“እግዚአብሔር የቀባው”
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ጽሁፉን በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ። “እግዚአብሔር የቀባው”
“እግዚአብሔር የቀባው”
ቀሲስ አስተርአየ
ሕዳር ፳፩ ቀን ፪ሽ፭
“እግዚአብሔር የቀባው” የምትለውን አነጋገር ብዙ ሰው በተደጋጋሚ ይናገራታል። ከየት መነጨች? ጠቀመች? ወይስ ጎዳች? ሊቃውንቱስ እንዲት ይተረጉሟታል?
ነቢዩ ዳዊት ባንድ ወቅት “እግዚአብሄር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ” (፩ኛ ሳሙ ፳፮፡ ፲፩) ብሎ ተናግሮ ነበር። በእውነት ይህ ቃል በሥልጣን በተለይም በክህነት አገልግሎት ያሉትን ሰዎች እግዚአብሔር የቀባቸው ናቸውና ቢሳሳቱም “እግዚአብሄር ይቅጣቸው” ብሎ ህዝብ እንዳይናገራቸው፤ እንዳይወቅሳቸውና እንዳይከሳቸው የሚከለክልና የሚያግድ ነውን?
ዳዊት “እግዚአብሄር በቀባው ላይ እጄን አልዘረጋም” ያለው፤ “አማልክተ ኢትህሚ ወለመኮንነ ህዝብከ ኢትበሎ እኪተ“ (ዘፍ ፳፪፡፳፰) ማለትም፦ “መሪህን አትንቀፍ አትተችም” የሚለው ህግ ያለ ምንም ገደብ እንዲጠበቅ አልነበረም። ስልጣኑን ወይም ክህነቱን መጋረጃ አድርጎ የፈለገውን ስህተት በህዝብ ላይ የሚፈጽም ማንም ሰው በዝምታ እንዲታለፍም አልነበረም።
ታሪኩ ባጭሩ እንደዚህ ነው። ሳኦል ዳዊትን አሳዶ ለመግደል ቀንና ሌሊት ይጥር ነበር። ከእለታት አንድ ቀን አቢሳና ዳዊት ሳኦልን እንቅልፍ ጥሎት አገኙት። አቢሳ “ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ ላይ ጥሎታልና እንደተኛ ባንድ ውግ ብቻ ገድየው ልገላግልህ? ብሎ ዳዊትን ፈቃድ ጠየቀው (ሳሙ ፳፮፡፰)። ዳዊት ግን “ሕያው እግዚአብሄር ይመታዋል። ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል። ወደ ሰልፍ ወርዶ ይገደላል” የሚል የትንቢት ቃል ተናገረ።
ዳዊት እንዳለውም፤ ሳኦል ከሌላ ሰራዊት ጋራ ለመዋጋት በተሰለፈበት ድል ተነስቶ ራሱን በራሱ ገደለ (፩ኛ ሳሙ ፴፩፡፩᎗፲፫)። ዳዊት በሳኦል ላይ እጄን አልዘረጋም ያለው፤ የሳኦልን ስልጣን ከመረከቡ በፊት የሳኦል ህይወት እንዴት እንደሚቆም በእግዚአብሔር መንፈስ አስቀድሞ ስለተረዳ ነበር።
“እግዚአብሄር በቀባው ላይ እጄን አልዘረጋም” ያለው ዳዊት፤ አስመሳዮችና በወሬ የሚተዳደሩ ሰዎች ደፍረው የማይናገሩት፤ የማይታለፍ ሊገለጽ የሚገባ የፈጸመው የተቀደሰ ነገር አለ። ሳኦል ከሌላ አቅጣጫ ከመጣበት ሰራዊት ጋራ ሲዋጋ ተሸንፎ ተስፋ ቆረጠና “በጣላቶቼ እጅ ከመውደቅ ግደለኝ” ብሎ የራሱን ጋሻ ጃግሬ ለመነው። ጋሻ ጃግሬውም አልገደለውም። ሳኦል እራሱን በራሱ ገደለ። ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል ራሱን በገደለበት መንገድ እዜያው ላይ ራሱን ገድሏል” (፩ኛ ሳሙ ፴፩፡፭)። የተፈጸመው ታሪክ ይህ ሆኖ ሳለ፤ ግርግሩን በመጠቀም ሹመት ሽልማት የፈለገ፤ ባካባቢ ሆኖ ይህንን የተመለከተ ወሬኛ፤ ዳዊት ያለምንም ተቀናቃኝ እንደሚነግሥ ተረድቶ፤ ይህን ይዤ ወደ ዳዊት ብቀርብ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ በመገመት ያልገደለውን “እኔ ሳኦልን ገደልኩልህ” እያለ ዳዊትን ቀረበው። ዳዊት በከንቱ ውዳሴ ህሊናውን ያላስጎነበሰ፤ በወሬ ሹመትና ሽልማት ለማግኘት የተቅነዘነዘውን ወሬኛ ሰው ለነገር አቀባይነት ይጠቅመኛል ሳይል መቀጣጫ ይሆን ዘንድ በሚመራው ህዝብ ፊት ቀጣው (፪ኛ ሳሙ ፩፡፲፮)። ይህ የዳዊትን ማንነት የሚገልጽና ጊዜ ላነሰው ባለ ስልጣን ነገር በማቀበል ለሚኖሩት ወሬኞች ተግሳጽን ያዘለ ትልቅ ትምህርት ነው።
ጥልቅና ምጡቅ በሆነ ምክንያትና ግንዛቤ “እግዚአብሄር በቀባው ላይ እጂን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሄር ከኔ ያርቅ” (፩ኛ ሳሙ ፳፮፡ ፲፩) ብሎ ዳዊት የተነገረውን ያልተረዱ ብዙ የዋሀን ሰዎች ሸፍጠኞችን ቢቃወሙ የሚቀሰፉ እየመሰላቸው፤ ጳጳስ ሰረቀ፤ ዘረፈ፤ ዋሸ፤ ዘሞተ፤ ወለደ የሚል ነገር ሲሰሙ መቃወማቸው ይቅርና “ኧረ ኧረረረረ መስማቱም ኃጢአት ነው!” ይላሉ። ሸፍጠኞችም ይህንን ጥቅስ እንደ ማስፈራሪያ አድርገው በመጠቀም መጋረጃ አርገውታል። ይህ አይነት መንፈስ ከዳዊት አባባል ጋራ ፈጽሞ የሚገናኝ አይደለም። ሊቃውንቶቻችንም አይቀበሉትም።
የሊቅውንቶቻችን የነ ኔታ አንዳርጌ ግንዛቤ
ከዕለታት አንድቀን አንድ በሰው ፊት የተከበሩ፤ ውስጣቸው ግን የተበላሸ ሰው፡ ውሻ ገደል ከሚባለው ቦታ ላይ ስህተት ፈጸሙ። “ስህተቱ ቢገለጽ እግዚአብሄር የቀባቸውን ክብር መንካት ነውና ዝም በሉ ሰውየውንም ሸፍኗቸው” ተባለ። ሰውየ ግን ይህንን ሽፋን በመጠቀም ወደ ጫጋልና ደብረ ጽጌ እየተዘዋወሩ በስህተቱ ቀጠሉ። በመጽሐፋዊው ቅኔያቸው የተደነቁት የደብረ ሊባኖሱ ገዳም የቅኔ መምህር የነበሩት፤ በኋላ ወደ ተወለዱበት አገር ብቸና ጊዮርጊስ ተመልሰው ያረፉት መሪጌታ አንዳርጌ ካሳ። “ካህን ቢሳሳት እግዚአብሄር የቀባው ነውና አትናገረው” የሚባለው ነገር ወደ ተሳሳተ ባህል ተለውጦ ህዝብ በመጉዳት ላይ መሆኑን በመግለጽ በመጻሕፍት ላይ መስርተው ሙሉ ቤት ዘረፉ። ቅኔው የገዳሙን ሊቃውንት አንቀሳቀሰ። ተመሳሳይ ችግር የነበረባቸው በሳቸው ላይ እያጉረመረሙ ተነሱባቸው።
በዚያው በውሻ ገደል ይኖሩ የነበሩት፡ የስመ ጥሩው የስሬው ቅኔ መምህር የኔታ ጥበቡ ደቀ መዝሙር የነበሩት፡ ሌላው የገዳሙ የቅኔ መምህር የኔታ አምዴ፡ የሳምንቱ የቅኔ ባለተራ ስለነበሩ በእጣነ ሞገር ቅኔያቸው የእለቱን ቅዱስ ካወሱ በኋላ፡ በአሰረ ንጉሡ ላይ የየኔታ አንዳርጌን ቅኔን የሚደግፍ በሊቃውንቱ ፊት ተቀኙ። በብህትውናቸው በቅድስናቸው የሚደነቁ የኔታ ላእከም፤ ግርማ በተሞላበት ድምጻቸው “ይበል” ብለው ከቀመጡበት ብድግ አሉ።
የኔታ አንዳርጌም “ስህተቱ ቢገለጽ እግዚአብሄር የቀባቸውን ክብር መንካት ነውና ዝም በሉ ሰውየውንም ሸፍኑት” እያሉ የሚያስተምሩ ሰዎች የሚቀጥሉና፤ ሕዝቡም ትምህርቱን አምኖ የሚቀበለው ከሆነ፤ ነውር ነው ተብሎ ሊታፈርበት የሚገባው ሁሉ ኃጢአት ባህል ይሆናል። መዋረድና ማፈር የሚገባቸው መልካም እንደሰሩ ሆነው ይሸለሙበታል። የሞራል፤ የስነ ምግባር ሰዎች፤ አንገታቸውን እንዲደፉ፡ እንዲናቁ፡ እንዲዋረዱና እንዲያፍሩ ይደረግበታል ብለው ከሳቸው በፊት የነበሩት አለቃ ንጉሤ የሚባሉት ሊቅም በዚህ ላይ የተቀኙትን ነግረውናል። ቅኔውም እንደሚከተለው ነው።
አይቴኑ ለነውር ብሔረ ሙላዱ፤ በውስተ ኩሉ ብሔር እስመ ከመነግድ ይሄሉ።
ትምህርተ ዝኒ ነገር ከመ ይትግሀድ ለኩሉ።
ኀጥዕ ይሳለቅ ላዕለ ጻድቅ፤ ከመ ዘንጹህ ወሠናይ ባህሉ።
እስመ እንዘ ሠርዌ በውስተ ዓይኑ፤ እምዓይነ ቢጹ ብሩህ አውጽኦተ ሠርዌ ዘያስተዴሉ።
አይሁድሂ ሐዋርያት በጽእለቶሙ ጸአሉ።
አብዳነ ዝንጉአነ ወሐሳውያነ እንዘ ይብሉ።
እስመ እንዘ ብእሴ ጻድቀ ዘሀለዎሙ ይስቅሉ።
ውጹአን እምነ ጽድቅ በጽድቅ ርእሶሙ ተለአሉ።
የቅኔው ይዘት ባጭሩ “አይቴኑ ለነውር ብሔረ ሙላዱ” ነውር ሊታፈርበት ሲገባ እንደሙያ ሆኖ እንደ ቅኔ የሚፈልቀው ኧረ ከየት ነው? እያሉ በመደነቅ ምንጩን ከጠየቁ በኋላ፤ “በውስተ ኩሉ ብሔር እስመ ከመነግድ ይሄሉ” ማለት “አሁንማ አገሩን ሁሉ ወሮት ያደልደረሰበት ምን ቦታ አለና፡ የነውርን መነሻ አጠያየቀኝ” ይሉና፤ “ኀጥዕ ይሳለቅ ላዕለ ጻድቅ፤ ከመ ዘንጹህ ወሠናይ ባህሉ” ማለትም ይህን ነገር ባጭር ካልቀጨነው ማፈር የሚገባው ነውረኛ፤ ንጹህ ባህል እንደሚከተል ሆኖ ደህነኛውን እንደሞኝ እንዳልተማረ በማየት ያጃጅለዋል። ካሉ ባኋላ ቀጠሉን “ውጹአን እምነ ጽድቅ በጽድቅ ርእሶሙ ተለአሉ” በማለት ቅኔውን ደመደሙ። ማለትም፦ ከመስመር የወጡት ነውረኞች በነውራቸው ይኩራራሉ ያልገባው ህዝብም ያከብራቸዋል። ወጣቱም እንደምሳሌ ይወስደውና መመለሻ ከሌለው ሞራል ውድቀት ውስጥ መውደቅ ይመጣል።
የኔታ አንዳርጌ ይህን ያለቃ ንጉሤን ቅኔ አስታውሰው የነገሩን፤ “እግዚአብሄር በቀባው ላይ እጂን አልዘረጋም” የሚለው አነጋገር ህዝቡን አፈዘዘው። ሞራለ ቢሶችንም መረን ለቀቃቸው ብለው በዘረፉት ቅኔ የተነኩ ሁሉ በወቀሷቸው ጊዜ፤ የተሰለፉበት ሙያ እንዳስገደዳቸው ባያደርጉት ግን ከሳቸው በፊት ከነበሩት መምህሮቻቸው የተረከቡትን የሞራል ሃላፊነት ለመወጣት እንዳደረጉት ለማሳየት ነበር።
እኔም ያለቃ ንጉሤንና የመምህሮቼን የየኔታ አንዳርጌንና የነ የኔታ አምዴ ብቃትና ችሎታው ባይኖረኝም። ጳጳሱ ወለደ፤ ከመንግስትና ከነጋዴ ጋራ የጥቅም ተሻሚ ሆነ፤ “ዋልባ የገባ አይወጣ፡ ከል የገባ አይነጣ” እየተባለ ይነገርለት የነበረው መነኩሴ ሁሉ ዋልባን እየለቀቀ ወደ ከተማ በመገስገስ ከህዝብ ጋራ እየተጎራበተ ማህበራዊ ኑሮ ጀመረ ሲባል እሰማለሁ፤ አያለሁም። በሌላ በኩል ደግሞ “እግዚአብሄር በቀባው ላይ መናገር ልክ አይደለም” የሚሉ ሰዎችም ገጥመውኛል። ታዲያ ከመምህሮቼ የሰማሁትን የዘረፉትንም ተቀብየ፤ እራሴ ሙሉ ቤት ቆጥሬ ነግሬበት እንዴት ሳልመሰክር ልለፈው?
ዳዊት በእግዚአብሄር ተመርቶ “እግዚአብሄር በቀባው ላይ እጂን አልዘረጋም” ያለበትንም ምክንያት ተረድቶ የተፈጸመውን ቅዱስ ተግባር፤ ለጥፋት ለኃጢአትና ለበደል መጋረጃ ማድረግ፤ በበደል ላይ በደል፤ በኩነኔ ላይ ኩነኔ፤ መፈጸምና ተያይዞ መጥፋትን የሚያስከትል እንጅ፤ ትህትናን ወይም ጻድቅነትን አያተርፍም። እነ ቅዱስ ጳውሎስም “እግዚአብሄር በቀባው ላይ እጂን አልዘረጋም” የሚለውን በዚህ አይነት ሽባ በሆነ መንፈሰ አልተረጎሙትም። የቅዱስ ጳውሎስን አቋም እንመልከት።
የቅዱስ ጳውሎስ አቋም
ባንድ ወቅት “የእግዚአብሄርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን”(፳፫፡፬_፭)። ብሎ አንድ ያልተረዳ ሰው ለቅዱስ ጳውሎስ ጥያቄ አቀረበ። ቅዱስ ጳውሎስም “ሊቀ ካህን መሆኑን ባላውቅ ነው” ብሎ መለሰለት። ይህንን ለይተው ያልተረዱ ሰዎች፤ “አንድ ጊዜ ካህን ነህ፤ ወይም ሹም ነህ ከተባለ በኋላ፤ ካህንን ወይም ጳጳስን መዝለፍ ትክክል አይደለም” ይላሉ። ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ንግግርም ለጥፋተኞች መጋረጃ በመሆን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከከፍተኛ ጉዳት ላይ ከጣሏት አስተሳሰቦች አንዱ እንደሆነ ለማየት እንሞክር።
ቅዱስ ጳውሎስ “ወኢያድሉ ለገጽ ወኢይንስኡ ሕልያን ፡እስመ ሕልያን ያዐውሮ ለጠቢባን ወያሴስሎ ለቃለ ጽድቅ“(ዘዳ ፲፮፡፲፱) የሚለውን፤ ማለትም፦ ዳኛ መዛኝ እንደሆነ፤ ዳኝነት መመዘን ሲሆን፤ ህግ ደግሞ ሚዛን እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ያውቃል። መማለጃ (ጉቦ) ዳኝነትንና ሚዛናው ፍትሕን ነቃቅሎ በመጣል ህብረተ ሰብን በድቅድቅ ጨለማ የሚጥል እንደሆነ ተምሮ የተረዳ የህግ ምሩቅ ነው። ህግ ተምሮ ማወቁ ብቻ ሳይሆን “እግዚአብሔር ቆመ ውስተ ውስተ ማኅበረ አማልክት። ወይኴንን በምእከለ አማልክት . . . ፍትሑ ለነዳይ.. ወአጽድቁ ግፉዐ ወምስኪን“ መዝ ፹፩፡፩_፬) ማለትም_እግዚአብሔር በፈራጆች መካከል ቆሞ ይፈርዳል። ስለዚህ ለተበደለው ለተገፋው ፍረዱ”ብሎ ዳዊት የተናገረውን ደጋሚ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ፦
- ፍርድ ቤትን፡ ከቤተ መቅደስ፤
- ፈራጅን ከካህን፤
- ፍርድን ከቅዳሴ
ለይቶ ለማያት ህሊናው፤ ትምህርቱና እምነቱ አልፈቅዱለትም። ከእለታት አንድ ቀን በፍርድ አደባባይ ተከሶ ቆመ።
“ወንድሞቼ ሆይ እኔ እስከዚህች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ”(የሐዋ ፳፫፡፩) በህግ ፍረዱብኝ እያለ ራሱን ለትክክለኛ ፍርድ አዘጋጅቶ አቀረበ። ዳኛው ሚዛናዊ ፍርዱን ጥሎ፤ ጳውሎስን አፉን በጥፊ እንዲመቱት ሰዎችን አዘዘ(፪)። ጳውሎስ የህግና የሞራል ሰው ስለነበረና ህግ ሲጣስ ሞራል ሲደመሰስ አላስችለው አለ። “አንተ በኖራ የተለሰንክ ግድግዳ! እግዚአብሔር ይምታህ! በህግ ልትፈርድብኝ በህግ ወንበር ላይ ተቀምጠህ ሳለህ፤ ያለ ሕግ እንድመታ እንዴት ታዝዛለህ? (የሐዋ ፳፫) ብሎ ዳኛውን ገሰጸው። አንድ አድርባይ “የእግዚአብሄርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን”(፳፫፡፬_፭)። ብሎ ጳውሎስን በፍርዱ አደባባይ ላይ አፋጦ ያዘው።
“ስሜን በማያምኑ ህብረተ ሰብ መካከል ያንጸባርቅ ዘንድ አገልጋይ እንዲሆነኝ መርጨዋለሁ” (የሐዋ ፱፡ ፲፭) ብሎ ክርስቶስ የመረጠለትን ሐዋርያዊ አገልግሎት በዝምታ፤ በይሉኝታና፤ በፍርሀት ረግጦት ማለፍ ለጳውሎስ ትልቅ ክህደት ሆነበት።
“የእግዚአብሄርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን” ሲባል በመስማት ብቻ፤ ውስጡን ጠልቆ ሳይረዳ ያፈጠጠበትን ግለ ሰብ፤ ዳኛውንና ባደባባይ የተሰበሰውን ህዝብ ለማስተማር ቅዱስ ጳውሎስ እድል አገኘ። ቅዱስ ጳውሎስ ህጉን ከዳኛውና ከግለ ሰቡ ይልቅ የበለጠ እንዲሚያውቅና ለህጉ እንደቆመለት ለመግለጽ ሲል “አማልክተ ኢትህሚ ወለመኮንነ ህዝብከ ኢትበሎ እኪተ“ (ዘፍ ፳፪፡፳፰ ማለትም፦ በህዝብህ አለቃ ላይ ክፉ አትናገር” የሚለውን ከህግ ጠቅሶ “ሊቀ ካህን መሆኑን ባላውቅ ነው” ብሎ የጥብቅና አመላለስ ባደባባይ መለሰ።
የኢትዮጵያው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከዚህ በላይ የተገለጸውን እንዴት እንደሚገነዘቡት ከዚህ በታች እንመልከት። ቅዱስ ጳውሎስ “ሊቀ ካህን መሆኑን ባላውቅ ነው” ያለበት ምክንያት፦
ካህኑና ህጉ አልተዋወቁም። መዛኝነቱንም አላወቀም። ባለማወቁም የህጉን ሚዛንነት ሰበረው። ለቅዱስ ጳውሎስ ይህ በህዝብ ፊት የተፈጸመውን የተደራረበ ስህተት ሳይቃወም ማለፍ መስማማትና ማጽደቅ ስለሆነ ከራሱ ህሊና ጋራ መጋጨት አልፈለገም። “ወንድሞቼ ሆይ እኔ እስከዚህች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ”(የሐዋ ፳፫፡፩) እያለ የመሰከረለትን የራሱን ህሊና መካድ ሆነበት።
ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሄርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን”(፳፫፡፬_፭)። ተብሎ ሲጠየቅ “ሊቀ ካህን መሆኑን ባላውቅ ነው” ብሎ የመለሰው፤ ለተሳሳተው ዳኛና፤ ለስህተት መጠቀሚያ ሆኖ ለቀረበው ህግ እውቅና በመስጠት የራሱን ህሊና እንዳያጎድፍ እንጅ ለተሳሳተው ካህን ወይም ዳኛ ክብር ለመስጠ አይደለም። ምክንያቱም ጳውሎስ “በሕግ ለመፍረድ በህግ ወንበር ላይ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ህግ እመታ ዘንድ ታዝዛለህን”(፫) በማለቱ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ እንዲመታ ያዘዘው ካህንና ዳኛ እንደሆነ ያውቃል። ይሁን እንጅ በፍርድ ወንበር ላይ የተቀመጠው የሚሰራውንና ያለበትን ሀላፊነት ሳያውቅ፤ ያለ ቦታውና ያል አቅሙ ተቀምጦ፤ ያለበትን ቦታና ፍርድን እያረከሰ ስለሆነ የጳውሎስ ሕሊና ሊቀበለው ይቅርና “አንተ በኖራ የተለሰንክ ግድግዳ እግዚአብሔር ይምታህ። በህግ ልትፈርድብኝ በህግ ወንበር ላይ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እንድመታ እንዴት ታዝዘለህ? (የሐዋ ፳፫ ) ብሎ ባደባባይ በህዝብ ፊት ዳኛውን ከዳኝነቱ አውርዶ ጣለው።
ቅዱስ ጳውሎስ ይህን የመሰለ ደካማ ባህርይ ያለውን ሰው እውቅና ሰጥቶ ከሚደርስበት ጊዜአዊ ችግር ከማምለጥ ይልቅ፤ እውቅናውን ነፍጎ የሚደርስበትን ስቃይ መቀበሉን መረጠ” ይላሉ ያብነቱ ጉባኤ ሊቃውንት።
እነዚህን የመሳሰሉ ጥልቅ ግንዛቤና ማስተዋል የሚጠይቁ ነገሮች ተብራርተው ለህዝብ ባለመነገራቸው፤ ላድር ባዮች ወይም ግንዛቤ ለሌላቸው ሰዎች “ሹም ዳኛ(ካህን) እግዚአብሔር የቀባው ወይም በእግዚአብሄር ፈቃድ የተሰየመ ነውና አትናገረው” እንዲሉ ምክንያት ሆኗቸዋል። ለብዙ ዘመን ሲነገሩ በመኖራቸው ወደ ባህል በመለወጥ ለህዝብ መጉጃም ሆነዋል።
ማንም ግለሰብ ይህንን ጥልቅ ግንዛቤ ሳይረዳ “የእግዚአብሄርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን”(፳፫፡፬_፭) ብሎ የተሳሳተውን ለመጋረድ መሞክር፤ ያለህግ ለተቀመጠ የኖራ ልስን ዳኛ (ካህን) ጀሌ መሆንን ያስከትላል። ይህን የተናገሩ እነ ነቢዩ ዳዊትና እነ ቅዱሳን ጳውሎስ ናቸው። ሲናገሩትም መስዋዕትነትን በሚጠይቁ ጊዜዎች ትምህርት ለመስጠት እንጅ ለሸፍጠኖች ሽፋን ለመስጠ አልነበረም።
እስቲ ቆም ብለን እናስብ! ያስቀመጥነውን ከቦታው ስናጣው ትእግስት የሌለን። ቤታችን ሲዘረፍ፤ ገንዘባችን ሲወሰድ፤ የልብሳችን ጫፍ ስትነካ፡ ባንዲት ሳንቲም ስንበለጥ ለመብታችን የምንታገል ሰዎች ስንሆን፤ ዳኛ የእውነት ሚዛንነቱን ሲሰብር፤ የተቀደሰውን ፍርድ ሲያረክስ፤ ለእምነት ለመንፈሳዊነት ለቅድስና ለሞራል ለታማኝነት ምንጭና መለኪያ ናት በምንላት ቤተ መቅደስ ይህ ሁሉ የሞራል ድቀት ጎርፍ ሲያጥለቀልቅ “እግዚአብሔር የቀባውን መናገር ኃጢአት ነው” እያልን ዝም ማለት ተገቢ ነውን? ለመሆኑ የእግዚአብሄር ቅባት ምንድነው? የእግዚአብሄር ቅባት በዚህ መንገድ የምንጠቀምበት ከሆነ እያረከስነው መሆናችንን አናስተውልምን?
ባለንበት አገር የሚኖረው ህዝብ የሚያደርገውን እንመልከት! ዓለማውያን መሪዎች ሲባልጉ “ለዓለማዊ ህይወታችን ምሳሌ ልትሆኑን አትችሉም” ብለው ሲያባርሯቸው እየተመለከትን ነው። “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም እንደ እኔ ቅዱሳን ሁኑ” የሚለውን ትእዛዝ ለማክበር ከተቀደሰው ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብተው አ፩ዱ አብ ቅዱስ የሚሉ አይደሉም። “ቅዱስ” ብለው ኪዳኑንም የሚመሩ አይደሉም። ይሁን እንጅ ህጸጽ የተገኘባቸውን “እግዚአብሄር ይይላቸው እንጅ እኛ ምን አገባን” ብለው አይሸከሟቸውም።
በዚህ መንገድ የኛን ስንመለከተው ከሁሉም እራቀ። ወንጌሉ የሚነገርበትን ፈረንጆች stage ብለው ከሚጠሩት አብልጠን ቅዱስ ለማድረግ ስንል “አውደ ምህረት” እንላለን። ፈረንጆች መታሰቢያ ያሉትን፤ እኛ “ሥጋውና ደሙ” እንለዋለን። የሚከናወንበትን “ቤተ መቅደስ” ብለን በማክበር ቅዱሳን ሕጻናት እንኳ እንዳይደርሱበት እንከላከላለን። ካህናትን በተፈጥሮ ህግና በወንጌል በተደነገገው ቁዱስ ጋብቻ የተወሰኑና የእግዚአብሄር አይኖች፤ የንስሀ አባቶች ናቸው እንላለን። ፤ ጳጳሶቻችን ሴት የማያዩ ገንዘብ የማይወዱ ዓለምን የናቁ ብጹአን ቅዱሳን ናቸው እንላለን። መነኮሳት በገንዘብና በሴት መከሰስ ይቅርና ከየገዳም መውጣት የለባቸውም የሚል ስርአትም ያለን ሰዎች ስንሆን፤ እንደኛ ይህን ያህል የተደራረበ የቅድስና ስርአት በሌላቸው ላይ ይህን ያህል መዘርክረክ ሳይታይባቸው፤ ለምንድነው በዚህ ዘመን በእኛ ይህን ያህል የተዝረከረከ ነገር የተከሰተው? “እግዚአብሄር በቀባው ላይ እጂን አልዘረጋም” የሚለው የተቀደሰ ቃል በተሳሳተ መንፈስ ሲነገር በመኖሩ አይደለምን? ሌላ ምክናያት አለ?
በቤተ ክህነቱ ላይ ቀጣፊ፡ አታላይ፡ ዋሾ፡ ዘራፊ፡ ከሀዲ፡ አድርባይና ቀላማጅ ተሰብስቦ ሲንጫጫበት “እግዚአብሄር ይውጉዳው እኔ ምን አገባኝ” ብለን ተስማምተንና ተቀብለን ለመኖር እንዴት እንወስናለን? ምን አይነት አዚም ዞረብን? በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን በዋሸንግተን ዲሲ ቅድስት ማርያም የተከሰተውን መልካም ምሳሌ ሳልጠቅሰው አላልፍም።
የተደራረበ ሸፍጡ፡ ቅጥፈቱና ክህደቱ አሰለችቷቸው የዋሸንገትን ቅድስት ማርያም ምእመናን በቅርቡ ያባረሩት ደፍተራ፤ ባንድ ወቅት “እጀን ከአፍአዊ እድፍ ጉድፍ ንጹህ እንዳደረኩ ንጹሀን ሆናችሁ ለመቀበል ባትቀርቡ እኔ ከበደላችሁ ንጹህ ነኝ” (ቅ ገ ፹፫ ቁ ፵፫) የሚለውን ቃል ከተናገረ በኋላ። እንደገና በዚያችው ቅጽበት ገልብጦ “እኛ ካህናቱ ብንሳሳት አትዩን ዝም ብላችሁ የምንነግራችሁን ስሙን” ብሎ ተናገረ ተብሎ፤ በይፋ በተነገረ ጊዜ፤ እንዴት ሰውን ሁሉ እንደ እቃ ቆጠረው? ብሎ ያላዘነ ሰው አልነበረም። ህዝቡ ነቅቶ በሱ ላይ የወሰደው ርምጃ ቢዘገይም፤ በሱና በመሰሎቹ የተወሰደው ርምጃ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ያሉትን አስመሳይ መነኩሴዎች ጳጳሳትና ካህናት ከያሉበት እየመነጠሩ ለማውጣት ለሚሞክሩ ቅዱስ ሞራል ላላቸው ክርስቲያኖች ቅዱስ ምሳሌ እንደሚሆን በሰፊው ተነገረ። ይህ በየቦታው ቢቀጥል ቤተ ክርስቲያናችንን ካማስተካከልም አልፈን፤ ኢትዮጵያን ካለችበት ማጥ ማውጣት እንደምንችል አልጠራጠርም።
ሸፍጠኞች የሚጠቀሷት እነሱን የምትደግፍ የምትመስል ምእመናንን የምታስፈራራ አንዲት ሐረግ አለችንና እሷንም አንመልከታት። “አንተሰ ሕዝባዊ አልብከ ሥልጣን ከመ ትኮንኖ ለካህን በእንተ መሥዋዕት አላ ሶበ ትሬእዮ ለካህን ይገብር ከመዝ ጉየይ ኀበ ክልእ መካን ወኢትኮንኖ”(ሃ. አ. ም. ፳፪፡ ፲፪) በማለት ሰለስቱ ምእት የተናገሯት ናት። ይህም ማለት “ክህነቱ የሌለህ አንተ ምእመን ሆይ! ካህኑ የምትነቅፍበትን ነገር ፈጽሞ፤ ለአምልኮት ህሊናህን የሚያውከው ከሆነ፤ የየታዘብከው ካህን በሚቀድስበት ጊዜ እራስህን አግልል እንጅ፤ ስለመስዋዕቱ ክብር ስትል ካህኑን መስዋእቱን በሚያቀርብበት ወቅት አትንቀፈው” ይህ ትእዛዝ የተሰጠው የካህኑ አገልግሎትና የመስዋዕቱ ክብር ተቆላልፎ ግለሰቡ ያየውን ያላዩ በንጹህ ህሊና በተመሰጦ አምልኮት ላይ ላሉ ሰዎች እንቅፋት ላለመሆን ነው። ብዙ ሰው በማስረጃ ያረጋገጠውን ስህተት የጸመውን ካህን ጳጳስ መነኩሴ በዝምድና በጓደኝነትና በመንደር ልጅነት ወይም በድርጅት ምክንያት ጋርደው ማለት አይደለም።
“ከማሽላ አዝመራ ሲያባርሩት፡ ወደ ዘንጋዳ ክምር፤ ከዚያ ሲያባርሩት፤ ወደ ስንዴና ጤፍ ክምር፡ እየዘለለ እንደ እሚያስቸግር የቆላ ዝንጀሮ፤ ካንዱ አገር፡ ወደ ሌላ አገር፤ ካንድ ሰባካ፡ ወደ ሌላ ሰባካ ፤ ካንድ ደብር፡ ወደ ሌላ ደብር እየተዘዋወረ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚያውከውን ዝም በለው፤ ተባበረው፤ ተከተለው፤ ወይም በሀሜት እለፈው ማለት አይደለም። የምነትና የሞራል ሰዎች ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይቃወሙታል።
የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አቋም
“እመሰ ወደቅነ ውስተ ግበ ፍትወት፤ ወነበርነ ውስተ ጽልመት ዘግብረ ዓለም። ይደልወነ ናንቃዕዱ ላዕለ ገዓር። ወንስጥጥ ልብሰ ጽልመት ዘየአውደነ ወይከልአነ ነጽሮ”( ተግ ገጽ ፪፻፵፩_፵፪) ማለትም፦ በስግብግብ ባህርይ ፈተና ተጠልፈን ጨለማው ጥቅጥቅ ካለበት ጉድጔድ ብንወድቅ፤ ከወደቅንበት ወጥተን ከጨለማው ለመላቀቅ እንጣር። የጋረደንን የሸፈንን ነገር ሁሉ ሰንጥቀን እንውጣ” እያለ ሸክሙ የከበዳቸውን ሰዎች ቅዱስ ዮሐንስ አበረታታ።
የምዕራቡ ክርስትና ቅዱስ የሚለው፤ በኋላ ተጸጽቶና ንስሀ ገብቶ ብዙ መጻህፍት ጽፎ ያለፈው አውግስቲን የሚባለው፤ ባንድ ወቅት የሮማ መንግስት ባደረሰባቸው መጫን አንገዛም ያሉትን ሰዎች ለማስገዛት ሲል፤ ከፖለቲከኞች ጋራ በማበር በፈጠረው የፖለቲካ ዘዴ “ሰው በውርስ ኃጢአት የተወለደ ስለሆነ መገዛት አለበት” ብሎ በግልጽ ሰበክ። ኦርቶዶክሳዊው ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፤ በተጫናቸው ጭቆና ተንገሽግሸው “በቃን ከላያችን ውረድ” የሚሉትን ድሆች “በኃጢአት ውርስ የመጣባችሁ መርገም ነውና ተገዙ የምትል ከሆነ። አንተና እንዲገዙ የምትሰብክላቸው ሰዎች እንዴት ተወልዳችሁ ወደ ዚህ ዓለም ልትመጡ ቻላችሁ?” በሚል ንግግሩ የገዥዎችንና ያውግስቲንን ቀልብ ገፈፈው። የአውግስቲን ሸፍጥ አንደ አዚም አፍዞት የነበረውን ህዝብ የዮሐንስ ትምህርት ከተኛበት ቀሰቀሰው። የተቀሰቀሰው ህዝብ ዮሐንስን “አፈወርቅ” የሚለውን የክብር ቅጽል አቀዳጀው። ከዚህ ቀደም፦
፩ኛ የዘመናችንን ጳጳሳት ከአርቶዶክስ ትምህርትና ትውፊት ምን ያህል እንደራቁ ለማሳየት “የዘመናችን ጳጳሳት በዮሐንስ አፈወርቅ ዐይን ሲታዩ” ሀምሌ ፲፭ ቀን ፪ሺ ፩ ዓ ም የተጻፈውን ይመልከቱ
፪ኛ የኦርቶዶክሱን ነገረ መለኮት አመሰራረትና ግንዛቤ ከሮማ ካቶሊክና ከፕሮቴስንታንት ለመየት፤ መስከረም ፲፯ ቀን ፪ሺ ፪ ዓም “ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በሮማ ካቶሊክና በፕሮቴስታንት የሚሰጣት አክብሮትና ግንዛቤ” በሚል የተጻፈውን ይመልከቱ።
የተሳሳተና ያለቦታው የተቀመጠ መሪ “እግዚአብሄር የቀባው” ነውና መንቀፍና መተቸት ኃጢአት ነው እያሰኙ የሚኖሩና ይህንንም የሚሰብኩ ሰዎች የሞራል ውድቀት የተጠናወታቸው እንደሆኑ ለማሳየት “የእምነትና የሞራል ግዴት” በሚል ርእስ ማቅረቤ ይታወሳል። “እግዚአብሔር የቀባው” በሚል ርእስ ያዘጋጀኋትን ይህችን ጦማር ያስከተልኩበት ምክንያት፤ ብቃት እውቀትና ሞራል ሳይኖራቸው የተሰየሙትንና ሊሰየሙ በዝግጅት ላይ ያሉትን ሁሉ አለመቃወም ትህትናንና ቅድስናን የሚገልጽ ሳይሆን ከውድቀት እጅግ ወደ ባሰ ውድቀት የሚከት መሆኑን ተገንዝበን የምንከላከልበትን መንገድ እንድንፈልግ ነው።
ማንም እነዚህን ተከታታይ ጦማሮች አንብቦ ከተረዳና፤ ወደፊት አከታትየ የማቀርባቸውን ጦማሮች ካነበበ፤ ለካ እንዲህ ነው እንዴ! ብሎ ባለጌውን አስመሳዩን ቀጣፊውን ጳጳስ ቄስ መነኩሴ፡ ባዲስ ፋሽን እራሱን መምህር እያለ በመሰየም የተነሳውንም መምህሬ እገሌ፤ ወይም ድርጅቴ በማለት ከመከተል ይልቅ ከነሱ አሉባልታ ተላቆ ምጻሕፍት ምን ይላሉ? ወደ ሚለው ደረጃ በመድረስ ለቤተ ክርስቲያናችን ቅድስና ቅድሚያ እንዲሰጥ ዓይኑን ይከፍትለታል። ለመቃወምም የሞራል ድፍረቱ ይዳብርለታል። የማይረቡ የማይጠቅሙ ሰዎች በተቀደሰው መንበር ተሰይመው በተራቸው ግልቢያቸውን እንዳይጀምሩ አሁኑን ተቃውሞውን ማሰማት እንዲችልም ይረዳዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን አካል የሆነ ሁሉ መጽሐፍ እያነበበ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የጉባኤ ሊቃውንት አተረጓጎምና አገላለጽ ተረድቶ ስህተቱን ልይቶ እየገለጸ አታላዩን ሁሉ አንቀበልም ወደሚለው የሞራል ብቃት ካልደረሰ፤ ዶክተረ አረጋዊ በርሄ ገልጸው በመጽሐፋቸው እንዳቀረቡልን፤ አቶ ስብሀት ነጋና ገብረ ኪዳን ደስታ በቤተ ክርስቲያናችን የጫኑብንን መርግ በቀላሉና ባጭር ጊዜ ፈንቅለን ከላያችን የምናስወግደው አይደለም። እንዲያውም አሁን ፓትርያርክ ለመሆን በጩነት ቀረቡ የተባሉት ሰዎች በቤተ ክርስቲያናችን ላያ ተጭነው ሸክሙ እየከበደ የሚሄድ ይመስላል።
ይቆየን
ለሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን ድህረ-ገጽ ይመልከቱ::
http://www.medhanialemeotcks.org/