ኢቴቪና ተዛማጅ ትዝታዎቼ (ክፍል ሁለት)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የኢቴቪ አንድ ‹‹እውቀት- አጠር›› ጋዜጠኛ ስለ አገሪቱ ‹‹ዝናብ አጠር›› እና ‹‹ምርት በሽበሽ›› ወረዳዎች እያወራ በጆሮና በዐይንህ ለሰላሳ ደቂቃ ያለማቋረጥ ከተዘባበተ በኋላ ‹‹እፎይ አበቃ›› ስትል ‹‹ከአፍታ ቆይታ በኋላ እንመለሳለን›› ይልኻል። ‹‹አይመልስህ!›› ብለህ በሆድህ ተራግመህ ሳትጨርስ ‹‹በያላችኹበት ጠብቁን›› ይልኻል፤ የጋዜጠኛው ንግግር በለበጣ ፈገግታ የታጀበና ካድሬያዊ ድምፀት ያለው መሆኑን እግረ መንገድህን ትታዘባለህ፡፡
ይኼኔ ትብሰለሰላለህ፡፡ ‘ለምንድነው የሚያስፈራራኝ? ለምንድነው ‹‹ባለኽበት ጠብቅ›› የሚለኝ?’ እያልክ ትጨነቃለህ፡፡ የመንግሥትህን ባህሪ ጠንቅቀህ ስለምታውቅ የገዛ ቴሌቪዥንህን ማጥፋት ሁሉ ትፈራለህ፡፡ በዓመት 50 ብር እየከፈልክ በራስህ ላይ ያመጣኸው 50 አይነት ጣጣ ፈንጣጣ ይታሰብኻል፡፡ እየተብሰለሰልክ ሳለ ማስታወቂያ ይመጣል፡፡ አንተም ይህ ማስታወቂያ ችክ ካለው እውቀት- አጠር ጋዜጠኛ ስለገላገለህ ፈጣሪ ከፈጠራቸው ጥበቦች ሁሉ ‹‹ማስታወቅያ›› ምንኛ መልካም ነገር እንደሆነ ታስባለህ፡፡ ኾኖም የአፍታ ሰላም ያስገኝልኛል ያልከው ማስታወቂያ የራሱን ህመም ይዞብህ ይመጣል፡፡
ከየት መጣ ሳትል ማስታወቅያ አንባቢው ድንገት በጆሮና በዐይንይ እንደ አውሊያ ይሰፍርብታል፡፡ ይህ ለዘመናት የምታውቀው ድምፅ በሱራፌል ጡሩምባ ተመስሎ እንዲህ ይልኻል፡- ‹‹ ለመኾኑ እርስዎ እንቶኔ የተባለውን ፍሪጅ ገዝተዋል? ምን ነካዎት! ፍሪጅ ከሌሎዎት ምን ንብረት አለኝ ይላሉ!››
ቆሽትህ ገሽለጥ ሲል ይሰማኻል፡፡ ለአንተና ለቤተሰብህ ፍሪጅ የጠፈር ቴክኖሎጂ ያህል ሩቅ ነው፡፡ እናትህ ምግብ የሚያቀዘቅዙት በስስ ፌስታል ቋጥረው ለረዥም ሰዓት የሲሚንቶ ወለል ላይ በማስቀመጥ ይኾናል፡፡ ሰው ቤትህ ድረስ ሰተት ብሎ ልክ ልክህን ሲነግርህ ድፍረቱ አያበሽቅም?
አንተና ቤተሰብህ እንደ ብዙኀኑ ኢትዮጵያዊ ለፍሪጅም ለስጋም ባእድ ኾናችሁ ይኾናል፡፡ ለዓመት በዓል የምታገኙትን ስጋ ‹‹ቋንጣ›› በተባለ ገመድ- አልባ ባልሆነ የሲባጎ ቴክኖሎጂ በማስጣት የ‹‹አገር በቀል›› የፍሪጅ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሆናችሁ ትዝ ይልኻል፡፡በመኾኑም ማስታወቅያ ለፋፊው ሰው ገመናህን ለሰፊው የኢትየጵያ ህዝብ የተናገረብህ ስለመሰለህ ትበረግጋለህ፡፡
በቀን ሁለት ጊዜ በልተህ፣ በሳምንት አንድ ጊዜ እቁብ ጥለህ፣ በወር ብዙ ጊዜ ራስህን ጥለህ በገዛኻው አንጡራ ቴሌቪዥንህ፣ ዳንቴል አልብሰህ በምትንከባከበው ውድ ቴሌቪዥንህ፣ በስስት በምታየው ድንቅ ቴሌቪዥንህ፣ በሰፈሩ በእድሩ በአድባሩ ባስከበረህ፣ ‹‹ጌጤ›› ብለህ በምትጠራውና ለበኩር ልጅህ ልታወርሰው በምታስበው ውድ ቴሌቪዥንህ ውስጥ መጥቶ ሙልጭ አድርጎ የሚሰድብህ ምን ነክቶት ነው፡፡ እሱስ ተከፍሎት ነው የሚሰድብህ፣ ለመሆኑ አንተ ተከፍሎህ ነው የምትሰደበው?!
ለማንኛውም አሳቢው መንግሥትህ የዜጎችን ስብእና የሚደፍሩ ፊልሞችን በቴሌቪዥንህ በኩል እንዳይደርሱህ ይከላከልልኻል፡፡ በገዛ ቤትህ መጥቶ ከሚዋሽህ ጋዜጠኛና ኑሮህን ከሚዘልፍ ማስታወቂያ ግን ራስህን መከላከል ይኖርብኻል፡፡ ‹‹ሪሞት›› የሚባል የቲቪ አጎበር አለልህ፣ተጫነው፤ አጎበሩ ከሌለህ ሶኬት ንቀል፡፡
ፍቅረኛዬን “ቡዳ” በላት
መቼ ለታ ከሴት ጓደኛዬ ጋር አምባሳደር ፊልም ልንገባ በጎማ ቁጠባ አድርገን፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል ቁልቁል እያዘገምን ነበር፡፡ ቁልቁለቱን እንደጀመርነው ድንገት አማርኛዋ ተደነቃቀፈብኝ፡፡ ምን ነካት ሆድዬን እያልኩ በሆዴ መገረም ያዝኩ፡፡ የአማርኛዋ የሰዋሰው ጥሰት ሳያንስ በእያንዳንዱ እርምጃችን የምታወራው ወሬ ሁሉ ያለገደብ ይጋነን ጀመረ፡፡
‹‹መሲ ለልደቷ ያስጋገረችው ኬክ ምን እንደሚያክል አይተኻል?›› አለችኝ፤ ወገቤን ይበልጥ እያቀፈችኝ፡፡
‹‹አላየሁትም›› አልኳት፣ አንገቴን ምስራቅ-ምእራብ በአሉታ እየወዘወዝኩ፡፡
በአቅራቢያችን የነበረውን የብሔራዊ ባንክ ክቡን ህንፃ በአገጯ እያሳየችኝ – ‹‹ማርያምን ከዚህ በምንም አይተናነስም ›› አለችኝ፣ ፍርጥም ብላ፡፡ በጣም ሳቅኩኝ፡፡ እርሷ ግን እያጋነነች መሆኑ ጭራሽ አልታወቃትም መሰለኝ -ወይ ፍንክች፡፡
ይኼኔ “ፍቅሬን ምን ነካብኝ?” ብዬ መጨነቅ ጀመርኩ፡፡ አመም አድርጓት ይኾን? ከነበርንበት በቅርብ ርቀት የሚገኘውን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን አሰብኩ፡፡ ወረፋው ታወሰኝና ተውኩት፡፡ ወደ አምባሳደር ትያትር ልንሻገር ነጩ የኢቴቪ ህንፃ ጋር ስንደርስ ፍቅሬን እንደማጥወልወል፣ እንደማቃሰት፣ እንደማስለፍለፍ አደረጋት፡፡ ድንገት የበሽታዋ መንስኤ ተገለጠልኝ፤ ለካንስ ነጭ ውሸት ወደሚያመርተው የኢቴቪ ነጩ ህንፃ እየተቃረብን ስለመጣን ነበር ፍቅሬ ቋንቋዋ እየተበላሸብኝ የነበረው፤ ወደዚህ መሥሪያ ቤት ይበልጥ በተጠጋን ቁጥር ፍቅሬ ይበልጥ እየዋሸችኝ ነበር፡፡
እንደሚታወቀው ይህ መስሪያ ቤት ‹‹ቅጥፈትና ግነት›› በሚባሉ ቫይረሶችና ተህዋሲያን በተደጋጋሚ ይጠቃል፤ በአካባቢው የሚያልፉ ሰዎችንም ቫይረሱ ሊያጠቃቸው እንደሚችል በመገመት በዚያ በኩል ሲያልፉ አፍና አፍንጫቸውን በማሀረብ መያዝ ያዘወትራሉ፡፡ የበሽታውን አማጭ ዋንኛ ተህዋስ ግን ቤታቸው ሳሎን ውስጥ ማስቀመጣቸውን ይዘነጋሉ፡፡
‹‹ሽባ ጆርናሊዝም››
ኢቲቪ መዓት እውቀት-አጠር ጋዜጠኞች አሉት፡፡ አውቀት አጠር መኾናቸው ደግሞ ደፋር እንዲሆኑ አግዟቸዋል፡፡ ድሪቶ ቃላት ሰብሳቢ ኾነው ስለኪራይ ሰብሳቢነት ያወራሉ፡፡ ከዚህ በማስከተል ኢቴቪ ደጋግሞ ከተለከፈባቸው የቋንቋ ተስቦዎች ጥቂቶቹን እንመለከታለን፡፡
አንዲት ኢቲቪ አለኝ የሚላት ‹‹ልምድ ጠገብ›› እና ‹‹ እውቀት አጠር›› ጋዜጠኛ መቼ ለታ በወጣቶች ፕሮግራም እንዲህ ስትል ሰማኋት፤
“ሀሪ ፖተር የተባለቸው ዝነኛ እንግሊዛዊት ደራሲ በአንድ ወቅት ስለልማት እንዲህ ብላ ነበር…” ልማትና ጅራት ከወደ ኋላ ነው፤ እውነት ብላለች…ሀገራችን የተያያዘችው የልማት ግስጋሴ እንደ ጅራት ወደኋላ አስቀርተዋት ከነበረው አስከፊ ስርአት ወጥታ ዛሬ በልማት ጎዳና እንድትገሰግስ ሁሉም ከመንግሥት ጎን በመቆም ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ አሁን አንድ ሙዚቃ እንጋብዛችሁ፡፡ አቀንቃኙ ብላክ አይድ ፒስ ይሰኛል፡፡ ታዋቂ የአር ኤንድ ቢ አቀንቃኝ ነው፡፡ ከዚህ ሙዚቃ በኋላ ሀሪ ፖተር ስለተባለችው ስኬታማ ደራሲ የሕይወት ታሪክ ብዙ የምንላችሁ ይኖራል፡፡ መልካም ቆይታ፡፡”
‹‹…ያለበት ሁኔታ ነው ያለው…››
ኢቴቪ ውስጥ አንድ ተስቦ ከገባ ቶሎ አይወጣም፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት ገብቶ ከነበረው የቋንቋ ተስቦ መሀል ዛሬም ድረስ የሚስተዋለው…‹‹ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፣ ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው›› የሚለው አገላለፅ ነው፡፡
ወቅታዊ ምሳሌ፡-
“…ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስግብግብ ነጋዴዎችን ያስጠነቀቁበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በአንፃሩ ስግብግብ ነጋዴዎችም እየተስገበገቡ ያሉበት ሁኔታ ነው የሚስተዋለው…›› ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያ ችላ የሚባልበት ሁኔታ ከቀጠለ፣ አገሪቱ ወደከፋ ስግብግብነት የምታመራበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በመሆኑም አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሰመሩበት ስግብግብ ነጋዴዎች ጣታቸው የሚቆረጥበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚገባ አንዳንድ የፍትህ አካላት እየመከሩበት ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡›”
ብሽቅ! ይላል ጋሽ ስብሀት ሲናደድ፡፡
“…አንዳንድ ነዋሪዎች…”
ይህ አገላለጽ የተወለደው በአስራ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሰባት ዓመት ምህረት በምርጫ ማግስት ሲሆን አሁንም በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋለ ያለ እጅግ አደገኛ ኢቴቪ ወለድ ቫይረስ ነው፡፡
ጥቂት ምሳሌዎችን ቀጥለን እንመለከታለን፡-
‹‹አንዳንድ የቆቦ ተሰናባች አርሷደሮች አሜሪካ የምትከተለውን ኒዎሊበራሊዝም ክፉኛ አወገዙ፡፡ከአፍራሽ ድርጊቷ እንድትቆጠብም አስጠንቅቀዋል፡፡››
‹‹ሰሞኑን መንግስት ያደረገው የጡረታ አበል ጭማሪ ተንደላቀው ለመኖር እንዳስቻላቸው አንዳንድ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ለፍቶ አዳሪዎች ገለፁ፡፡››
‹‹መንግስት በቅርቡ በቢራ ላይ የወሰደው የዋጋ ተመን ማስተካከያ ወቅታዊና የመንግስትን አርቆ አሳቢነት የሚያስመሰክር ተግባር ነው ሲሉ አንዳንድ የካዛንቺስ ሴተኛ አዳሪዎች አስታወቁ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በስራ ላይ ሳሉ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው እነዚህ በማህበር የተደራጁ አንዳንድ ሴተኛ አዳሪዎች ለሪፖርተሮቻችን እንደገለጹት ከቢራ ተመኑ በኋላ የ‹‹ሾርት›› ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል፡፡››
በመጨረሻም
‹‹ኢትዮጵያ በጠፈር ምርምር ከዓለም አንደኛ መኾኗን አንዳንድ የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ምሁራን አስታወቁ፡፡››
ሰማይ ጠቀስ በቆሎዎች
የኢቴቪ ቁጩ ጋዜጠኞች እውነተኛ ጋዜጠኞችን ለመምሰል ይናፍቃሉ፡፡ (ኢቴቪ ውስጥ የባለሞያ ሥራ ለማቅረብ አቅምም ሆነ ፍላጎት ያላቸው ጥቂት ጋዜጠኞች አሉ፤ አሳዛኙ ነገር ግን እነርሱ ለሕዝብ ጥቅም በቁጩ ጋዜጠኞች ቁጥጥር ስር ውለዋል።) ቁጩ ጋዜጠኞቹ ከውጭ ጋዜጠኞች የኮረጁት ማንበብን ሳይሆን እጅ እያወራጩ ካሜራ ላይ መደቀንን ብቻ ነው፡፡ እጅ እያወናጨፉ መዘገብ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የብዙ ዜጎችን አይን አጥፍተዋል፡፡ አንድ የአዲስ አበባ መስተዳደር ጋዜጠኛ ስለ ሽንት ቤት የትቦ ፍሳሽ ለመዘገብ ትቦ ውስጥ ከገባ በኋላ እጁን እያወናጨፈ ”ስታንድ አፕ” ለመዘገብ ሲሞክር በዚያው ሰምጦ ሊቀር እንደነበረና ድርጊቱን ይቀርጽ የነበረ የካሜራ ባለሙያው ሕይወቱን እንደታደገው ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡
አንድ በውፍረትም በቅጥፈትም ቱባ ካድሬዎችን እያስናቀ የሚገኝ ሌላ ጋዜጠኛ ደግሞ መቼለታ እንዲህ ብሎ ሲዘግብ ሰማሁት፣ አየሁት፤ ( ዘገባውን በሚያቀርብበት ወቅት በበቆሎ ማሳ ውስጥ ሆኖ ማሳውን በእጁ እየቀዘፈ እንደነበር ልብ ይሏል፡፡)
“ድሮ ሲባል የምናውቀው ‹‹ሰማይ ጠቀስ ፎቅ›› ነበር፤ አሁን እድሜ ለልማታዊው መንግሥታችን ሰማይ ጠቀስ በቆሎዎችን ለማየት በቃን፡፡”
ወደ ሁለት የሚጠጉ ሕንፃዎች
ከሁለት ሳምንት በፊት የአቴቪ ታናሽ ወንድም በሆነው ኤፍ ኤም 97.1 ላይ በጥያቄና መልስ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሞቅ ባለ ድምጹ እንዲህ የሚል ጥያቄ ለአድማጮቹ አቀረበ፡፡
“አድማጮች ይህንን ጥያቄ ልብ ብላችሁ አድምጡ፤ ‘man is born in china but found everywhere’ ብሎ የተናገረው ዝነኛ ፈላስፋ ማን ይባላል፡፡ እደግመዋለሁ! ‹‹man is born in china but found everywhere’ ያለው ዝነኛ ፈላስፋ ማን ይባላል?”
“MAN IS BORN FREE, BUT EVERYWHERE HE IS IN CHAINS” ማለቱ ነበር፡፡ ደግነቱ አንድ ትሁት አድማጭ ደውለው እንዲያስተካክል ነገሩት፡፡ ጋዜጠኛውም የዋዛ አልነበረም፤ ቀልጠፍ ብሎ ይቅርታ ጠየቀ፡፡
አንድ የኤቴቪ ጋዜጠኛ በአንድ ክፍለከተማ ስለተገነቡ የወጣቶች ማእከላት ሲዘግብ ደግሞ እንዲህ አለ፡፡ “መስተዳደሩ ወደ ሁለት የሚጠጉ ህንፃዎችን ገንብቶ አገልግሎት ላይ አውሏል”
ለመኾኑ ‹‹ወደ ሁለት የሚጠጉ ህንፃዎች›› ማለት ምን ማለት ይኾን? ‹‹ወደ ሁለት የሚጠጉ ታክሲዎች››፣ ‹‹ወደ ሁለት የሚጠጉ ግለሰቦች››፣ ‹‹ወደ ሁለት የሚጠጉ የምክር ቤት አባላት››…ወዘተ በኢቴቪ ጋዜጠኞች የሚዘወተር ቋንቋ ነው፡፡
ዜና ማንበብ
ብዙዎቹ የኢቴቪ ዜና አንባቢዎች ተመልካች ፊት ሲቀርቡ ከመጠነ ያለፈ መሽቆጥቆጥና ከልክ ያለፈ ትህትና ያበዛሉ፡፡ በሰላምታቸው ውስጥ የሚከተለው የማይሰማ መልእክት እንዳለ ግን ብዙ ተመልካች ልብ አይለውም፡፡
“እንደምን አመሻቹ፣ የምንዋሻቹ፤ በቅድሚያ ዋና ዋና ውሸቶችን፡፡”
ሲሰናበቱን
“ለሰዓቱ የያዝናቸው ውሸቶች ይህንን ይመስሉ ነበር፤ በደኅና አምሹ”
የኢቴቪ ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ አንድ ብትሆንም በሁለት ትከፈላለች፤ የኢቴቪ ኢትዮጵያና የምንኖርባት ኢትዮጵያ፡፡ የኢቴቪ ኢትዮጵያ ለም፣ የበለጸገች፣ ማርና ወተት የሚንዠቀዠቅባት ስትሆን የምንኖርባት ኢትዮጵያ ግን በአጭሩ እኛን ትመስላለች፡፡
አንድ ወንደላጤ ጎረቤቴ ቴሌቪዥኑ ከእለት እለት እየገረጣች፣ እየወየበች አስቸገረችው፡፡ ዲሽ ከማስተከሉ በፊት ቲቪው ትበላሽበትና ሰሪ ቤት ይወስዳታል፡፡ ቴክኒሻኑ ቲቪውን ሲከፍተው የቲቪው “ቺብስ ና ቦርድ” ክፉኛ ተቃጥሎ ያገኘዋል፡፡ ቴክኒሻኑ ከዚህ ቀደም እንዲህ የነደደ የቲቪ “ቦርድ” አጋጥሞት ስለማያውቅ በሁኔታው ይደመማል፡፡ እጥፍ የኤሌክትሪክ ኋይል ወደ ቲቪው ቢለቀቅ እንኳ በዚህ መልኩ ሊነድ እንደማይችል ገብቶታል፡፡ ሁኔታው ስለገረመው የቲቪውን ባለቤት አንዳንድ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይጀምራል፡፡
ቴክኒሻኑ፡- ወንድሜ! ቲቪህን ምድጃ ላይ ጥደኸው ታውቃለህ?
ባለቲቪ፤- አንዴት፤ ምን ማለትህ ነው!?
ቴክኒሻኑ፡- አይ! ለማወቅ ነው፤ የምጠይቅህን ብቻ መልስልኝ፡፡ ቴሌቪዥንህ ከመበላሸቱ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ያሳያቸውን ምስሎች ማስታወስ ትችላለህ?
ባለቲቪው፡- አዎን!
ቴክኒሻን፡- እስኪ ንገረኝ!
ባለቲቪው፡- አንድ የምርጫ ቦርድ ባለስልጣን ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክሪያሳዊ እና እንከን የለሽ እንደነበር ሲናገሩ ትዝ
ይለኛል
ቴክኒሻኑ፡- ሌላስ
ባለቲቪው፡- የገንዘብ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ተሰልፋ ውጪ ስትባል እንቢ እንዳለች ሲናገሩ ነበር
ቴክኒሻኑ፡- ሌላስ
ባለቲቪው፡- ሌላ…አንድ ገበሬ መንግሥት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ 60 አይሱዙ መኪና፣ 6 ቪላ ቤቶችና 60 ሚሊዮን ብር ባንክ ማስቀመጡን ሲናገር ትዝ ይለኛል፡፡
ቴክኒሻኑ፡- ሌላስ?
ባለቲቪው፡- ሌላ…. የዓለም ኅብረተሰብ ከኢትዮጵያ ፓርላማ ብዙ ሊቀስማቸው የሚገቡ ቁምነገሮች እንዳሉ አንዲት አፈ ጉባኤ ሲናገሩ ነበር፡፡
ቴክኒሻኑ፡- በል እንካ ቲቪህን ውሰድልኝ
ባለቲቪው፡-ምን ሆንክ?
ቴክኒሻኑ፡- ተቃጠልኩ!!
ኢቴቪና ጋዳፊ
ኢቴቪ ድሮም ለኢትዮጵያ ሕዝብ አልተፈጠረም፡፡ ቶምሰን በተባለ የእንግሊዝ ድርጅት እገዛ በ1957 ዛሬ እነጋዳፊ የሚፈነጩበትን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለማድመቅ ሲባል ነበር ኢቴቪ የተወለደው፡፡ እድሜ ለጃ! ይኸው ኢቴቪ ከጋዳፊ እኩል የኢትዮጵያን ሕዝብ ላለፉት አርባ ምናምን ዓመታት ሲቀጥፍ ኖሯል፡፡ ጋዳፊ የኢቴቪ እኩያ ናቸው፣ ኢቴቪም የጋዳፊ አቻ ነው፡፡ እርሳቸው ዛሬም ሕዝቤ ተሳስቷል፣ እኔ ትክክል ነኝ ይላሉ፡፡ ኢቴቪም ሕዝብ አያውቅም፣ እኔ አውቃለሁ እንዳለ ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታት ተለዋውጠዋል፡፡ ከጋዳፊ እኩል የመጣው ኢቴቪ ግን ዛሬም ሥልጣኑን የሙጥኝ እንዳለ ነው፡፡
አንድ ተውኔት መድረክ ላይ ሲተወን ትያትር ይባላል፡፡ ተውኔቱ ደጅ ተቀርፆ በሲኒማ ቤት እና በቴሌቪዥን ስታየው ፊልም ተብሎ ይጠራል፡፡ አንድ ደረቅ ፕሮፓጋንዳ በአላዋቂ ጋዜጠኛ ወይም በአዋቂ ዋሽቶ አደር በሰፊ ብራና ሲጻፍ ‹‹አዲስ ዘመን›› ይባላል፡፡ ያው ፕሮፓጋንዳ ጥሩ የመተወን ብቃት ባላቸው ጋዜጠኞች ተቀርፆ ሲቀርብ ‹‹ኢቴቪ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ አዲስ ዘመንና ኢቴቪ የእድሜ ዘመናቸው ረዥም ነው፡፡ ሁለቱም እድሜ ያጎበጣቸው አዛውንቶች ናቸው፤ ተከብረው ግን አያውቁም፡፡
“አዲስ ዘመን” ሞኝ ሰውነት ስላለው ውሸት ሲበዛበት ዝም ብሎ ወደ ጎን ይለጠጣል፡፡ በአንጻሩ ኢቴቪ ውሸት እያሸማቀቀው በየቀኑ ይከሳል፡፡ ስንቶቹ ዲያስፖራዎች 21 ኢንች እየገዙ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ከሄዱ በኋላ በዓመቱ ሲመለሱ 14 ኢንች እየኾነ ጠበቃቸው መሰለህ፡፡ ይህ ነገር ቀልድ ሆኖ ይወራል እንጂ የየቤቱ እውነት ነው፡፡ ቲቪ የሚያከሳ ነቀዝ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሳሎን ኖሮ አይደለም የኢትዮጵያ ቲቪዎች የሚከሱት፤ በሐሰት ወሬዎች እየተሸማቀቁ እንጂ፡፡ ተመሳሳይ የበሽታው ምልክቶች በአሥመራ ቲቪዎችም ይስተዋላል፡፡
ዕድሜዬ እየገፋ ነው፡፡ የኢቴቪን ዉለታዎች ዛሬም አልዘነጋቸውም፡፡ በአባባ ተስፋዬ ተረቶች አዝናንቶኛል፣ በአፍሪካ ዋንጫዎች አስቦርቆኛል፡፡ ማራዶና የሚባል የኳስ ንጉሥ እንዳለ አሳይቶኛል፡፡ ጥላሁን ገሰሰ የሚባል የሙዚቃ ንጉሥን አሰምቶኛል፡፡ ኢቴቪ በሁሉም መልኩ አሳድጎኛል፡፡ ለዚህም አመሰግነዋለሁ፡፡
ኢቴቪ በልጅነቴ ዐይንና ጆሮዬ ነበር፡፡ አሁን ዐይንና ጆሮዬ በገዛ አገሬ በይፋ ታሽገውብኛል፡፡ ይህ የእኔ አቻ ትውልዶች ሁሉ የሚጋሩት ሀቅ ነው፡፡ ኢቴቪን ያንገሸገሻቸው “I hate etv›› የሚል የፌስቡክ ቡድን እስከማቋቋም ደርሰዋል፡፡ ይህ ንቅናቄ ከስምንት መቶ በላይ አባላት አሉት፡፡ የአገሪቱ ዝነኛ ሰዎችም በዚህ ድረ ገጽ ለኢቴቪ ያላቸውን ጥላቻ ይተነፍሳሉ፡፡ አንድ ወጣት በዚህ የማኅበረሰብ ድረ ገጽ ላይ እንዲህ ጽፎ አነበብኩ “ኢቴቪ እናት ኢትዮጵያ ላይ ያለ ትልቅ እባጭ ኾኖ ይሰማኛል።”