­

ከፍ ያለ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተደረገ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


(ኤፍሬም ካሳ)
ከመጋቢት 1 እስከ 30 2003 ዓ.ም ተግባራዊ የሚኾን አዲስ የዋጋ ጭማሪ ተመን ትላንትን ይፋ ተደረገ። በዚህ መሰረት ቤንዚን፣ነጭ ጋዝ/ኬሮሲን/ እና ነጭ ናፈታ ከፍ ያለ የዋጋ ማሻቀብ አሳይተዋል። ናፍታ በሁለት ብር ከ45 ሳንቲም እንዲሁም ነጭ ጋዝ 1 ብር ከ70 ሳንቲም ጨምሯል፡፡

ትናንት ምሽት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለሕዝብ ይፋ በተደረገው ጭማሪ መሠረት በሊትር 12.36 ብር ሲሸጥ የነበረው ነጭ ጋዝ (ኬሮሲን) ከዛሬ ጀምሮ በ14.05 ብር መሸጥ ጀምሯል፡፡ የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ ሲሸጥበት ከነበረው 16.50 ወደ 18.33 በማሻቀብ የ1ብር ከሰማኒያ ሳንቲም ግሽበት አሳይቷል፡፡ በሊትር 13.94 ብር ይገኝ የነበረው የነጭ ናፍታ ዋጋ አሁን ወደ 16.37 አሻቅቧል፡፡

የነዳጅ ምርቶች ላይ የተደረገው ጭማሪ ትላንት አመሻሽ 12፡00 ሰዓት ላይ በይፋ እንደተደረገ በማግስቱ ከሚገጥማቸው ጭማሪ ለመዳን የአዲስ አበባ የነዳጅ ማደያዎችን በረጃጅም ሰልፎች ያጨናነቁ ባለመኪናዎች ተሳክቶላቸው ነዳጅ ሊቀዱ አልቻሉም፡፡ የነዳጅ ማደያዎቹ በማግስቱ የሚያገኙትን ትርፍ በማሰብ ምርቶቻቸውን ይዘው የለም ማለቱን መርጠዋል፡፡ የታክሲ ትራንስፖርትን በተመለከተ ከአጭር መንገድ እስከ ረጅም መንገድ የሚጓዙ ባለ ታክሲዎች ከ 5ሣንቲም እስከ 20 ሣንቲም ጭማሪ አድርገዋል፡፡

አዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው ኮቢል ነዳጅ ማደያ ውስጥ በነዳጅ ቀጀነት የሚተዳደሩ አንድ ሰራተኛ”‹‹ እስቲ አስበው! እኔ ከሥራዬ ልምድ እንዳየሁት የነዳጅ ምርት ዋጋ ሲጨምር የኑሮም ነገር በዚያው ልክ እሳት ይሆናል፡፡ አሁንስ እንዴት እንደምንዘልቀው እንጃ!?” ብለዋል ለሪፖርተራችን።

በዚሁ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ጭማሪ ሳቢያ በሸቀጦች ላይ የተደረገው “የዋጋ ንረት ማረጋጊያ ተመን እርባና ቢስና ፍሬ-አልባ ሊሆን እንደሚችል አዲስ ነገር ያነጋገራቸው አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሞያ ይናገራሉ። ‹‹ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከዋጋ ግሽበት ጋር በተያያዘ እየተከሰቱ ያሉት እንግዳና ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ ኹነቶች የኢህአዴግ መንግሥት ኑሮውን ማረጋጋትና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችን በብቃት መምራት እንደተሳነው ጠቋሚ ናቸው›› ይላሉ።

ባለሞያው ‹‹ የነዳጅ ዋጋ ንረት ከኑሮ ውድነትና ፖለቲካዊ እመቃ ጋር ተደምሮ ሕዝባዊ ንቅናቄን ሲያስከትል በአገራችንም ሆነ በዓለም ያልተለመደ ክስተት አይደለም›› በማለት የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ሥርዓት ውድቀትና የ1970ዎቹ የአረቡን ዓለም እና የኃያላን አገራት ማህበራዊ ምስቅልቅል በአስረጅነት ያቀርባሉ፡፡

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የትራንስፖርት ዋጋን በማናር ብቻ አያበቃም፡፡ የቀጥታ ተፅዕኖውን በሸቀጦች ዋጋ ላይ ያሳርፋል። የትራንስፖርት ዋጋ መጨመር ተከትሎ በአገር ውስጥ የሚመረቱ እህሎችና ሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋም ይጨምራል፡፡ “ይህ በተዘዋዋሪ ሥራ አጥነት በተንሰራፋበት እና አብዛኛው ሕዝብ በድህነት በሚኖርባት አገራችን ላይ የሚያስከትለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አያጠያይቅም “ይላሉ ባለሞያው።

በቅርቡ በግብፅና በቱኒዚያ የተካሔዱት አብዮቶች ዋነኛ መንስኤ የዋጋ ንረት፤ሥራ አጥነት፤ ጭቆናና አምባገነንነት ናቸው። ሁሉም መንሳኤዎች በኢትዮጰያ ተንሰራፍተዋል። ከትላንት ምሽት ጀምሮ የነዳጅ ምርቶች ላይ የተደረገው ጭማሪ እና ተያይዞ ሊመጣ የሚችለው የኑሮ ግሽበት የአዲስ አበባ ነዋሪ አበይት ርእሰ ወሬ ኾኖ ውሏል።
የተደረገው ጭማሪ ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የአሁኑ ለዘጠነኛ ጊዜ መኾኑ ነው፡፡