የቢሾፍቱ ሪፈራል ሆስፒታል በተጽዕኖ ሐሰተኛ መግለጫ ሰጠ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


BBN –

እሁድ ዕለት በቢሾፍቱ በንጹኃን ላይ የተፈጸመውን መንግስታዊ ጭፍጨፋ ተከትሎ ተጎጂዎችን ሲያክም የነበረው ቢሾፍቱ ሆስፒታል ሁኔታውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ፡፡ መግለጫውን ለጋዜጠኞች የሰጡት በሆስፒታሉ ጠቅላላ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ማንደፍሮ ኬሲ እና የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ባይሳ ተገደው በሰጡት በዚህ መግለጫ ላይ በጥይት ተመትተው የሞቱ ሰዎች እንደሌሉ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት በኢሜርጀንሲ ዲፓርትመንት ተረኛ ሐኪም የነበሩት ዶክተር ማንደፍሮ ‹‹እኛ ጋር የመጡ ሰዎች አፈር፣ አመድ የለበሱ፣ የረጠቡ፣ በአፍ በአፍንጫቸው ውስጥ አሸዋና አፈር የገባ ሰዎች ናቸው፡፡ ሁሉም ሰዎች የሞቱት በዚህ ዓይነት መልኩ ነው፡፡ እንጂ ምንም ዓይነት በጥይት የተመታም ሆነ የቆሰለ ሰው አልነበረም፡፡›› በማለት እውነታውን ለመካድ ሞክረዋል፡፡ የሞታቸው መንስኤም መረጋገጥ እና መተፋፈን ብቻ እንጂ ጥይት አለመሆኑን ተረኛው ዶክተር ተናግረዋል፡፡

ከ700 በላይ ሰዎች ህይወት በጠፋበት እና የጥይት ድምጽ ሲያጓራ በዋለበት የእሁድ ዕለቱ የኢሬቻ በዓል ላይ ታንክ እና ሄሊኮፍተር ጭምር ተሰማርቶ ንጹኃንን ሲፈጅ መዋሉ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ፣ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት እና ሌሎች የመንግስት አካላት በዕለቱ ተኩስ ቀርቶ ወፍ አለመጮሁን ሲናገሩ ተስተውለዋል፡፡ የታጠቁ ወታደሮች ጥይት ሲያርከፈክፉ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ለመረጃ ቢኖሩም፣ ቢሾፍቱ ሪፈራል ሆስፒታልን ጨምሮ የመንግስት አካላት ግን አሁን ድረስ የውሸት መግለጫ በመስጠት ተጠምደዋል፡፡ የፈጸሙትን ጭፍጨፋ ተከትሎ የተለያዩ ጫናዎች እየመጣባቸው የሚገኘው በተለይ የህወሓት ባለስልጣናት፣ ጉዳዩን ለማስተባበል እና ከተጠያቂነት ለማምለጥ የቢሾፍቱ ሪፈራል ሆስፒታል የሐሰት መረጃ እንዲሰጥ ማስደረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡