ይድረስ ለክቡር አቶ ፈቃደ ሸዋቀና (ከፌስቡክ የተገኘ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ከሰለሞን አባ
ሰላምታየን እንደ “ያ ትውልድ” የፍቅር ደብዳቤ ሳላስረዝም ወደዋናው ጉዳየ ልግባ ።
ክቡርነትዎ ኢሳት የግንቦት ሰባት ልሣን መሆኑን አውቀው በአንዳንድ ነገር ሊያጋድል ይችላል ብለው መጠርጠርዎ መልካም ። ነገር ግን ለፖለቲካል ሰርቫይቫል ተብሎ ድንበር ያልለፈን አካሄድ ደግሞ ሌላው ወገን አይቶ እንደማያልፍ አልጠረጠሩም ። በሌላ በኩል ደግሞ የሌሎች ድርጅቶችንም አቤቱታ አልተመለከቱም ወይንም ሌሎች ድርጅቶችን ለመውቀስ ድፍረቱን ስላጡ ያማራ አክቲቪስቶችን ከነካካሁ ሌሎቹም መልዕክቱ ይደርሳቸዋል ብለው አስበውም ይሆናል ። አለበለዚያማ መኢአድን ያህል ድርጅት ሳያውቁት ብቻ ሳይሆ ሳይከታተሉትም አልቀሩም ። መኢአድ በም/ሕዝብ ግንኙነቱ አቶ ለገሠ ወ/ሀና አማካኝነት ወያኔ አባሎቻችንን ያፍናል ኢሳት ደግሞ ያባሎቻችንን የመታፈን ዜና ያፍናል ብሎናል ። በተደጋጋሚ ለኢሳት መግለጫ ቢልኩም ኢሳት በጓሮ በር አውጥቶ እንደሚጥል በግልፅ ተናግረዋል (ይህ እንግዲህ የዚህ ሦስት ቀን መነጋገሪያችን ሆኖ የሰነበተ ነው) ።
ክቡርነትዎ የራሳቸውን አይሰሩምና ኢሳትን ለማፍረስ የተነሱ የአማራ ነፃ አውጪዎች ብለው ክስ አቅርበዋል ። ለማፍረስ ያሚለውን ሐሜት ሳልፈራ ፤ ሳልሸማቀቅ እንዲሁ ችላ ብየ አልፈውና (ምክኒያቱም ስለሌለ) ኢሳትን መተቸት ሜድያ ይኑረንም አይኑረንም ይቀጥላል ። ኢሳት ከትችት የሚድነው ስነምግባሩን ሲያሳርም እንጅ አማራ ሜድያ ስለያዘ አይደለም ። ሜድያውን ደግሞ በቅርብ ያ ትናንት የግንቦት ሰባት አባሎችን ስድብ (degradation) ተቋቁሞ ለዛሬው ያማራ ልጆች መነቃቃት መሠረት የሆነው ሞረሽ ወገኔ በሬድዮ መልክ በቀናት ውስጥ ይጀምረዋል ። እርሰዎም ይህን ሞረሽ የዐማራ ድምፅ ሬድዮ በመርዳት ወደተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል የበኩለዎን እንደሚያበረክቱ ጥርጥር የለኝም ።
ክቡርነትዎ ኢሳትን ከስሕተቱ እንዲማር መምከር ተገቢ እንደሆነ ያስቀመጡት ድንቅ ሐሳብ በሌሎች በሐሳብ የተለዩዋቸውን “ጭቃ” እና የመሳሰሉ ቃላቶችን በመገብየት የስድብ ናዳ በሚያወርዱ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት የለውም ፤ አልተቀበሉትምም ። (ጭቃ! የሚለውን ኦድዮ ሰምተው ይሆናል) ።
ክቡርነትዎ እርሰዎ አማራነትን ከኢትዮጵያዊነት የሚነጥሉ ሐይሎች ብለው መሠረት የሌለው ክስ አቅርበዋል ። ኢሳት አማራ ብሎ ሊጠራን ያፍርና “ያማራ ክልል ሰው” ብሎ ከኢትዮጵያ ነጥሎ በክልል አጥሮ ሲያስቀምጠን የማይሰቀጥጠው የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ድምፅ በምን ሒሳብ ነው ከአማራ ልጆች ጋር ተወዳድሮ አማሮች አማራነትን ከኢትዮጵያዊነት የሚነጥሉ ኢሳት ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ዘማሪ ሆኖ የሚቀርበው ??
ክቡርነትዎ ሙሕር እንደመሆንዎ መጠን አንድ ነገር ተገንዝበዋል ። ይህም አሁን አማራ ነህ ብለው ሲነካኩት የሚሸማቀቅ ሳይሆን እምቢ የሚል ሐይል ለኢሳት አደጋ እንደሆነ “ኢሳትን ሊያፈርሱ” በሚለው ቃል ውስጥ ያለዎትን ስጋት አስቀምጠዋል ። ፈፅሞ ስጋት አይግባዎት !! ባይገርመዎት ኢሳትን ተችተዋል ከተባሉት አንዱ ሄኖክ የሽጥላ በቅርብ ኢሳትን የምንተቸው እንዲያስተካክል እንጅ ለማጥፋት አይደለም በማለት ኢሳትን መርዳት እንዳለብን አመላክቶናል ። ባይሆን የራሳችን ሜድያ ልክ የኦሮሞ ወንድሞቻችን እንዳላቸው ሁሉ እኛም ይኖረናል ። ይህ አማሮች የራሳቸው የሆነን የሬድዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ መመስረት ኢሳትን የሚያፈርሰው ከሆነ ግን ተጠያቂ የሚሆን አካል የለም ።
ክቡርነትዎ ኢሳት የማንኛውን ያማራ ድርጅት እንደሚያገል እንዲነገርዎትና ወቀሳ እንደሚያቀርቡ አስተያየት መስጫ ላይ ጥያቄ አቅርበዋል ። ለዚህ መልስ አልለኝ ነገር ግን ስሞታ እንዲነግሩልኝ አለመሆኑ ይታወቅልኝ ። ባይሆን ከእርሶ የሚደበቅ ነገር አይኖረንምና በግልፅ አስቀምጠዋለሁ ። አዴሐን ከግንቦት 7 ቀደም ብሎ ኤርትራ በርሀ የገባው ያማራ ልጆች ድርጅታችን አንዱ የዚህ ደባ ሰለባ ነው ። ኢሳት ኤርትራ ገባሁ ባለበት ወቅት እባካችሁ ከሕዝብ አገናኙን እኛንም አናግሩን ብለው ኢሳቶችን ሲጠይቋቸው ኢሳት እነ ሳልሳይ ወያኔና ሌሎች የጎሣ ሓይሎች ጋር ስራ በዝቶበት ስለነበር ጆሮ አልሰጣቸውም ። በተደጋጋሚ በመደወል ኢሳትን ስለትግላቸው እንዲዘግብላቸው የሚያቀርቡትን ሁሉ አንድም ቀን አቅርበው አያውቁም ። ይህን ድርጅት ኢሳት ከመሬት ተነስቶ ከግንቦት ሰባት ጋር አንድ ሆነ የሚል ዜና ባሰራጨበት ወቅት ድርጅቱ መሠረት የሌለው ወሬ ነው ብሎ መልስ ሰጥቶ ነበር ። ኢሳቶች ይህን ድርጅታችንን በዚያ አቂመውበት ይሆን ?? ካልጋለብኩህስ ተብሎ ቂም ይያዛል ??
በሁለተኛ ደረጃ ዳግማዊ መ.ዐ.ሕ.ድ. የታላቁን መሪያችንን ፕሮፌሰር አስራት ፈለግ ተከትሎ የወጣው ድርጅታችን ወራትን ቢያስቆጥርም የጎሣ ሐይሎችን በባትሪ ፈልጎ የሚያቀርበው ፤ አማርኛን የሚጠሉትን ደግሞ በእንግሊዝኛ ለውይይት የሚጋብዘው ኢሳት ሊያናግራቸው ፈቃደኛ አይደለም ። እነርሱም አይለምኑትም (ቆራጦች ናቸዋ! ሲፈልግ በራሱ ይምጣ) ። መሪውን አናቅም በማለት ማስተባበል ውሐ አያነሳም ። ምክኒያቱም የድርጅቱ ድሕረ ገጽ ላይ ሊገናኟቸው ስለሚችሉ ። ሲጀመር የአንድን ድርጅት አመራር አፈላልጎ ማግኘት የጋዜጠኛ ስራ ሲሆን ለኢሳት ደግሞ በዘመነ ኢንተርኔት በጣም ቀላሉ ነው ። እባክዎን ሂደው እንዳይወቅሱ ። ይሄን እርሰዎ ስለጠየቁ ብየ እንጅ ላማራ ልጆች ኢሳትን እንዲሸመግሉ አይደለም የጻፍኩት ። እባክዎን ስሞትልዎ ።
ከምላጭ የሰላው ወጣቱ የአማራ ትውልድ ሳይሽመደመድ ፤ ሳይሳቀቅ ፤ ያለምንም ይሉኝታ መሰናክል ሆነው የሚገቡ ሐይሎችን እያገለለ ትግሉን ጥግ ያደርሰዋል ። ዕድሜና ጤና ይስጠን ብቻ ። እርሰዎን ያህል የሐገር ሐብት ትምክህተኛ አማራ ተብለው ከአዲሳባ ዩኒቨርስቲ የተባረሩበት አማራ መሆን መጭውን ትውልድ (የእኔን ትውልድ ጨምሮ) ሊያሸማቅቅ ከቶውኑ አንፈቅድለትም ።
ክቡርነትዎ ኢሳትን እየወቀስኩ አለመሆኑ ይታወቅልኝ ። ስለኢሳት ላውጋ ያልኩ እንደሆን ቀኑ ባጠረኝ ። ባንድ ወቅት በሞረሽ ላይ ከዘመተው የኢሳቱ ሊቀመንበር ጀምሬ እስከ ዛሬዋ ዕለት ያልሉ ስሕተቶችን ለመጻፍም አልተነሳሁም ። ባይሆን ዋናው ቁም ነገር እርሰዎ የጻፉትን እንደመደፋፈሪያ አድርገው የስድብ ናዳ የሚያወርዱትን ለማስገንዘብ ነው ።
ክቡርነትዎ ባሉበት ሰላምን እመኝለዎታለሁ ። ሰላም ውለው ይግቡ ።