ስለ እውነት፤ እውነት የት ነው?


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ስለ እውነት፤ እውነት የት ነው?

የዛሬን አያድርገውና የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እውንተኛ ሊቃውንት ስለነገረ መለኮት የሰጡት ምስክርነትና እውነት ጊዜና ታሪክ የማይሽረው ዛሬ አንዳንዶች ሊያስተካክሉትና ሊገለብጡት ቢሞክሩም እውነተኛ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ግን አረጋግጠውት ወንጌል የሚያስከፍለውን የደም ዋጋ እየከፈሉ አልፈዋል። የእነኛን እውነተኛ የተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ኮቴ እየተከተሉ ያሉትም በብዙ መከራና ጭንቅ እውነቱን እየመሰከሩ ይገኛሉ።ሆኖም ዛሬ በተለይ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የነገረ መለኮትን ትምህርት እያፋለሱ እያንሸራተቱ ወደ ካቶሊክና ፕሮቴስታንት ጉያ ሊከቱ ሲጣደፉ በሚሯሯጡበት ተዋህዶ ፈተናዋ በበዛበት በዚህ አጣብቂኝ ወቅት የተዋህዶን ሊቃውንት ምላሽ የሚሻ ጉዳይ ሆኖ ባለበት በዚህ ወቅት እድሉ ባያመልጠንስ  ሲሉ ዶክተር መርዓዊ ተበጀ የፃፉትና በድረገፅ የለጠፉት ፅሁፍ ለዚህ ጽሁፍ የጥያቄ ሃሳብ “ስለእውነት እውነት የት ነው?” በሚል ተጻፈ።

የተከበሩ ዶክተር መርዓዊ ተበጀ መጽፍዎት ጥሩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ “ፓትርያርክ እያለ፣ ፓትርያርክ አይሾምም” ፍትሃ ነገስት አንቀጽ 4 ቁጥር 70-78 ጠቅሰው አስቀምጠዋል። ነገር ግን እራስዎን በራስዎ ጠይቀው ህሊናዎት ለምን ያንን ጥያቄ እንደጠየቀ መልሱን ለእርስዎ ትተን “አንተ ለምን ዳር ዳር ትላለህ የሚለኝ ካለ ይሉና  በስደት ያሉት ፓትርያርክ በዘመነ ደርግ የፈጸሙት በደል ኖሮ ከመንበረ ፕትርክናቸው የሚያስወርድ በደል ከተገኘባቸው እንደ ብጹዕ አቡነ መልከ ጸዲቅ በቀኖና ቤተክርስትያን ይታይባቸው ባይ ነኝ”  ብለዋል። ይገርማል!

የተከበሩ ዶክተር መርዓዊ ለመሆኑ ብጹዕ አቡነ መልከ ጸዲቅ እርስዎ እንዳሉት ከሆነ ምን ብለው ነው የተወገዙት? ጭብጡስ ምንድንነው? ወይንስ አህያ በበላ ዳዋ ተመታ እንዲሉ ሆኖ ነው? ባልተወሰነ ነገር አሉባልታን እስከዛሬ ተሸክሞ እንዴት ወደህዝብ ጭንቅላት ዛሬ ለመላክ በምን ነጥብ (አስተምህሮ) መነሻዎት ምንድን ነው? ከየት መነጨ? ወሬውስ በነማን ተሰራጨ? በየትኛው ሲኖዶስ? መቼ? በምን እርዕስ ተወገዙ? የውግዘቱ ውሳኔና ነጥቦቹስ ምንድን ናቸው?

ነገረ መለኮቱን ህዝብ ማሰልቸት ይሆናል ብለው ለዓመታት እርስዎ ካህኑ ከሸሹና ያልተወገዘን እንደተወገዘ አድርጎ አዛብቶ ማቅረብዎት ከምን አንጻር ነው? እንዴትስ ተሸክመውትስ እሰከዛሬ እያነከሱ ቆሙ? ማንን ለማስደሰት ይሆን? ማንም ሳይጠይቅዎት ዳር ዳር ትላለህ ብለው የራስዎትን ዳር ዳር ማለትዎትን መስክረዋልና ዳኝነቱን ለህሊናዎት ትተን እድል አያምልጠን ብለው እርቅ እንዲፈጸም በሚል ሃሳብ ጀምረው ለእርቅ እንቅፋት በሚሆን ሃሳብ ሲደመድሙት እርቅ እንዳይፈጸም የተወላገደ ሃሳብ ያቀረቡ አይመስልዎትም?

እድሉ አያምልጠን ሲሉ የእግዚአብሔር ሰው የሆኑትን አረጋዊውን አባት ብጹዕ አቡነ መልከ ጸዲቅን በነገር ዝርቅ (ተረት ተረት) ለፍርድ አቀርባለሁ ነው የሚሉን? ወይንስ ሌላ? የነገር መለኮቱ እውነት የት ላይ ነው? ይህ ካልሆነ ስህተት ሲደጋገም ብዬ ሰባት ገጽ ጻፍኩኝ ብለው እንዳሉት ሁሉ ስለነገረ መለኮቱ ምን ይላሉ? ስለምንስ ይህንን መድፈር ተሳነዎት?

በአጠቃላይ ሌሎች ሊቃውንተ ቤተክርስትያን በያላችሁበት፣ ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ፣ የሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሎጅ፣ ቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና ሌሎችም ይህ አሳሳቢ ጉዳይ የሚመለከታችሁ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ዶክተር መርዓዊ ተበጀ ብጹዕ አቡነ መልከ ጸዲቅ ተወገዙ ያሉበትን ጉዳይ እንዴት ታዩታላችሁ?       ስለ እውነት፤ እውነት የት ነው?

ቸር ይግጠመን።

ከእውነቱ ታየ

December 2, 2012