስ በቁ። በነቀሲስና በአቡነ ማትያስ መካከል በተነሳው ጉዳይ ቀሲስ የተናገሩትንና የወሰዱት አቋም የደግፈውን ጉባዔ የመሩትና ያስተናገዱ ሊቀ ማእምራን ዶክተር ካህን ዛሬ ደግሞ አስታራቂ በመሆን በሁለቱ ሲኖዶሶች ዋናኛውን ቦታ በመምራት ላይ ናቸው። የተወጋገዙት አባቶች አብረው ሲቀድሱ ምን አሉ? ምንስ ተሰማቸው? ፕሬዝደንቱ የተለያየ ቃል እየተናገሩ ዓቃቤ መንበረ ፓትርያርኩም ልኡካን ከላኩ በኋላ የተናገሩትን እየሰሙ የተወጋገዙትን አፈራርሞ መልቀቅ መልካም ሽምግልናን ያሳያልን? የተጣሉትማ ተጣልተዋል። ዶክተር አማረ ከላይ የተገለጸውን ራሳቸው እንዳካሄዱት እያወቁ እሳቸው በጀመሩት መንገድ ችግሩን መፍታት እንደማይችሉም ግልጽ ሆኖ ሳለ የዶክተር አማረ ላይ ታች ማለት ከተወቃሽነት ለማምለጥ ነው እንዴ?
ህዝቡ ማንን ይመን? የተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን በማን እጅ ነች? ስለመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ያሉ መጻህፍት ምን ይላሉ? ቀሲስ እስካሁን ብዙ ጽፈዋል፤ በጽሑፎዎም ብዙ ሰው ተምሮበታል፤ በሰሞኑ የተካሄደውን ሳይሰሙ የቀሩ አይደሉምና ምን ይሰማወታል? መፍትሄውስ ምንድነው ይላሉ? እስካሁ አዝነው ተበሳጭተው ከገለጿቸው ችግሮች ይህ አሁነ የተከሰተው ችግር ዝቅተኛ ሆኖ በዝምታ ታዝበው የሚያልፉት አይመስልምና አስበውበት ከዚህ በኋላ መደረግ ያለበትን ጭምር በመጠቆ ም ቢገልጹት መልካም ነው። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት በቅዱስ መንፈስ እየተመሩ ያስቀመጡትን እውነት ማለትም በነገር መለኮት ጥናት ውስጥ ቅዱስ ቁርባን እግዚኦ ተብሎ በቅዳሴ የሚደመደም ነው። ያለ ጾም ፋሲካ፣ ያለፋሲካ ጾም የለም እንደሚባለው ማለትም ሁሉም በዓሎቻችን ጾሞች ናችው፣ ሱባዔዎች ናችው፣ ቅዳሴያችንም የሁሉ ነገር መደምደሚያ ነው። ስለዚ ግዝት ሳይወርድ አብሮ ቅዳሴ ከቶ ሊሆን አይችል። ተደርጎም ከሆነ ሲኖዶሶቹ በይፋ ማብራሪያ እንዲሰጡበት እንጠብቃለን።ለሥጋችሁ መጥቶ ይረፍ ወይም ይውደቅ ከሆነ ሽንገላው አትጨነቁ። ጌታችን መድኃኒትችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመጣ በቅዱስ ሚካኤል መለከት ይነፋል። ሥጋን ከየትም ያመጣል ይሰበስባል። ውጭ ሁን፣ ውስጥም ሁን፣ የትም ሁን ጌታ ሊሰበስብ አዎ ይመጣል። የቀኖና ቤተክርስቲያን ጥሰት፣ ውግዘት እውነትን በትኖ ለመቃብር መሆን የለበትም። ሁለቱም ሲኖዶሶች ልብ በሉ። የማይሰበረው የቤተክርስቲያን ሞራል ነውና አስተውሉ።
የአስታራቂ ኮሚቴ አባላት ነን ከሚሉ አንዳንዶች በዳላስ እንደሰማነው ለማገናኘት እንጂ ለማስታረቅ አይደለም ከሆነ ቤተክርስቲያናችንን አያውቋትም። ለዚህ ነበር እንዴ ማስታረቁን ከጀመሩት በዕድሜ፣ በዕውቀትና በጥበብ ከበሰሉ ኮሚቴዎች እኛ ካህናት ነን በሚል “መፈንቅለ ኮሚቴ” በማድረግ የምትውተረተሩት? (በአንድ ወቅት በኢሳት ቲቪ በጋዜጠኝ አቶ ሲሳይ አጌና የተላለፈውን ይመልከቱ) ይልቁንስ ወደነበሩት ኮሚቴዎች ጋር አብራችሁ ብትራመዱ ሊሰምር ይችላል። ልብ በሉ ቤተክርስቲያናችን የራሷ የሆነ ቋንቋና ሂደት ያላት ከፖለቲካው ሁሉ የረቀቀ፤ ረቂቅ ምህዋር ያላት ነች። እውነት ካልመጣ ለማገናኘት ነው በሚል ሽፋን ከእውነት ውጭ ዕርቅ የለም። አይመጣምም። ነፍሳቸውን ይማርና የሊቀመዘምራን አበባው ይግዛው መቃብር ፖለቲካዊ ማባበያ እንጅ ትጥቅ ማስፈቻ ሆኖ “ስጋችን ከገባ ምን አገባን” መሆን የለበትም። የመሰደዳችሁ ምክንያት ምን ሆነና! እስኪ ንገሩን? ለምን ተሰደዳችሁ? ለምንስ ተወጋገዛችሁ? እሳተ መለኮት ቀልድ ሆነ እንዴ? እንዲያ ከሆነማ ሳትሰደዱ ያማረ፣ ያማር ገዳም እኮ ነበረላችሁ። ትውልዱ ያልተሸራረፈ እውነት ይሻል። እውነት ነው ጊዜዎቹ አሰልችዎች ናቸው፤ አንዳንዶችም በውስጣችሁ ቡርቦራውን ተያይዘውታል። ለሁሉም ግን ጽናት ይሻል።
ሊቀ መዘምራን አበባው ይግዛው አሁን በስልጣን ላይ ካለው ወያኔ-ኢህ አዴግ ጋር የተስማሙበት አንዳችም ማስረጃ የለም። ይልቁንስ በመጀመሪያው የዕርቅ ኮሚቴ ውስጥ ሆነው ግዝቱን አውርዳችሁ ተጨባበጡና ለእርቅ ተቀመጡ ነበር ያሏችሁ በግምባር ቀርበው። የምንታገለው ለመቃብር ወይንስ ለመንፈሳዊ አርበኝነት ነው? መንፈሳዊ አባትነት ሰው ይቀብረኛል ብሎ ሳይሆን በመንፈሳዊ አርበኝነት ማለፍ ነው። ሁላችንም እንሄዳለን፣ እናንቀላፋለን ለዘላለም። በውስጥም በውጭም ያላችሁ ብጹአን አባቶች ከውድቀት መጋረጃ መውጣት አለባችሁ። መንፈሳዊ ታሪክ ስሩ። የቤተክርስቲያን ቀኖና እንደ ልጆች “አየሁሽ፣ አየሁሽ” የድብብቆሽ ጨዋታ ሆነ እንዴ? ይህ ከቶ ሊሆን አይችለም። ጉዳዩ አገር ውስጥ ገበተው ወይንም ውጭ ተገናኝተው ህክምን እየታከሙ አብሮ መብላትና መጠጣት አይደለም። ይህንንማ አህዛብም ያደርጉታል። ጉዳዩ የፈርሰው ቀኖና ቤተክርስቲያን መጠገን (መከበር) ነው።
የአሁኖቹ እናስታርቃለን የሚሉት ኮሚቴዎች በትዕዛዝ ብጹአን አባቶችን አትናገሩ፣ ጭጭ እረጭ በሉ በሉ ብለው በሌላ አንጻር ግን ከአራት ኪሎው መንግስትም ሆነ ከአራት ኪሎው ሲኖዶስ ፓትርያርክ መርቆሪዎስ “ለአገራቸው አፈር ይብቁ በአንዲት ቦት ተወስነው (በግዞት) ይቀመጡ” ብሎ የተዘበራረቀና የተመሰቃቀለ መግለጫ በጽሁፍም በሬዲዮም ሲሰጡ ኮሚቴው አትናገሩ ብሎናል ብለው መልስ አለመስጠት ሕዝቡን ማጃጃል ነውና የሽማግሌ ሊቃውንት ያለህ! ማንን እንመን? ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን በማን እጅ ነች?