50 በርሜል አዲሱ ባለ አንድ ብር ሣንቲም ከኢትዮጵያ ሲወጣ ተያዘ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
(ኤፍሬም ካሳ)
50 በርሜል ሙሉ አዲሱ የኢትዮጵያ ባለ አንድ ብር ሣንቲም በኮንትሮባንድ ከኢትዮጵያ ሊወጣ ሲል በኢትዮጵያና ኬንያ ፖሊሶች ትብብር ድንበር ላይ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ምንጮች አስታወቁ፡፡
በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር ላይ በቁጥጥር ሥር የዋለው 50 በርሜል ሙሉ ባለ አንድ ብር ሣንቲም በቁጥጥር ሥር የዋለው በኢትዮጵያዊያን እና ኬንያዊያን ትብብር ነው። በአሁኑ ጊዜ በበርሜል የታሸጉት ባለ አንድ ብር የኢትዮጵያ ሣንቲሞች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ተደርጎ በፌዴራል ፖሊስ እና በብሔራዊ ባንክ ሥር እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲሱ ባለ አንድ ብር ሣንቲም የመሐል መደቡ ላይ በቅይጥነት የተሰራበት መዳብ ትንንሽ የሞተር ጥርሶች (ጊር) ሊሰራበት ስለሚችል በቅርቡም መኖሪያቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉ ቻይናዎች በድብቅ በሻንጣዎቻቸው አከማችተው ይዘው ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር። “ምናልባትም በቅርቡ መንግስት አዲሱ ባለ አንድ ብር ሣንቲምን በመሰብሰብ ሥራ ላይ እንዳይውል ሊያደርግ ይችላል” ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለሪፖርተራችን ተናግረዋል።
አንድ ብር የወረቀት ገንዘብን ለማተም የሚወጣውን ወጪ ከገንዘቡ የመገበያያ ዋጋ (ዕሴት) እጅግ እንዲቀንስ ታስቦ የተዘጋጀው ባለ አንድ ብር ሣንቲም ገና ሳይቆይ ከገንዘቡ ዋጋ ይልቅ ሣንቲሙ የተሰራበት ብረትና መዳብ ዋጋው ልቆ በመገኘቱ ለሌላ የፋብሪካ ሥራ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚሯሯጡ ግለሰቦችና ቡድኖች በዝተዋል፡፡
የአንድ ብር ሳንቲም ከሀገር ሲያሰውጡ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በቅርቡ በኮልፌ- ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቅርቡ መታየት ይጀምራል ብለውናል-ምንጮች፡፡
ዜና -2-
ሃሙስ መጋቢት 1 ቀን 2003 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- በአቶ በረከት ስምዖን የሚመራው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በወቅታዊ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለማቀፍአዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰጡ ሊያደርግ ነው፡፡
የግል ብዙሃን መገናኛዎች (ሚዲያ) በነገው ዕለት የሚልኩትን ጋዜጠኞች አስቀድመው እንዲያሳውቁ የብሄራዊ ጸጥታና ደህንነት ጽ/ቤት መሰናዶውን መጨረሱን የዜና ምንጮቻችን አስታውቀዋል፡፡
በመጪው ቅዳሜ መጋቢት 3 ቀን 2003 ዓ.ም ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዳራሽ አቶ መለስ ዜናዊ የሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ዋና ዓላማ ሰሞኑን በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ የዓረብ አገራት የተነሳው ሕዝባዊ ንቅናቄ አንድምታ እና ሰሞኑን ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከሥልጣን እንዲነሱ ተደርጎ ወደ ማረሚያ ቤት የወረዱ የኦህዴድ ኃላፊዎች ጉዳይ ይሆናል ብለውናል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ኢትዮጵያን ሄራልድ እንግሊዝኛ ጋዜጣ፣ በሪሳ የኦሮምኛ ጋዜጣ እና ዓል-ዓለም የአረብኛ ጋዜጣ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት፣ በቀድሞው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት (ቅርንጫፍ ዴስክ)፣ በአዲስ አበባ ብዙሃን መገናኛ፡- አዲስ ልሳን ጋዜጣ፣ ኢቲቪ 2 እና ኤፍ ኤም 96.3 ብዙሃን መገናኛዎች ውስጥ ”የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ‘ የሚል ዴስክ አስቀድሞ አቋቁሟል ያሉን የዜና ምንጮቻችን በዚህ ዴስክ ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞች ህብረተሰቡ ውስጥ በመግባት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የዳሰሳ ጥናቶችን በማካሄድ መንግሥት አስቀድሞ ህብረተሰቡ ያለውን ወቅታዊ ግንዛቤ አውቆ ተገቢውን ትምህርትና ማሻሻያ እንዲወስድ የሚያስችል ነው በማለት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊም የሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅታዊ ውጥረቶችን የሚያስተነፍስ ነው ብለውናል፡፡