ስብስብ የሆነ ነገር ሁሉ አገልግሎት መስጠት የሚችልን ስርአት መፍጠር የሚችለው ህግና ደንብ ሲኖረው ነው ህግና ደንብ የሌለው ነገር በዘፈቀደ የሚኖር ዝብርቅርነትና ግጭት የሚበዛበት የምስቅልቅል ስብስብ ነው። በአለም ዉስጥ ለብዙ ቢሊዮን አመታት የታወቀ ቦታ ይዘው የሚኖሩ ነገሮች ሁሉ ህግና ደንብ ያላቸው ስርአቶች ናቸው በምስቅልቅልነት ያሉት ግን ይህ ነው የሚባል ቦታም አይዙም የሚታዩትም እጅግ በጣም አጭር ለሆነ ጊዜ ነው። አንድ መንግስት እንደ መንግስትነት የህዝብ ታማኝነትን አግኝቶ ህዝብን ማገልገል የሚችለው በህዝብ ተቀባይነት ያለው ህገ መንግስትና ህገ ህዝብ ሲኖረው ነው ፤ህገ መንግስትና ህገ ህዝብ የሌለው ድርጅት መንግስት ሳይሆን ሽፍትነትና አስተዳዳሪዉም ሽፍታ ነው።
በአለም ላይ ሃያል ሃገር ሆነው የምናያቸው ህዝቦች የጥንካሪያቸው መንስኤ ህዝቡን ያሳተፈ ህገ መንግስትና ህገ ህዝብ መባጀታቸው ነው። ይህ ህገ መንግስትና ህገ ህዝብ ያኗኗራቸውን ስነ ልቦና ያካተተና የወደፊት ማህበራዊና እኮኖሚያዊ ራአያቸውን እዉን ለማድረግ የሚያስችል ህግና ደንብ የያዘና አስፈጻሚ አካል ያለው ነው። ህግና ደንብ ፈዋሽነቱ ህጉን በጣሱ የህብረተሰብ አባላት ላይ ህጋዊ እርምጃ የመዉሰድ ባህሪው ነው። በተቃራኒው በአለም ላይ ሲቸገሩ፤የሌላው አለም እድገት ምትሃት የሆነባቸውና የሌላዉን እጅ እያዩ የሚኖሩት ደግሞ ትልቁ የጥፋታቸው መንሴ ተግባራዊ የሆነ እዉነትን መሰረት ያደረገ የጋራ ደንብና ህግ የሌላቸው ህዝቦች ናቸው ወይም ደንብና ህጉን በወረቀት ላይ አስቀምጠው ህገወጥነትን ባህል አድርገው የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው። በህብረተስብ ዉስጥ ህግና ደንብን ገንብቶ አዳጊ የህብረተስብ ስርአትን መገንባት ከትምህርት እውቀትን ማግኘት ጋር ተመሳሳይነት አለው ። ህብረተሰብ መማርን የሚፈልገው እዉንተኛ የሆነ ሳይንሳዊ እዉቀትን አግኝቶ ችግር መፍታት እንዲችል ነው፤እዉቀት የሌለው ሰው እዉቀት የሚጠይቅን ችግር መፍታ አይችልም፤ እዉቀት መኖሩን ደግሞ የምናረጋግጠው በትምህርት ጊዜው ተምሮ አጥንቶ ፈተና ወስዶ ማለፉናን በሙያዉ ላይ የሚያሳያቸው ክህሎወች ናቸው ፈተናዉን በትክክል ያልመለሰ ሰው የሚወድቀዉም ተገቢ የሆነዉን እዉቀት ስላልያዘና ይዞ ስላልቀረ ነው፤ ጥያቄዉን በትክክል ሳይመልስ ስህተት መሆኑና ነጥብ ተቀንሶ መሰጠቱ የግድ የሚሆነዉን መማር እዉቀት መያዝን ይጠይቃል፤ ዩኒቨርሲቲወችና ኮሌጆች ክፍል መገኘትን ብቻ መመዘኛ ቢያደርጉት ኖሮ ህዝብ እዉቀት አልባ ሆኖ አለምም በችግር ዉቅያኖስ ዉስጥ ትዘቅጥ ነበር። ህብረተሰብም በዚህ መልኩ ነው የሚታየው፤ የወጣዉን ህገ መንግስት ተግባራዊ የማያደርጉ ህዝቦች ችግር ዉቅያኖስ ዉስጥ ይኖራሉ፤ ሌሎች በህጋቸው መሰረት ሲያድጉና ሲመነደጉ ተአምር ይሆንባቸዋል።
ህገ ህዝብና ህገመንግስት የህዝብና የመንግስት መተዳደሪያ ደንብ ነው፤ በዚህም መሰረት ህግን ማክበርና ህገወጥ ተብለው የተፈረጁ ነገሮች አሉ፤ ህገ ወጥ ለሆኑ ነገሮችም ህጋዊ ቅጣትን ደንግጓል። በህጉ መሰረት ነገሮችን መፈጸም አለማቻል ነው የህብረተሰቡን ምንነትና የወደፊት አኗኗር ህይወት የሚወስነው። አንድ ዜጋ ወንጀል ሰራ ሲባል ወንጀሉ በህግ ከተረጋገጠ በህጉ መሰረት ቅጣት መፈጸሙ የህብረተሰቡን ሃያልነትና ህጋዊ ጥንካሬዉን ያሳያል። ለምሳሌ የሰዉን ንብረት መዝረፍ ወንጀል ነው የሚል ህግ ካለ ለዚህ ህገወጥነት ቅጣት አለው ያ ቅጣቱም መፈጸም አለበት የወደፊት ዘራፊነትን ለማስቆምና ጥሩ ህብረተሰብን ለመገንባት። ሃገርን የሚበደል ነገር መፈጸም ወንጀል ነው የሚል ወንጀል ካለ የዚህን አይነት ወንጀል የፈጸመ ዜጋ በህጉ መሰረት ቅጣት ማግኘት እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ተመሳሳይ የሆነ ሃገርን የማፍረስ ወንጀልን ለመከላክልና ሃገራዊ ስሜትን ለመገንባት። ትልቁ የድሮ አባቶቻችን ሃገራችን አንድ አድርገው ያቆዩአት ሃገርን በተመልከተ የነበራቸው የማያወላዉል እርምጃ ነበር። ያም ነው አሁን በኢትዮጵያ ዉስጥ ለወያኔወች አልጠፋ ብሎ ያስቸገራቸው፤ አንድነትና ኢትዮጵያዊ መንፈስ፤ ይህ መንፈስ ነው ኢትዮጵያን በሁሉም ደም የተገነባችና የብዙ ባህሎች ባለቤት የሆነች የአንድ ህዝብ ሃገር ያደረጋት።
ሃገራችን ኢትዮጵያ በዉጭ ጠላት ስትወረር ለጠላት ማደርና ከጠላት ወገን ሆኖ ወገንን በመግደል ሃገር በቅኝ ግዛት እንድትያዝ ማድረግ ወንጀል ነበር ተግባሩም ባንዳ ሆድ አደር ይባል ነበር፤ቅጣቱም አሰቃቂ ነበር። ኢትዮጵያዉያን ባንዳ ከመሆን መሞትን መርጠው ሃገራቸዉን በክብር ጠብቀው ሞተዋል፤ በተቃራኒው እንደ ትግራዩ ሃይለስላሴ ጉግሳ የመሳሰሉት ደግሞ ባንዳ ሆነው ህዝባቸዉን ለግፍና ሰቆቃ ተገዢ እንዲሆን ከጠላት ጋር ሆነው ሰርተዋል፤ በህብረተሰቡ ግን እጅግ በጣም እርኩስ ተብለው በሃገር ከሃዲነት ተወንጅለው ሰው ሳይሆን እንደ የሆድ እንስሳ ተቆጥረው በሃግራችን ታሪክ ዉስጥ የአሳፋሪነት ቦታን ይዘው ይገኛሉ። ላለፉት 25 አመአታት የትግራይ ወያኔ ይህ ቀረ የማይባል ግፍና በደል በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሲፈጽም ኖሯል፤ እየፈጸመም ይገኛል። ይህን ወንጀል የሚፈጽመው ግን እራሱ ብቻዉን ሳይሆን ከሌላው ህዝብ በመለመላቸው ሆድ አደር ባንዳወች በመታገዝ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚመኛቸውና ተግባራዊ እንዲሆኑ ከሚፈልጋቸው ነገሮች አንዱ ሆድ አደርነትንና ባንዳነትን ትልቅ ህዝባዊና ሃገራዊ ወንጀል እንዲሆኑ ማድረግ ነው ፤ ወንጀል ከሆኑ ደግም ቅጣት መኖሩ ማህበራዊ እዉቀትን ይፈጥራል፤ትክክለኛ የሆነ ስርአትን ለመገንባትም ያስችላል፤ የህገወጥነት ቅጣት የሌለው ህብረተሰብ ዝብርቅርቅነት ዉስጥ የሚኖርና ማደጉንም ሆነ ወደኋል የመጓዙን ምክንያት ማወቅ የተሳነውና የሌሎች እድገት ምትሃት የሆነበት ስብስብ ነው። በዚህም መሰረት ወያኔን ያጠናከረ አብሮ ሃገርን በትጥቅ ሲያፈርስ የነበረና አብሮ የሰራን ሰው፤ የወያኔ ጋሻ አጃግሬ ሆኖ ለሆዱ የሚሰጠዉን ነገር በማየት ግን የህዝቡን ስቃይና የሃገሩን በደል በመተው ለረጅም ጊዜ ወንጀል ሲፈጽምና ሲያስፈጽም የነበረን ግለሰብ አስፈላጊ የሆነ ቅጣት እንጅ የሚሰጠው አሁን ከወያኔ አልተስማማም ወደእዉነተኛዉና መገንባት ወደምንፈልገው ጎራ መምጣት ፈልጓል ተብሎ እንደ ጥሩና ህጋዊ ዜጋ ተቆጥሮ በየቦታው እንዲናገርና እንዳዉን የበለጠ ጥሩ ኑሮ እንዲኖር ማስቻል፤ ወንጀልን በህዝብና በሃገር ላይ ለመፈጸም ቅንጣት ያህል ወደኋላ ለማይሉ ሰወች የኑሮ ማስቻያ ስልት እያደረግነው ነው። እንደዚህ አይነትን ሰው የኢትዮጵያ ህዝብ ማድረግ ያለበት በህጉ መሰረት ግለሰቡ እንዲቀጣ ማድረግ ፤ የሚያዉቀው ምስጢር ካለና የኢትዮጵያን ህዝብ ትግል የሚረዳ ከሆነ መረጃዉን መቀበልና መጠቀም ግን ግለሰቡ ከወንጀለኛነቱ ነጻ የሚያደረገው ምንም አይነት ነገር አለመኖሩን በተግባር ማሳየት፤ምክንያቱም የምንፈልገው ህጋዊነት(ህዝባዊም ይሁን መንግስታዊ) ማየት ለምንፈልገው ሁለገብ ለሆነው ማህበራዊ የእዉነት ተገዢነትና እድገት መለኪያችን ነዉና ።
ታምራት ላይኔ፤ ስየ አብርሃ ፤ገብሩ አስራት፤ አረጋዊ በርሄ፤ ጁነዲን ሶዶና ወዘተ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር መኖር ያላመኑ የኢትዮጵያን ህዝብ አብሮ መኖር ወንጀል ያደረጉና ተበታትኖ እንዲጠፋና ለስኬታዉም እስከመጨረሻው ድረስ የወያኔን ጥይት በኢትዮጵያውያን አናት ላይ ሲተኩሱና ሲያስተኩሱ የነበሩትን ጸረ ህዝብና ጸረ ሃገር ግለሰቦችን እንደ ህዝባዊ አጋር አድርጎ የአየር ጊዜ ወይም ቦታ መስጠትና የሚሉትን መስማት ወይም ጻፉ የተባለዉን ማስነበብ የምንፈልገዉን ነገር ለማድረግ መንገዱ የተሰወረብን መሆኑን ነው። እንደነዚህ ያሉ ሰወች መጀመሪያም ህገ ህሊና የሌላቸው ጸረ ኢትዮጵያ በመሆን ወይም በሆደ ህግ የሚተዳደሩ የህዝብና የሃገር ጠላቶች ፤ የትም ይሁን የት የበለጠ መኖር የሚያስችል ሁኔታ ከተፈጠረ አሁንም ያሉበትን ሰፈር በሆድ አደርነት ለመሸጥ ወደኋላ የማይሉ ግኡዛን ናቸው። ከወያኔ ተቃራኒ የሆነው ወገንም የሚመኘው ነገር እንደነዚህ ያሉ ሰወች በሃገር ላይ እንዳይወጡና ተመሳስይ ወንጀል እንዳይፈጸም ማስቻልና እዉነት የሚገዛው ህገህዝብና ህገመንግስት ያለው ስርአትን መፍጠር ነው። ለምሳሌ በአንድ አካባቢ ብዙ ነፍሰ ጋዳዮች ይፈለጋሉ፤ ግን ከነሱ አንዱ ብዙ ወንጀል ከሰራ በኋላ ሳይስማማ ቀርቶ ስራቸዉንና እንቅስቃሴአቸዉን አውቃለሁ ብሎ ወደ ህግ አክባሪው ወገን ከመጣ የሰራው ወንጀል አይሰረዝለትም፤ ሰው ስለገደለና የህዝቡን የመተዳደሪያ ህግ ስላፈረሰ በነፍሰገዳይነት ተከሶ በህጉ መሰረት ቅጣቱን ይቀበላል፤ የሚሰጠዉ መረጀ ደግሞ እዉነተኛ ከሆነ እንደአስፈላጊነቱ እየታየ ወንጀለኞችን ለመፈለግና ለመያዝ የህግ ክፍሉ ሊጠቀምበት ይችላል፤ ግን ግለሰቡ የሰራው ወንጀል ተሰርዞ እንደንጹህ የህብረተሰብ አባል እንዲቀጥል ካስቻልነው ህግና ህገወጥነት ልዩነቱ ጎራን መለየት ብቻ ነው ማለት ነው፤ የጥፋት መንገድም ይህ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገዉና ማድረግም ያለበት እነዚህ ሰወች በህግ ፊት ተይዘው ፍትሃዊ ቅጣት እንዲያገኙ ነው፤ የእዉነተኛ ህግና ህገወጥነት የህብረተሰባችን የእድገት መለኪያው ነው፤እድገት ካልተለካና የእድገት ለዉጡ በህብረተሱ የእለት እለት ኑሮው ላይ ካልታየ አለምን ያሰለቸውና የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያታልለው የታወቀው የወያኔ የተረት ተረት 11% አመአታዊ የመቀጨጭ ዘፈን ነው የሚሆነው።