የለውጥ ማዕበል ገፈት ቀማሽ ሳንሆን፣ ተቋዳሽ ለመሆን፣… የመፍትሄው ጅምር ይሄውና! ( ዮሃንስ ሰ. )
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
አምናና ዘንድሮ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይበልጥ እየተጋጋለ፣ እየተበላሸና አስፈሪ እየሆነ የመጣው፣ በአጋጣሚ ይመስላችኋል? በየአገሩኮ፣ ተመሳሳይ ትዕይንቶችን እያየን ነው። ግራ እየተጋባን፣ እውነታውን በግልፅ ለማየት ፈርተን፣ ራሳችንን ለማታለል ካልፈለግን በቀር፣ የፖለቲካ ማዕበሉ፣ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። አስፈሪነቱ ደግሞ፣ ጭራና ቀንዱ አልያዝ ብሎ፣ ጨርሶ መፍትሄ የሌለው መምሰሉ ነው። ነገሮች ሁሉ ሲምታቱብንና የመፍትሄ ጭላንጭል ሲጠፋብን፣ አብዛኞቻችን፣ ከጭንቀት ለመገላገል፣ አይናችንን እንጨፍናለን። በሰበብ በማመኻኛ፣ ራሳችንን እናታልላለን። የመንግስት ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ፣ ብዙም ልዩነት የለውም። ከእውነታው ለመሸሽ ይሽቀዳደማሉ – አለማቀፋዊው ማዕበል እኛን የማይመለከት ለማስመሰል።
ማዕበሉ የኢትዮጵያ መንግስትን አይነካካም? ማዕበሉ የኢትዮጵያ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን አይመለከትም? ብዙዎቹ የመንግስት ደጋፊዎች፣ ይህንን ማሰብ አይፈልጉም። ከግብፅ የሆስኒ ሙባረክ መንግስት፣ ከየመን፣ ከቱኒዚያና ከሌሎች የማዕበሉ ገፈት ቀማሽ መንግስታት ጋር እንዳይመሳሰልባቸው ይፈራሉ። በጥንቃቄ ማሰብ፣ አመፅን እንደማባባስ የሚቆጥሩም አሉ። ብዙዎቹ ተቃዋሚዎችስ? ብዙዎቹ፣ ሊያስቡበት አይፈልጉም። ከግብፅ፣ ከየመን፣ ከቱኒዚያና ከሌሎች አገራት አስፈሪ የትርምስ ማዕበል ጋር እንዳይመሳሰልባቸው ይፈራሉ። እንዲያውም፣ በጥንቃቄ ማሰብ፣ ተቃውሞን እንደማዳከም የሚቆጥሩ አሉ።
ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች፣ በአብዛኛው እንዲህ ከእውነታ መሸሻቸውና ላለማሰብ መንገታገታቸው፣ ትርጉሙ ምንድነው? ያው… አይንን ጨፍኖ እንደ መጠበቅ ወይም አይንን ጨፍኖ እንደ መሮጥ ነው – “የሚሆነውን ነገር እናያለን… ከሆነ በኋላ” እንደማለት።
አንዳንዱ፣ “በአንዳች ተአምር፣ ከማዕበሉ እናመልጥ ይሆናል” ብሎ ይመኛል – ነገር እንዳይደፈርስ በመመኘት። አንዳንዱ ደግሞ፣ “ደፍርሶ አይቀርም፤ በማግስቱ በአንዳች ተዓምር፣ ነገሩ ሁሉ እየጠራ መልክ ይይዝ ይሆናል” ብሎ ይመኛል። በደፈናው ከመመኘት በቀር፣ እውነታውን በጥንቃቄ አስተውሎ፣ የማዕበሉን ምንነት አገናዝቦ፣ የሚያዛልቅ መፍትሄ ለማበጀት፣ አብጠርጥሮና አንጥሮ የሚያስብ ሰው ሲጠፋ፣ ‘አደጋ አለው’።
አብዛኛው ሰው፣ የአገሬው አዝማሚያ አልጥም እያለው፣ በዝምታና በስጋት መሃል ይወዛወዛል – በማዕበሉ እየተንሸራተተ። አብዛኛው “ንቁ ተሳታፊ” ደግሞ፣ በእያንዳንዷ ቁንፅል ወሬ የእለት የእለቷ የብሽሽቅ ጨዋታ ላይ ‘እየተመሰጠ’ ይደናበራል – ወጀቡን እያባባሰ። እንዲያም ሆኖ፣ የብዙዎቹ የጋራ ምኞት ምንድነው? በቃ፣ “በአንዳች ተዓምር ሁሉም ነገር ሰላም ይሆናል” እያሉ፣ በድፍን ምኞት ራሳቸውን ያታልላሉ። እና… ሌሎች በርካታ አገራት፣ ሰላም ያጡት፣ በእርግማን ነው? እዚህም እዚያም ትርምስ የሚፈጠረው፣… እንዲሁ በአጋጣሚ ነው?
የማዕበል ተቋዳሽ – ‘በአጋጣሚ’
ዛሬ፣ በጥቂት አመታት ውስጥ፣ ብዙ አገራት በየተራ የማዕበል ገፈት ቀማሽ ለመሆን እየተዳረጉ የሚገኙት፣ በአጋጣሚ ከሆነ፣ ያስገርማል።
አሃ፣ ከሃምሳ ዓመት በፊት፣ ከ30 በላይ የአፍሪካ አገራት፣ በጥቂት አመታት ውስጥ፣ ተራ በተራ ከቅኝ ግዛት የተላቀቁትም፣ በአጋጣሚ በግጥምጥሞሽ ነዋ። ደግሞም፣ ከቅኝ ግዛት መላቀቅ ብቻ አይደለም። ከዛምቢያ እስከ ኬንያ፣ ከካሜሩን እስከ ማዳጋስካር፣ ከሞሪታኒያ እስከ ሶማሊያ፣ ከሴኔጋል እስከ ብሩንዲ… በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት፣ በዚያን ወቅት፣ ከ50 ዓመት በፊት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተፎካከሩ በርካታ ምርጫዎች ተካሂደዋል። የአፍሪካ አገራት … ታሪክ፣ በጥቂት አመታት ውስጥ … በየተራ ተቀየረ። ከቅኝ ግዛት የወጡ አገራት፣ ከ25 በላይ የአፍሪካ አገራት፣ በአራት አመታት ውስጥ፣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በመፍጠር፣ በተመሳሳይ ጊዜ፣ ተመሳሳይ ታሪክ ሰሩ። “የአጋጣሚ ነገር”!
የማዕበል ገፈት ቀማሽ – ‘በአጋጣሚ’
ከ1950 እስከ 1955 ዓ.ም ድረስ፣ በአብዛኛው እንደ መልካም ጅምር የታየው የለውጥ ማዕበል፣ በዚያው አልዘለቀም። ብዙ ሳይቆይ፣ እንደገና በሌላ ማዕበል ተተክቷል።
አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት…. ከአራት አገራት በስተቀር ሌሎቹ ሁሉ፣… (ማለትም፣ ‘እንደ አጋጣሚ’ ከ40 በላይ የአፍሪካ አገራት ውስጥ)፣ በተመሳሳይ ጊዜ፣ ሃሳባቸውን በተመሳሳይ መንገድ ቀየሩ። የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር ወንጀል ነው ብለው ወሰኑ። የአንድ ፓርቲ አገዛዝን አወጁ። እንደ ደርግ፣ የሶሻሊዝም ስርዓት መስርተናል በማለት በኩራት፣ አምባገነንነትን ያወጁ መንግስታት ብዙ ናቸው – ከ30 በላይ የአፍሪካ መንግስታት – ከሊቢያ እስከ አንጎላ፣ ከሲሸልስ እስከ ሴራሊዮን፣ ከአልጄሪያ እስከ ኢትዮጵያ፣ ከኮንጎ እስከ ሶማሊያ… በሶሻሊዝም ማዕበል ተጥለቀለቁ። ለዚያውም፣ ይሄ ሁሉ የሆነው አስር ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ነው! ይሄም ግጥምጥሞሽ ነው?
በ1960ዎቹ ዓ.ም፣… ገዢ ፓርቲና መንግስት ብቻ አልነበሩም፣ ሶሻሊዝምን ያራገቡት። እንደ ኢህአፓ እና እንደ ኢህአዴግ የመሳሰሉ፣ ብዙዎቹ የአፍሪካ ተቃዋሚዎችና ተዋጊዎችም፣ ‘እንደ አጋጣሚ’፣ ያው… ሶሻሊስቶች ነበሩ። ምን ይሄ ብቻ።
ሌላ የሲሳይ ማዕበል “በአጋጣሚ”
በ1982 ዓ.ም፣ መንግስት አዲስ ነገር ይዞ መጣ። ሶሻሊስት ያልሆነ ፓርቲ እመሰርታለሁ አለ። መንግስት የሰዎችን ንብረት እየወረሰ፣ ኢኮኖሚውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር በኩራት ዘመቻ ሲያካሂድ እንዳልነበረ፤ ‘ድንገት’ ተነስቶ፣ የግል ቢዝነስ እንዲስፋፋ እፈቅዳለሁ በማለት አወጀ – “ቅይጥ ኢኮኖሚ”፣ “ገበያ ቀመስ ኢኮኖሚ” የሚል አባባል በረከተ።
በዚያው አመት፣ ኢህአዴግም በረሃ ውስጥ፣ “ለጊዜው ሶሻሊዝምን ለቀቅ አድርጌለሁ” የሚል መግለጫ አሰራጨ። ቅይጥ ኢኮኖሚን እንደሚፈቅድም ገለፀ። “የአንድ ሶሻሊስት ፓርቲ አገዛዝ” የሚል ሃሳቡንም በመቀየር፣ ብዙ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት ስርዓትን እመሰርታለሁ አለ።
ደርግ እና ኢህአዴግ ምን ነክቷቸው ነው፣ ድንገት በተመሳሳይ ጊዜ፣ በተመሳሳይ መንገድ ሃሳባቸውን የቀየሩት? ታዲያ፣ ሃሳባቸውን የቀየሩት የአገራችን ፓርቲዎች ብቻ አይደሉም። የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ወይም የሶሻሊዝም አምባገነንነት ሰፍኖባቸው የነበሩ ብዙ የአፍሪካ አገራት ውስጥ፣ ‘ድንገት’ ተመሳሳይ ለውጥ የተከሰተው፣ በዚያን ጊዜ ነው – ከ1982 እስከ 1986 ዓ.ም።
ሲኮሩበት የነበረውን የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ትተው፣ ብዙ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት ስርዓት ለመመስረት ወሰኑ።
ማዕበሉ በቃ፣ አህጉሪቱን አጥለቀለቀ፡፡ በአራት ዓመታት ውስጥ፣ በ34 የአፍሪካ አገራት፣ በየተራ አዳዲስ የህገመንግስት አዋጆች ተዘጋጅተው ፀድቀዋል። “ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲቋቋሙ” ለመፍቀድ የህገመንግስት ማሻሻያዎች ታውጀዋል። ይሄም ግጥምጥሞሽ ነው? ከአልጀሪያ እስከ አንጎላ፣ ከቤኒን እስከ ጂቡቲ፣ ከጋና እስከ ታንዛኒያ፣ ከኒጀር እስከ ሞዛምቢክ… በሁሉም አቅጣጫ፣ የምድረ አፍሪካ የፖለቲካ መነጋገሪያዎች ተቀየሩ – “መድብለ ፓርቲ” እና “የገበያ ኢኮኖሚ” የሚሉ ርዕሶች ነገሱ። ኢትዮጵያም የዚሁ አዲስ የሲሳይ ማዕበል ተቋዳሽ ነበረች። ‘የአጋጣሚ ነገር’!
የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም – ራሳችንን አናታልል
የዛሬ 50 ዓመት፣… እዚህም እዚያም፣ የሶሻሊዝምና የአንድ ፓርቲ አገዛዝ በየአገሩ ታወጀ። መንግስታት የየአገራቸውን ኢኮኖሚ ተቆጣጠሩ። የግል ንብረትና ቢዝነስ ተወገዘ። በጥቂት አመታት ውስጥ፣ ከ30 በላይ የአህጉሪቱ አገራት፣ የማዕበሉ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል – ኢትዮጵያም አላመለጠችም።
የዛሬ 25 ዓመት ደግሞ፣ እዚህም እዚያም፣ በየአገሩ ብዙ ፓርቲዎችን የሚያስተናግድ ‘ዲሞክራሲ’፣ ቢዝነስ እንዲስፋፋ የሚፈቅድ ‘የገበያ ኢኮኖሚ’… የሚሉ አዋጆች ተበራከቱ። በአራት አመታት ውስጥ፣ ከ30 በላይ አገራት የማዕበሉ ተቋዳሽ ሆነዋል – ኢትዮጵያም ጭምር።
እነዚህ ሁሉ፣ ‘የግጥምጥሞሽ ጉዳይ ናቸው’ የምንል ከሆነ፤ ራሳችንን እስከ ወዲያኛው ድረስ ለማታለል ቆርጠናል ማለት ነው – አይናችንን ጨፍነን ለመቀመጥ፤ ለመሮጥ መርጠናል ማለት።
ይሄውና ዛሬም ሌላ ‘ግጥምጥሞሽ’ እያየን ነው – አዲስ የፖለቲካ ማዕበል በየአገሩ ሲያስገመግምና ሲገለባበጥ እየተመለከትን ነው። ካሁን በፊት እንዳየነው፣ ኢትዮጵያም የግጥምጥሞሹ ተቋዳሽ ወይም ገፈት ቀማሽ መሆኗ ይቀራል?…
ታዲያ፣ ቢያንስ ካሁን በኋላ፣ “ነገሩ ሁሉ የአጋጣሚ ነገር ነው” እያልን ራሳችንን ማታለል አይበቃንም?
ነገርዬው የግጥምጥሞሽ ጉዳይ አይደለም። ዋና ዋና ሃሳቦች፣ የፖለቲካ ሃሳቦችም ጭምር፣ ንብረትን የሚያራቁትና የአንድ ፓርቲ አገዛዝን የሚያስፋፋ ሶሻሊዝም፣ አልያም ነፃ የገበያ ስርዓትን የሚያስፋፋ ‘የመድብለ ፓርቲ’ ሊበራሊዝም፣ እና ሌሎች ሃሳቦች፣ ድንበር የለሽ ናቸው። አንደኛው ወይም ሌላኛው ሃሳብ፣ በአንድ አገር ውስጥ ብቻ ተስፋፍቶ አይቆምም። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣ ወደ ሌሎች አገራትም መዛመቱ አይቀርም። ይሄ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። የሰው ዋነኛ ልዩ ተፈጥሮ፣ ማሰብ የሚችል መሆኑ ነውና። እናም፣ አለማቀፋዊ የሃሳብ ለውጥ፣ የለውጥ ማዕበል አንዱ መንስኤ ነው።
ሁለተኛው መንስኤ ደግሞ፣ በአብዛኛው አገር፣ በአብዛኛው ጊዜ፣ ብዙ የኑሮ ቅሬታዎች፣ እሮሮዎችና ተቃውሞዎች መኖራቸው ነው። ከኑሮ ቅሬታና እሮሮ ጋር ደግሞ፣ በደፈናው ለውጥን የመመኘት ስሜት አብሮ ይኖራል። አቤቱታ ማቅረብና ተቃውሞ ማሰማትም እንዲሁ።
በ1960ዎቹ ዓ.ም፣ እንደሌላው ጊዜ፣ በየአገሩ በኑሮ ችግር የተማረሩ ብዙ ሰዎች መኖራቸውና በየአገሩ የተቃውሞ ሰልፎች መበራከታቸው አይገርምም – ለውጥን በመመኘት። ነገር ግን፣ በደፈናው ‘ለውጥ’ን መመኘት፣ መልካም ለውጥን ያስገኛል ማለት አይደለም።
መልካም ለውጥን የሚያስገኝ፣ ትክክለኛ አስተሳሰብን ማዳበርና፣ ጠቃሚ የመፍትሄ ሃሳብን መያዝ ያስፈልጋል። ግን ያኔ ምን ዋጋ አለው? አለምን፣ ከዚያም አፍሪካን አጥለቅልቆ የነበረው የአእምሮ ማዕበል፣ በአብዛኛው በጭፍን የሶሻሊዝም አስተሳሰብና፣ በመጥፎ የሶሻሊዝም ሃሳብ የተሞላ ማዕበል ነው። በዚህም ምክንያት፣ የያኔው የለውጥ ማዕበል፣ የአፍሪካ አገራትን ወደ ባሰ ቀውስ የሚያስገባ ክፉ ማዕበል ሆኖ አረፈው የአፈና፣ የድህነት፣ የግድያ ማዕበል። በ1980ዎቹ ዓ.ምም እንዲሁ፣ የኑሮ ችግሮች ሰማይ ደርሰው ነበር – በየአገሩ፣ የተቃውሞ ድምፆች የተበራከቱበት። ደግነቱ፣ በዚያ ወቅት፣ አለምንና አፍሪካን እያጥለቀለቀ የነበረ አዲስ የአእምሮ ማዕበል፣ በአመዛኙ ፈካ ያለ የሊበራሊዝም አስተሳሰብና፣ ከዚሁ የሚመነጩ ጥሩ ሃሳቦችን የያዘ ማዕበል ነው። በዚህም ምክንያት፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት፣ የዚሁ ቅዱስ ማዕበል ተቋዳሽ ሆነዋል።
ታዲያ፣ በየጊዜው የተለያዩ የለውጥ ማዕበሎች ሲፈጠሩ፣ ገፈት ቀማሽ ከመሆን ማምለጥ አይቻልም፤ ወይም ተቋዳሽ ሳንሆን ሊያመልጠን አይችልም ማለት አይደለም።
የአፍሪካ አገራትን የሚያሰቃይ፣ የአንድ ፓርቲ የሶሻሊዝም አገዛዝ፣ በ1960ዎቹ በየአቅጣጫው እንደ ማዕበል ብዙዎችን ቢያጥለቀልቅም፣ በአስተዋይነትና በፅናት፣ “የተሻለ መፍትሄ” ለማበጀት የሞከሩ አገራት አሉ። አዎ ጥቂት ናቸው። ግን፣ ተሳክቶላቸዋል – ሞሮኮ፣ ሞሪሸስ፣ ቦትስዋና።
ለአፍሪካ አገራት የመሻሻል እድል የሚሰጥ ሌላ የለውጥ ማዕበል በ1980ዎቹ ዓ.ም ሲፈጠርም፣ ብዙ አገራትን ቢያዳርስም፣ በዚሁ እድል በፍጥነት ለመጠቀምና ውጤታማ ለመሆን ከመጣር ይልቅ፣ ከለውጥ ለመሸሽ ሲንገታገቱ ወይም በዘፈቀደ ሲደናበሩ፣ ፈጠነም ዘገየም፣ ለብጥብጥና ለእልቂት የተዳረጉ አገራት አሉ – እነ ኮንጎ ወዲያውኑ፣ እነ ሊቢያ ደግሞ የኋላ ኋላ ለጥፋት ተዳርገዋል።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
በ1960ዎቹ ዓ.ም፣ የወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የአለምን ሁኔታ አገናዝቦና የአገሬውን ችግር አስተውሎ፣ በአንድ በኩል ክፉ የሶሻሊዝም ማዕበልን ለመቋቋም የሚያስችል፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኑሮ ችግርን የሚያቃልል፣ ትክክለኛና ጠቃሚ የመፍትሄ ሃሳብ ቢያበጅ ኖሮ… ብላችሁ አስቡ። ኢትዮጵያውያን ከብዙ ስቃይ ይድኑ ነበር። ሰላሳ ዓመታት በከንቱ አይባክኑም ነበር። በኑሮ፣ አሁን ካለንበት ደረጃ፣ አስር እጥፍ ከፍ ለማለት የሚያስችል የለውጥ እድል በተገኘ ነበር።
በ1980ዎቹ ዓ.ም ደግሞ፣ ዘረኝነትና የብሄር ብሄረሰብ ተወላጅነት የፖለቲካ መቆመሪያ እንዳይሆን የሚረዳ፣ የኑሮ ችግርን ለማቃለል ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ለብልፅግና የሚበጅ፣ በአጠቃላይ ለስልጣኔ የሚያግዝ የፖለቲካ ማዕበል በአለማቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ መቆየቱን ቀደም ብሎ መገንዘብ ቢቻል ኖሮና፣ እንደ ታይዋንና እንደ ደቡብ ኮሪያ ባንፈጥን እንኳ፣ የቻይናን ለውጥ በማየት ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ፣ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ፣ ከዚያም ወደ ሊበራል ዲሞክራሲ የለውጥ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢቻል ኖሮ ብላችሁ አስቡት። ኢትዮጵያውያን በስንትና ስንት እጥፍ የመሻሻል ድንቅ የለውጥ እድል ባገኙ ነበር።
እነዚህ ሁሉ፣ ተመልሰው የማይለወጡ፣ የድሮ ታሪኮች ናቸው። ነገር ግን፣ ዛሬና ነፈ የለውጥ ማዕበሎችን ሲከሰት፣ በጭፍን ተደብቆ ከመጠበቅ ወይም በጭፍን ከመንደርደር ይልቅ፣ እያንዳንዱን ማዕበል በማገናዘብ፣ የአገሬውንም የኑሮ ችግር በማስተዋል፣ እያንዳንዱን ለውጥ፣ መልካም ለውጥ እንዲሆን የማድረግ ምርጫ አለን።
አዎ የምርጫ ጉዳይ ነው። የማሰብ እና ያለማሰብ፣ መፍትሄ የማበጀትና የመሸሽ ወይም በዘፈቀደ የመደናበር ምርጫ ነው። ይሄ ነው፣ የመፍትሄው ጅምር! ማስተዋል፣ ማገናዘብና ማሰብ መጀመር፣ መፍትሄ ማበጀት እንደሚያስፈልግ ማወቅና ራሳችንን ሳናታልል በቅንነት መመርመር፣ በትጋት ማሰብ!