የተማረ ሰው የማጣጣል ድርጅታዊ ባህል – ዶ/ር አዲስአለም ባሌማ ፎረሹ ፣ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግም እርቃኑ ወጣ::
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
Daniel Berhane = ሐሙስ የጀመረውን የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ስልጠና ሊያወያዩ የሄዱት ዶ/ር አዲስአለም ባሌማ ነበሩ አሉ – የትግራይ ም/ፕሬዚዳንትና የህወሓት ሰራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል።
ሰውየው ወደ ከፍተኛ ስልጣን በቅርብ ስለመጡ ሰዉ እሳቸው ላይ አይበረታም ተብሎ መሰለኝ እሳቸው የተመረጡት።
እሳቸው ደግሞ የተማሩ ቢሆኑም የተማረ ሰው የማጣጣል ድርጅታዊ ባህል ተጋብቶባቸው ይሁን ተሰብሳቢው ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ይሁን ግልጽ አይደለም፤ ስለራሳቸው የማውራት አዝማሚያ አሳዩ። አምባሳደር እንደነበሩ፣ ከመለስ ጋር እንደሰሩ፣ “ፌስቡክ ላይ ስለጻፍክ አዋቂ የሆንክ እንዳይመስልህ”፣ ምናምን።
ሐሙስ ጥዋት እንደነገሩ አለቀና ከሰዓት ተሰብሳቢው በቡድን ተከፋፍሎ ጥያቄዎችን ሲጠይቅ ቆየ። ጥያቄዎቹ ተሰበሰቡ።
አርብ ጥዋት ዶ/ር አዲስአለም ለጥያቄዎቹ ምላሽ እየሰጡ ካረፈዱ በኋላ 4 ሰዓት ገደማ ላይ ዶ/ር ገብየሱስ የሚባል ትንታግ ተነሳና፡-
“በቴሌቪዥንም ሰማናችሁ በራዲዮም ሰማናችሁ በጋዜጣም ምንም ረብ የለውም። ሰልችቶናል። አሁንም ምንም የሚነግሩን አዲስ ነገር የለም። እኛ እዚህ ምሁራን አለን። አዳምጡን የምንለውን በማስታወሻ ያዙና ከመንግስት ጋር ተነጋገሩበት።”
“ዝም ብለህ ተቀመጥ” ብለው ሊቆጡት ሞከሩ።
ዶ/ር ገብረየሱስ ግን ቀጠለ፦ “ለጥያቄዎቹ ምንም መልስ እየሰጠባቸው አይደለም። እንዲህ በቀላሉም መልስ የሚሰጣቸው አይደሉም። ጥያቄዎቹን ያቀረቡት መምህራን ዝም ስላሉ ነው እንጂ እየተቃጠሉ ነው ያሉት። ደግነቱ እኔ ምንም ጥያቄ አልጠየቅሁም። እንኳንም ያልጠየቅሁ።”
የድጋፍ ጭብጨባ ተከተለ።
ጥቂት ደቂቃዎች ሊቀጥሉ ሞከሩና ሻይ ሰዓቱ ሳይደርስ በትነውት ወጡ። ኋላ እንደገና ሰብስበው ሊቀጥሉ ሞከሩና ከ30 ደቂቃ በኋላ በራሳቸው ግዜ ስብሰባውን ዘግተው ሄዱ። ተቋረጠ ማለት ይቀላል።
የቅዳሜ ግማሽ ቀን ስብሰባም እንዲሁ በማጉረምረምና ሁካታ ተሞልቶ እንደነገሩ አለፈ። እሳቸው ተለሳልሰው መደረኩን ፈር ሊያስይዙት ቢሞክሩም መምህራኑ በጄ አላሉም።
በብዙዎች ግምትም ሌላ አወያይ እንደሚቀየር ነው።
ይታያችሁ። ዶ/ር አዲስአለም ብዙም የሚጠላቸው ሰው የሌለ እንዲያውም ተግባቢ የሚባሉ ናቸው። ክልሉ ውስጥ ያለቀጠሮ መግባት የሚቻለው እሳቸው ቢሮ ብቻ ነው። በቃ ቢሮአቸው ትሄድና ከሰው ጋር ከሆኑ ተራህን ትጠብቃለህ።
እንግዲህ የተሰብሳቢው ቁጣ እሳቸው ላይ ሳይሆን መንግስት ላይ መሆኑ አያጠያይቅም።
ስለሆነም እሳቸው የመድረኩን ግለት መቋቋምና ማለስለስ ካልቻሉ ሌላ በመጥፎ የሚታይ ባለስልጣን ቢሄድ እንዴት እንደሚሆን እንጃ።