ዒድ አል አድሐን አስመልክቶ ከ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› የተሰጠ መግለጫ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


#EthioMuslims #EidAlAdha2016 #EthioMuslimPeacefulStruggle

ዒድ አል አድሐን አስመልክቶ ከ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› የተሰጠ መግለጫ

ሰኞ መስከረም 2/2009

 

የመግለጫው የአማርኛ ቅጂ የፒዲኤፍ ሊንክ፡-

http://goo.gl/fxGgce

 

የመግለጫው ሙሉ ቃል በጽሑፍ፡-

 

**************************

**************************

 

ዒድ አል አድሐን አስመልክቶ ከ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› የተሰጠ መግለጫ

‹‹እንኳን ለ1437ኛው የዒድ አል አድሃ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!››

ሰኞ መስከረም 2/2009 አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ

 

አላሁ አክበር! አላሁ አክበር! አላሁ አክበር! ላኢላሃ ኢለላህ!

አላሁ አክበር! አላሁ አክበር! ወሊላሂል ሐምድ!

 

ለመላው ሙስሊም ህብረተሰባችን እንኳን ለ1437ኛው የዒድ አል አድሃ በዓል በሰላም አደረሰን እያልን በዓሉ የደስታ እንዲሆንልን እንመኛለን። ዒድ አል አድሃ ሙስሊሞች በልዩ ሁኔታ የምናከብረው እና በተለይም ደግሞ ራሳችንን ለፈጣሪያችን ትእዛዝ ተገዥ ለማድረግ የቱን ያክል መጓዝ እንዳለብን የአባታችንን ኢብራሂምን (ዐ.ሰ) ገድል ዘወር ብለን የምናይበት በዓል ነው። በዚህ ልዩ በዓል ወቅት በአቅራቢያችን ያሉ ምስኪኖችን እና የቲሞችን፣ እንዲሁም ወላጅ ዘመዶቻችንን በልዩ ሁኔታ እንድናስባቸው ጥሪያችንን እናቀርባለን።

 

ውድ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሆይ!

 

የ1437ኛውን የኢድ አል አድሃ በዓል ስናከብር በተመሰቃቀለ ስሜት ነው። በአንድ ጎኑ ለአራት ዓመታት ያክል ከጎናችን ያጣናቸውን፣ ለዲናቸው እና ስለ እኛ ሲሉ የሰው ልጅ ያልፈዋል ለማይባል ስቃይ እና መከራ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተው በእስር ቤት አካላዊ እና መንፈሳዊ ስቃይን ሲያሳልፉ ከቆዩ መሪዎቻችን እና ወንድሞቻችን መካከል ከፊሉ ከጎናችን በመቆማቸው ነፍሳችን በሀሴት ተሞልታለች። ለአራት ዓመታት ያክል አባቶቻቸውን ለናፈቁት ልጆች፣ ባልተቤቶቻቸውን ላጡት ሚስቶች፣ የአይን ብሌን የሆኑ ልጆቻቸውን ላጡት ወላጆች፣  እንዲሁም ከመንፈስ ምግብ መቋደሻ መድረኩ አስተማሪዎቹን ላጣው እና ለናፈቀው ሙስሊም ህብረተሰብ በእርግጥም ይህች ዒድ በአምስት ዓመታት የትግል ሂደት ውስጥ ልዩ ቦታ የምትይዝ ዒድ ናት።

 

በሌላ ጎኑ ደግሞ ይህንን ዒድ ስናከብር አንድ ዓይነት ኃላፊነት ሰጥተን የላክናቸው እና ራሱን ፈላጭ ቆራጭ አድርጎ በሰየመው ስርዓት አሁንም በእስር ቤት ላሉ ከፊል መሪዎቻችን እና ወንድሞቻችን ውስጣችን በሐዘን እየተናጠች፤ ሰውነታችንም እየተሸማቀቀ መሆኑ አልቀረም፡፡ ለአምስተኛ ዓመት ይህንን ልዩ የሆነ በዓል በእስር ቤት እንዲያሳልፉ መደረጋቸው አቅፎ ሊስማቸውና ድምጻቸውን ሊሰማ የሚናፍቅ ቤተሰብ እና ህብረተሰብ ልብ የሚያደማ ክስተት ነው፡፡ ግና ግልጽ ብሎ የሚታየን አንድ ነገር ደግሞ ሊዘነጋ የሚችል አይደለም – ትግላችን ከግቡ ሳይደርስ የማይቆም መሆኑ!

 

ውድ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሆይ!

 

መንግስት በአንድ መዝገብ ተከሳሽ የሆኑትን ጀግኖቻችንን በመለያየት ከፊሉን ለቅቆ ሌሎችን ወደ ኋላ ማስቀረቱ አሁንም በሙስሊሙ ላይ እያደረገ ያለውን ጭቆናን በተመለከተ ከጥፋቱ ለመማር አለመዘጋጀቱን በግልጽ የሚያሳይ ነው። ወትሮም ታሳሪዎቻችን እንዲፈቱ የሚለው ጥያቄያችን የሌሎች ዋና ጥያቄዎች ቅጥያ ሆኖ የቀረበ እንጂ ሰዎች ታስረውብን ወደትግል አለመግባታችን  ግልጽ ነው፡፡ መፍትሄ ያፈላልጉ ዘንድ ፈርመን የላክናቸውን የኮሚቴ አባላት እና ከዚያም የህዝብን ጥያቄ በማሰማታቸው በተለያዩ ጊዜያት እና ቦታዎች የታሰሩ ንጹሃንን አስሮ ለማቆየት ሲወስን መሰረታዊ ጥያቄዎቻችንን ለመመለስ ገና ሀሳቡም እንደሌለው ተጨማሪ መልእክት እየሰጠን ነው። ይህ በዚህ እንዳለ ግን መንግስት ቀድሞውንም በምንም መልኩ መታሰር ያልነበረባቸውን ንጹሃን በመፍታት ትግላችንን የማዳከም ዓላማ ካለው በእጅጉ መሳሳቱን ልንነግረው ይገባል፤ ትግላችን ከማይመለስበት እና ከማይቀለበስበት መሰረት እና ደረጃ ላይ ይገኛልና፡፡

 

ትግላችንን ስንጀምር ለመንግስት መልስ ለመስጠት እጅግ ቀላል የነበሩ፣ ነገር ግን ለእኛ ደግሞ እንደ አማኝ መሰረታዊ የሆኑ ሶስት ጥያቄዎችን ማንሳታችን እሙን ነው። በሂደት ግን ስርዓቱ በመስሊሙ ላይ ይዞ የተነሳውን በደል ለማስፋት እና ለማጠናከር በመወሰኑ እኛም የተጫነብንን ዘርፈ ብዙ እና ሁለገብ ብሄራዊ ጭቆና በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችለንን የትግል ስልት አስምረናል። ለህዝብ ጩኸት ደንታ የሌለው ስርዓት ‹‹የህዝብ መብት አክብር›› ተብሎ ቢጠየቅም ምላሽ የማይሰጥ ከመሆኑ አንጻር መብታችንን ማስከበርን የራሳችን ድርሻ እና ሃላፊነት አድርገን ወስደናል። መንግስት የሚወሰዳቸው የማታለያ እርምጃዎችም የጽናታችን ውጤት እና የትግላችን ፍሬዎች እንጂ ድምጻችንን ለመስማት ከመዘጋጀት የመነጩ አይደሉም። ሙሉ መብቶቻችን በዘላቂነት ለማስከበር በምናደርገው ሂደት ላይ የበለጠ ጸንተን መገኘት እንዳለብን የሚያመላክት ነው።

 

ውድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሆይ!

 

ብሄራዊ ጭቆናን በዘላቂነት ለማስወገድ የምናደርገው የትግል ሂደት ከቅጽበታዊ ለውጥ ይልቅ ዘላቂ ውጤትን ግቡ ያደረገ፣ የሁላችንንም ተሳታፊነት ያረጋገጠ እና በየትኛውም መልኩ በምናገኛቸው ድሎች ላይ እየተገነባ የሚሄድ ረጅም የትግል ሂደት ነው። የትግላችን ሁሉን አሳታፊነት ምንጭም የበደሉ ብዛት ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው ያሉን የተለያዩ ችሎታዎች፣ ክህሎቶች እና እድሎች ናቸው። ይህም ‹‹በሁሉም ነገር ላይ አንድ አይነት ሀሳብ ይኑረን›› ከሚል እሳቤ በመራቅ በዓላማ አንድነት ላይ የተመሰረተ ትስስርን ያካትታል። ስለዚህ ሁላችንም በትግላችን ዙሪያ በመሰባሰብ ለመብታችን መከበር የምናደርገውን ትግል በማጠናከር እናፋጥነው ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

 

ውድ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሆይ!

 

ትግላችን የሁላችንንም ርብርቦሽ የሚፈልግ ነው። ከመሪ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች እንዳሉ ሁሉ እንደ ተመሪም ኃላፊነቶች አሉብን። ትግላችን ውጤት የሚያመጣው ሁላችንም ያሉብንን ኃላፊነቶች መወጣት ስንችል ነው። ዛሬ ላይ በከፊልም ቢሆን የመሪዎቻችንን ከእስር መፈታትን ስናይ ትግሉን በእነሱ ትከሻ ላይ ብቻ የምንጥለው እና ሁሉንም ነገር ከእነርሱ የምንጠብቅ አይሆንም። የጠንካራ አመራር ምንጩ የነቃ፣ መብቱን የሚያውቅና ለመብቱ መከበር ጸንቶ የሚቆም ህዝብ ነው። ይህን የህዝብ ወኔ ለመስበር መንግስት የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደማይኖር በተደጋጋሚ አሳይቶናል። ሂደታችንን በኃይል ከመጨፍለቅ፣ ትግላችንን ከማጠልሸት እና የትግል ሂደታችንን ለአገር እና ወገን ጸር አድርጎ ከማቅረብ ጀምሮ በመካከላችን መተማመን እንዳይኖር፣ ከመሰረታዊ መንፈሳዊ አንድነት ወጥተን በጥቃቅን ጉዳዮች ሽኩቻ ውስጥ እንድንገባ ለዓመታት ጥሯል። አሁንም እየጣረ ነው። በዚሁ እንደማይቀጥልበትም አስተማማኝ ነገር የለም። በዚህ ወቅት የእኛ መልስ ከምንጊዜውም በላይ በመቀራረብ እና ለጋራ ዓላማ ርብርቦሽ በማድረግ መሆን ያለበትም ለዚህ ነው። ይህ ግዴታ እንደ ግለሰብም እንደ ስብስብም ሆነን ልንወጣው የሚገባ ነውና ልዩ የሆነውን ዒድ አል አድሃን ከእስር ከተፈቱ ወንድሞቻችን ጋር ሆነን ስናከብር ይህንን ግደታችንን ለመወጣት ጽኑ ውሳኔ በመውሰድ መሆን አለበት።

 

ውድ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሆይ!

 

ትግላችን በጀግኖቻችን መታሰር የተጀመረ እንዳልሆነ ሁሉ ከፊሎች ስለተፈቱልንም የሚቆም አይደለም። ከዚህ አንጻር ብሄራዊ ጭቆናው እስኪቆም እና የእኛን ውክልና ይዘው ሲንቀሳቀሱም ይሁን ድምጻቸውን በማሰማታቸው አሁንም ድረስ እስር ላይ ያሉ ጀግኖቻችን በሙሉ እስከሚፈቱ ድረስ የምናደርገው ግፊት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

 

ባሳለፍናቸው አምስት የትግል ዓመታት ውስጥ የኖርናቸው ክስተቶች በርካታ ናቸው። በእነዚህ ጊዜያት መሪዎቻችን እና የቅርብ የትግል አራማጅ ጓዶቻቸው በትግሉ ወቅት ከፊት ሆነው እንደመሩን ሁሉ በመስዋዕትነቱም ጥግ የደረሰውን ለእኛ እና ለመብታችን ሲሉ ተጋፍጠውታል፡፡ ዛሬ ላይ ከእስር ተፈትተው ህዝባቸውን ሲገናኙ በአዕምሮአቸው የሚመላለሱ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በአንድ የክስ መዝገብ የታሰሩ የትግል አጋሮቻቸው አለመፈታት ደስታቸውን ጎዶሎ፣ እረፍታቸውንም ያልተረጋጋ ያደርገዋል፡፡ በማእከላዊ ያሳለፉት ስቃይ የቀናት ያህል እንኳን ርቆ አይሰማቸውም፡፡ ቃል አስገብተውት የታሰሩለት ህዝብ ሁኔታ ዛሬም ከራሳቸው በላይ እንደሚያሳስባቸው ግልፅ ነው፡፡ ቤተሰባዊ እና ማህበራዊ ኃላፊነቶቻቸውም የአምስት አመት ክፍተታቸውን ይዘው ነው የጠበቋቸው፡፡

 

በጀግኖቻችን መፈታት ደስታችንን እየገለፅን እና ለመሪዎቻችን እና ወንድሞቻችን ያለንን አጋርነት እያሳየን እንገኛለን። ይህ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ ይህን ስናደርግ ግን ኢስላማዊ እና ማህበራዊ አብሮነትን ማጠናከርን ተጨማሪ ዓላማው ቢያደርግ ለትግላችን ትልቅ ግብዓት፣ ለመሪዎቻችንም ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆናቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የምናደርጋቸው የአጋርነት መገለጫዎች በእነሱ እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ጫና በሚፈጥር መልኩ ሳይሆን ያሳለፉትን የስቃይ ጊዜ የምናረሳሳበት እና የሞራል ካሳ የምንሰጥበት እንዲሆን አጥብቀን አደራ እንላለን፡፡

 

ለመላው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን መልካም ዒድ አል አድሐ እንመኛለን!

 

አላሁ አክበር! አላሁ አክበር! አላሁ አክበር! ላኢላሃ ኢለላህ!

አላሁ አክበር! አላሁ አክበር! ወሊላሂል ሐምድ!

 

**************************

**************************

 

ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!

ድምጻችን ይሰማል!

አላሁ አክበር!

 

Like ☑ Comment ☑ Share ☑