እንደማሙሽ እንሳቅ!
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ሆድዎትን በዕጅዎ ደግፈው በሁለቱም ዓይኖችዎ ጣምራ የዕንባ ዘለላዎች እስከሚወርዱ ድረስ ከትከት ብለው እንዲስቁ ምክንያት የሚሆን ጓደኛ ካለዎት እንደ ግል ሃኪምዎ ይቁጠሩት። ሳቅ ወይም ቀልድ ጤናማ ህይዎት ለመምራት ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ምርምሮች አረጋግጠዋል። ሳቅና ጤንነት ምን አገናኛቸው የሚል ጥያቄ ማንሳትዎ አይቀርም። በሁለቱ መካከል ያለው መስተጋብር እንዲህ ነው። በምንስቅበት ጊዜ የሥነ ፍጥረትን ህግ ተከትለው ኬሚካላዊ ለውጦች በሰውነታችን ውስጥ ይካሄዳሉ። ጭንቀትና መረበሽን የሚፈጥሩብን አድሬናሊንና ኮርቲሶል የተሰኙት ኬሚካሎች በሳቅ ጊዜ መጠናቸው ሲያሽቆለቁል በአንፃሩ ፍንድቅድቅ እንዲንል የሚረዱን ኢንዶርፊንስ የተሰኙት ኬሚካሎች መጠን ወደላይ ያሻቅባል።
ታዲያ ሳቅ ሲባል ከአንገት በላይ ከንፈር ሸሽቶ ጥርስ የሚገጥበትን የአሜሪካኖቹን ዓይነት የይስሙላ ፈገግታ ሳይሆን ለማቆም እስከሚቸገሩ ድረስ እንደኮረኮሩት ልጅ ልብዎ እስኪጠፋ የሚከሰተውን ሳቅ ነው። ለአብነት ያህል ይህንን ይመልከቱ። ሌላም አለ። ከልብ በምንስቅበት ጊዜ በሽታ ለመቋቋም የሚረዳን የተፈጥሮ መከላከያ በእጅጉ ይጠናከራል። የኮሜዲ ፊልሞችን የሚያዩ ግለሰቦች ትኩረት ከሚስብ ፊልም ተመልካቾች ጋር ያነፃጸረ ጥናት እንደሚያስረዳው አዘውትረው ኮሜዲ የሚመለከቱ ሰዎች ልባቸው የተሻለ የጤና ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተረጋግጧል። የኮሜዲ አፍቃሪዎች የደም ዝውውር 25% መሻሻል ሲታይበት በአንፃሩ ትኩረት የሚስብ ፊልም ተመልካቾች በ35% ዝቅ ብሎ ተስተውሏል።
ሳቂታነት አመለ ሸጋ ያደርጋል። ቆንጆና ማሽላ ሳይስቁት ይስቃል ስለሚባል በምክሬ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆኑት የኔ ቢጤ ፉንጋ ከሆኑ ነው። ይሳቁ። ጤናማ ብሎም ቀና ሰው ይሆናሉ። ቀና ሲሆኑ ጨለምተኝነት ለብሩህ ተስፋ ቦታውን ይለቃል። ውድ ወገኖቼ፡ የልባችን ባይሞላም፣ ያሰብነው ባይሳካም፣ በአገራችን ፖለቲካ ወልጋዳነት ብንንጨረጨርም አጋጣሚ ስናገኝ እንደማሙሽ ከትከት ብሎ መሳቅ እንልመድ፡)
በወርቁ ለገሠ (3/1/11)