መንግስት የቅሊንጦውን እሳት አደጋ በታሳሪዎች ላይ ለመደፍደፍ የሚያደርገውን ጥረት ያቁም! ድምፃችን ይሰማ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ድምፃችን ይሰማ
#EthioMuslims #EthioMuslimPeacefulStruggle
#EthioMuslimPrisoners
መንግስት የቅሊንጦውን እሳት አደጋ በታሳሪዎች ላይ ለመደፍደፍ የሚያደርገውን
ጥረት ያቁም!
ንጹሃን ታሳሪዎችን ማንገላታት ይብቃ!
ቅዳሜ መስከረም 21/2009
መንግስት የአገርን ህልውና የማስጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት አካል እንደመሆኑ
መጠን የአገር ህልውና ምሰሶ የሆነውን ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት።
ይህንን ማድረግ ሲችል የአገር እና የህዝብ አለኝታ መሆኑን ያስመሰክራል፡፡
መንግስት አሁን እየሄደበት ያለው የዚህ ተቃራኒ ጉዞ በህዝብ ልቦና ውስጥ
የሚታነፅ ጥቁር ታሪክ ገንብቶና ከገዛ ህዝቦቹ ጋር ደም ተቃብቶ የታሪክ ባለ እዳ
እንደሆነ ወንበሩን ለተረኞች የሚያስረክበትን አይቀሬ ሂደት አመላካች ነው።
ሃያ አምስት ዓመት ያለፈው የገዢው መንግሰት የአገር አስተዳዳሪነት ታሪክ
ለህዝብ ሰላማዊ ጥያቄዎች ከአፈና የተለየ መልስ እንደሌለው እና ለአገር
ዲሞክራሲያዊ እድገት የሚጠቅሙትን የመብት ጥያቄ ያነሱ ዜጎች ላይ
በየትኛውም አጋጣሚ የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡
የመብት ጥያቄ ያነገቡ ዜጎች ከመነሻው በማስፈራሪያና በዛቻ የፍርሀት ድባብ
ውስጥ እንዲኖሩ የመንግስት ፀጥታ ሃይሎች ሌት ተቀን የሚለፉ ሲሆን ብዙሃኑን
ህዝብ በድብደባና በግድያ፣ ከዚህ የመብት ጥያቄ ጀርባ ንቁ ተሳታፊ ናቸው
የሚሏቸውን ደግሞ በእስር በማንገላታት ይበቀላሉ፡፡ እነዚህ ታሳሪዎች ተገቢ
ባልሆነ የህግ ሂደት በማዕከላዊ ያልሰሩትን ወንጀል እንዲናዘዙ ከአራት ወር
ለሚበልጥ ጊዜ በተለያዩ መንገዶች የሚሰቃዩ ሲሆን የግፍ ክሱ ተመስርቶባቸው
ወደ ቂሊንጦ ሲሄዱም ይኸው ስቃይ መልኩን ቀይሮ ይጠብቃቸዋል፡፡ በካንጋሮው
ፍርድ ቤት የሚከናወነው ተውኔታዊው የክስ ሂደት ሳይቀር እነዚህን ንፁሃንን እና
ቤተሰቦቻቸውን በሚያሰቃይና ተስፋ በሚያስቆርጥ መልኩ የሚካሄድ ነው፡፡
ንፁሀን ታሳሪዎችን የማሰቃየቱ ሂደት ቀጥሎ በወርሃ ነሐሴ በቂልንጦ ማረሚያ
ቤተ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ንፁሀን ታሳሪዎች
ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በርካቶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህንን አደጋ
ተከትሎ ንፁሀን ታሳሪዎች ወደ ሸዋሮቢትና ዝዋይ ማረሚያ ቤት የተዘዋወሩ ሲሆን
በእነዚህ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ምግብና መጠጥ መከልከልን ጨምሮ በርካታ
ስቃዮች እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡ የማዕከላዊ መርማሪዎች ወደእነዚህ ማረሚያ
ቤቶች በመሄድ ታሳሪዎቹን ‹‹እኛ ነን እሳቱን ያቃጠልን ብላችሁ እመኑ›› በሚል
ከባድ እንግልትና ስቃይ እያደረሱባቸው እንዳለ ከውስጥ የሚመጡ መረጃዎች
እያሳዩ ነው፡፡ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከተመለሱም በኋላ ስቃይና እንግልቱ
ከቀን ወደ ቀን እየጨመረባቸው ይገኛል፡፡ ንፁሃን ታሳሪዎች ላይ በማረሚያ ቤቱ
በተነሳው የእሳት ቃጠሎ የጥፋተኝነት ብይን ለመስጠት ክስና ለክስ ሂደቱ
የሚሆኑ የሀሰት ምስክሮችንም መንግስት እያዘጋጀ ይገኛል፡፡
እነዚህ ትንኮሳዎች እና በደሎች ህዝብን ለማሸማቀቅ፣ የመብት ትግልን ለማፈን
የሚደረጉ የተለመዱ ከንቱ ሙከራዎች ናቸው፡፡ መንግስት እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ
በዚህ የግፍ ተግባሩ በህዝብ ዘንድ የተቀጣጠለውን የትግል ስሜት ከማጋጋልና
እየተከናነበ ያለውን የፖለቲካ ኪሳራ ከማባባስ ያለፈ አንዳች ጥቅም የማያገኝበት
በመሆኑ ንፁሃን ታሳሪዎችን ማንገላታት እንዲያቆም በጥብቅ እናሳስባለን! በዚህ
ሂደት በሚደርሱ ጉዳቶች ሁሉ ተጠያቂው መንግስት መሆኑን ህዝብ በሙሉ ልብ
የሚያውቀው እውነታ በመሆኑም ትርፍ የማያገኝበት የበቀል እርምጃ ከተጠያቂነት
እንደማያድነው መንግስት ሊያውቅ ይገባል!
በዚህ አጋጣሚ ህዝብ ከእነዚህ በግፍ እየተሰቃዩ ከሚገኙ ጀግኖችና
ቤተሰቦቻቸው ጎን በመቆም አጋርነቱን እንዲያሳይ ጥሪ እናቀርባለን!!!
መንግስት የቅሊንጦውን እሳት አደጋ በታሳሪዎች ላይ ለመደፍደፍ የሚያደርገውን
ጥረት ያቁም!
ንጹሃን ታሳሪዎችን ማንገላታት ይብቃ!
ትግላችን በአላህ ፍቃድ እስከድል ደጃፎች ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!
Like ☑ Comment ☑ Share ☑
