“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ያሉትን ከስራ ላይ እናውል (አክሎግ ቢራራ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ዶ/ር አክሎግ ቢራራ
አባቶች እናቶቻችን አያቶቻችን፤ በአጠቃላይ ወገኖቻችን፤ ለእኛ መኩሪያና መታወቂያ የሆነችውን ኢትዮጵያን ለእኛ ከተከታታይ አደጋ መክተው ያቆዩልን በብሄር፤ በሃይማኖት፤ በጾታ፤ በእድሜ፤ ወዘተ ተለያይተው ሳይሆን ለነጻነታቸው፤ ለክብራቸው፤ ለማንነታቸው በመተባበር ታግለው፤ ደማቸውን አፍሰው፤ ህይወታቸውን ሰውተው ነው። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ያሉትን ወርቃማ አባባል በተግባር አሳይተው የተውልንም ለዚህ ነው። ሆኖም፤ የቅርብ ታሪካችን የሚያሳየው የእኛ ትውልድ ለዚህ አባባል ብቁነት አላሳየም፤ አሁንም፤ አብዛኛው፤ በባህርይም ሆነ በአሰራር ገና ብቁነት ለማሳየት እንደ ኤሊ በመጎተት ላይ ነው ለማለት የሚያስገድዱ አመልካቾች አሉ። መመልከት ያለብን ግን ይህን የረጋ የመሰለ አሳሳች ምልክት አይደለም። ከስሩ የሚቭላላውን ከልብ የመሸፈት ምልክት ነው።
በቁጥር ስምንት እንዳሳየሁት፤ ዛሬ ለፍትህ-ርትህ የሚታገለው ተራው ሕዝብ፤ ተማሪው፤ አስተማሪው፤ ወጣቱ ትውልድ ነው። የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት መሪወችና ተከታዮች በተከታታይ የሚያደርጉት ሰላማዊ ትግል ለዚህ ምልክት ነው። የፖለቲካ ድርጅቶችን፤ የህብረተሰብ ስብስቦችን ቀድመው ሂደዋል። በዚህ ሰላማዊ ትግል ውስጥ ወጣቱ ትውልድ አመልካች ሚና ይጫወታል። እነ አንዷለም አራጌ፤ እነ እስክንድር ነጋና ሌሎች በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ያለውን አፈናና ግፍ ተቋቁመው ለፍትህ፤ ለእውነተኛ እኩልነት፤ ለህግ-የበላይነት፤ ለመላው ሕዝብ ሉአላዊነት፤ ለሃገር አንድነት የሚያደርጉት ሰላማዊ ትግል የቆራጥነት ምልክት ነው። እንደ ተመስገን ደሳለኝ ያሉ ከፍርሃት ነጻ የሆኑ ጋዜጠኞች በአገር ቤት ሆነው ህወሓትን/እሃዴግን በማስረጃ ሲያጋልጡ ለግል ጥቅም ብሎው አይደለም። አፈና፤ ግፍ፤ የእስራት አደጋ፤ ወዘተ አልገታቸውም። እነዚህ አገርና ወገን ወዳዶች ለፍትሃዊ ለውጥ፤ ለወጣቱ ትውልድ፤ በውጭ በስደት ላለን፤ ራሳችን ዲያስፖራ ብለን ለምንጠራው ሁሉ አርአያ ናቸው።
የታመቀ ሃይል ታምቆ አይቀርም፤
የእነዚህ ወጣቶች ትግል የሚያጠነክረው ምልከት፤ የህወሓት አምባ-ገነንነት ዘላቂነት እንደማይኖረው ነው። ዛሬ ጥቂት የሚመስሉት ወጣት ታጋዮች፤ ነገ ብዙ ሚሊዮን እንደሚሆኑ አንጠራጠር። ሌላም ምልክት አለ። እነዚህ ወጣቶች የሚታገሉት ባየር ላይ አይደለም። የሚጋሯት አገር አለች። ይህች አገር ታሪክ ያላት መሆኑን ያውቃሉ። ኢትዮጵያ የሁላችንም መንፈስ ናት። መንፈስ እንደመሆኗ መጠን እነሱና እኛ ካልፈለግን አትጠፋም። እነሱ አትጠፋም ብለው ይታገላሉ፡፡ ቁጥራቸው ይነስ እንጅ በውጭም የእነዚህን አገር ወዳድ፤ ዲሞክራት ታጋዮች አስተሳሰብና እሴቶች የሚጋሩ በአለም ተሰራጭተዋል። በፖለቲካ ድርጅትም ሲታይ፤ አፈናና ግፍ ያገባቸው አገራዊ ድርጅቶች አሉ። በተደጋጋሚ ያሳሰብኩት፤ አሁንም በዚህ ትንተና የማሳስበው፤ ይህን የታመቀ ሃይል ሁሉ ካጎለመስነው፤ ከደገፍነው፤ ካበረታታነው፤ ህወሓት/ኢሃዴግ ሊያቅበው አይችልም።
አንዱን ሲበላው አይቶ ዝም ማለት አያዋጣም፤
ችግሩ፤ ከብሄር፤ ከሃይማኖት፤ ከፖለቲካ እምነት፤ ከጾታ፤ ከእድሜ፤ ከመደብ፤ ካለፈ ታሪክ፤ ከቡድን ባሻገር በማሰብ ተሳስቦ፤ ተባብሮ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የስልጣኑ ባለቤት የሚሆንበትን ብሩህ አቅጣጫ መንደፍና በአንድ ክንድ ከስራ ላይ ከማዋሉ ላይ የተከሰተው ድክመት ነው። ኦሮሞወች የሚሉት ዘላለማዊ ተረት በአርእስቱ ከተጠቀሰው አስተሳሰብ ጋር ተያይዞ ለትንተናየ አጋዥ ስለሆነ፤ አቀርበዋለሁ። “ነጭ፤ ቀይ፤ ጥቁር፤ ዳልቻ፤ ወርቃማ፤ የሆኑ በሬወች አንድ ላይ ሁነው ከጂብ (አውሬ) አደጋ ራሳቸውን ለመከላከል በጋራ ተስማመተው፤ አካላቸውን (ቂጣቸውን) አገጣጠመው፤ ፊታቸውን በያቅጣጫው አዙረው ጠላታቸውን ለመከላከል በመደጋገፍ ለመዋጋት ተስማሙ። አውሬው/ጅቡ ሊበላቸው ሲመጣ፤ በሁሉም አቅጣጫ ያሉት በሬወች ቀንዳቸውን ቀስረው አላስቀርበው አሉ።” ድር አበረ ማለት ይህ ነው።
ጅቡ የበሬወቹን የማይበገር ሰንሰለት በማየት ለመከፋፈል መላ መፍጠር መረጠ። እንዲህ ይላል። “እኔኮ ሌሎቻችሁን አልፈልግም። ነጩ በሬ ብቻ ጎልቶ እየታየኝ ለአይኔ ስላስቸገረኝ፤ እሱን ብቻ ነጥላችሁ አውጡ፤ እናንተን አልፈልጋችሁም” አላቸው። ሞኞች እውነት መስሏቸው ነጥለው ነጩን ያሰወጡታል። ነጩ በሬ የመጀመሪያው መስዋእት ይሆናል። ጅብ አሸነፈ። ይህን በሬ በልቶ ሲጨርስ፤ “ዳልቻው በሬም ከነጩ አይለይም፤ እርሱንም ነጥላችሁ አስወጡልኝ፤ ሌሎችን አልፈልግም” ብሎ ቃል ይገባል። ነጥለው አስወጡት፤ ጅብም ሁለተኛውን በሬ በላ። መጥገብን አያውቅምና ሌላ ለመብላት ተዘጋጀ። የወርቃማው ተራ ይመጣል። በለመደው ዘዴ “ወርቃማው ነጭ ስላለበት ለአይኔ አስቸግሮኛል። አስወጡት፤ ሌሎቻችሁ አታስቡ፤ አልፈልጋችሁም ይላቸዋል።” ደጋግመው የተሞኙት ካለፈው አልተማሩም። አሁንም ከመካከላቸው ወርቃማውን ያስወጣሉ። እንደዚህ ባለ ዘዴ እየለያየ ሁሉንም ጨረሳቸው ይባላል። የእኛም “የከፋፍለህ ግዛው፤ የከፋፍለህ ምታው”ታሪክ ይህን ይመስላል።
ህወሓት/ኢሃዴግ፤ እየመረጠ አማራውን፤ ኦሮሞውን፤ አፋሩን፤ ደቡቡን፤ አኟኩን፤ ትግራዩን፤ ክርስቲያኑን፤ እስላሙን፤ ወዘተ በየምክንያቱ ይገድለዋል፤ ያስረዋል፤ ያስድደዋል፤ ከቀዩ ያስወጣዋል፤ በሰላም ጎን ለጎን የሚኖርውን ሕዝብ እርስ በርሱ ያጣላዋል። በዚህ ሳምንት በቦረናና በጋሪ ህብረተሰቦች መካክል የተካሄደው፤ ለአስራ ስምንት ኢትዮጵያዊያን ሞት ምክንያት የሆነው፤ የመሬት ይዞታ ግጭት የተፈጠረው ህወሓት በፈጠረው የመሬት ነጠቃና ሰፈራ ፖሊሲ ነው። ይህን የመሳሰሉ ግጭቶች በየአካባቢ ሲካሄዱ ቆይተዋል። መቀጠላቸው አይቀርም።
በኢትዮጵያ ላይ አሁን እየተፈጸመ ያለው “ነጣጥለህ ምታው፤ ነጣጥለህ እሰረው፤ ነጣጥለህ ግደለው፤ ነጣጥለህ አሳደው፤ ነጣጥለህ አክብረው”፤ የበሬወቹንና የጅቡን ተረት ይመስላል። የአገራችን ታሪክ፤ ጥንት የውጭ ጠላቶች (ጅቦች) ሲመጡ የተከተለውዘዴ ልዩነትን ወደ ጎን ትቶ መከታ መሆንን ነበር። ዛሬ፤ የምእራብ አገሮች፤ ቻይና፤ ለጋስ ድርጅቶች፤ ኢንቪስተሮችና ምርጥ የህወሓት ፓርቲ አባላት የኢትዮጱያን ጠንካራነት፤ የህዝቧን በሰላም የመኖር ፍላጎት፤ የወጣቱን ትውልድ ዘላቂነትና ተሳትፏዊ ያለው የእድገት ፍላጎት የማይሹ መሆናቸውን፤ እንዲያውም፤ ወደ ትንንሽ አገሮች በክልል ዙሪያ በመከፋፈል፤ ቀስ በቀስ እንድበታተን የማድረግ ምኞታቸውን የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ፤ ህወሓት/ኢሃዴግ በሰላም አብሮ ተሳስቦ የሚኖረውን የክርስቲያንና የእስልምና ተከታይ ህብረተሰብ እርስ በእርሱ እንዲናከስ ሲያደርግ ቆይቷል፤ እየከፋፈለ ወገን በወገኑ ላይ ላይ እንዲነሳ አድርጓል። ይባስ ብሎ፤ ህወሓት የኢትዮጵያን ድሃ ገበሬ በመርዳት፤ አቅሙን በመገንባት ፋንታ፤ ለም መሬቱንና ወንዙን ለውጭ ሃብታሞች ሲነግድ ቆይታያል፡፡ የውጭ ከበርሬወችንና መንግስታትን አላማ አስፈጻሚ አገልጋይ ሆኖ ይገኛል። የዚህ አይነት በዳይ አገዛዝ በታሪካችን ያልታየ ነው።
“የመቶ አመት ታሪክ” ከየት መጣ?
አንባቢው ሊገነዘበው የሚገባ ከታሪካችን ከምንማራቸው አበይት ነገሮች መካከል አንድ ለማስታወሥ እፈለግላለሁ። ባለፈው እንዳመለከትኩት፤ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ፤ የአገራችን ታሪክ አሳጥረው ወደ መቶ አመት ሲለውጡት፤ አላማቸው ግልጽ ነበር። እሳቸው የሚያስቡት ለአጭር ጊዜ ስልጣንና ጥቅማቸው እንጂ፤ ለረጅሙ የአገራችን ጥቅም አለመሆኑን አይተናል። ሆኖም፤ የእርሳቸው ልብ ወለድ ታሪክ ሃቁን አያጠፋውም። ሃቁም፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያኮራ አስተዋጾ በማድረግ፤ አገራችን ከሶስት ሽህ አመታት በላይ እውቅና ሰጥቷታል። መለስ ዜናዊ በተወለዱበት በትግራይ የተደረገውን የጣሊያን ጦርነት፤ ማለትም፤ የአድዋን ድል፤ የሁለተኛውን የፋሽስት የበቀል ወረራ ማየቱ ይበቃቸው ነበር። አዶልፍ ፓርለሳክ የተባሉት የቸክ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ፤ “የሃበሻ ጀብዱ” በተባለው አስደናቂ የምስክር መጽሃፋቸው የመለስን ሃሳብ በለወጠው ነበር።፡ ኢትዮጵያዊያን “እምነትህ ፈረሰ፤ ደንበርህ ተጣሰ” በተባለ ቁጥር፤ ቋንቋ፤ ሃይማኖት፤ ብሄር፤ ጾታ፤ እድሜ ሳይለያቸው በጋራ፤ አገራቸውን ከጠላት ተከላክለው ለተከታታይ ትውልድ አስተላልፈዋል።
ይህን ሲያደርጉ፤ ኢትዮጵያ ከእራሷ ስብጥር ጀግኖች ውጭ ማንም ደርሶላት አያውቅም። ፓርልሳክ ስለ ጣሊያን አሰቃቂ ወረራ እንዳሉት፤ “ኢትዮጵያን ማንም አይረዳትም። ብቻዋን ናት። ….በደበረታቦር (ጎንደር) ብቸኛ አውሮፓዊ መሆኔ ሃዘን ተሰማኝ። ወዲያው ለዚች ለተቀደሰች ሃገር ከነዚህ ምስኪን የገበሬ ወታደሮች ጎን በታላቅ ድፍረትና ጀግንነት በእግዚአብሔር የሚታደሉት ታላቅ ጸጋ መሆኑን ስረዳ ልቤ በደስታ ተሞላች። ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ ኢትዮጵያዊ ሆኛለሁ።” ይህ ፈረንጅ ኢትዮጵያዊ ያደረጉት አስተዋጾ ለእያንዳንዳችን ምሳሌ እነደሚሆን እመኛለሁ። የአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅበት ለሰላም፤ ለፍትህ፤ ለሕግ የበላይነት፤ አብሮ ተቻችሎ ድህነትን ለማስወገድ መቀራረብ፤ መቻቻል፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሩ አዛዥ እንዲሆን ማድረግ ነው።
ከፓርልሳክ የምማረው፤ ዛሬም እንዳለፈው አገርም ውጭም ያሉ ወጣት ታጋዮችና ተቃዋሚወች ለፍትህ የሚታገሉት ማንም ይደርስልናል ብለው ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ህያውነትና መንፈስ ስለሚያምኑ፤ ለመላው የስብጥር (Diverse) ህዝቧ ፍትህ ፍላጎት እውን መሆን ድጋፍ ለመስጠት ስለሚፈልጉ ነው ለማለት ይቻላል። ፓርልሳክ እንዳሉት፤ አሁን ያለው ችግር ካለፈው ይበልጣል እንጂ አይቀልም። በአብዛኛው፤ መላው ሕዝብ የሚሰቃየው በራሱ ወገን ነው። መተባበር የሚያስፈልገው ችግሩ ከመቸውም የበለጠ ከባድ በመሆኑ፤ ብዙ የውስጥና የውጭ ተጠቃሚወች ስላሉ ጭምር ነው። ለጊዜው ሀወሓት/ እሃዴግ የሚረዳው፤ የገንዘብ፤ የመሳሪያና የሌላም ሃይል የሚያገኘው ከውጭና ከእያንዳዳችን ድጎማ ነው። ተቃዋሚ ክፍሎች በአንድ ላይ ከቆሙ፤ በአንድ ድምጽ ለመናገር ከቻሉ ቢያንስ፤ ሶስት ነገሮችን ለማድረግ ይችላሉ፤ አንደኛ፡ አገር ቤት ታፍኖ ላለው እምቅ ተቃዋሚ ብርታት ይሰጡታል፤ ሁለተኛ፤ የገንዘብ፤ የሞራል፤ የሃሳብ ድጋፍ ለመስጠት ይችላሉ፤ ሶስተኛ፤ በውጭ በአንድ ድምጽ የአለምን ህዝብ አስተሳሰብ የመለወጥ እድላቸው ይጠነክራል። መጀመሪይ፤ በስደት ላይ ያለው ህብረተሰብ መደራጀት፤ አብሮ መስራት፤ መተባበር አለበት። በግል/በተናጥል የሚያደርጉት የስልጣን ድርድር የትም አያደርስም። መሰባሰቡና አብሮ መስራቱ፤ ሌላው ስደተኛው በቀጥታም ሆነ በግልጽ ለህወሓት የሚሰጠው ድጋፍ ያቆማል፤ ቢያንስ ይቀንሳል። ተቃዋሚው ክፍል በአንድ ድምጽ ከተናገረ፤ ይህ ለሃያ አንድ አመታት ያገለገለ አገዛዝ መላላቱና መገርሰሱ አይቀርም። የውጭ አገር መንግስታት የተቃዋሚውን ክፍል ሃሳብ ማዳመጥ ይጀምራሉ። አሁን ያለውን ወርቃማ እድል ለመጠቀም ካልቻልን ሌላ ልንገነዘበው የሚገባን ጉዳይ አለ። ህወሓት የሃይል ምንጩን በእየጊዜው ይለዋውጣል።
የህወሓት የገቢ ምንጮች እየተቀየሩ ነው፤
ለምሳሌ፤ ህወሓት አሁን በብዙ ቢሊየን የሚገመት መዋእለንዋይ (investment) በውሃ ግድብ የሃይል ምንጭ ላይ (Hydroelectric Power generation) ፤ በቻይና ድጋፍ የሚያፈሰው ከምእራባዊያን ጥገኝነት ነጻ ለመሆን ነው። ኤሌክትሪክ ለጎረቤት አገሮች በመሽጥ በአመት ብዙ ቢሊዮን ዶላር እንደሚያገኝ አያጠራጥርም። የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ አራት ጥቅሞች እንደሚኖሩት ከዚህ በፊት በማስረጀ አሳይቻለሁ–ገንዝብ ለማሸሽ፤ ትርፍ የሚያስገኙ ተቋሞችን ለመገንባት፤ የውጭ አገሮችን ድጋፍ ጭብጥ ለማድረግ፤ የገዥውን ፓርቲ የመከላከያ ሃይል ለማጠናከር። ይህ ከሆነ፤ የአበዳሪ ድርጅቶችና ለጋስ የምእራብ አገርች ሚና ይለወጣል ማለት ነው። ጫና የማድረግ ችሎታቸው የበለጠ ዝቅ ይላል። ሆኖም፤ ይህ ለውጥ ለተቃዋሚው ክፍል እድል ይከፍታል። እድሉን ለመጠቀም ከተፈለገ፤ ተቃዋሚ ፓርቲውች ከዘጠና በላይ ሆነው የትም አይደሱም። መሰብሰብ አለባቸው። ተቃዋሚወች፤ የለውጥ አሰፈላጊነት ከዚህ ህወሓት ከሚያደርገው፤ የአገርን ጥሬ ሃብት ተጠቅሞ ታማኞችን ከማክብር፤ የእራስን ደጋፊ ከማጠንከር፤ አምባ ገነንነትን ከማጠናከር ግብ ጋር አብረው ማየት አለባቸው። አለበት። አሁንም፤ ዋናው ተጠቃሚ፤ ማፍያ መሳዩ የህወሓት ምርጥ ቡድን ይሆናል። የመተባበር ሰንሰለት አሁን ካልተጀመረ እየቆየ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
የኦሮሞወች ተረት አንደሚያስተምረን፤ በእኛ (የተማርን ወገኖች ማለቴ ነው) የእራስ መውደድ የተነሳ፤ ህወሓት በመሳሪያ/ጠበንጃና በውጭ ድጋፍ ሃይል ስልጣን የያዘ፤ በእኛ መከፋፈል የበላይነትን ጭብጥ ባደረገው ህወሓት በተባለ የጠባብ ዘር ስያሜ በያዘ ድርጂት ፍጹማዊ ቡድን ነው። ቀርበን ብንመረምረው፤ ህወሓት መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀርቶ፤ የትግራይን ሕዝብ አይወክልም። እርግጥ ነው፤ ስልጣን ከያዘበት ወቅት ጀምሮ፤ ህወሓት፤ አድሏዊ በሆነ መንገድ፤ ከማንኛውም ክልል የበለጠ ባጀት ወደ ትግራይ አፍሷል። የትምርት፤ የጤና፤ የመንገድ፤ የሃይል ማመንጫ፤ የእርሻ፤ የእንዱስትሪ ተቋሞችንና የምርት ዘርፎችን ዘርግቷል። ራሱንና ጥቂት ተጠቃሚወችን አፍርቷል። በአብዛኛው ግን፤ ድሃው የትግራይ ህብረተሰብ፤ በተለይ ወጣቱ ከህወሓት/ኢሃዴግ ዘላቂነትና ፍትሃዊ ያለው ጥቅም አግኝቷል ለማለት አይቻልም። ተጠቃሚወቹ፤ የህወሓት የበላይ አዛዦች መሆናቸውን አመልካች ማስረጃወች አሉ። ሁለት ምሳሌወች። ተመስገን ደሳለኝ “የመለስ አምልኮ” በተባለው በማስረጃ የተደገፈ ጽሁፍ ላይ እንዳሳየው፤ “ማይጨው፤ ሽሬ፤ ሽራሮ፤ አድዋ፤ ተንቤን፤ አዲግራት፤ አክሱም፤ ውቅሮ፤ አዲሮቢ…ሂዱና” ቀርባችሁ መርምሩ። “ምናልባት ባለጸጋ የህወሓት አመራር ታገኙ እነደሆነ እንጂ አርሶ አደሩ እንደኔና እንደናንተ ነው” (እንደ ሌላው ድሃ ኢትዮጱያዊ ማለት ነው)። ቀጥሎም፤ “ የስልጣኔ መጀመሪያ የምትባለውን አክሱምን ተመልከቱ፤ የእነ ኢዛና፤ የእነ ካሌብ አገር….ኢትዮጵያ ነች። የፖለቲካና የንግድ ማእከል የነበርችውስ?” ህወሓት አንድ “ፋኖስ ዲተርጀንት ፋብሪካ የሚባል የሳሙና ፋብሪካ” ከመስራቱ ባሻገር ለአክሱም የድህነት መላቀቂያ ምን አመጣላት ይላል። አብዛኛው የአክሱም ወጣት ኑሮውን የሚያሟላበት ጥንት ከተሰሩት ከሃውልቶች የቱሪስቶች ገቢ ነው። የአክሱም “ብቸኛ ገቢ ቱሪዝም ነው.” ለዚህ ነው፤ ዋልድባን ሆነ፤ የአክሱምን ሃውልቶች፤ ወዘተ እንደ አገራዊ ቅርሶች ጠንቅቆ መያዝ አስፈለጊ የሚሆነው፡፡
የማን ልጅ ይማራል፤ የማን ልጅ ይሰደዳል?
ሁለተኛው ምሳሌ፤ የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣኖች በእቅድ የሚሰሩት የወጣቶች ማጎልመስ (educational investment in youth) ተግባር ሙሉ በሙሉ አድሏዊ ነው። ከተራው የትግራይ ወይንም ሌላድሃ ኢትዮጵያዊ ገበሬ ልጆች እድገትና የወደፊት እድል ሲታይ ቀጭ ነው ለማለት ያስደፍራል። ማን ተጠቃሚ ሆነ? የህወሓት የበላይ ባለስልጣኖች ልጆች ናቸው። ህወሓት የወደፊት መሪወችን፤ ሃብታሞችን፤ እያሰለጠነ ነው ለማለት ይቻላል። የስዮም መስፍንን ምሳሌ ተጠቅሞ “ይድረስ ለኢሃዴግ አመራር አባላት፤ ልጆቻችሁ ቻይና ምን እየሰሩ ነው?” በማለት ተመስገን ደሳለኝ “እናንተ የግንባሩ አባላትና ደጋፊወች! ለመሆኑ አብዛኞቹ የፓርቲያችሁ አመራሮች ምን እያሰቡ እንደሆነ ቀርቶ ምን እያደረጉ እንደሆነ ታውቃላችሁ? ለምሳሌ ስዮም መስፍን፤ ስብሓት ነጋ፤ አባይ ጸሓዪ፤ ክንፈ ገ/መድህን (በህይወት የሌሉ)፤ አርከበ እቁባይ፤ በረከት ሰምኦን፤ አዲሱ ለገሰ…ልጆቻቸው የት ናቸው?…..ካላወቃችሁ እኔ ልንገራችሁ፤ እነዚህ የባለስልጣኖች ልጆች የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፤ የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ከቅርብ አመታት ወዲህ “ወዳጅ” በሆነቻቸው ቻይና ይከታተሉ ዘንድ ተልከዋል….” ድሃው የትግራይና የሌላው ኢትዮጵያ ገበሬ ወይንም መካከለኛ መድብ የለት ጉርስ ለማግኘት ይቸገራል። እነዚህ ምርጥ ተጠቅመው ሲታዩ፤ ማንም ሊጠይቀን አይችልም ብሎው ነው።
ወጣቶች እውነት ወላጆቻቸው በራሳቸው ጥረት ባገኙት ገቢ ሳይሆን የሚደገፉት በኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ ገቢ ነው። ጸሃፊው እንዳሳሰበው፤ “ እነዚህ ወላጆች ነጋዴ አይደሉም፤ ወይም ተራ ኢትዮጵያዊ አይደሉም። የሃገሪቱ ፈላጭ ቆራጮች እንጅ።” ልጆቻቸውን ምርጥ እድል የከፈቱላቸው “ፈላጭ ቆራጭነታቸውን” ተጠቅመው፤ ማንም ሊጠይቀን አይችልም ብሎው ነው። የስርአቱ አድሏዊ፤ በደላዊ፤ ዘራፊያዊ መሆን በዚህም ተከስቷል።
የእነዚህን ምርጥ ወጣቶች በድሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወጭ በወዳጇ ቻይና ብዙ ሽህ ዶላር እየተከፈለ መማር ስናይ፤ የእነሱ መማር ለምስኪኑ የትግራይ፤ የጋምቤላ፤ የአፋር፤ የኦሮምያ፤ የሶማሌ፤ የጉራጌ፤ የአማራ ወዘተ ድሃ ገበሬ ልጅ፤ በብዙ ሽህ በየወሩ ለሚሰደደድው ወጣት፤ እንደ ተራ ሸቀጥ በእየቀኑ ወደ ሳውዲ አረቢያ ለሚላኩት እህቶቻችን ምን ፋይዳ አለው። የሚደጉመው የወደፊት ገዥወችን መሆኑን ለመጠራጠር አይቻልም። የህወሓት አገዛዝ፤ በተለይ ለድሃው የሚዘገንን የሚሆነው ለዚህም ጭምር ነው።
አፈጣጠሩን ስናይ፤ ልክ እንደ ጣሊያኖች የ “ከፋፍለህ ግዛውን” አገዛዝ አይነት- ለመግዛት፤ ለመማር፤ ሃብት ለመያዝ፤ አመቻች የሆነውን ዘዴ በመጠቀም መጀመሪያ፤ አንድ ብሄርን፤ “መኳንንት፤ መሳፍንት፤ ነፍጠኛ፤ ፌውዳል፤ አህያ፤ ኢሰፓ፤ አድሃሪ” እያለ ህብረተሰቡን ከከፋፈሉ በኋላ፤ በዘርና በቋንቋ–አማራ፤ ኦሮሞ፤ ትግሬ፤ ጉራጌ፤ ሶማሌ፤ አፋር፤ አገው፤ ደቡብ፤ አኟክ፤ ወዘተ እያለ፤ ለያየን። መለያየቱ የእኛ መጥፊያ መሳሪያ እየሆነ ነው። በቋንቋና በዘር፤ በሃይማኖትና በመደለል ሊለያየን የሚሞክረው እንደ በሬወቹና ጅቡ ተረት እያታለለ ሊገዛን፤ “ሊያጠፋን”፤ ሊያደክመን፤ ሊያሳድደን እንጅ ሊያጎለምሰን አይደለም። መከፋፈል ለሙስና፤ ለዘረፋ አመቻች ነው።
ምሳሌ ልስጥ። እኛ ከጋና የባሰ የብሄር/ብሄረሰብ ስርጭት የለንም። እንዲያውም፤ በትብብራችን የተነሳ፤ ሃገራችን ለጋና ሆነ ለመላው የጥቁር ህዝብ መኩሪያና አርአያ፤ የነጻነት አምባ ነበረች። ዛሬ፤ የጋና ህገ መንግስት በብሄር መደራጀትን ከከለከለ ቆይቷል። ጋና፤ የህዝብ ድምጽ የተከበረባት አገር እየሆነች ነው። ጥንታዊቷን ኢትዮጵያን ግን ወደ ኋላ የጎተቷት ህወሃትና መሰል በብሄር የተደራጁ የፖለቲካ መሪወች ናቸው። እነደ ኢትዮጵያዊ አብሮ መኖር፤ መታወቅ ዋጋ እዳይኖረው መደረጉ የዱሮ መታወቂያችንና መከበሪያችን፤ የዛሬ ሃፍረታችን ሆኗል። ስደታችን የዚህ ዋና ምስክር ነው።
እኛ ኢትዮጵያዊያን ቋንቋችን፤ ቀለማችን፤ ሃይማኖታችን፤ አኗኗራችን ቢለያይም የማያለያዩን ብዙ እሴቶች አሉ። አገራችን የመጀመሬያው ሰው የተፈጠረባት አነደመሆኗ መጠን፤ የሁላችንም የሰው ግንድ አንድ ነው። ደምና አጥንቱ ቢመረመር ሰንሰለቱን ያሳያል። ማንም ኢትዮጵያዊ በአራት አያቱ ያለው የዘር ግንድ አመጣጡ ሲታይ ድብልቅ ነው። ድብልቅነታችን ክብራችን ነው። ባደግሁበት ጎንደር፤ የትግራይ፤ የኦሮሞ፤ የሰላሌ፤ የአገው፤ የጉራጌ፤ የየመን፤ የግብጽ፤ የጣሊያን፤ የአርመን፤ የግሪክ፤ የአይሁድ ወዘተ ተወላጆች ነበሩበት፤ አሁንም እንዳለኡበት አልጠራጠርም። ኢትዮጵያን የሚለያትም ይህ የህዝብ ስብጥር (Diversity) መሆኑን እኔ አልጠራርም። ይህ ስብጥር መኩሪያችን እንጂ መጥፊያችን ሊሆን አይችልም። Black Athena የተባለውን የምርምር ጽሁፍ ብቻ ማንበብ የማንለያይ መሆናችን ያመለክታል። በዘር የተርመሰረተ አስተዳደር የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአንድ የሰው ግንድ መፈጠር አይፍቀውም። የህዝብ ቁጥር እያደገ መሄድ ሰንሰለቱን ሊያጠናክረው ይገባል እንጂ፤ ሊሰብረው አይችልም። ከፋፋዮች ቢፈልጉም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪኩም፤ የወደፊት እድሉም የተሳሰረ መሆኑን ማጤን ለመላው ሕዝብ ጠቃሚ መሆኑን ደጋግሞ ማሳሰስብ ተገቢ ነው። እስካሁን ያሳየው ባህል፤ ጭቆናውና አድሎው መጥፎ ቢሆንም፤ እርስ በእስሩ በዘር ሳቢያ የማይገዳደለው አኩሪ መታወቂው መሆኑን ነው።
የህወሓት/ኢሃዴግ የአገዛዝ ስርአት ከፋፋይ ቢሆንም ያለው የዘር ግንድ ድብልቅ መሆኑ፤ (ማለትም፤ ከሁሉም የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪወች የተወለደና የተመዘዘ)፤ ለውጥ ቢመጣ የእርስ በእርስ መተላለቅ ይመጣል ብሎ መገመት አይቻልም። ሕዝቡ፤ በስር አቱና በስርጭቱ መካከል ያለውን ልዩነት ያውቃል። ሌላው ቀርቶ የኤርትራዊያንን የዘር ስርጭት ብንወስድ፤ አንድም “ንጹህ (ethnically pure) የሚል ለማግኘት ያስቸግራል። ጠቅላይ ሚንስትር መለስ በጻፏቸው ዘገባወች እንኳን፤ የሰራየ፤ የአካለጉዛይና የሃማሴን ህዝብ ከጎንደር የመጣ ነው ብለዋል። ም እራባዊ ቆላማው ምድር ኦሮሞወች ስፍረው የኖሩበት ስለሆነ የኦሮሞ ህብረተሰብ (ዘር) የተቆራኘ መሆኑን ያሳያል።
በአጠቃላይ፤
ይህ የሚያሳየው፤ የትም ብንሄድ፤ ማንኛውንም የዘር ክፍል ብናይ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃገሩን ለመጠበቅ በእየጊዜው “በጦር አበጋዞች” እየዘመተ በአራቱም ማእዘን ሲሰፍር የኖረ፤ እየተዋለደ፤ እየተዛመደ የተቀራረበ በመሆኑ ከሚለያየው ይልቅ የሚያቀራርበው ያይላል። በቋንቋ ወይንም በሃይማኖት ያለው ልዩነት፤ የሚጋራውን ኢትዮጵያዊነት ሊፍቀው የማይችለው ለዚህም ጭምር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ አመጣጡ አንድ መሆኑን ታሪክ ጸሃፊወች ብቻ ሳይሆን፤ መጽሃፍ ቅዱስ፤ ቁራን ደጋግመው በማስረጃ አቅርበውታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ህወሃት አዲስ አድርጎ በፈጠራ በሚጽፋቸው የሃሰት ታሪክና ፕሮፓጋንዳ መደለል የለበትም። መተሳሰቡ፤ መተሳሰሩ፤ አብሮ ለፍትህ፤ ለእውነተኛ እኩልነት፤ ለሃገር አንድነት፤ ለመላው ሕዝብ ሉአላዊነት መታገሉ ለመልካም አገዛዝ በር ይከፍታል። መከፋፈሉ ግን፤ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ታመው ቢቆዩም ባይቆዩም፤ በሌላ ቢተኩም ባይተኩም፤ የህወሓትን የበላይነት አይለወጥም።
የስርአቱ ተጠቃሚወች ጥቅማቸውን ትተው፤ ሊመጣ የሚችለውን የሃላፊነት ጥያቄ ወደ ጎን አድርገው፤ “ኑ፤ አዲስ የሽግግር መንግስት አብረን እንመስርት” አይሉም። የህወሓት የበላዮች፤ የውስጥ ቅራኔወቻቸውን አስወግደው፤ ተቻችለው ያለው አገዛዝ እንዲቀጥል የሚያደርጉ መሆናቸውን አልጠራጠርም። የውጭ መንግስታትም ቢሆን፤ ለራሳቸው ጠቃሚ የሆነ አማራጭ ካላዩ፤ በዘር የተከፋፈለውን የክልል ስርአት፤ በዘር የተመሰረተውን ሕገ መንግስትና አስተዳደር፤ በዘር የተመሰረተውን የስለላና የመከላከያ ተቋም፤ ለውጡ አይሉም። ማነን አይተው? በማን ተማምነው? ጥቅማቸው የሚገለገለው ባለው ወይንም በተመሳሳይ አገዛዝ ነው።
በዘር የተመሰረተው የከፋፍለህ ግዛው፤ የከፋፍለህ ምታው ዘዴ አይበቃ ብሎ፤ አሁን ደግሞ የአገራችን ሕዝብ በሃይማኖት እየበከሉት ነው። መጀመሪያ፤ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን እንደፈለጉ አመሱ፤ ህገኛውን ሲኖድ አፈረሱ፤ የበላዮቹን አሳዳደዱ፤ በምትካቸው የፖለቲካ ካድሬወችን ሾሙ፤ የታወቁ ገዳሞችን ማፍረስ ጀመሩ፤ ዋልድባን እንረስ አሉ፤ የማይተኩ ቅርሶች እንዲፈርሱ፤ እንዲሰረቁ አደረጉ፤ ወዘተ። ልክ የበሬወቹንና የአውሬውን ተረት በሚመስል ሁኔታ፤ አሁን ደግሞ በእስልምና ሃይማኖት መሪወችና ተከታዮች ላይ በተከታታይ አስቃቂ አፈና፤ እስራት፤ ማሳደድ እየተካሄደ ነው። በሰላም የሚደረገው የእስልምና ሃይማኖት ሰላማዊ አመጽ (Peaceful Arab Spring type resistance) ከስምንት ወራት በላይ ሲካሄድ ቆይቷል፤ ሊቆም አይችልም። የእስልምና ሆነ የክርስቲያን መሪወችና ተከታዮች ጥያቄ የሃይማኖት ነጻነት ጥያቄ ነው፡፡ ስለሆነም፤ የሌሎች የፍትህ፤ የሰብአዊ መብቶች፤ የህግ የበላይነት፤ የሰላም፤ የመቻቻል ወዘተ ጥያቂወች ዘርፍ ነው። ተቃዋሚወች ሁሉ በየፊናቸውና በጋራ ሊድግፉት ይገባል፡፡የሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖት መሪወችና ተከታዮች በመቀራረብ፤ በመተባበር፤ እየሰሩ መሆናቸው ለፍትህ፤ ለዲሞክራሲ፤ ለገር አንድነት፤ ወዘተ የሚደረገውን ትግል ወደ አዲስ ምራፍ እነዳሸጋገሩት ያመለክታል።
ለዚህ ሁሉ አገር ውስጥ ለሚንቀሳቅስና ታፍኖ ላለው የለውጥ ፈላጊ፤ የተሰደደው ግዙፍ ኢትዮጵያዊ (ዲያስፖራ) ምን አስተዋጾ ሊያደርግ ይችላል? በጥቃቅን ልዩነቶች ላይ ማተኮሩን ከተወ፤ ከፈቀደ፤ ከቆረጠ፤ ከተሰበሰበ፤ አብሮ ከሰራ የገንዘብ፤ የእውቀት፤ የቴክኖሎጅ፤ የዲፕሎማ፤ ወዘተ ሃይሉ ሰፊ ነው። ይህን ሃይል ለሃገርና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትህ ሊጠቀም ይችላል። ሆኖም፤ አገር ቤት ያለውን ተስፋ የሚሰጥ ሁኔታ ለማጎልመስና ለመርዳት፤ በመጀመሪያ በስደት ያለው ግዙፍ ሃይል የበታተነውን ችግር ተቀብሎ፤ ራሱ መፍታት አለበት። ራሱን ማደራጀት፤ ማጎልመስ፤ አብሮ የመስራት፤ የመደጋገፍ፤ በአንድ ድምጽ የመናገር ባህሪና አሰራር ልምዶችን በተግባር ማሳየት ይኖርበታል። ባጭሩ፤ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የተባለውን ቅርስ በስራ ማሳየት የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ይህን ካላደረገ፤ አገር ውስጥ ላለው ተንቀሳቃሽና እምቅ ሃይል የረባ አስተዋጾ ሊያደርግ አይችልም።
ይቀጥላል
July 30, 2012