በዳላስ የተካሄደው የሁለቱ ሲኖዶሶች እርቀ ሰላም ውይይት ያለተጨባጭ ውጤት ተጠናቋል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በዳላስ የተካሄደው የሁለቱ የሲኖዶሶች እርቀ ሰላም ውይይት ያለተጨባጭ ውጤት ተጠናቋል

በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

ሳምሶን መኮንን

ከዳላስ

December 9, 2012

ለፓትርያርክነት ዕጩ ተወዳዳሪ በሆኑት በአቡነ ገሪማ የሚመራው የአዲስ አበባው ሲኖዶስ መልዕክተኞች ቡድን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ በመረጡት ቦታ በጸሎት ተወስነው ይቀመጡ፣ ለሀገራቸው አፈር ይብቁ ሲል በአንጻሩ ደግሞ እውነትን በሚያከብሩት ለታሪክ ምስክርነት እግዚያብሔር ባስቀመጣቸው በብጹዕ አቡነ መልከ ጸዲቅ የሚመራው ህጋዊው በውጭ የሚገኘው ሲኖዶስ መልዕክተኞች በበኩሉ ወደ እውነቱ ተመልሰን ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሪዎስ ከነሙሉ ማዕረጋቸውና ክብራቸው ወደ ፓትርያርክ መንበራቸው ይመለሱ፣ የተጣሰው (የተሰበረው) ቀኖና ቤተክርስቲያን ይጠገን፣ ለትውልድ ያልተከፋፈለች አንዲት ቤተክርስቲያን እንድናስተላልፍ፣ የታሪክ የትውልድ ተወቃሽ አንሁን ሲል ሃሳቦች ቀርበው ክርክሩ በርትቶ በዚህ ዋናው ቁም ነገር ነጥብ ላይ ያለምንም ውጤት ተጠናቋል። ባለፈውረቡዕ።

ዳሩ ግን እንደው ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ሆኖ ነገሩ ለአምስት ቀናት ስብሰባው እንዲዘልቅ ተደርጎ ለድጋሚ ስብሰባ ለአራተኛ ዙር ውይይት ለሰላም በር መዘጋት የለበትም በሚል ሰበብ መላውን በሳተ መቋጫ ወደ ሰባት ነጥቦች የሚሆኑ የአቋም መግለጫ ብጤ በማውጣት ተጠናቋል። ይሁን እንጅ የአዲስ አበባው ሲኖዶስ አዲስ ፓትርያርክ ከሾመ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ካለመገንዘብ ፓትርያርኩ ይመለሱ ብሎ አስረግጦ ታሪካዊ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በር ላለመዝጋት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች ላይ መግለጫ እንዳይጥ በሚል ተልካሻ ምክንያት የኮሚቴው ሃሳብ በዝርዝር ለህዝብ ሳይገለጽ ለቀጣይ ስብሰባ ተላልፏል። ይህን ስብሰባ ያካሄደው ኮሚቴ ከፍተኛ የአገር ጉዳይ ተሸክሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናን የልብ ትርታ የሆነ አንገብጋቢ ጉዳይን የተበላሸ የዕድር ስብሰባ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አድርጎታል። በጣም ያሳዝናል። በታሪክም ያስጠይቃል።

በዚህ እግዚያብሔር ባመቻቸው ወሳኝ ጊዜና ወቅት እልባት ካልተገኘ መቼ ሊገኝ ይችላል? ውግዘቱ እያለ አባቶች ተገናኝተው ኪዳን ካደረሱና በጋራ “ቅዱስ” ካሉ፣ ማዕድ ከተቋደሱ፣አብረው ሁሉንም ነገር ከከወኑ ግዝት ማለት ውሉን ስቷል ማለት ነው። እውነትም ወፈ-ግዝት። በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፣ በምድርም የፈታኽው በሰማይ የተፈታ ይሆናል የሚለው አምላካዊ ቃል ተረት ተረት ሆኗል ማለት ነው። ግዝቱ ሳይወርድ ማን እየተባባሉ ሊጠራሩ ነው። ወይንስ በመልዕክተኛና በስማ በለው በተለያየ ክፍል ነበር ጉዳዩ የተከናወነው። ጉዳዩ የመብልና የመጠጥ ወይም የግል ጠብ አይደለም። ጉዳዩ እጅግ ከፍተኛና አንገብጋቢ የሆነው የቀኖና ቤተክርስቲያን ጉዳይ መሆኑ ልብ ያለው ልብ ይበል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከአጼ ዘርያቆብ ዘመነ መንግስት (1444-1468 ዓ.ም. ) አንስቶ በስራ ላይ የዋለውን የቤተክርስቲያኗ መተዳደሪያ ሕግ የሆነው ፍትሃ ነገስት ላይ ስለ ሹመት አስንቶ አንቀጽ 4 ቁጥር 70 ላይ በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ እንደተቀመጠው ይህች ሹመት በ፩ ዘመንና በ፩ ሀገር ለሁለት ሰዎች ልትሆን አይገባም። ይህ በአንድ ሀገር ከተደረገ ግን አስቀድሞ ለተሾመው ትጽና። ለሚገባቸው ሰዎች በሁለት ሀገሮች ብትሰጥ ልማድ ተገቢ በሚያደርገው አገር አስቀድሞ ለተሾመው ትጽናለት። ይህ በአንዲት ቦታ ቢሆን አስቀድሞ ለተሾመው ትጽና። ይህ በአንድ ጊዜ ቢሆን ከነርሱ አንዱም አንዱ ሊተዋት ይገባል። መራጮችም አስቀድሞ የተሾመውን መምረጥ ይገባቸዋል። ተካክለው ቢገኙ በታቦቱ ፊት ቆመው በዕጣ ይሁን። በዚህም መሰረት አስቀድመው ለተሾሙት ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሪዎስ ሥስጣናቸውን መልሰው በመስጠት ፋንታ ህገ ወጥ ተግባራቸውን በቤተክርስቲያንና በምዕመናን ላይ ለመጫን እንቅልፍ አጥተው በመራወጥ ላይ የሚገኙት። ይህንን የቤተክርስቲያንችንን የማዕዘን እራስ የሆነ የማይሻር፣ የማይተካ፣ የማይሰረዝ፣ የማይደለዝና ከሰዎች የግል ሥስጣንና ጥቅም ጋር የማይለወጥ ህግ በጫማቸው እረግጠው ነው እነአቡነ ገሪማ ለሹመት በመተራመስ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እያላገጡ  የሚገኙት።

ገና እርቅ ይመጣል ተብሎ የቤተክርስቲያኗ ስርዓት በድጋሚ ሊጣስ አይገባውም። ሲሆን የሚገባው የተበላሸውንና የተጓደለውን አስተካክሎ ለአንዴና ለመጨረሻ የቤተክርሲቲያኗን አንድነት መገንባት ነበር። በእውሸት ላይ የተመረኮዘ ዕርቅ ቢመጣም ስር ስለሌለው አይጸናም። እውነትንና ጽናትን ለትውልድ ሳይሸራረፍ በተሟላ ሁኔታ ማስተላለፍ ይዋል ይደር የሚባልበት ጉዳይ አይደለም። ከዚህ ውጭ ሁለቱንም ወገኖች ብዙ የሚያራምዳቸው አይሆንም። ነገሮች ይለወጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ነገሮች ብሰው ተገኝተዋል። ከሚሰጡት የሬዲዮ መግለጫዎች እስከ ስብሰባው ፍጻሜ ያለውን መመልከት ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው።

ስለሆነም ለሃያ ዓመታት ቤተክርስቲያንን ሲያናውጥ ለነበረ ችግር ትክክለኛና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ሁሉም ምዕመን የዚህ የዛ ሳይባባል የጋራ ድምጹን ፓትርያኩ እንዲመለሱ በማሰማት ለአንዴና ለመጨረሻ ችግሩ እንዲቀረፍ የበኩሉን የምዕመንነቱንና የዜግነቱን አስተዋኦ ማበርከት ይጠበቅበታል። አባቶችንስ አየናቸው። ትናንት በአባ ጳውሎስ እምቢተኝነት ሲያመካኙ ቆይተው አሁን ደግሞ “እሽ ይመለሱ ብንልም መንግስት አይደግፋቸውም” አሉ። ወያኔ በወኪሉ በፕሬዝዳንት ግርማ ደብዳቤ ይመለሱ ብሎ ሲያረጋግጥ የአዲስ አበባው አባቶች ቅዱስ ፓትርያርኩን “ለሃገራችው አፈር ይብቁ በሚሰጣቸው ቦታ ይቀመጡ” ብለው ለራሳቸው መንበሯን እያዩ እየቋመጡ እንቅፋት መሆናቸውን ሕዝብ ጠንቅቆ የተገነዘበ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። ልቦና ይስጣቸው፣ ለሚያልፍ ቀን ይህችን ታሪካዊት፣ በብዙ መስዋዕትነትና የእግዚያብሔር ቸርነት ተጠብቃና ተከብራ የነበረች ቤተክርስቲያንን አዋርደው ለአዋራጅ ዳርገዋታል። የጊዜ ጉዳይ ነውእንጅ ቤተክርስቲያን የቀደመ ክብሯንና አንድነቷን ስትጉናጸፍ  የተዋረዱና የቀለሉ እነሱ መሆናቸውን ታሪክ ሲዘግበው ይኖራል።

በዚህ ግትርና እውነቱን ያላገናዘበ አቋም ምክንያት የዳላሱ የእርቀ ሰላም ውይይት ገንዘብ በማሰባሰብ ለሌላ ቀጣይ ስብሰባ ያለውጤት ተበትኗል። ለቀጣይ አራተኛ የተበላሸ የዕድር ስብሰባ። መግለጫውንና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን አካተን በተከታታይ መረጃዎችን እንደምናወጣ እንገልጻለን። ማንም ወደደም ጠላም ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ያነጻትና ቤተክርስቲያን አንድ መሆኗ አይቀርም። ይህ ሁሉ አልፎ፣ ቸሩ እግዚያብሔር የቤተክርስቲያናችንና የአገራችንን ትንሳዔ ያሳየን።